Sunday, May 20, 2012

ዓለም አቀፋዊ ሰላማዊ ሰልፍ ስለ ዋልድባ


(አንድ አድርገን ግንቦት 12 ፤ 2004ዓ.ም )፡-  በመጪው ግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ .. በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተዘጋጅቷል፥ ሰልፉም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል በሚገኘው ታላቁ የዋልድባ ገዳም አካባቢ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ፣ የፓርክ ይዞታ፣ እንዲሁም የመንገድ ጥርጊያ እሰራለሁ በሚል ሰበብ የዋልድባ ገዳም ይዞታን የተለያዩ ከባድና ቀላል የእርሻ መሳሪያዎችን በመጠቀም አጽመ ቅዱሳንን በማፍለስ፣ ቦታውንም በዶዘር በማረስ መጠነ ሰፊ የሆነ የጥፋት ዘማቻ ከጀመረ ውሎ አድሯል፤ ቦታው የመድኃኒዓለም ስም የሚወደስበት የሚሰለስበት ቅዱስ ቦታ ነው
 ቦታው ላይ ያሉ ገዳማውያኑም አቤቱታቸውን ከማይፀብሪ አውራጃ እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ /ቤት ብሎም በመንበረ ፖትሪያሪኩ /ቤት ድረስ አቅርበው ነበር ነገር ግን ሰሚ ሊያገኙ አልቻሉም። ለዚህም ነው ድምጻቸው ድምጻችን ነው፣ አቤቱታቸው አቤቱታችን ነው፣ መገፋታቸው መገፋታችን ነው ያልን በተለያዩ ዓለማት የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆንን በሃገር ውስጥ የገዳማውያኑን አቤቱታ ሊሰማ የፈቀደ ከመንግሥትም ሆነ ከቤተክህነቱ ሰው ስለሌለ እኛ ልጆቻቸው አቤቱታቸውን ለዓለም ሕብረተሰብ ማሰማት ይኖርብናል በሚል ቅን ሀሳብ በመነሳት በመጪው ግንቦት ፳፯ የመድኅኒዓለም እለት በተለያዩ የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁኔታውን ለዓለም ለማሳወቅ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅተናል፥ እርስዎም ስለ ዋድባ ገዳም እና ስለ ቅድስት ቤተክርስትያን ብለው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንዲካፈሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ 



በኢትዮጵያ ሀገራችን የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ከገዳማውያኑ ጋር የዓላማ አንድነታችንን ለማሳየት፣ ይልቁንም እንደሻማ ቀልጠው ብርሃን ለሆኑት ለክርስቶስ ፍቅር ብለው በረሃ ለበረሃ ለተቅበዘበዙት አባቶቻችን መነኩሳት በዚሁ እለት የመድኅኒዓለም እለት የመድኀኒዓለም ታቦት ባለበት ቦታ ሁሉ አባቶች፣ እናቶች፣ እህቶች፣ ወንድሞች በአንድነት በፍቅር ሆነን እነዚህን ሦስት መዝሙራት እየዘመርን የአላማ አንድነታችንን እንድናሳውቅ መልክታችንን በመላው የኢትዮጵያ ለሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ ያስተላልፉን።


በአዲስ አበባ (ቦሌ መድኅኒዓለም) በመቌሌ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ በደሴ፣ በሸዋ፣ በደብረዘይት፣ በናዝሬት፣ በነቀምት፣ በአርዚ፣ በሐዋሳ፣ በዲላ፣ በይርጋለም፣ በኢሉባቡር፣ በጅማ፣ በሐረር፣ በድሬደዋ፣ በይርጋለም፣ በሻሸመኔ፣ በአባ ምንጭ፣ እና በደብረብርሃን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከተሞች በሙሉ በሚገኙ የመድኀኒዓለም ደብር በሙሉ በግንቦት ፳፯ ቀን ፳፻፬ .. 


፩ኛ/ "ማርያም ሐዘነ ልቦና ታቀላለች"

፪ኛ/ "መድኀኒዓለም አዳነን በማይሻር ቃሉ"

፫ኛ/ "ኀይል እግዚአብሔር ነው"

ማሳሰቢያ: ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፍፁም ሰላማዊ ናትና መርኃ ግብሩ በፍፁም ሰላማዊ ይሆን ዘንድ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ገዳማቶቿን በቸርነቱ ይጠብቅልን !!!
በኢ//// ዋልድባን ለመታደግ የሚንቀሳቀሰው ዓለም አቀፍ ጊዚያዊ 

ኮሚቴ

ሰሜን አሜሪካ



2 comments:

  1. ማሳሰቢያ ፡
    የጥሪው ዓላማ ቅዱስና ሰላማዊ ነው ፤በማንኛውም ክርስቲያን አማኝ ፣ ሰብአዊ መብት ተቆርቋሪና ሰላማዊ ሰው ይደገፋል ፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ከተሞችና መንደሮች የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ ፣ ወደ ረብሻና ያልሆነ መስመር እንዳይቀየር ፣ በምክንያትም የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ፣ ሰርጎ ገቦችን የሚቆጣጠርበትን ዘዴ ፣ ማድረግ የሚገባውን ፣ መውሰድ ያለበትን ርምጃ ለህዝቡ ከወዲሁ ማስተማርና መምከር ያስፈለጋል ፡፡ ቢያንስ ከጐኑ ሆኖ የሚሰለፈውን ሰው እንቅስቃሴ መከታተልና መቆጣጠር እንደሚኖርበት መመከር አለበት ፡፡ አለበለዚያ ግን ጠላቶች ተመሳስለው ተሰልፈው ፣ የማይገባ ሥራ እየሠሩ ስሙን ለመበከል ፣ ዓላማውን ለማክሸፍ ፣ ጩኸቱን ለመበረዝ የማይሄዱበት መንገድ አይኖርም ፡፡ በጥምቀት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነበበ የሉትን ዓይነት ጽሁፍና ሌላም ከመንግሥት ጋር የሚያቆራቁስ ኃይል የተቀላቀለ ቃል እንዳይኖር ዝግጅቱ ከወዲሁ መጠናቀቅ አለበት ለማለት ፈልጌ ነው ፡፡ ተሰላፊውን ሁሉ የማኀበረ ቅዱሳን ደጋፊ አድርገው ስለሚመለከቱ በመንግሥት ለማስረሸን እንኳን አይመለሱም ፡፡ ጅምራቸውና አካሄዳቸው ከፖለቲካ ጉያ ገብተው መታደማቸውም ያንን ሁሉ ስላሳሰበኝ ነው ፡፡

    ReplyDelete
  2. ውድ የዚህ የተቀደሰ ሀሳብ አስተባባሪዎች በሙሉ፦

    ከላይ የተጻፈው ማሳሰቢያ በጣም በጣም በሚገባ ሊታሰብብት የሚገባ ጉዳይ ነው።
    ምንም እንኳን ሀሳባችሁ ቅዱስ ቢሆንም ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን አጋጣሚውን ተጠቅሞ የተለመደ እኩይ ስራውን ለመስራት ያለ የሌለ ሃይሉን አስተባብሮ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ እረፍት አይኖረውም እንቅልፍን አይተኛም።

    ስለዚህ የእኔም አደራ በዝግጅቱ ላይ ትልቅ ጥንቃቄ እንዲደረግብት ነው።

    ሌላው በዋድባ ቅዱስ ገዳማት ጉዳይ በሚደረገው ኢ-ኦርቶዶካዊ በሆነው የመንግስትና የቤተ ክህነት ስራ የሚያዝኑና የሚያለቅሱ ከሁሉም በላይ አልማካችንንና አዳኛችንን መድሃኒ ዓለምን በጸሎት የሚማጸኑ የተዋህዶ ተከታይ ምዕመናን ሁሉም ከላይ የተጠቀሱትን መዝሙሮች ልናውቃቸው ስለማንችል መዝሙሮችን በድምጽና በንባብ እዚሁ ብሎግ ላይ ቢወጡ ፤ በተጨማሪም ቢያንስ 2 መዝሙሮች ቢጨመሩና “ኀይል የእግዚአብሔር ነው” የሚለውን ከማስገንዘብ ውጪ ወደ አምላካችን ልዑል አግዚአብሄር የሚደረገው ልመና እና ወደ እመቤታችን ቅድት ድንግል ማርያም እንደዚሁም ወደ ጻደቃንና ሰማእታት የሚደረገው የምልጃ ጥያቄዎች ሁሉ ምንም አይነት የመፈክር መልክ እንዳይኖራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግበት መልካም ነው እላለሁ።

    አባቶቻችን እንዳስተማሩንና ቅ/መጽሀፍም እንደሚነግረን "… የሚመካ ቢኖር በእግዚአብሄር ይመካ” ነውና ልመናችንና ጩኸታችንን የዘወትር መመኪያችን የሆነው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ይሰማን ዘንድ፤ በበረሃና በየዋሻው እንደዚሁም በየደኑ ውስጥ ያሉ የአባቶቻችንና የ እናቶቻችንን ጸሎት ይቀበልልን ዘንድ የርሱ ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን። አሜን !

    ሰላም ያቆየን

    ReplyDelete