- አጀንዳ አዘጋጅ ኮሚቴው 20 ጉዳዮችን በረቂቅነት አቅርቧል።
- ከአቡነ ፋኑኤል ጋራ በተያያዘ በዋሽንግተን የተፈጠረው ችግር በአጀንዳዎቹ ዝርዝር ውስጥ ራሱን ችሎ አልተመለከተም።
- ፓትርያርኩ የዕርቀ ሰላም ንግግር አጀንዳን ተቃውመዋል፤ በተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አጀንዳ አቋማቸው ጸንተዋል።
- “በእኛ ዘመን የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ለቀጣዩ ትውልድ አናስረክብም፤ ሹመቱ ዕርቀ ሰላሙን የሚያደናቅፍ በመኾኑ ወቅቱ አይደለም።” /ብዙኀኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት/
እኒህም በተቀመጡበት ቅደም ተከተል መሠረት፡- 1) የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የመክፈቻ ንግግር፤ 2) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ዓመታዊ ሪፖርት፤ 3) ስለ ቤቶችና ሕንጻዎች ጉዳይ፤ 4) በላሊበላ የሰባት ወይራ ሆቴል መመለስ እና ወደ ማእከል ስለሚመጣበት ጉዳይ፤ 5) ስለ ማኅበራት ጉዳይ፤ 6) ማእከልን ጠብቆ አለመሥራት እያስከተለ ስለ አለው ችግር፤ 7) ስለ ሰላም ጉዳይ፤ 8)በላሊበላ ስለተፈጠረው ችግር፤ 9) ስለ ቃለ ዐዋዲው መሻሻል፤ 10) ስለ ልማት ኮሚሽን፤ 11) ስለ ሕፃናት እና ቤተሰብ ጉዳይ፤ 12)በአኲስም ሀገረ ስብከቱና በርእሰ ገዳማት ወአድባራት መካከል ስለ አለው ችግር፤ 13) ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በኮሚቴ የሚቀርበውን ሪፖርት መስማትና መወሰን፤ 14) ስለ ሲዳማ ሀገረ ስብከት ጉዳይ፤ 15) ስለ ሰንበት ት/ቤት እና ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ፤ 16) ስለ ስብከተ ወንጌል ጉዳይ፤ 17) ስለ አብነት መምህራን ፍለሰት ጉዳይ፤ 18) ስለ ተጀመረው የአሜሪካው ዕርቅ ጉዳይ ሪፖርት መስማት፤ 19) ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ 20) የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ምርጫ የሚሉ ናቸው፡፡
አጀንዳ አዘጋጅ ኮሚቴው ዝርዝሩን ለምልአተ ጉባኤው ካቀረበ በኋላ ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተራ ቁጥር 18 ላይ በሰሜን አሜሪካ በስደት ከሚገኙ አባቶች ጋራ የተጀመረው ዕርቅ ጉዳይበአጀንዳነት መያዙን ተቃውመዋል፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት “ፖሊቲከኞች ናቸው” በሚልም በዕርቀ ሰላሙ ሂደት መቀጠል ላይ እንደማያምኑበት ተናግረዋል፤ ከመንበረ ፓትርያርኩ ተወክለው ከሄዱት ልኡካን መካከል አንዱን አባል በስም በመጥቀስ “ወደኋላ ቀርተው ከእነርሱ ጋራ ነገር ሲሸርቡብኝ ነበር” በማለት ወቅሰዋል፡፡
በአንጻሩ ፓትርያርኩ በዕርግና እና በሞተ ዕረፍት የተለዩ አባቶችን በመቁጠር ተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት መሾም እንዳለባቸው ከዚህ ቀደም በያዙት አቋም ጸንተዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሚያንጸባርቋቸው አብዛኛዎቹ አቋሞች የብፁዕ አቡነ ገሪማን፣ የብፁዕ አቡነ ማርቆስን፣ የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስንና የብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን ድጋፍ ያገኙ ቢኾንም ከብዙኀኑ የመደበኛው ጉባኤ አባላት ግን ጠንካራ ተቃውሞ ነው የገጠማቸው፡፡
አቡነ ጳውሎስ በሰሜን አሜሪካው የዕርቅ አጀንዳ ላይ ስለሰነዘሩት ተቃውሞ ሐሳባቸውን የሰጡ አባቶች÷“በእኛ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ አትቀርም፤ ለቀጣዩ ትውልድ ለሁለት የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ማስረከብ አንሻም፤ የዕርቅ ሂደቱ መቀጠሉ ግድ ነው፤ በእግራችንም ቢኾን እዚያው ሄደን እናሳካዋለን” የሚሉ ጠንካራ ምልልሶችን ከፓትርያርኩ ጋራ መለዋወጣቸው ተዘግቧል፡፡ ምልአተ ጉባኤው በአጀንዳው እንደተመለከተው የመንበረ ፓትርያርኩ ልኡካንና በስደት የሚገኙት አባቶች ተወካዮች በየካቲት ወር ተደርጎ በነበረው ውይይት ላይ የሚያቀርቡትን ሪፖርት እንደሚያዳምጥ የስብሰባው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
አቡነ ጳውሎስ ያለማሳለስ እየተሟገቱበት ያለውንና በብዙዎች ዘንድ “የፓትርያርኩ አዳዲስ የዓላማና ጥቅም ወዳጆች ማፍሪያ ነው” የሚባለውን የተጨማሪ ኤጴስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይንም “ለጊዜው ያለነው እንበቃለን፤ ከተጀመረው ዕርቅ አንጻር ወቅቱን የጠበቀ አይደለም፤ የዕርቁን ሂደት ያደናቅፋል፤ ያለውንም ችግር ያባብሳል”በሚል በሚበዙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመካከል የወዲያውንም የወዲሁንም ሐሳብ በመዳኘት ለመሸምገል የሞከሩ ብፁዓን አባቶች የነበሩ ቢኾንም ምልአተ ጉባኤው ቀትር ላይ የተነሣው የሚጠቀስ መግባባት ላይ ሳይደረስ ነው፡፡
ከስብሰባው ጋራ በተያያዘ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ገና ባልተወሰነባቸው አጀንዳዎች ሳይቀር መሠረት የሌላቸው አሉባልታዎች እያናፈሱ ይገኛሉ፡፡ ከእኒህም አንዱ በአጀንዳ ተራ ቁጥር 13 “ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በኮሚቴው የሚቀርበውን ሪፖርት መስማትና መወሰን” በሚል የተመለከተው ሲኾን÷ ሊቃውንት ጉባኤው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተመርቶለት በጥቅምትና ኅዳር ወራት በመረመራቸው ማስረጃዎች “መወገዝ ያለባቸው፣ ከዕውቀት ማነስ የተሳሳቱና ወደ ት/ቤት መግባት ያለባቸው፣ መመከር የሚገባቸው” በሚል የከፈላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችና አቀንቃኞች መኖራቸው ተዘግቧል፡፡ እንዲህ ዐይነት አሉባልታዎች የሚናፈሱት ምናልባትም ሊቃውንት ጉባኤው የውሳኔ ሐሳቡን ለሊቃነ ጳጳሳቱ ኮሚቴ ከመራ በኋላ በክትትል ማነስ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በመበዝበዝ ጠንካራ አቋም በያዙቱ ላይ ጫና ለመፍጠር፣ ጉዳዩን የሚከታተለውን ቀናዒ አገልጋይና ምእመን አስተያየትንም በማዛባት ተስፋ ለማስቆረጥ ከመቋመጥ አያልፍም፡፡
ከቀትር በኋላ ቅዱስ ሲኖዶሱ ወደ አጀንዳው በመግባት መወያየቱን እንደሚቀጥል የጉዳዩ ተከታታዮች ተስፋ አድርገዋል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment