በመፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች የተነዛው አሉባልታ
(አንድ አድርገን ግንቦት 5 ፤ 2004ዓ.ም)፡- የመናፍቃኑ ድረ-ገጾች ሲኖዶስ ስብሰባ ሳይጀመር
ቀድመው «ቅዱስ ሲኖዶስ አባ ሠረቀ ብርሃንና ዲ/ን በጋሻውንን የኃይማኖት ህጸጽ የለባቸውም ተሃድሶ መናፍቃንም አይደሉም አለ» የሚል ጽሁፍ በመለጠፍ ምዕመኑን ግራ ለማጋባት ሞክረዋል ፤ አጀንዳ ሳይቀረጽ ይህን
የመሰለ የሀሰት ዘገባ በማውጣት ሰውን ለማወዛገብ ሞክረው ነበር ፤ እስከ አሁን ድረስ አባቶችም በዚህ ጉዳይ ያልተነጋገሩ
አጀንዳውም ያልተነሳ መሆኑን ለማወቅ ችለናል ፤ ይህን የመሰለ አካሄድ ዓላማው ጉዳዩን በሚያዩት አባቶች ላይ ቀድመው
ፕሮፖጋንዳቸውን በመንፋት ተጽህኖ ማሳደር ነው ፤ ነገር ግን የቀረበው በርካታ የቪዲዮ ፤ የድምጽና የጽሁፍ መረጃ እነርሱን ነጻ
የሚያደርግ አይደለም ፤ መረጃዎቹ ጠቅላላ በቁጥር ከ200 ይበልጣሉ ነው የተባለው ፤ ምንፍቅናቸውን በማን አለብኝነት
በየአውደምህረቱና በመጻህፍት ላይ ሲዘሩ ቆይተው አሁን ላይ ነጻ መውጣት ያለ አይመስለንም ፤ ሲጀመርም የእኛ ያልሆኑት ሰዎች
ጉዳያቸው በሲኖዶስ መታየት የለበትም ነበር ፤ ከባለፈው ጥቅምት ጀምሮ እነዚህ
ሰዎች የሚይዙት ዓውደ ምህረት ጠቅላላ ባይጠፋም ቀንሶ ማየት ችለናል ፤ ከሰንበት ትምህር ቤቶች ጋር በቅርበት በመስራት
ዱካቸውን መከታተልና መድረክም እንዳያገኙ የማድረግ ጥሩ ስራ ተሰርቷል ፤ ይህም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል የሚል እምነት አለን
፤ አውደ ምህረቱ ሲነፈጋቸው ምዕመኑን አዳራሽ እየጠሩት ይገኛሉ ፤ ይህ ተግባር በፊትም ሲያደርጉት የነበረ በመሆኑ ብዙም
አልገረመንም ፤ ነገር ግን አሁን ደግሞ ሰዎች አዳራሽ እንዳይሄዱ የሚያስችል ስራ መሰራት አለበት ብለን እናምናለን ፡፡
ከስብሰባው ጋራ በተያያዘ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ገና ባልተወሰነባቸው አጀንዳዎች ሳይቀር መሠረት የሌላቸው አሉባልታዎች እያናፈሱ ይገኛሉ፡፡ ከእኒህም አንዱ በአጀንዳ ተራ ቁጥር 13 “ስለ ሃይማኖት ሕጸጽ በኮሚቴው የሚቀርበውን ሪፖርት መስማትና መወሰን” በሚል የተመለከተው ሲኾን÷ ሊቃውንት ጉባኤው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተመርቶለት በጥቅምትና ኅዳር ወራት በመረመራቸው ማስረጃዎች “መወገዝ ያለባቸው፣ ከዕውቀት ማነስ የተሳሳቱና ወደ ት/ቤት መግባት ያለባቸው፣ መመከር የሚገባቸው” በሚል የከፈላቸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችና አቀንቃኞች መኖራቸው ተዘግቧል፡፡ እንዲህ ዐይነት አሉባልታዎች የሚናፈሱት ምናልባትም ሊቃውንት ጉባኤው የውሳኔ ሐሳቡን ለሊቃነ ጳጳሳቱ ኮሚቴ ከመራ በኋላ በክትትል ማነስ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በመበዝበዝ ጠንካራ አቋም በያዙቱ ላይ ጫና ለመፍጠር፣ ጉዳዩን የሚከታተለውን ቀናዒ አገልጋይና ምእመን አስተያየትንም በማዛባት ተስፋ ለማስቆረጥ ከመቋመጥ አያልፍም፡ ‹‹ይልቁንም በሃይማኖት ሕጸጽ ጉዳይ ማስረጃ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በሊቃውንት ጉባኤና በብፁዓን ሊቃነጳጳሳት ኮሚቴ ከታየ በኋላ ሪፖርቱ ገና ወደ ምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ ውሳኔ ሳይሰጠበት የተወሰኑ ግለሰቦች ከሕጸጽ ነጻ መኾናቸው እንደተረጋገጠ በመፍቀሬ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ብሎጎች የተነዛው አሉባልታ ብዙዎቹን አባቶች ክፉኛ አስቆጥቷል፤ የሚቀርበውን ሪፖርት በጥንቃቄ እንዲመለከቱትም ከወዲሁ አነቃቅቷቸዋል፡፡ አሉባልታውን ከሚያናፍሱት ብሎጎች የአንዳንዶቹ ጸሐፊዎች ሃይማኖታቸው እንዲመረመር ውሳኔ ከተላለፈባቸው ግለሰቦች መካከል እንደሚገኙበት ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተለው የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መርበብ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡›› (ደጀ ሰላም)
አሁን ምን እየሰሩ ይገኛሉ?
ከሚያዚያ 19 እስከ 21 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ጉባኤ በሐዋሳ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ተዘጋጅቶ
ነበር በዚሁ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ዘማሪ ይልማ ኀይሉ
ተገኝቶ የነበረ ሲሆን ይህ ጉባኤ እንዳበቃ በ22/08/2004 ዓ.ም ደግሞ በዲላ
ደ/ሰ/ቅ/ዑራኤል ቤ/ክ/ ተገኝቶ እንዲያገለግል ወንድሞች ጠይቀውት ነበር ፤ በሚቀጥለው ቀን በ23/08/2004 በንግሱ በዓል ተገኝቶ እንዲያገለግል በመጋበዙ በዕለቱ
ከሌሊት ጀምሮ ቅዳሴ አስቀድሶ የንግስ ሰዓቱ ከመድረሱ በፊት ባለው አገልግሎት ለማገልገል ሲጠይቅ በዕለቱ የነበሩት መርሀ ግብር
መሪው የእነ አቶ በጋሻው ደሳለኝ ተከታይና ምንፍቅና አቀንቃኝ ሰው ከተወሰኑ በዓላማ ከሚጋራቸው ግለሰቦች ጋር “እኛ የያዝነው መርሀ ግብር አለን ይበቃናል፤ አንፈልግም፤ አይቻልም፡፡”
ብለው እንዳያገለግል አድገውታል፡፡ ፤ በዚያ ቀን የቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ ከዘማሪ ይልማ ጋር አብረው የነበሩ አባቶችን ‹‹የማይታወቅ
ዘማሪ እና ፍቃድ የሌለውን ዘማሪ እንዴት ትጋብዛላችሁ? እንዴትስ መድረክ ለመስጠት ትሞክራላችሁ ›› በማለት ፤ በተጨማሪም ‹‹ህዝብን ለማጋጨት
በመሞከር›› በሚል ክስ የጽሁፍ ማጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እረ ማነው
የማይታወቅ ዘማሪ ? እነ ወ/ሪት ዘርፌ ከበደ እና መሰሎቻቸው ቢሆኑ በአውደ ምህረቱ እንዲዘሉ በፈቀዱላቸው ነበር ፡፡ ለምን
እንደዚህ ተደረገ ብለው ለጠየቁ ምዕመናን የተመለሰው ምላሽ እዚህ ላይ ለመጻፍ የሚከብድ ነው፡፡ በዚያው ቀን በቅን ልቦና
ለማገልገል የመጣውን የዘማሪ ይልማ ሀይሉን መኪና በተላላኪዎቻው አማካኝነት ጎማውን አስተንፍሰው ዘማሪ ይልማን ክፉኛ
አሳዝነውታል፡፡ በሁኔታው በቀኑ የተደረገው ነገር በመመልከት በርካታ ምዕመናን ስለተፈጠረው ነገር ሲያለቅሱ
ተስተውለዋል ፤ በርካቶችም አዝነዋል፡፡
መርሀ ግብሩን የሚመራው ሰው ክብር ይግባውና ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “የተንጠለጠለው” በማለት ፕሮግራም
ሲመራ እና ከመሰሎቹ ጋር ሲዘምሩ “ማራናታ፣ አሸነፍን” ሲሉ
እንቅስቃሴያቸውም ከፕሮቴስታንት ምንም በማይለይ መልኩ ነበር፡፡ እነዚህ ናቸው ንጹህ ነን የሚሉት ፡፡
የአባቶቻችን አምላክ ወንበዴዎቹን ከቤቱ ገርፎ የሚያስወጣበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ሙሉ እምነታችን ነው፡፡ የቅዱስ
ጊዮርጊስ አምላክ እርሱ ዝም አይልም፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ረድኤት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ
አንድነት፣ የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላዕክት ጥበቃ አይለየን፡፡
ከወደ ደብረብርሀን የሰማነውን ወሬ ወደፊት እንነግሮታለን
ቸር ያሰማን
አሜን
egziabiher yirdachiw hayl ina birtatun yistachiw yekidusan amlak betekiristiyanachinin yitebikilin
ReplyDelete