Monday, August 24, 2015

ቤተ ክርስቲያኒቱ ሙሰኛ ሓላፊዎችን አሳልፋ እንደምትሰጥ ፓትርያርኩ ተናገሩ




 በካህናትና ሠራተኞች ስም የሚደረግ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም

  (From Addis Admass) :-   በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት፣ ዘረፋ እና ምዝበራ ጥፋታቸው የተረጋገጠባቸው የአድባራት እና የሀገረ ስብከት ሙሰኛ ሓላፊዎች ለሕግ ተጠያቂነት ተላልፈው እንደሚሰጡ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ፓትርያርኩ ይህን የማረጋገጫ ቃል የተናገሩት፣ ስለ አድባራቱ የመሬት፣ የሕንጻ እና የልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ተቋማት ኪራይ ተመን በተካሔደው ጥናታዊ ሪፖርት ላይ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፤ ባለፈው ማክሰኞ ጠዋት በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡ጥናታዊ ሪፖርቱ፣ ‹‹አድሏዊ እና ግለሰቦችን ለማጥቃት የተደረገ ነው›› በሚል በአንዳንድ አድባራት ተቃውሞ ማስነሣቱን ዋና ሥራ አስኪያጁ ለፓትርያርኩ ጠቅሰዋል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ የጥናታዊ ሪፖርቱን የመፍትሔ ሐሳቦች በሙሉ ድምፅ በመቀበል፣ የአድባራቱ ሓላፊዎች ጥፋት በሕግ አግባብ እንዲታይና ክሥ እንዲመሠረትባቸው ያሳለፈው ውሳኔም ሌላ አማራጭ እንዲፈለግለት ፓትርያርኩን ጠይቀዋል ተብሏል፡፡ 

Sunday, August 9, 2015

በቤተ ክርስቲያን የሀብት ምዝበራ የፈጸሙ በሕግ እንዲጠየቁ ተወሰነ





  •  ‹‹በመዝባሪ ላይ አልደራደርም፤ እስከ መጨረሻው ከፊት ለፊት ነኝ››
  • የቤተክርስቲያኒቱን መሬት እና ሕንጻ በአዲስ አበባ የመሬት ገበያ አንጻር ሊታሰብ ከማይችልበት ዝቅተኛው በካሬ ሜትር 0.37 ሳንቲም፣ ከፍተኛው ብር 70 ያለጨረታ 15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ የኪራይ ውል የተፈጸመባቸው ውሎች ተገኝተዋል፡፡


(አዲስ አድማስ ነሐሴ 02 2007 ዓ.ም)፡-  በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአድባራቱን ሰፋፊ መሬቶችና የገቢ ማስገኛ ተቋማት እየመዘበሩ ራሳቸውን ያበለጸጉ የአስተዳደር ሓላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መመሪያ ሰጡ፡፡
 
የአስተዳደር ሓላፊዎቹ የአድባራቱን ሰፋፊ መሬቶችና የንግድ ተቋማት ያለጨረታ ከገበያ ዋጋ በታች 15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በመዋዋል የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅሞች አሳልፈው በመስጠት ራሳቸውን አበልጽገዋል- ተብሏል፡፡

Saturday, August 1, 2015

መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ የሙስና ወንጀሎች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ




‹‹መልካም ዜጋ የምታወጣው ተቋም በሙስና መጎዳቷ ለሀገርም ጉዳት ነው ወንጀሉ ላይ መንግሥት መዋቅሩን  ጠብቆ ይገባል፤ በሃይማኖቱ መሸፈን አይችሉም›› / ሺፈራው ተክለ ማርያም


ከመልካም አስተዳደር ዕጦት እና ከተጠያቂነት ሥርዐት መጥፋት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ ሰፍኗል በተባለው ምዝበራ እና ሙስና  መንግሥት መዋቅሩን ጠብቆ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከትላንት በስቲያ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት /ቤቶች አንድነት አመራሮች ጋር በተካሔደው ውይይት፣ መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በሰላም እና በልማት ጉዳዮች ላይ አብሮ እንደሚሠራ የጠቀሱት የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ሓላፊዎች፣ ‹‹ የሕዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም መዋል አለበት፤ በሕዝብ ገንዘብ እንዲቀለድ አንፈልግም፤ መንግሥት ሰላምንና የሕግን የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ ደረጃውን ጠብቆና የሙስና ወንጀል መፈጸሙን አጣርቶ ርምጃ ይወስዳል፤›› ብለዋል፡፡