Thursday, September 28, 2017

የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በኢትዮጵያ




ማክሰኞ መስከረም 16 ቀን 2010 .. በተከበረው የደመራ በዓል ላይ የተገኙት የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ሲሪያን ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፣ በኢትዮጵያ አቻቸው በአቡነ ማትያስ ግብዣ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ከልብ እንዳስደሰታቸው ተናገሩ፡፡ ሰኞ መስከረም 15 ቀን 2010 .. ከቀትር በኋላ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አቀባበል የተደረገላቸው አቡነ ባስሌዎስ ማርቶማ ጳውሎስ ሁለተኛ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲደርሱ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዘማሪያን ‹‹ማንዳሊን›› በሚባል የህንድ ቋንቋ ያጠኑትን ዝማሬ በማቅረብ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ የህንዱ ፓትርያርክ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹በመጀመርያ በአገራችን ቋንቋ በዝማሬ ስለተደረገልን አቀባበል እናመሠግናለን፤›› ብለዋል፡፡ በማስከተልም፣ ‹‹የአገራችንና የቤተ ክርስቲያናችን ጥሩ ወዳጅ በነበሩት በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ማረፊያ በሆነችው በተቀደሰች አገር መገኘታችን ትልቅ ደስታ ይሰማናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ከአሥራ አንድ ወራት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ህንድን በጎበኙበት ጊዜ ምዕመናን ማግኘታቸውን አስታውሰው፣ እሳቸውም በአምስት ቀናት ቆይታቸው ምዕመኑ ከልብ እንደተቀበሉዋቸው ገልጸዋል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓልን በኢትዮጵያ እንዲያከብሩ አቡነ ማቲያስ ግብዣ ሲልኩላቸውም ለሰከንድ ሳያስቡ ተቀብለው ወዲያው እንደመጡም አስረድተዋል፡፡ አቡነ ማቲያስም፣ ‹‹ቅዱስነትዎ በኢትዮጵያ በመገኘትዎ ጥንታዊና ታሪካዊ እህትማማች ቤተ ክርስቲያኖቻችን አንድነታቸውን የመለሱበት በመሆኑ ደስታችን ወሰን የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ሁለቱ ቤተ ክርስቲያናት 52 ዓመታት በኋላ ግንኙነት መጀመራቸው ተገልጿል፡፡ 

source :- ethiopian Reporter