Friday, July 3, 2015

ቤተክርስትያኗ በአይ ኤስ ለተገደሉ ወገኖች ቤተሰቦች ድጋፍ አደረገች
 አዲስ አበባ ሰኔ 25 2007 (ኤፍ ) በስዊዘርላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን በአይ ኤስ ለተገደሉ ወገኖች ቤተሰቦች 400 ሺህ ብር በላይ ስጦታ አበረከቱ። ድጋፉ የተደረገው 11 ተጎጂ ቤተሰቦች ሲሆን፥ ለእያንዳንዳቸው 27 ሺህ 500 ብር በአጠቃላይ 400 ሺህ ብር በላይ ተብርክቶላቸዋል። እጅግ ችግረኛና በእድሜ ለገፉ ስድስት ቤተሰቦችንም ለመደገፍ ቃል ገብተዋል። የቤተክርስትያኗ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት ቤተክርስትያኗ ይሄን አሰቃቂ ድርጊት ከሰማችበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት አከናውናለች።

የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ምንም ዋስትና ወደ ሌለበት አገራት እንዳይሰዳዱ ትልቅ ትምህርት ነው ያሉት ብፁእነታቸው በቀጣይም ቤተክርስትያኗ ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ትሰራለች ብለዋል።ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የተወከሉት አምባሳደር ሙሌ ታረቀኝ በበኩላቸው መንግስት ችግሩን ከምንጩ ለመድረቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ምንጭ:-ኢዜአ

Tuesday, June 30, 2015

ሰበር ዜና – ከብር 4.6 ሚልዮን ብር በላይ ገንዘብ የመዘበሩ ሒሳብ ሹም እና ገንዘብ ያዥ ቃሊቲ ወረዱ

ለትውስታ፡- የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሶስት ዓመት ውስጥ 4.6 ሚሊየን ብር መመዝበራቸው ተገለጠ (ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ የጥቅምት 2006 . ዕትም)
  •  
  • የታገድነው በደብሩ የተፈጸመውን ከፍተኛ የገንዘብ ምዝበራ በማጋለጣችን ነው (ሰበካ ጉባኤው)
  • ጉዳዩን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዚዮን ተይዟል፡፡ 

(አንድ አድርገን ጥቅምት 28 2006 ዓ.ም)፡- በአዲስ አበባ ደቡብ ክፍለ ከተማ የሚገኝው የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ጳግሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ሕገ ወጥ ተግባር ፈጽሟል  በሚል በመታገዱ ችግር መፈጠሩ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ የመጋቢ ሐዲስ ቀሲስ ይልማ ቸርነት ፊርማና ማኅተም ያለበት በቁጥር 450/25/06 በቀን 03/01/2006 ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ የታገደው የሥራ ዘመኑን መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ቢያጠናቅቅም ሌላ የሰበካ ጉባኤ ሳይመረጥ በመቅረቱ በተለያየ ጊዜ ጭቅጭቅ ንትርክና ሁከት እንዲፈጠር በማድረጉ ማታገዱ ይገልጣል፡፡

Sunday, June 21, 2015

የድረሱልን ጥሪ ከአቃቂ ቃሊቲ ምዕመናን!!!


በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ላለፉት ሃምሳ አመታት ከዘጠኝ በላይ ገዳማትና አድባራት ለጥምቀት በዓል ሲገለገሉበት የነበረውን በሀገረ በቀል ዛፎች ያጌጠውን ጥምቀተ ባህር ለልማት በሚል ሰበብ በክፍለ ከተማው  የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ባለስልጣናት ከቤተክርስቲያኗ ዕውቅና ውጪ ስፍራውን  አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ እየታረሰና እየወደመ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡


ከዚህ ቀደም የከተማዋን የመስቀል ማክበሪያ ስፍራን ነጥቀው ሌላ ምትክ ስፍራ እንዳይሰጥ በማድረግ በዓሉን የማጥፋት ተልእኮ በማንገብ እየተንቀሳቀሱ ያሉት  መናፍቃን አሁን ደግሞ ከሃምሳ አመት በላይ የቤተክርስቲያኗን የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ስፍራን ለልማት ሽፋን የማጥፋት ስራቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቦታው ሲወድም እስካሁን አንድም የቤተክርስቲያን አባቶችና አስተዳዳሪዎች ለምን? ብለው  መጠየቅና ጉዳዩን ለምዕመናን ለማሳወቅ አልፈቀዱም፡፡


ታላቅ ሰማያዊ አደራ የተጣለባችሁ አባቶች ከዝምታ ወጥታችሁ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግራችሁ አንድ ትውልድ እግዚአብሔርን የሚያመልክበትና ሃይማኖታዊ ስርዓት የሚፈፅምበት ቦታ ታስከብሩልን ዘንድ በልዑል እግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡