Wednesday, January 29, 2014

ከለበጣ ይቅርታ በኋላ አቶ በጋሻው ደሳለኝ ወደ አውደ ምህረት ሊመለስ ነው


(አንድ አድርገን ጥር 21 2006 ዓ.ም)፡- አቶ በጋሻው ደሳለኝ በሲኖዶስ ዘንድ ከሁለት ዓመት በፊት በአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ስለ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ትምሀርቱ ፤ ስለ ተሃድሶ አቀንቃኝነቱ እና መሰል ጉዳዮችን በሰፊው የያዘ የድምጽ ፤ የምስልና የሰነድ ማስረጃዎች እንደቀረቡበት ይታወቃል ፡፡ ክሱ የቀረበው ከበርካታ መናፍቃንና ተሀድሶ አቀንቃኞች ጋር ሲሆን ግማሾቹ ታግደው ግማሾቹ በይደር መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ ክሱንም በአካል መጥቶ እንዲያስረዳ ለቀረበበት ጉዳይ መልስ እንዲሰጥ የተጠየቀው አቶ በጋሻው ጉዳዩን የማስረሳት መንገድ በመከተል የሀዋሳ ምዕመናን ባልገመቱትና ባልጠበቁት ሁኔታ ጉዳዩን ከውስጥ ሰዎች ፤ ከአባቶችና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን የለበጣ ይቅርታ መጠየቁ በይቅርታውም ብዙዎች እንዳዘኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውሃ በማያዝል የለበጣ የይቅርታ ጉባኤ በኋላ ወደ አውደ ምህረት ይመለሳል ወይስ አይመለስም? የሚለው ጉዳይ በምዕመኑ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል፡፡ አሁን በደረሰን መረጃ መሰረት አቶ በጋሻው ደሳለኝ ከለበጣው የይቅርታ ጉባኤ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብር አበሮቹን በማስከተል ከጥር 23-25 2006 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ጦና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የስብከትና የመዝሙር መርሀ ግብር ማዘጋጀታቸውንና ምዕመኑ ከጉባኤው እንዳይቀር ማስታወቂያ እየሰሩ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል፡፡ ዛሬ ጥር 21 በተከበረው የእመቤታችን የአስተርእዮ(የእመቤታችን በዓለ እረፍት) በዓል ላይ የዕለቱ መርሀ ግብር መሪ ‹‹ከጥር 23 እስከ 25 ድረስ ታዋቂ ሰባኪያን እንደ መጋቢ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ ፤ ዘማሪ ምርትነሽ እና ሌሎችም አገልጋዮች ስለሚገኙ እልል ብላችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑ ፤ በጉባኤውም ተሳተፉ›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Saturday, January 25, 2014

ጥር 18 የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርዎተ አጽሙ


ቅዱስ ጊዮርጊስ ብሩክታይትን ከድራጎን ያዳነበት ስፍራ ፤ ቤሩት

(አንድ አድርገን ጥር 17 2006 ዓ.ም)፡- ከሃዲ ንጉስ ዱድያኖስ ግንድ አምጥተው ቅዱስ ጊዮርጊስን በግንዱ ላይ እንዲቸነክሩት አዘዘ  ፤በላዩም ላይ ሰም አፍስሰው እሳት እንዲያነዱበት አደረገ ከዚህም በኃላ እንደመጭመቂያ ሆኖ ከተሰራ የስቃይ መሳሪያ ላይ አወጡት ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት እንዲጨምቁት አዘዘ ፤ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ እንዲሁ አደረጉበት ነፍሱ ከስጋው ተለየች የሰማእቱን ሰጋ አቃጠሉት ፈጩት አመድም ሆነ ፤ በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ላይ በነፋስ ዘሩትደብረ ይድራስ” ማለት ምድረ በዳ የሆነ ቦታ ነው፡፡ ወታደሮቹ የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ። ያንጊዜም መብረቅ ነጎድጓድ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ ምድርም ከመሰረቷ እስክትናወጽ ድረስ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በብሩ ደመና ወረደ በተራራውም ላይ ተቀመጠ አራቱን የምድር ነፋሳት የሰማእቱን ስጋ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው ከሞትም አስነሳው ኃይሉን አሳደረበት ባርኮትም ወደ ሰማይ አረገ ፤ ከዚህ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየሮጠ ወታደሮቹን ተከተላቸውወንድሞቼ ቆዩኝ ከእናንተ ጋር ልሂድ” እያለ ተጣራ ፤ የእነዚህ የወታደሮች ቁጥራቸው አራት ነበረ ስማቸው ህልቶን ፤ አግሎሲስ ፤ ሶሪስና አስፎሪስ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህንን ታላቅ ተአምራት አይተው አምነዋል፡፡ በኋላም በሰማእትነት አልፈዋል፡፡  ይህ የሆነው ጥር 18  ቀን ነው ይህንንም ቀን " ዝርዎተ አጽሙ " ስትል ቤተ ክርስቲያን ሰማእቱን አዘክራ ትውላለች፡፡ በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ታቦተ ህጉ ውጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንንን የተከሉት ደጉ ንጉስ እምዬ ምኒሊክ ሲሆኑ የዚህን ታላቅ ደብር መሰረቱን ሲጥሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ከሚገኝበት ቦታ አፈሩን በመርከብ አጓጉዘው በበቅሎ በፈረስ አስጭነው  የቤተክርስቲያኑን መሰረት አድርገውታል፡፡

Friday, January 24, 2014

አንጎለላ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን የዝርፊያ ሙከራ ተካሄደባት

(አንድ አድርገን ጥር 15 2006 ዓ.ም)፡- ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ከደብረ ብርሀን ወደ ጁሁር መስመር 12 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝው አንጎለላ ኪዳነ ምህርተ ቤተ ክርስቲያን ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም ዕለተ እሁድ ለሊት ለጥር 12 አጥቢያ የዝርፊያ ሙከራ መደረጉን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ዝርፊያ የተከናወነባት ሲሆን በዝርፊያውም ውስጥ አዋቂ ካህናት እና ደብረ ብርሃን አካባቢ የሚገኙ የተደራጁ ባለሃብቶች መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡ የአሁኑ ዝርፊያ ለማድረግ የተሞከረው በካህናት በር በኩል ሲሆን የካህናት በር የመግቢያው ቁልፍ በብረት መጋዝ ገዝግዘው ቆርጠው ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ እጅግ በርካታ ቅርስ የሚገኝበትን የመቅደሱን በር ሰብሮ ለመግባት ከፍተኛ ድብደባ አድርገው ሲያበቁ በሩ አልከፈት በማለቱ በቦታው የሚገኙትን ሁለት ሙዳይ ምፅዋት ተሸክመው በመውሰድ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ወስደው ሲያበቁ ሙዳይ ምጽዋቱን ጫካ ጥለውት ዘራፊዎቹ ከአካባቢው ተሰውረዋል፡፡ ቅርስ ዘርፎ በመሸጥ በማኅበረሰቡ የሚጠረጠሩት የደብረ ብርሃን አካባቢ ባለሃብቶች እንደ ከዚ ቀደሙ በአሁኑ ላይ ይሳተፉ አይሳተፉ የተገኝ መረጃ ባይኖርም ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራው እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ፖሊስ ይህን ዝርፊያ ሊያደርጉ ይችላሉ ወይም ሊተባበሩ ይችላሉ ያላቸውን የውስጥ ካህናት ቃለ መጠይቅ በማድረግ አንዳንድ መረጃዎችን የሰበሰበ ሲሆን ከዚህ በማለፍ በጥርጣሬ የተያዘ ማንም ሰው አለመኖሩን ለማወቅ ችለናል፡፡ አንጎለላ ኪዳነምህርተ ቤተክርስቲያን ውስጧ ከሚገኝው በብር የማይገመቱ በርካታ ቅርሶች በተጨማሪ ቤተክርስቲያኒቱ አጼ ምኒሊክ የሥላሴን ልጅነት ያገኙባት (ክርስትና የተነሱባት) ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም መናፍቃን እንደ አሸዋ በሚበዙባት በሆሳህና ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝው የቡሻሻ በዓታ ለማርያም ገዳም ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀት ከወረደ በኋላ ምክንያቱ እስከ አሁን ባልታወቀ እሳት ሙሉ በሙሉ መውደሟን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነገስ ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናት ላለመቃጠላቸው ምን ዋስትና አለን… ?
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን

Monday, January 13, 2014

የአ/አበባ ሀ/ስብከት የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ተቃዋሚዎች ገዳማቱንና አድባራቱን አይወክሉም

  •  ‹‹ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት አስተዳደር በቤተ ክርስቲያን ለመዘርጋት የተረቀቀው ሕግ ወደ ኋላ አይመለስም፤ መሥመሩን አይለቅም›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

(አዲስ አድማስ ) ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ /ስብከት ለመዋቅርና አሠራር ለውጥ በባለሞያ ያካሔደውን የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት እንቃወማለን የሚሉ ውስን አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች አይወክሉንም ሲሉ የሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ልዩ ልዩ አገልጋዮችና ምእመናን ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡ ለዘመናት የቆየው የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና የሥራ ሒደት ከነበረው ተስፋፍቶ፣ የወቅቱን አሠራርና ሥልጣኔ የዋጀ ኾኖ በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔና በፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በባለሞያዎች መዘጋጀቱንና ረቂቁ ወደ ታች ለግምገማ ወርዶ እንደተወያዩበት አስተዳዳሪዎቹና አገልጋዮቹ ጠቅሰዋል፡፡