ተጻፈ ፡ በፍቅር ለይኩን
- ‹‹በምስክርነት ካልጻፍንና ካልተናገርን የሚመጣው ትውልድ በምን ያውቃል ትውልድ ያውቅ ዘንድ ጥቂት እንጽፋለን፡፡ እኛማ እንሞታለን፣ እንጣላለንም …፡፡›› (ከአራቱ ኃያላን መጽሐፍ የተወሰደ)
ጥንታዊውንና የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ ለማጥናትና በወጉ ለመሰነድ ካሉብንና ከሚጠቀሱ ችግሮች መካከል የመረጃ እጥረትና ክፍተት ዋንኛውና ተጠቃሹ ነው፡፡ በዘመናችንም ቢሆን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ሲነገርም ሆነ ሲጻፍ ‹‹የትኛዋ ኢትዮጵያ›› ወደሚል ክርክርና ማብቂያ የሌለው ወደሚመስል ሙግት ወይም እሰጥ አገባ እያስገባን ያለው በከፊልም ቢሆን ስለትናንትና ያለን መረጃ የሳሳና እንዲያም ሲል ደግሞ እንደ ለማኝ እህል የተደበላለቀ የመሆኑ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
የሺሕ ዘመናት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ባለቤት የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ይህን ታሪኳንና ሥልጣኔዋን በተመለከተ የነበሩን ታሪካዊ መረጃዎቻችንና ቅርሶቻችን በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ በውጭ አገር ወራሪዎችና በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ በተከሰቱ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ስደትና የእርስ በርስ ጦርነቶች ምክንያት ለመጥፋት፣ ለዝርፊያና ለውድመት እንዲዳረጉ ሆነዋል፡፡
በእጃችን አሉን የምንላቸውና ከመጥፋት፣ ከውድመት፣ ከዝርፊያና ከመበላሸት የተረፉትን ታሪካዊ መረጃዎቻችንና የሥነ ጽሑፍ ቅርሶቻችንንም በወጉ መርምሮና በሚገባ አጥንቶ በማቅረብ ረገድ በጣት ከምንቆጥራቸው ኢትዮጵያውያን ጥቂት ምሁራን በስተቀር በታሪካዊ መዝገቦቻችንና ቅርሶቻችን ላይ በአብዛኛውና በቀዳሚነት ሰፊና ጥልቅ የሆነ ጥናትና ምርምር ያደረጉት የውጭ ምሁራንና ተመራማሪዎች ናቸው፡፡
መሰንበቻውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የቀደምት ምሁራንን ፈለግ በመከተል ለአብዛኞቻችን እንግዶች ስለሆኑት አባቶች (አቡነ አኖሬዎስ፣ አቡነ ፊሊጶስ፣ አቡነ በጸሎተ ሚካኤልና አቡነ አሮን) አስተምህሮታቸውንና ተጋድሎአቸውን፣ የአገራችንን የመካከለኛው ዘመን ታሪክንና ተጓዳኝ የሆኑ ርእሰ ጉዳዮችን በሰፊው የሚተርከውን ‹‹አራቱ ኃያላን›› መጽሐፍን በእጃችን እንዲገባ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን የዋጋው መናር ብዙዎችን እያነጋገርና ጉልበቴ በርታ በርታ በማለት ላይ ያለውን ደካማውን የኅብረተሰባችን የንባብ ባህል ላይ ሌላ ተግዳሮት እንዳይሆን የሚል ስጋትን መፍጠሩ ሳይዘነጋ፡፡
የዚህ መጽሐፍ መታተም ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ በመጽሐፉ ምረቃ ዕለት ሙያዊ የሆነ አስተያየትና ግምገማ ያቀረቡ ምሁራን በሰፊው አንስተውታል፡፡ በዚሁ መጽሐፍ ላይ ሙያዊ አስተያየታቸውን ከሰጡ ምሁራን መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በመጽሐፉ ላይ ባቀረቡት አጭር ዳሰሳ፣ ‹‹በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ በወጉ ለማጥናትና ለመሰነድ ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት ረገድ እንደነዚህ ያሉት መጻሕፍት ያላቸው ጠቃሜታ የጎላ እንደሆነ ነው፤›› ያሰመሩበት፡፡ ፕሮፌሰሩ ጨምረው እንደገለጹትም መጽሐፉ በአካዴሚያዊ አጻጻፍ ስልት፣ በማብራሪያዎች፣ በግርጌ ማስታወሻዎችና መዘርዝሮችን ጭምር አካቶ በጥንቃቄ ታስቦ የተዘጋጀ መጽሐፍ በመሆኑ ለአጥኚዎችና ለተመራማሪዎች ጥሩ ማጣቀሻ ሥራ ሊሆን እንደሚችል ጭምር ነው የጠቆሙት፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ላይ ያደረጉት የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ውዱ ጣፈጠም፣ መጽሐፉ የአገራችንን መካከለኛ ዘመን ታሪክና ተጓዳኝ ዘመነኛ እውነቶችን አካቶ ያቀረበ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በየዘመናቱ ተነስተው በነበሩ የሃይማኖት ሰዎችና ጥልቅ አሳቢዎች ላይ ነገሥታቱና ገዢዎች ሲፈጽሙባቸው የነበረውን አሰቃቂ የሆነ ቅጣትና ኢሰብአዊነት የተንጸባረቀበትን ግፍ በደርግ ዘመን ከሆነው ከቀይ ሽብር ጋር አነጻጽረው አቅርበውታል፡፡
ሌላኛው የጥንት ጽሑፎችና መዛግብት (የፊሎሎጂ) ምሁሩ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ በበኩላቸው ባቀረቡት አስተያየት፣ ‹‹አራቱም መጻሕፍት በአንድ ቅጽ ተጠቃለው መቅረባቸው ለአንባቢው የበለጠ ዕድል ይሰጣል፡፡ የአራቱ አበው የተጋድሎ ታሪክ ሕዝባችን በሚረዳው በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሞ መቅረቡም ጠቀሜታውን ከፍ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ ለቋንቋ፣ ለሥነ ጽሑፍ፣ ለታሪክና ለፊሎሎጂ ጥናት ያለው ጠቀሜታ ጉልህ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
የአራቱ ኃያላንን ሕይወትና ተጋድሎአቸውን በጨረፍታ
እንደአለመታደል ሆኖ በዓለም ታሪክ ስለ እምነታቸው፣ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ሰለ ሰው ልጆች ነፃነት፣ ሰብአዊ መብትና ክብር ስለተሟገቱ ሰዎች ሲነሳ ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ አባቶችና ጥልቅ አሳቢዎች ስማቸውም ሆነ ታሪካቸው እምብዛም አይነሳም፣ አይተረክም፡፡ ዓለማችን ግን ከሃይማኖት መምህርነታቸውና አገልጋይነታቸው ባሻገር ዘረኝነትንና ጠባብነትን በመዋጋት፣ ለእውነትና ለፍትሕ በመቆም፣ ለተጨቆኑና መብታቸውን ለተገፈፉ የምድራችን ምንዱባንና ግፉአን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ ረገድ እውቅና የሰጠቻቸው ውድ የሆኑ ጀግኖች አሏት፡፡ የምትዘክራቸው፣ የምታከብራቸው፡፡
እነዚህ የእምነት አርበኞች እንደየሃይማኖታቸው የሥነ ምግባር ድንጋጌዎች፣ የሞራል ሕጎችና አስተምህሮቶች ሕይወታችውን ጭምር ሳይቀር በመሠዋት ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ጽፈው አልፈዋል፡፡ ከእነዚህም ምሁርና የጥቁር ሕዝቦች መብት ታጋይ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ በሕዝባቸው ዘንድ ‹‹ታላቁ ነፍስ›› በመባል የሚጠሩት የሂንዱ እምነት ተከታይና ወግ አጥባቂ የሆኑት የህንድ የነጻነት አባት ማህተመ ጋንዲ ይገኙበታል፡፡
አራቱ ኃያላን መጽሐፍም ልክ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግና ማኅተመ ጋንዲ ሁሉ ለእምነታቸው ስለ ተጋደሉ፣ ስለ እውነትና ፍትሕ አጥብቀው ስለተሟገቱ ኢትዮጵያውያን አባቶች አስገራሚ ሕይወትና ተጋድሎአቸውን ያስነብበናል፡፡ እነዚህ አባቶች ይላል የአራቱ ኃያላን ደራሲ ዲያቆን ዳንኤል፣ ‹‹ዘረኝነትንና ጠባብነትን እስከመጨረሻው የተዋጉ፣ የፍቅር መሥፈርታቸው ሰው መሆን ብቻ የሆነ፣ ለእምነታቸውና ለአቋማቸው ሲሉ ከነገሥታቱና ከገዢዎች ጋር ፊት ለፊት የተገዳደሩ፣ ከእሳት፣ ከግርፋት፣ ከአራዊት፣ ከዘንዶ፣ ከግዞት፣ ከስደት ጋር ተጋፍጠው እምነታቸውን ያስከበሩ፣ ነገሥታቱ በተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ ያለ ፍርኃት የገሠጹ …›› የእምነት አርበኞችና ጀግኖች ናቸው ሲል ይገልጻቸዋል፡፡
እነዚህ አባቶችና ጥልቅ አሳቢዎች ነገሥታቱና ሹመኞቻቸው የማይገባቸውን ሀብት ሲያከማቹ፣ ከሥነ ምግባር ሕግ ሲወድቁ፣ ፍትሕን በማዛባት ድኃውን ሲገፉና ሲያንገላቱ፣ መኳንንቱን፣ ነገሥታቱንና ገዢዎችን እንዲሁም ከቤተ መንግሥቱ ጋር እጅና ጓንት የሆኑ የቤተ ክህነቱን መሪዎችንና አገልጋዮችን ሳይቀሩ ሕገ እግዚአብሔርን ጥሳችኋል፣ ድኃን በድላችኋል፣ ገፍታችኋል፣ ፍርድን አጉድላችኋል በማለት ፊት ለፊት የተሟገቱ፣ ዕኩይ የሆኑ ሥራቸውን በማውገዛቸው፣ ለእውነትና ለፍትሕ እስከ መጨረሻው በመቆማቸው የተነሳ ግዞት፣ መከራና እንዲያም ሲል አሰቃቂና ኢሰብአዊ የሆነ ግፍ የደረሰባቸውና ሞት የታወጀባቸው በርካታ ጀግኖች እንደነበሩን ነው ታሪካችን በሰፊው የሚነግረን፡፡
በእነዚህ ሰዎች ስለ እምነታቸውና ሕግ ይከበር፣ ፍትሕ አይጓደል፣ ፍርድ አይጣስ፣ ድኃ አይበደል በማለታቸው የተነሳ የደረሰባቸውን የቅጣቱን ዓይነት፣ ኢሰብአዊነቱን፣ ዘግናኝነቱንና የተላለፈባቸውን ርኅራኄ የለሽ የሞት ፍርድ በታሪክ ድርሳኖቻችን ውስጥ ስንፈትሽ የትናንትናይቱ ኢትዮጵያ ነገሥታትና ገዢዎች አምባ ገነንነት፣ ጭካኔና ክፋት የት ድረስ እንደነበር እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡
ለዚህም ይመስላል ከጥቂት ዓመታት በፊት በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በተዘጋጀው ‹‹በሕግ አምላክ›› መጽሐፍ መቅድመ ሐተታ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ‹‹ … በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከግእዝ ወደ አማርኛ የተተረጐመው የደቂቀ እስጢፋኖስ ሰቆቃ ያስደነግጣል፤ ያሳዝናል፤ ያስቆጣል፤ የማናውቀውን ራሳችንን እርቃናችንን ያሳየናል፡፡ ከስድስት መቶ ዓመታት በኋላም ፍንክች አለማለታችን ውስጣችንን እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡ ይህንን መጽሐፍ ሳነብ ምዕራባውያን (በእንግሊዝኛ) ‹‹ቶርቸር›› (የግእዝ ፀሐፊዎች “ኩነኔ”) የሚሉትን ሰውን የማሰቃየትን ዘዴ እኛ የፈጠርነው መሰለኝ፤›› ለማለት የተገደዱት፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ‹‹አራቱ ኃያላን›› በሚል የቀረቡት አባቶች እንደ ዛሬዎቹ አንዳንድ አባቶችና የሃይማኖት መሪዎች ‹‹ዘመን የወለደውን ንጉሥ የወደደውን ሰጥ ለጥ ብለህ ተቀበል›› እና ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይወቀስ›› በሚል ያረጀና ያፈጀ ብሂል አንደበታቸውን ሸብበው የመከራንና ጭቆናን ቀንበር የሚያጠብቁ፣ እውነት እንደ ዝንብ በአደባባይ ሲደፈጠጥ፣ ፍትሕ ሲጓደል ‹‹የዝኆን ጆሮ ይስጠኝ›› በማለት ዝም የሚሉ አባቶች፣ አሊያም በሚያግባባን ቋንቋ ለመጠቀም ‹‹አድር ባይና አስመሳይ›› አባቶች እንዳልነበሩ በዚህ መጽሐፍ የተተረከው ታሪካቸውና ተጋድሎአቸው አስረግጦ ነው የሚነግረን፡፡
በእኛ ዘመንም በየትኛውም ዘርፍ በማኅበራዊው፣ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እንዲህ ዓይነቶቹን ለእውነት ስለእውነት የሚቆሙ፣ ለፍትሕ የሚከራከሩ፣ ለምድራችን ጎስቋሎችና ምንዱባን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙ፣ ከራሳቸው ይልቅ የሚመሩትን ሕዝባቸውን የሚያስቀድሙ ለትውልዱ ምሳሌና አርአያ የሚሆኑ ሰው የሆኑ ሰዎች በእርግጥ ያስፈልጉናል፡፡
በአራቱ ኃያላን መጽሐፍ የመንፈስ ጽናታቸው፣ እስከ ሞትም ድረስ የዘለቀው ተጋድሎአቸውና የእምነት አርበኝነታቸው የተተረከላቸው አባቶች ታሪካቸው እጅጉን ይመስጣል፡፡ በእኛ ዘመንም እንዲህ ዓይነቶቹን ሰው የሆኑ ሰዎች በሃይማኖትና በፍትሕ ተቋሞቻችን፣ በፖለቲካው መድረክ፣ በቤተ መንግሥቱና በቤተ ክህነቱ፣ በማኅበረሳባችን መካከልም በዝተው እንዲኖሩልን አብዝተን፣ አጥብቀን እንመኝ፡፡ ታዲያማ እስከመቼ እኛና አፍሪካ ‹‹The Beautifuls are not yet
born!›› (ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም!) በሚል ፍቅርን፣ እውነትን፣ ፍትሕን፣ ነጻነትን … የሚሰብኩና በተግባር የሚገልጹ ጀግኖችን እንደተጠማንና እንደተራብን እንዘልቃለን፡፡
ሰላም እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አምላካችን በሰላም አደረሰን።
ReplyDeleteይህን ከላይ የተጻፈውን ጽሁፍ ሳነብ “አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።” የተባለው ሰቆቃ እስካሁን ድረስ እውን ሆኖ እንደቀጠለ አየሁትና በጣም በጣም አዘንኩ። በመጀመሪያ ስለመንፈሳውያን ሰዎች ታሪክ የራሳችን የሆነውን አጥብቀው የያዙ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እያሉን የአካዳሚክ ስኮላሮች አስተያየት ስጡ የሚባልበት የነሱም አስተያየት ከነማእረጋቸው እየተሞካሼ ለኛ ለአንባቢዎች የሚቀርብበት ምክንያት አልገባኝም። የምእራባዊ ስኮላርሺፕ ዋነኛ ኢላማ የእግዚአብሔርን እምነት ከጨዋታ ውጭ ማድረግ እንደሆነ ብዙ ኢትዮጵያውያን ገና የገባቸው አይመስልም። በምእራባዊ ትምህርት የባቢሎን ክህነት (PhD) ያገኙ አንድ ወይም ሁለት ኢትዮጵያውያን ማእረጋችን ከምእራባውያን ቢሆንም እግዚአብሔርን እናምናለን ስላሉ ብቻ መንፈሳዊው ነገር ለምእራባዊ ዓለማዊ የምርምርና የድፍረት ግሽለጣ ተጠፍሮ መቅረብ የለበትም።
ወንድማችን ዳንኤል የጻፈውን “አራቱ ኃያላን” የሚባለውን መጽሐፍ አላነበበኩም። በአቅራቢያየ ከመጣ እግዚአብሔር በፈቀደ ገዝቸ አነባለሁ። መልካም ይሆናል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። ከላይ ያለውን ጽሁፍ የጻፉት ሰውየ እንደጠቀሱትና እነ ዶክተር ጌታቸው በምእራባውያን አነሳሺነት (እኔ አጣርቸ አላወኩም እንጂ ዶክተር አለሜ እሸቴ በአንድ ጽሁፋቸው ጠቆም እንዳደረጉት ከሆነ በጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ብዙ ዶላር ተከፍሏቸው) መጀመሪያ ከግእዝ ወደ እንግሊዝኛ የተረጎሙት ከዛ ቆይቶ ደግሞ ወደ አማርኛ የተረጎሙት “ደቂቀ እስጢፋኖስ” እንደሚባለው መጽሐፍ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውጭ ሰዎች የሚጠቀሙበት መሣሪያ አይሆንም ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። “ደቂቀ እስጢፋኖስ” የሚባለውን መጽሐፍ በመጠቀም ሉተራውያን ብዙ ኢትዮጵያውያንን ከኃይማኖት አስወጥተው ወደ ተረገመው ወደ ፕሮቴስታንት ሠፈር ወስደዋል። የተወሰዱትም እንዳይመለሱ የክህደት ማበራታቻ አድርገው ተጠቅመውበታል። ይህን መጽሐፍ የተረጎሙት ሰውየ “ባህረ ሐሳብ” በተባለው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያን ታሪክ ተችተዋል። ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የዘመን ቆጠራ የላትም ብለዋል። በዚሁ መጽሃፋቸው አፋቸውን ሞልተው በባቢሎን ድፍረት መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ ዝቅ በማድረግ ተችተዋል። (ለአብነት ገጽ ፳፰ ን ይመልከቱ)። በነገራችን ላይ ትችታቸው የሳይንስን ትንታኔ በመጥቀስ መጽሐፍ ቅዱስን ተሳስቷል እያሉ ሲሆን አስተካክለው የማያውቁትን ሳይንስን ተጠቅመው መንፈሳዊ ሚስጢሩን የማያውቁትን መጽሐፍ ቅዱስ መተቸታቸው የሚያሳዝን ነው። የትችታቸው አይነት ህሊናቸው ምን ያህል በትእቢት እንደደነቆረ ያሳያል። ብዙ ኢትዮጵያውያን የባቢሎን ማእረጋቸውን እያየ በተለይ አማኝ የሚመስል መልክ ስላላቸው ሳይገባቸው ይከተሏቸዋል። መጨረሻው ውድቀት ነው። ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤልም እሳቸውን ሲጠቅስ አይቼ ስለጉዳዩ ላማክረው ፈልጌ ከየት ላግኘው? ተራ ሰው ነኝና እሱ እኔን አያውቀኝ፣ ከሳቸው ጋር ያደረገውን ቁርኝት ሳይ የሚሰማኝም አይመስለኝም። እኔም ያየሁት አንድ ጊዜ ነው። የዛሬ አስራ አንድ አመት አካባቢ አሜሪካ አገር መጥቶ አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲያስተምረን ከመስማቴ ውጭ አላውቀውም። ዳንኤል የሚባለው እሱ መሆኑን ያወኩትም ከሄደ ከብዙ ጊዜ በኋላ ነበር። ትዝ እንደሚለኝ ያን ጊዜ ያስተማረው ትምህርት ጥሩ ሆኖ ነበር የተሰማኝ። ያን ጊዜ በነበረው እምነቱ ጸንቶ ይቆያል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደነ ዶክተር ጌታቸው ለመሆን መፈለግ ግን አስጸያፊ ምኞት ነው። የተቀደሰውን መንገድ ትቶ የክፉዎችን ምክር መሻት፣ የዋዘኞችንም ወንበር መመኘት እግዚአብሔር የሚወደው አኪያሄድ አይሆንም።
እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።
ኃይለሚካኤል
ሰላም ጋይለሚካኤል በአጭሩ የሰቀመጥከው ትንተናሕ ስርአት የያዘ ግሩም ነው ።ወንድሚችን ዳንኤልም በተፈጥሮው ዝንጉ ሰው አይመስለኝም በሆነው የመገናኛ መንገድ ተጠቅሞ ጥርጣሪሕን እንደሜቀርፍልሕ ተስፋ አለኝ። አዲሱን መጽሐፍ ማንበብን በተመለከተ ባልሳሳት ባሕር ማዶ ለመድረስ በእግረኛ የተላከ ይመሰለኛል። ለሁሉም ያለው ምርጫ በጉጉት መጠበቅ ነው ።
ReplyDelete