Saturday, January 25, 2014

ጥር 18 የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርዎተ አጽሙ


ቅዱስ ጊዮርጊስ ብሩክታይትን ከድራጎን ያዳነበት ስፍራ ፤ ቤሩት

(አንድ አድርገን ጥር 17 2006 ዓ.ም)፡- ከሃዲ ንጉስ ዱድያኖስ ግንድ አምጥተው ቅዱስ ጊዮርጊስን በግንዱ ላይ እንዲቸነክሩት አዘዘ  ፤በላዩም ላይ ሰም አፍስሰው እሳት እንዲያነዱበት አደረገ ከዚህም በኃላ እንደመጭመቂያ ሆኖ ከተሰራ የስቃይ መሳሪያ ላይ አወጡት ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት እንዲጨምቁት አዘዘ ፤ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ እንዲሁ አደረጉበት ነፍሱ ከስጋው ተለየች የሰማእቱን ሰጋ አቃጠሉት ፈጩት አመድም ሆነ ፤ በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ላይ በነፋስ ዘሩትደብረ ይድራስ” ማለት ምድረ በዳ የሆነ ቦታ ነው፡፡ ወታደሮቹ የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ። ያንጊዜም መብረቅ ነጎድጓድ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ ምድርም ከመሰረቷ እስክትናወጽ ድረስ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በብሩ ደመና ወረደ በተራራውም ላይ ተቀመጠ አራቱን የምድር ነፋሳት የሰማእቱን ስጋ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው ከሞትም አስነሳው ኃይሉን አሳደረበት ባርኮትም ወደ ሰማይ አረገ ፤ ከዚህ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየሮጠ ወታደሮቹን ተከተላቸውወንድሞቼ ቆዩኝ ከእናንተ ጋር ልሂድ” እያለ ተጣራ ፤ የእነዚህ የወታደሮች ቁጥራቸው አራት ነበረ ስማቸው ህልቶን ፤ አግሎሲስ ፤ ሶሪስና አስፎሪስ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህንን ታላቅ ተአምራት አይተው አምነዋል፡፡ በኋላም በሰማእትነት አልፈዋል፡፡  ይህ የሆነው ጥር 18  ቀን ነው ይህንንም ቀን " ዝርዎተ አጽሙ " ስትል ቤተ ክርስቲያን ሰማእቱን አዘክራ ትውላለች፡፡ በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ታቦተ ህጉ ውጥቶ በደማቁ ተከብሮ ይውላል። ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንንን የተከሉት ደጉ ንጉስ እምዬ ምኒሊክ ሲሆኑ የዚህን ታላቅ ደብር መሰረቱን ሲጥሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ መቃብር ከሚገኝበት ቦታ አፈሩን በመርከብ አጓጉዘው በበቅሎ በፈረስ አስጭነው  የቤተክርስቲያኑን መሰረት አድርገውታል፡፡


ከዚህ ጋር በተያያዘ ይኽ በዓል በደብረ ብርሀን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ሁኔታ እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ ደብረ ብርሀን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ከ22 ዓመት በፊት በደርግና በኢህአዴግ መካከል በሚደረገው ጦርነት ወቅት በቤተ ክርስቲያኑ በስህተት ይሁን ሆን ተብሎ እስከ አሁን ባልታወቀበት ሁኔታ 50 ሜትር ራዲየስ ላይ የሚገኝ ማንኛውንም ነገር ማጥፋት የሚችል ከፍተኛ ቦንብ በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ ከአየር ተዋጊ ጀቶች አማካኝነት ተጥሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜው የተጣለው ይህ ብዙ ነገር ማጥፋት የሚችል ተቀጣጣይ ቦምብ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተዓምር ውስጡ ያለው ነገር በመፍሰሱ ምንም ጉዳት ሳያደርስ በባለሙያዎች ተነስቶ ጠባሴ የሚገኘው የጦር ካምፕ ተጓጉዟል፡፡

በደብረ ብርሀን ከጥር 10 እስከ ጥር 18 ድረስ ታቦታት ጥምቀተ ባሕር በመገኝት በአሉን በደማቅ ሁኔታ ያከብራሉ፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በቦታው ላይ ተገኝተን እንደተመለከትነው ጥር 10 በከተራ በዓል ሁሉም ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባሕር የሚወጡ ሲሆን ጥር 11 አብዛኞቹ ተመልሰው ጥር 12 ወደ ማደሪያው የሚገባው የቅዱስ ሚካኤል ታቦታ በቦታው ይቀራል፡፡ ጥር 12 ምዕመኑ የቅዱስ ሚካኤልን ታቦታ ወደ ማደሪያው ከመለሰ በኋላ ወዲያው የእግዚአብሔር አብን ታቦትን ለማውጣት ወደ ቤተክርስያኑ ያመራል ፤ ጥር 12 የወጣው የእግዚአብሔር አብ ታቦታ ጥር 13 ወደ ማደሪያው ሲመለስ ፤ በዓሉን በመቀጠል ጥር 14 የሕጻኑ ቂርቆስ ታቦትን  በጥምቀት ቦታ በማሳደር ጥር 15 ቀን በታላቅ ድምቀት በእናቶች እልልታ በሰንበት ተማሪዎች ዝማሬ ወደ ማረፊያው ይመለሳል፡፡ ከአንድ ቀን ቆይታ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዝርዎተ አጽሙ እና ከ22 ዓመት በፊት በቤተ ክርስቲያኑ ስለተደረገው ታላቅ ተዓምራት በማስመልከት ጥር 17 ቀን የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦታ ከማረፊያው ተነስቶ ጥምቀተ ባሕር ታቦታት ማረፊያ ድረስ በመሄድ አዳሩን እዚያው በማድረግ በጥር 18 ቀን ወደ ማደሪያው ይመለሳል፡፡ ጥር 10 ቀን በከተራ ቀን የተጀመረው በዓል ጥር 18 በቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል በታላቅ ስርዓት ፍጻሜውን ያገኛል፡፡  

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን ።

3 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን።

    ReplyDelete
  2. Ye KIDUS GIORGIS AMILAL YETMSEGNE yehun qale hiwoten yasemali Amen

    ReplyDelete