Friday, January 24, 2014

አንጎለላ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን የዝርፊያ ሙከራ ተካሄደባት

(አንድ አድርገን ጥር 15 2006 ዓ.ም)፡- ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ከደብረ ብርሀን ወደ ጁሁር መስመር 12 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝው አንጎለላ ኪዳነ ምህርተ ቤተ ክርስቲያን ጥር 11 ቀን 2006 ዓ.ም ዕለተ እሁድ ለሊት ለጥር 12 አጥቢያ የዝርፊያ ሙከራ መደረጉን ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ዝርፊያ የተከናወነባት ሲሆን በዝርፊያውም ውስጥ አዋቂ ካህናት እና ደብረ ብርሃን አካባቢ የሚገኙ የተደራጁ ባለሃብቶች መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡ የአሁኑ ዝርፊያ ለማድረግ የተሞከረው በካህናት በር በኩል ሲሆን የካህናት በር የመግቢያው ቁልፍ በብረት መጋዝ ገዝግዘው ቆርጠው ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ እጅግ በርካታ ቅርስ የሚገኝበትን የመቅደሱን በር ሰብሮ ለመግባት ከፍተኛ ድብደባ አድርገው ሲያበቁ በሩ አልከፈት በማለቱ በቦታው የሚገኙትን ሁለት ሙዳይ ምፅዋት ተሸክመው በመውሰድ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ወስደው ሲያበቁ ሙዳይ ምጽዋቱን ጫካ ጥለውት ዘራፊዎቹ ከአካባቢው ተሰውረዋል፡፡ ቅርስ ዘርፎ በመሸጥ በማኅበረሰቡ የሚጠረጠሩት የደብረ ብርሃን አካባቢ ባለሃብቶች እንደ ከዚ ቀደሙ በአሁኑ ላይ ይሳተፉ አይሳተፉ የተገኝ መረጃ ባይኖርም ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራው እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ፖሊስ ይህን ዝርፊያ ሊያደርጉ ይችላሉ ወይም ሊተባበሩ ይችላሉ ያላቸውን የውስጥ ካህናት ቃለ መጠይቅ በማድረግ አንዳንድ መረጃዎችን የሰበሰበ ሲሆን ከዚህ በማለፍ በጥርጣሬ የተያዘ ማንም ሰው አለመኖሩን ለማወቅ ችለናል፡፡ አንጎለላ ኪዳነምህርተ ቤተክርስቲያን ውስጧ ከሚገኝው በብር የማይገመቱ በርካታ ቅርሶች በተጨማሪ ቤተክርስቲያኒቱ አጼ ምኒሊክ የሥላሴን ልጅነት ያገኙባት (ክርስትና የተነሱባት) ቤተ ክርስቲያን መሆኗ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ጥር 10 ቀን 2006 ዓ.ም መናፍቃን እንደ አሸዋ በሚበዙባት በሆሳህና ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኝው የቡሻሻ በዓታ ለማርያም ገዳም ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀት ከወረደ በኋላ ምክንያቱ እስከ አሁን ባልታወቀ እሳት ሙሉ በሙሉ መውደሟን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነገስ ተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናት ላለመቃጠላቸው ምን ዋስትና አለን… ?
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቅልን

1 comment:

  1. አሜን! አጽራረ ቤተክርስቴያንን ያርቅልን ።

    ReplyDelete