Saturday, January 4, 2014

በአዲስ አበባ የወንድ የጎዳና ሕጻናት ላይ የሚደርሰው የወሲብ ጥቃት አስመልከቶ የተደረገ ጥናት


  • በጥናቱ ላይ 35 መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተጨማሪ ቁልፍ የመረጃ ምንጮች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል፡፡
  • ጥቃት የደረሰባቸው አካላት ፍትህ እንዳያገኙ የምርመራው ሂደት ውጤታማ እንዳይሆን የከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ተጽህኖም አለበት ተብሏል፡፡
  • አንድ የፖሊስ መኮንን ባልደረባ በቃል እንደተናገረው “ በጉዳዩ ጥቂት ደረጃ ላይ እንደደረስክ ርቀህ እንዳትሄድ በአንዳንድ ሃላፊዎች ትከለከላለህ፡፡ በተወሰነ ደረጃ በኋላም ክትትል እንድታቆም ትታዘዛለህ፡፡”
  • “ከፍተኛ የመንግሥት አካላትን ለውይይት በምንጋብዝባቸው ጊዜ በጉዳዩ ላይ መነጋገርን የሚጠሉ ሃላፊዎችና ህግ አውጪዎች አጋጥመውናል፡፡”
  • ቁልፍ የመረጃ ምንጮች በወንዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ጥልቀት በአስፈሪ ሁኔታ በከተማዋ እየተስፋፋ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
  • 25 በመቶ ያህል የወሲብ ጥቃት ሰለባ የጎዳና ወንድ ሕጻናት በአጥቂነት ተሰልፈዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ህጻናቱ በድርጊቱ ተሳታፊ እየሆኑ እንደመጡ ነው፡፡
  • በህብረተሰቡ ዘንድ የችግሩ ስፋት አይታወቅም፡፡ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ በርካታ ሕጻናት የወሲብ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ችግሩ በአስከፊ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ መገናኛ ብዙሀን ድርጊቱን ለማስቆም የራሳቸው ድርሻ እየተወጡ አይደለም፡፡

(አንድ አድርገን ታህሳሥ 27 2006 ዓ.ም)፡- ከ2 ዓመት በፊት አዲስ አበባ የመጀመሪያውን የግብረ ሰዶም ስብሰባ ስታስተናግድ በርካቶች ድምጻቸውን በግልጽ በማሰማት ከፍተኛ ተቃውሟቸውን መግለጻቸው ይታወቃል ፡፡ የተቃውሞ ድምጹ ስብሰባው ከመደረግ ባይከለክለው እንኳ ፤ በወቅቱ ወጣቱ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት አባቶች ተቃዎሟቸውን ለመግለጽ የተሰበሰቡበት የጊዮን ሆቴሉ ስብሰባ በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አማካኝነት አቋማቸውን እንዳይገልጹ የተደረገበት ድራማዊ ትዕይንት መከናወኑ ትዝ ይለናል ፡፡ የግብረ ሰዶማውያን ስብሰባ ይካሄድበታል የተባለው ካሳንቺስ አካባቢ የሚገኝው አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ፊት ለፊት በአካል ለመቃወም የወጡት ጥቂት ወጣቶች በፌደራል ፖሊስ ተይዘው ወደ ማረፊያ እንደወረዱ እና ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ከእስር እንደተፈቱም የምናስታውሰው የወቅቱ ትኩስ አጀንዳም ነበር ፡፡ ስብሰባውን ያስተናገድው  ኢንተርናሽናል ሆቴልም አይኔን ግንባር ያድርገው “ግብረሰዶማውያን በሆቴሌ እልተሰበሰቡም” በማለት እንደሸመጠጠም የሚታወቅ ነገር ነው ፡፡ ጊዜው አልፎ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታው ከተመለሱም በኋላ መንግሥት ሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን የሃይማኖት አባቶች በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ በመሰብሰብ ይህን ጸያፍ ድርጊት ከረፈደም እንዲኮንኑና እንደማይቀበሉት መግለጫ እንዲሰጡም ማድረጉ ይታወሳል፡፡ 

ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ በየጊዜው በየጋዜጣው የሚነበቡት እና በኤፍ ኤም ሬዲዮኖች ከሚሰሙት ከተማዊ ወሬዎች ውስጥ የወንድ የጎዳና ሕጻናት ላይ የሚደርሰው የወሲብ ጥቃት አንዱና አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ከቀን ቀን የሚሰማው ወሬ ለጆሮ ድሎት የሚሰጥ ባይሆንም ይህ ጉዳይ ዘር ቀለም ሃይማኖት ሳይለይ ጥቁር እንግዳ ሆኖ በሀገራችን ውስጥ እጅጉን ከመስፋፋቱ በፊት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ተመልክተው ዘለቄታዊ መፍትሄ ካልተበጀለት ችግሩ ችግር ሆኖ መቀጠሉ እና በመላው ሃገሪቱ ተዛምቶ የሁሉ ችግር የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ማህበረሰቡ ይህን ጸያፍ ነገር ዘወትር የሚሰማበት ጆሮ የሚሸከምበት ጫንቃ ሊኖረው አይገባም ፤ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማነት ፤ ሁሉም ሃይማኖት  በአንድ ላይ በመሆን ችግሩን ከመሰረቱ ሊያደርቅ  በሚችል መልኩ ሥራዎችን ወርደው መስራተ መቻል አለባቸው የሚል እምነት አለን፡፡ ዛሬ ያልኮተኮቱትን ፤ ዛሬ ያላስተማሩንት ሰው ነገ ጥሩ ዜጋ ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልምና ፤ የነገ ችግሮቻችን እንዳይብሱ እና ከአቅማችን በላይ ሆነው እንደ ምዕራብያውያኑ ከሰው ልጆች መብት እኩል አይተን ሰዶማውያንን በማበረታታት እንደ መብት እንዳንፈቅድ ዛሬ ላይ ስራዎችን መስራት ይገባናል፡፡  አንድ የ‹‹አንድ አድገን›› ጸሀፊ በቅርብ ከሚያውቃቸው የሕጻናትን ጉዳይ የሚመለከቱ የፖሊስ አባላትና ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁት አቃቢ ሕጎች ባገኝው መረጃ መሰረት ፤ ችግሩ ቀድሞ በጎዳና ልጆች ላይ አልፎ አልፎ የሚታይ ሲሆን አሁን ግን በጎዳና ልጆች ላይ በቁጥር ጨምሮ ሲገኝ በተለያዩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና መሰል ተቋማት ጋር በተደጋጋሚ ከመታየቱም በላይ ቁጥሩም ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን ባገኝነው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡ 
አሁን የቀረበው ጥናት ታትሞ ያገኝነው Ethiopia Public Health Association በየሶስት ወር ከሚያሳትመው Public Health Digest Volume 6 No 1 (July 2013 Addis Ababa) ህትመት ላይ ሲሆን ይህ ጥናት ቀድሞ Ethiopia Journal of Health Development Vol. 23 መውጣቱን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
መግቢያ
በተለያዩ የጥናት ውጤቶች እንደተገለጸው የሕጻናት የወሲብ ጥቃት ‹‹በየትኛውም ሁኔታ ሊከሰት የሚችል ድርጊት›› በማሕበራዊ ፤ በኢኮኖሚዊ እና በጂኦግራፊያዊ ሁኔታዎች ሳይወሰን በየትኛውም ስፍራና ሁኔታ ሊከሰት የሚችል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ጥቂት ጥናቶች ደግሞ ወንዶች ከወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት በሚፈጽሙበት ሁኔታ እንዳለ ያሳያሉ፡፡ በአዲስ አበባ  ሕጻናት ላይም የወሲብ ጥቃቱ እንዳለ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በወንዶች ላይ የሚደርሰው የወሲብ ጥቃት አስመልክቶ በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተደረገ ጥናት በአጠቃላይ ተጠቂዎች 22 በመቶ (47 ያህሉ) ለፖሊስ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ 44 ያህሉ በጎረቤቶቻቸው ፤ 3 በመቶ ያህሉ ደግሞ በማይታወቁ ሰዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ከተጠቂዎች መካከል 26 በመቶ ያህሉ የጎዳና ሕጻናት ናቸው፡፡
ይኽው ጥናት እንዳመለከተው የጥቃቱ ፈጻሚዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ 84 በመቶ ያህሉ ደግሞ ትዳር የሌላቸው ናቸው ይላል፡፡በጥናቱ ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች በጣም ጥቂት በመሆናቸው አጥኚዎች ስለ ችግሩ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን አጥኚው ይገልጻል፡፡ በመሆኑም በወንድ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የወሲብ ጥቃት የችግሩን ስፋት መንስኤና ውጤት እንዲሁም በተጠቂዎች ላይ የሚደርሰው የስነልቦና ችግርና የህግ አግልግሎት ላይ ያላቸው እውቀት ውስን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ይህ ጥናት በወንድ በጎዳና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የወሲብ ጥቃት ፤ ማህበራዊ ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ገጽታ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑትንና  ሃሳባቸው ተቀባይነት የሌለውን  የጎዳና ሕጻናትን ይዳስሳል፡፡፡ እድሜያቸው ከ8 - 18 የሆኑ ሕጻናትን በተለያዩ መስፈርቶች በሶስት ቦታ ከፋፍሎ ጥናቱ ተካሂዷል፡፡ በጥናቱ ከ250 በላይ ሕጻናት ተሳትፈዋል ፤ በ24 ወንድ የጎዳና ሕጻናት ላይ ጥልቅ የህይወት ታሪክ መጠይቅ ተካሂዷል፡፡ ሕጻናቶቹም ከተለየዩ እምነቶች ፤ ከተለያዩ የቤተሰብ ሁኔታዎች እንደመጡ ጥናቱ ያረጋግጣል፡፡ ጥናቱ የተካሄደው በአውቶቡስ ተራ ፤ በጎጃም በረንዳ ፤ መሳለሚያ ፤ ሰባተኛ እና አትክልት ተራ አካባቢ በሚገኙ የጎዳና ወንድ ሕጻናት ላይ መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል ፡፡ በጥናቱ ላይ 35 መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተጨማሪ ቁልፍ የመረጃ ምንጮች  ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል፡፡ 
ጥናቱ የችግሩን ስፋት ፤ ሕጻናቱን ለጥቃት የዳረጋቸውን ምክንያት ፤ የሕጻናት  ጥቃት መንስኤ ምክንያቶችን ፤ ችግሩን ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶችንና ሌሎችንም ይቃኛል፡፡ አህዛዊ መረጃው በSPSS ሶፍትዌር በመጠቀም መተንተኑን ይገልጻል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉት 28.6 በመቶ ያህሉ የተለያዩ የወሲብ ጥቃቶች እንደደረሱባቸው ሪፖርት አድርገዋል፡፡ በተቃራኒው አብዛኞቹ 71.4 በመቶ ያህሎ ምንም ዓይነት የጾታ ጥቃት አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ያስረዳሉ፡፡ ቁልፍ የመረጃ ምንጮች በወንዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ጥልቀት በአስፈሪ ሁኔታ በከተማዋ እተስፋፋ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ጥቃቱን ፈጻሚዎች ህጻናቱ በተገኙበት ስፍራ በመምጣት በተለያዩ ስጦታዎችን ከሰጡአቸው በኋላ በመጨረሻ ጥቃቱን እንደሚፈጽሙ ተጠቅሷል፡፡
እንደ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው ከ126ቱ ሕጻናት መካከል 64 በመቶው ያህሉ እንደገለጹት በሚሰበሰቡበት ቦታ እና በሌሎች የመርካቶ አካባዎች የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸውን ሕጻናት ያውቃሉ፡፡ 32 በመቶ ያህሉ ቢያንስ አንድ የወሲብ ጥቃት የደረሰበት ሕጻን  ያውቃሉ፡፡ 22 በመቶ ያህሉ ደግሞ ከ2-5 ያህል ሕጻናትን እንዲሁም ከ8.7 በመቶ ያህሉ ደግሞ አምስትና ከአምስት በላይ ሕጻናትን እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡
በጥናቱ የተካተቱ ቁልፍ የመረጃ ምንጮች እንደሚያሳዩት ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት እና ለጎዳና ሕይወት አዲስ የሆኑት ከነባሮች ጋር ሲወዳደር የበለጠ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፡፡
ለጥቃቱ ኢላማ የሚሆኑበት  ምክንያት ራሳቸውን እንዴት መከላከል እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ነው፡፡ ይሁንና ጥቃት እንደደረሰባቸው ወዲያው ሪፖርት የሚያደርጉት  እነርሱ ራሳቸው ናቸው ፡፡ ጥናቱ ላይ ማርቆስ የተባለ የ16 ዓመት የጎዳና ታዳጊ ወደ ጎዳና እንደወጣ ያጋጠመው ልምድ እንደ ምሳሌ ጥናቱ ሲያስቀምጥ፡፡
          ‹‹ብዙውን ጊዜ አዳደዲስና በእድሜያቸው ለጋ የሆኑ ሕጻናት ለወሲባዊ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው፡፡ የዛሬ 2 ዓመት ገደማ አዲስ አበባ እንደመጣሁ ሁሉ ነገር ለእኔ እንግዳ ነበር ፡፡ በከተማዋ የማውቀው አንድም ሰው አልነበረኝም፡፡ እንደመታደል ሁለት ትግረኛ መናገር የሚችሉ ሕጻናት አገኝሁ ፡፡ እኔ ከመጣሁበት አካባቢ የመጡ ናቸው፡፡ ለሁለት ቀን ከእነርሱ ጋር ተኛሁ፡፡ በሦስተኛው ቀን ግን አንድ ሽማግሌ ወደ ተኛሁበት ስፍራ መጡና ከእኛ ጋር ለመተኛት ጠየቁን፡፡ ፈቀድንላቸው ፡፡ ምንም ነገር ይኖራል ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡ ሸለብ አድርጎኝ ነበር እና ሽማግሌው ጥልቅ እንቅልፍ እስኪጥለኝ ድረስ ይጠብቁ ነበር፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ  ሠውየው ሱሪዬን ማውለቅ ጀመሩ፡፡ እኔም የለሊት ልብሴን ሊጋሩኝ እየሞከሩ እደሆን አሰብኩ፡፡ እና እኔም የተኛሁ መስዬ ጸጥ አልኩ፡፡ ቀስ ብዬ ለጓኛዬ ሰውየው በማድረግ ላይ ያለው ነገር ነገርኳቸው፡፡ ጓደኞቼ ወዲያው ተነስተው ሁኔታውን ተመለከቱ፡፡ ሽማግሌው ጥቃት ሊፈጽምብኝ እንደሆነ አዩ፡፡ ቀደም ብለው ቢነግሩኝ ኑሮ ቀድሞውን ሠውየውን አላስጠጋውም ነበር፡፡ እናም ጓኞቼ ሰውየውን ከአካባቢው አባረሩት፡፡ በኋላም ጓደኞቼ በርካታ አዳዲስ የጎዳና ሕጻናት የጥቃት ሰለባዎች እንደሆኑ አጫወቱኝ፡፡ ከዚያ እለት አንስቶ ስለ ወሲብ ጥቃት ግንዛቤ ስላገኝሁ ራሴን ከዚህ መሰሉ አደጋ መከላከል ጀመርኩ፡፡” ብላል
በርካታ ቁጥር ያላቸው (25 ያህሉ) የጎዳና ሕጻናት የጥቃት ሰለባ የሆኑት ለአንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን 11 ሕጻናት ደግሞ ከአንድ ጊዜ በላይ የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ጥቂት ሕጻናት እንደሚያሰምሩበት ወሲባዊ ጥቃትና የጎዳና ሕይወት የማይለያዩ ናቸው፡፡
ለምሳሌ ለ8 ዓመታት  ያህል በጎዳና ኑሮ ያሳለፈው የ17 ዓመቱ ታዳጊ እንዳብራራው “እኔ እስከማውቀው ድረስ ማንም ሕጻን ከጥቃት አያመልጥም ፡፡ ችግሩ ያጋጥመዋል፡፡ እዚህ ጎጃም በረንዳ ያሉ ሁሉም ጓደኞቼ ቢያንስ አንድ ጊዜ ጥቃት አጋጥሟቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ ጥናቱ 17 በመቶ ያህሉ ብቻ የፖሊስ እርዳታ ፈልገው ሪፖርት እንዳደረጉ ያሳያል፡፡ቀሪዎቹ አላመለከቱም ይህም ከፍተኛ አሃዝ ያለው ችግሩን ያለማመልከት ሁኔታ መገለልን ከመፍራት ፤ ከአጥቂው በኩል የሚደርስ በቀልን ከማሰብና በፖሊስ በኩል ያለውን የሕጻናት የሕግ ከለላ እጥረት ጋር ይያያዛል፡፡ ዮሐንስ የተባለ የ16 ዓመት ተጠቂ ሪፖርት አድርገሃል ወይ? የሚለው ጥያቄ እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ “የለም ፤ አላደረኩም  ፤ለዚህ 3 ዋና ዋና ምክንያቶች አሉኝ ፡፡ አንደኛው ለከተማው አዲስ አንደመሆኔ የት ሪፖርት እንደማደርግ አላውቅም፡፡ ሁለተኛ ጉዳይ በሌሎች ቢታወቅ  በሁሉም ሰው መገለልና አድሎ ይደርስብኛል የሚል ፍርሃት ስላደረብኝ ‹‹ቡሽቲ›› የሚል ቅጽልስም ይጠሩኛል ብዬ ስለሰጋሁ ሲሆን ፤ ሶስተኛ ደግሞ ፖሊሶቹ የወንዶችን የወሲብ ጥቃት ትኩረት ሰጥተው አይከታተሉም  ሲባል ስለሰማሁ ነው” በማለት አብራርቷል፡፡
ጥቃት ፈጻሚዎችን አስመልክቶ ለተሳታፊዎቹ በቀረበው ጥያቄ  በመጀመሪያው ተርታ የሚሰለፈው(47 በመቶ ያህሉ) አቻ ጓደኞቻቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡17 በመቶ ያህሉ ደግሞ የማይታወቁ እንግዶች ናቸው ፤ 11 በመቶ ያህሉ ዘመዶች ፤ 10 በመቶ ያህሉ ደግሞ ተማሪዎችና ሃብታም ነጋዴዎች ከአጥቂዎች ጎራ የተሰለፉ ሲሆን የውጭ ዜጎች ፤ በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እና የቡና ቤት ባለቤቶች እንዲሁም ፖሊሶች ጥቃት ከሚያደርጉባቸው ውስጥ ተጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም 25 በመቶ ያህል የወሲብ ጥቃት ሰለባ የጎዳና ወንድ ሕጻናት በአጥቂነት ተሰልፈዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ህጻናቱ በድርጊቱ ተሳታፊ እየሆኑ እንደመጡ ነው፡፡
የጥልቅ ቃለ መጠይቅ እና ሀተታዊ ጥናት ክፍል የቡድን ውይይት ውጤት እንደሚያሳየው በተለያዩ ምክንያቶች በተመሳሳይ ጾታ በደረሰባቸው ተደጋጋሚ የወሲብ ጥቃት ሳቢያ ድርጊቱን በመለማመዳቸው በጉዳዩ እየተሳቡ ተለማምደውታል፡፡ እና በመጀመሪያ እንደ አጥቂ የሚፈርጃቸው ስለሌ ከህጻናቱ ይቀላቀላሉ፡፡ ነገር ግን አንዴ ከታወቁ በኋላ ከአካባቢው ይባረራሉ፡፡ ያለው አማራጭ አንድም በእነሱ ማህበረሰብ አጋር መፈለግ ወይም አካባቢውን ለቀው በማይታወቅ ስፍራ ሄደው ጥቃት ማድረስ ነው፡፡ እናም ከቦታ ቦታ እንዲሁም ከከተማ ከተማ ይቀያይራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ልምድ የጎዳና ሕጻናትን ስላስተማራቸው በምንም መንገድ አዲስ መጤዎችን እንዳያምኑ ሆነዋል፡፡ ጥቂት የጥናቱ ተሳታፊዎች “ሀብታሞች እና አዛውንቶች በጎዳና ወንድ ሕጻናት ላይ ጥቃት በማድረስ ረገድ ግንባር ቀደም ናቸው” ብለዋል፡፡
ከሃተታዊ የጥናት ክፍል ቡድን ተሳታፊዎች በአንዱ የተነገረው ሃሳብ ይህን ይመስላል፡፡
“አብዛኞቹ ጥቃት ፈጻሚዎች ሀብታሞች ናቸው ፡፡ ብዙ ጊዜ በምሽት በዘናጭ መኪናቸው ወደ ተኛንበት ስፍራ ይመጣሉ፡፡ እንደተለመደው አንድ ሰው ከጎዳና ሕጻናት ጋር ወሲብ መፈጸም  ሲፈልግ የእኛን ፍላጎት ሁሉ ስለሚያውቅ ብር በመስጠት ሊታልለለን ይሞክራል፡፡ አጥቂዎቹ እንደሚርበን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ልብስ ምግብና መጠለያ እንደሌለን የታወቀ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ‹ ረሃብ ከጦርነት ይልቅ ክፉ ነው›  እንላለን፡፡ እንዳንዶቹ  ለእኛ ያዘኑ መስለው እኛን ከጎዳና ኑሮ ለማላቀቅ  ሊረዱን ያሰቡ መስለው ይቀርቡናል፡፡ ለመደለያም ብስኩትና ልብስ ያመጡልናል፡፡ ሌላው እኛን ለማሳመን የተለመደው የማታለያ መንገድ ሥራ እንደሚያስገቡን ወይም ከእነርሱ ጋር እንደሚያሰሩን ቃል መግባት ነው፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ ጋር ለመሄድ ከተስማማን  በኋላ ወደ ሆቴል ይወስዱናል፡፡ ሆቴል እንደደረስን እንድንዝናና በግልጽ ይጋብዙናል፡፡ በዚያች ቅጸበት ድብቅ አላማቸውን እንረዳለን፡፡ አዲስ መጤ ከሆንክ ግን በቀላሉ ትያዛለህ፡፡ ጥቂቶች ግን ወደ ሆቴል ከመሄድህ በፊት በግልጽ ይጠይቁሃል፡፡” ይላል የ16 ዓመቱ ታዳጊ ሕጻን ብሩክ::
ወንድ የጎዳና ሕጻናትን ለወሲብ ተጠቂነት የሚዳርጋቸው ምክንያች
ጥናቱ የወሲብ ጥቃት ችግርን ለማየት የወሲብ ጥቃት ለምን ይከሰታል ? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው ይላል ፡፡ ህጻናቱ ያለ ጠባቂ ጎዳና ላይ ከመሆናቸው ባለፈ እነኚህን ወንድ የጎዳና ሕጻናት ለወሲብ የሚዳርጉ ሌሎች መንስኤዎችን እንዲለዩ የጥናቱ ተሳታፊዎች ተጠይቀው እንደነበር ይገልጻል፡፡ በጥናቱ የተካተቱት ቁልፍ የመረጃ ምንጮቻችንና የተለያዩ ቡድኖች የተወያዩባቸው መንስኤዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

Ø  የልጆቹ ብስለት ማጣት

ይህን መሰሉ ተግባር በኢትዮጵያ ባሕልም ሆነ ሃይማኖት የተወገዘ ህገ ወጥ ተግባር ስለሆነ  በህብረተሰቡ ዘንድ  በከፍተኛ ሁኔታ የሚነወርና በጥቂቶች ብቻ ተቀባይነት ሊያገኝ የቻለ ተግባር ስለሆነ አጥቂዎቹ ትልልቅ ሰዎችን ለዚህ ተግባር መጠየቅ  ስለሚፈሩና  በአካልና በአእምሮ ያልበሰሉ ራሳቸውም ለመከላከል በማይችሉ ሕጻናት ላይ ድርጊቱን ይፈጽማሉ፡፡

Ø  የወሲብ ፊልሞችን የማየት አጋጣሚ

በጥናቱ በሁሉም ከጎዳና ልጆች ጋር ባደረገው የውይይት ጊዜ የወሲብ ፊልሞች እንደ ዋና ምክንያት አውርቧል፡፡ አንድ አብርሃም የተባለ የ14 ዓመት የጎዳና ወጣት እንደገለጸው “ከ2 ዓመት በፊት ወደ አዲስ አበባ እንደመጣሁ ‹ቡሽቲ› የሚል አዲስ ቃል ሰማሁ፡፡ እናም በመጀመሪያ ቃሉን እንደሰማሁ ጓኛዬን ትርሙን ጠየኩት፡፡ ጓደኛዬም ወንዶች ከወንዶች ጋር ወሲብ ሲፈጽሙ የሚሰጥ ስያሜ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ ነገሩ ለእኔ እንግዳ ነበርና በጣም ደነገጥኩ ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ይኽው ጓደኛዬ መርካቶ አካባቢ ካሉ ቪዲዮ ቤቶች ፊልም ጋበዘኝና ‹ቡሽቲዎች› እንዴት ወሲብ እንደሚፈጽሙ አሳየኝ” ብሏል 
የወሲብ ፊልሞች እና መጽሄቶች በተለይም በወሲብ ዙሪያ  የጠለቀ እውቀት ለሌላቸው ለተጠቂ ሕጻናት የተሳሳተ መረጃ ይሰጣሉ፡፡ እንደተለመደው ህጋዊ ተግባር ወይም የሰለጠነ የወሲብ ልምድ አድርገው እንዲወስዱትና ራሳቸውንም ለድርጊቱ እንዲያለማምዱት  ያደርጋል፡፡ በጎዳና ሕጻናት ጥበቃ ላይ  የሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ  ድርጅቶች መካከል ከድር የተባለ ዳይሬክተር በሁለት ወንድማማቾች በአንድ ጊዜ የተደፈረ የ14 ዓመት ታዳጊ የጎዳና ወጣት ገጠመኝ እንዲህ ያስታውሰዋል፡፡
“ከጥቃቱ በኋላ ታዳጊው  በምክር አገልግሎት ጊዜ  በብዥታ ውስጥ ነበር፡፡ ለራሱም ደጋግሞ ጥያቄ ያቀርብ ነበር ፡፡ “እኔ ሴት ነኝ እንዴ?” የሚል፡፡ “ እንዴት ወንድ ልጅ ወንድን ለወሲብ ይፈልጋል?” የሚል ግራ መጋባት  አደረበት፡፡ ይሁንና ከጊዜ በኋላ ምላሹን ከቪዲዮ ቤቶች አገኝው፡፡ ወንድ ከወንድ ጋር ወሲብ ሲፈጽም ተመለከተ፡፡ ከዚህ በኋላ  የታዳጊው ግራ መጋባት ተወገደ፡፡ ድርጊቱ የተለመደና ነውር የሌለበት አድጎ ወሰደው፡፡ እናም እርሱም ከሌሎች እንደተማረው በእድሜ ከእርሱ በታች ባሉ ሕጻናት ላይ ይተገብረው ጀመር፡፡

Ø  የኢኮኖሚ ሁኔታ

በተሳታፊዎች የተጠቀሰው ሌላው ምክንያት በተለይም አዲስ መጤ ሕጻናት በጥቂት ገንዘብና በዝቅተኛ ስጦታዎች መደለል ነው፡፡ የጎዳና ሕጻናት የዕለት ጉርስ ልብስና መጠለያ ለማግኝት ይቸገራሉ፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ የሲጋራና የጫት ሱሰኞች ናቸው እና ለጥቂት ሕጻናት ከወንዶች ጋር ወሲብ መፈጸም  እንደ ገቢ ምንጭ ይቆጠራል፡፡ ጥቂት የጎዳና ወንድ ሕጻናት ቋሚ የወሲብ ደንበኞች እንዳሏቸው ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል ኑሮን ለመግፋት በሌሊት በምሽት ክለቦችና በቡና ቤቶች ሲጋራ ጫት የሚሸጡ ሕጻናትም ለወሲብ ጥቃት ይዳረጋሉ፡፡

Ø  የእጽ ተጠቃሚነትና ጥቃት

የአልኮል ሱስና የሌሎች እፆች ተጠቃሚነት የጎዳና ወንድ ሕጻናት ላይ ጥቃቱን እንዳባባሰው ይናገራሉ፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎቹ ህጻናቱ እስኪሰክሩ ድረስ መጠጥ እንዲጠጡ እና ሕጻናት ዘንድ በስፋት የተለመደው ማሪዋና የተባለ እጽ እንዲወስዱ ካደረጉ በኋላ  ራሳቸውን መቆጣጠር ሲሳናው ጥቃቱን ይፈጽማሉ፡፡

Ø  የመጠለያ እጥረት በጎዳና ህይወት

ጥናቱ እንዳመለከተው የመጠለያ ችግር የጥቃት ተጋላጭነትን  ትልቁን ስፍራ እንደሚይዝ አስቀምጧ፡፡ አንዳንዶች ሌሊት በፍርሃት ሲዞሩ ያድሩና ቀን ይተኛሉ፡፡ የ14 ዓመቱ የጎዳና ህፃን ካሳሁን እንደገለጸው “ማንኛውም የጎዳና ሕጻን ቢያንስ አንድ ጊዜ ጥቃቱ ሳይድስበት ይቀራል ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው፡፡ ወደ ጎዳና በመጣ በመጀመሪያዎቹ  ሳምንታት ለጥቃት ይጋለጣል፡፡ ጎዳናን ያህል ኑሮ ተቀላቅሎ ያለ ችግር  ተጠብቆ በሰላም ይኖራል ማለት ዘበት ነው፡፡” በማለት የችግሩ አስከፊነት ምን እንደሚመስል ከኖረበት ሕይወት በመነሳት ሃሳቡን ሰጥቷል፡፡
በመርካቶ አካባቢ ያሉ ንጽናቸውን ያልጠበቁ ሆቴሎች የተጨናነቁ እና የፈረሱ ቤቶችና ማደሪያዎችም ለችግሩ መስፋፋትና ለአጥቂዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ የራሳቸውን ድርሻ እንዳላቸው ጥናቱ አስቀጧል፡፡

Ø  ድብቅነት የግንዛቤ ማነስና ትኩረት አለመስጠት

በጥናቱ ላይ ወደ ጎዳና የተቀላቀሉ አዳዲስ ሕጻናት በይበልጥ ተጎጂ እንደሆኑ ተገልጿል ፤ ለዚህ ዋና ምክንያት ተጠቂዎች ስለ ጉዳዩ ምንም አይነት መረጃ ስለሌላቸው መሆኑን በግንባር ቀደምት ያስቀምጣል፡፡ ወንድ ከወንድ ጋር የሚያደርገው ወሲብ መገለልን የሚያስከትል በመሆኑ ድብቅ ነው፡፡ ጉዳዩም በሕዝቡ ዘንድ  እንደ ችግር አይታይም ፡፡ ወላጆችም በሴት ልጆቻቸው የሚደርሰውን ችግር  በወንዶች ላይ ሊደርስ እንደሚችል  አያስቡም፡፡ ከወንዶች ጋር ወሲብ እንደሚያደርጉት እና ይህን መሰል ጥቃት ከሚያደርሱ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አያሳስቧቸውም፡፡ ከአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ  የመረጃ ምንጭ እንደተጠቀሰው አንዳንድ ጊዜ ከማኅረሰቡ በኩል የሚመጣ ተቃውሞ አለ፡፡ “ በአጥቂዎች ላይ ለፖሊስ ሪፖርት በምናደርግበት ጊዜ ከፍተኛ ተግዳሮት የሚገጥመን የችግሩ ኢላማ ከሆነው ሕብረተሰብ ዘንድ ነው፡፡ የጥቃት ፈጻሚው ቤተሰቦችና ጎረቤቶች ቢሮ ድረስ መጥተው ይጮሁብናል፡፡ ይህን አሳፋሪ ድርጊት በማሳወቃችን ይኮንኑናል፡፡ ክሱን እንድናቋርጥ ያስገድዱናል” በማለት ገልጿል፡፡
ሌላው የመረጃ ምንጭ የጥናቱ ተሳታፊ እንደገለጸው ስለ ጉዳዩ ግልጽ ውይይት ያለመኖሩ ለችግሩ መባባስ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ሕጻናት አንዳንድ ጊዜ በቤተሰቦቻቸው አባላትም ተጠቅተው እንደሚገኙ ገልጿል፡፡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በችግሩ ላይ ያላቸውን ትኩረት አስመልቶ ለቀረበው ጥያቄ የሁሉም ምላሽ ተመሳሳይ ነው፡፡ በበቂ ሁኔታ እየተሰራበት አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡
 
አንድ የፖሊስ መኮንን የሚከተለውን ተናገሯል፡፡ “መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ችግሩን በመዋጋት ሂደት  እየተሳተፉ ነው ለማለት አልችልም፡፡ አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ጥቃት የደረሰባቸውን  ሕጻናት ፊታቸውን ከልሎ በብልጭታ አሳይቶን ነበር፡፡ ይህ ግን ህብረተሰቡ ችግሩን ለማስቆም እንዲነሳሳ አላደረውም፡፡ በህብረተሰቡ ዘንድ የችግሩ ስፋት አይታወቅም፡፡ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ በርካታ ሕጻናት የወሲብ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፡፡ ችግሩ በአስከፊ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ መገናኛ ብዙሀን ድርጊቱን ለማስቆም የራሳቸው ድርሻ እየተወጡ አይደለም፡፡ በሴቶች ላይ ስሚደርሰው ጥቃት ብቻ ነው ሲያወሩ የሚደመጡት፡፡ በመገናኛ ብዙሀንም ሆነ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ባላቸው ተቋማት ችላ የተባለው የወንዶች ጥቃት ግን  በሚያስፈራ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡” በማለት ሃሳቡን ሰጥቷል፡፡
ከፖሊስ አካል የጥናቱ ተሳታፊ የራሱን ሃሳብ እንድህ በማለት አስተጋብቷል “ ማንም ሰው ይህን መሰል አሰቃቂ ወንጀል ሲሰማ ጥሩ አይሰማው ማለት እችላለሁ፡፡ ግን ከህግ አውጪዎችም ሆነ ከሎሎች  ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ባለው ስራ ላይ ከተሰማሩ አካላት ድርጊቱን ለማስቆም የሚደረግ ምንም አይነት ተጨባጭ እንቅስቃሴ የለም፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ለስብሰባ በምንጠራቸው ጊዜ እንኳን አይገኙም፡፡ ይልቁንም ተወካዮቻቸው ይልካሉ ፤ ለውይይት በምንጋብዝባቸው ጊዜ በጉዳዩ ላይ መነጋገርን የሚጠሉ ሃላፊዎችና ህግ አውጪዎች አጋጥመውናል፡፡ከሚመለከታቸው አካላትም ሆነ ከህብረተሰቡ በኩል ያለው ትኩረት አናሳ መሆንና ለጉዳዩ ቀና አመለካከት አለመኖር የሚመነጨው ስለ ችግሩ ካላቸው ውስን ግንዛቤ የተነሳ ነው፡፡ በዚሀ መሰል ዝምታ ውስጥ ግን ሕጻናት በተለይም የጎዳና ልጆች በከፍተኛ ጥቃት ውስጥ ያልፋሉ ፡፡” ብሏል፡፡

Ø  ውስን የህግ ከለላ

ጥናቱ እንደሚያረጋግጠው የጎዳና ሕጻናት የወሲብ ጥቃትን አስመልክቶ በህጉ ላይ ጫና ማሳደር የሚገባቸው አካላት ቸል ብለው ይታያሉ፡፡ በሁሉም የውይይት ጊዜ ተሳታፊዎች በአጠቃላይ  በህጉ ላይ ባለው ውሱን ጥበቃ እንደማይደሰቱም ገልጸዋል፡፡ እንዳውም አስመላሽ የተባለ የ17 ዓመት የጎዳና ታዳጊ መከፋቱን በእንዲህ ገልፆታል፡፡ “በእኔ አመለካከት የህ ከለላው ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡ ፖሊስ በሙስና ውስጥ እስካለ ድረስ መፍትሄ አይገኝም፡፡ ጥቃት ፈጻሚዎችም ብዙውን ጊዜ በማግስቱ ይለቀቃሉ፡፡ በሚገርም ሁኔታ ፖሊሶቹ የጎዳና ሕጻናትን እንደ ምስክር አይቀበሉንም፡፡ ምክንያቱም ውሸታሞች አድርገው ይቆሩናል፡፡ የወሲብ ጥቃት በደረሰብን ጊዜ ለፖሊስ ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን የፖሊስ አባላቱ አያምኑንም፡፡ የምንናገረው ሁሉ አይቀበሉንም፡፡ ለገንዘብና ለጥቅም ስንል የፈጸምነው አድገው ይወስዱታል፡፡” በማለት ገልጿል፡፡
በጥናቱ የተሳተፉ የፖሊስ አባላት ቀደም ሲል የቀረበው ሃሳብ ተጨባጭነት እንዳለው ሲስማሙ ጥቂቶች ገድሞ ሀሳቡን ተቃውመውታል፡፡
በጥናቱ ላይ ሌላው የጥናቱ ተሳታፊ “እርግጥ ነው ህጻናቱ ችግራቸውን በግልጽ ለመናገር የሚፈሩበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ እንደተባለውም የመረጃው ችግር ህጻናቱ ጉዳታቸውን በፖሊስ ፊት ለመናገር መፍራት ነው፡፡ ሆኖም ግን ህጻናቱ ከዚህ ህይወት ለመውጣትና ድርጊቱን ለማቆም አይፈልጉም፡፡ ገቢ እስካገኙበት ድረስ ከወንዶች ጋር የሚደረገውን  የወሲብ ግንኙነት  የማድረግ ልምዱን ማቋረጥ አይፈልጉም፡፡ የዕለት ተዕለት ችግራቸውን የሚፈቱበት የገቢ ምንጭ የሚያገኙት ከዚሁ ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ በግብረ ሰዶም ድርጊት ተስበዋል፡፡ በእኔ እምነት ከዚህ መሰል አስጸያፊ ድርጊት እንዲወጡ የህክምና ባለሙያ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል፡፡” የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
በጥቱ ላይ ቁልፍ የመረጃ ምንጮች እንደሚያሳዩት  ፖሊሶችና ሌሎች ባለሙያዎች በጥቃቱ ተሳታፊ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የምርመራው ሂደት ውጤታማ እንዳይሆን የከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ተጽህኖም አለበት በማለት ያስቀምጣል፡፡ አንድ የፖሊስ መኮንን ባልደረባ በቃል እንደተናገረው “ በጉዳዩ ጥቂት ደረጃ ላይ እንደደረስክ ርቀህ እንዳትሄድ በአንዳንድ ሃላፊዎች ትከለከላለህ፡፡ በተወሰነ ደረጃ በኋላም ክትትል እንድታቆም ትታዘዛለህ፡፡” ሲል ገልጿል፡፡ 
የዚህ ጥናት ባለቤት(አጥኚ) ጥቃቱ በምስክሮች ሊደገፍ የሚችል ድርጊት ካለመሆኑ አንጻር አጥቂዎችን ለመወንጀል አስቸጋሪ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህም ህግ አውጪዎች በጉዳዩ ላይ  በሚመክበት ጊዜ በርካታ ተግዳሮትና ፍርሃትን ይፈጥራል ብሎ ያምናል፡፡ 
ምንጭ ፡- Ethiopian Journal of Health Development Vol.23
በዚህ ዙሪያ ወደ መሬት በመውረድ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችል ዘንድ እርስዎ ምን ይላሉ…?

No comments:

Post a Comment