Thursday, February 21, 2013

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ማን ናቸው?




  •  ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከአሜሪካ ቦስተን ዩኒቨርሲቲ በቴዎሎጂ የክብር ዶክትሬት ድግሪ አግኝተዋል፡፡
  • 24 ሺህ ሰው በማሳመንና በማጥመቅ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች አድርገዋል::
  •  መንፈሳዊ ኮሌጅ በማቋቋም እንደ አንድ መምህር ከክፍል እየገቡ በማስተማር ምሳሌነታቸውን አሳይተዋል፡፡
  •  የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ድርጅት መስርተዋል፡፡
  •  ቤተ ክርስቲያን ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር ጎን ለጎን መራመድ ትችል ዘንድ ሰባኪያን ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚሰለጥኑባቸው የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማትን በየሀገረ ስብከቱ እንዲቋቋሙ አድረገዋል፡
  •  በአሜሪካ ከሚገኝው  ብሔራዊ የሰብአዊ ጥናቶች መርጃ ድርጅት  የገንዘብና የመሳሪያ እርዳታ በመጠየቅ የብራና መጻህፍት  የማይክሮ ፊልም ድርጅት አቋቁመዋል(አሁን በመንግስት የተወረሰ)፡፡
  • የዘመን ጥርስ የበላቸው በርካታ  በሺህ የሚቆጠሩ የብራና መጻህፍት ጨርሰው ሳይጠፉ ከየገዳማቱና ከየአድባራቱ በማሰባሰብ በማይክሮ ፊልም እንዲቀረጹ አድርገዋል፡፡
  • ቤተክርስቲያን በራሷ ገቢ የምትተዳደርበት የሰበካ ጉባኤ ሃሳብ በማቅረብ አደራጅተው  በቃለ አዋዲ እንዲመራ አድርገዋል፡፡
  • የሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እንዲቋቋም አድርገዋል ፡፡
  • ቤተክርስቲያን ያፈራቻቸው አለም አቀፋዊ ብቁ ዲፕሎማት መሆናቸውን ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡

ክፍል አንድ  (በርካታ ታሪካዊ ፎቶዎች ተካተውበታል)
(አንድ አድርገን የካቲት 14 2005 ዓ.ም)፡- ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሚያዚያ 16 ቀን 1902 ዓ.ም ጽኑእ ክርስቲያናዊ እምነት ከነበራቸው ከአቶ ወልደ ማርያም ውቤና ከእመት  ዘርትሁን አደላሁ በምስራቅ ጎጃም በማቻከል ወረዳ በደብረ ገነት ኤልያስ ተወለዱ፡፡ መልዕክቱ የሚል ስም በወላጆቻቸው ተሰጥቷቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስያን ስርዓተ ትምህርት መሰረት በተወለዱበት ደብር ንባብ ከመሪጌታ ረዳኽኝ  ፤ ንባብ ከግራ ጌታ ሳህሉ ፤ ቅኔና የመጻህፍት ትርጓሜ ከታወቁት መምህር ገ/ሥላሴ ተምረው በተለይ በቅኔ ለመምህርነት ከሚያበቃ ደረጃ በመድረስ ተመርቀዋል ፡፡ አስከትለውም ከእኝሁ መምህር የውዳሴ ማርያም የቅዳሴ ማርያምና የወንጌል ትምህርት ቀጽለዋል፡፡


በ1920 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከመምህር ሐዲስ ተክሌ በኋላ ንቡረ ዕድ ተክለሃይማት በመጨረሻም ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ይባሉ ከነበሩት ታላቅ ሊቅ የመጻህፍት ሐዲሳትን ፤ የፍትሐ ነገስትን ትርጓሜና የአቡሻኽርን ትምህርት ጠንቅቀው በመማር ለመምህርነት በቁ ፡፡ ጉባኤ ዘርግተውም በማስተማር አያሌ ምሁራንን አፍርተዋል፡፡ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ሲያስተምሩ ከቆዩ በኋላ 27 ዓመት ሲሞላቸው መንፈሳዊውን ሕይወት በመምረጥ በ1930 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም መዐረገ ምንኩስና ተቀበሉ፡፡

በዘመናዊ ትምህርት ረገድም ቅዱስነታቸው በቀሰሙት እውቀትና በአርቆ ተመልካችነታቸው ዓለማችን የደረሰችበትን የሥልጣኔ ደረጃ የማወቅና የመገንዘብ ችሎታቸው ከፍተኛ መሆኑን የተረዱት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በ1934 ዓ.ም በቅዱስነታቸው አቅራቢነት 20 ሊቃውንት ተመርጠው በዚያን ጊዜ ገነተ ልዑል ይባል በነበረው ቤተ መንግሥት (የዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ቅጽረ ግቢ ዘመናዊ ትምህርት ፤ በተለይም እንግሊዘኛ ቋንቋ እንዲማሩ ሲያደርጉ ትምህርቱን ተግተው በመከታተል ከግብ ካደረሱት መካከል የመጀመሪያው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ነበሩ፡፡ ት/ቤቱ ዛሬ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ወደሚገኝበት ስፍራ እስከተዘዋወረ ድረስ ዘመናዊውን ትምህርት ሲማሩ ቆይተው በ1935 ዓ.ም መንፈሳዊውንና ስጋዊውን ትምህርት አጣምሮ በሚሰጥ ስልት ተቀይሶ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በሚል ሥያሜ በትምህርት ሚኒስቴር ስር በቅዱስነታቸው የበላይ አስተዳዳሪነት እንዲመራ ተደረገ፡፡

  1.   ከመምህርነት እስከ ፓትርያርክነት

ከመንፈሳዊ ትምህርት በተለይም በፍትሐ ነገስት የቀሰሙት ጥልቅ ዕውቀት ከዘመናዊ ጋር ተዳምሮ ኃፊነትን መወጣት የሚያስችላቸው መሆኑ ስለታመነበት በ1935 ዓ.ም የመካነ ሥላሴን ገዳም እንዲያስተዳድሩ በመምህርነት ማዕረግ ተሾሙ በዚህ ደረጃ 3 ዓመት ካገለገሉ በኋላ በ1938 ዓ.ም የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ስልጣናት ተብለው በመሾም በግርማዊ ጃንሆይ ከራስ ወርቅና ከላንቃ ካባ ጋር ሙሉ ሽልማት ተሸለሙ፡፡



ነብዩ ዳዊት “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” እንዳለው ከብዙ ዓመት ጥረት በኋላ የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ ለኢትዮጵያውያን አበው የጵጵስና ማዕረግ እንዲሰጥ በኢትዮጵያና በእስክንድርያ ቤተክርስቲያን መካከል ስምምነት ሲደረግ በ1938 ዓ.ም ሚያዚያ 19 ቀን በአዲስ አበባ በተደረገው ምርጫ ሊቀ ስልጣናት መልዕክቱ ከ5 ኢትዮጵያውያን እጩዎች መካካል አንዱ ሆነው በከፍተኛ ድምጽ ተመረጡ፡፡ ይሁን እንጂ በእስክንድርያ ቤተክርስቲያን በኩል በተፈጠረ ምክንያት ሳይሾሙ 2 ዓመት ቆይተው ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓ.ም በእስክንድርያው ፓትርያርክ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ተቀብተው የሐረርጌ  ጳጳስ በመሆን ተሾሙ፡፡

በ1942 ዓ.ም  ብፁዕነታቸው ባላቸው ዘመናዊና የጥንታዊ ትምህርት ችሎታ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው የብጹዕ አቡነ ባስልዮስ እንደራሴ ሆኑ፡፡ እንደገና ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ጋር በተደረገው ተጨማሪ ስምምነት ብጹዕ አቡነ ባስልዮስ በ1943 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ ብጹእ አቡነ ቴዎፍሎስ በኢትዮጵያ የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ ወኪል እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በ1952 ዓ.ም በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከፍተኛውን የፓትርያርክነት መብት ካገኝች በኋላም ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በያዙት ሀገረ ስብከት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ተሰጣቸው፡፡

ባላቸው ከፍተኛ እውቀት ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ሰፊ አገልግሎት የሰጡት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቀዳሚያቸው ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባልዮስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ተጠባባቂ ፓትርያርክ በመሆን ለተወሰኑ ወራት ከቆዮ በኋላ  መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ አንደኛ ሆነው በመመረጣቸው ከ1 ወር በኋላ ግንቦት 1 ቀን 1963 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር  በኢትዮጵያውያን ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ካህናትና ምዕመናን  ጸሎት 2ተኛው  የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ፡፡ በደርግ መንግሥት ያለ ሕግና ያለ ፍትህ ከስልጣናቸው ወርደው እንዲታሰሩ እስከተደረገበት እስከ የካቲት 9 1968 ዓ.ም ድረስ በፓትርያርክነት ስልጣን ላየ ቆይተዋል፡፡
 
2.  ቅዱስነታቸው ከፈጸሟቸው ዋና ዋና ተግባራት

በትምህርት
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ለመንፈሳዊም ሆነ ለስጋዊ እድገት ትምህርት አቻ የሌለው መሣሪያ መሆኑን የተረዱ ስለነበሩ የሀገሪቱ የትምህርት ቦርድ ሲቋቋም ቤተክርስቲያንን እንዲወክሉ  በንጉሡ ተመርጠው ቦርድ አባል በመሆን ለትምህርት መስፋፋት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

በደርግ ዘመነ መንግሥት በተጽህኖ ተወስዶ የነበረው ዛሬ በኢትዮጵያ  መንግሥት ፍቃድ ለተቋቋመበት አላማ እንዲውል ለቤተክርስቲያን የተመለሰውን መንፈሳዊ ኮሌጅ ገና 1ኛ ደረጃ በነበረበት ጊዜ ጀምሮ በበላይነት በመምራትና በማስተዳደር ጥንታዊና ዘመናዊ ትምህርት እንዲሰጥበት አድርገዋል፡፡


በስተግራ (ለዩኒቨርሲቱ ተማሪዎች መንፈሳዊ ትምህርት ሲሰጡ)
በስተቀኝ (ለመንፈሳዊ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት ሲሰጡ)



ከመንግሥት በሚያገኙት ድጋፍ እየታገዙ በሀገረ ስብከታቸው ዋና ከተማ በሐረርና በቁልቢ ገዳም ሁለት ትምህርት ቤቶች አቋቁመዋል ፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ከአካባቢው ህብረተሰብና ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየተመለመሉ በስጋዊና በመንፈሳዊ ትምህርት እንዲሰለጥኑ ያደረጉ ሲሆን ፤ በተለይ በሀረር ከተማ የሚገኝውን  መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያቋቋሙት ቀደም አድርገው ስለነበር በርካታ ወጣቶችን አሰልጥኖ ቤተክርስቲያንንና ሀገሪቱን በልዩ ልዩ መስክ እንዲያገለግሉ ለማድረግ ችለዋል፡፡

መንፈሳዊ ኮሌጅ ከመቋቋሙ በፊትም ሆነ በኋላ አያሌ ደቀ መዛሙርትን ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ ሀገር እየላኩ (ለምሳሌ ግብጽ ፤ ግሪክ ፤ ሩሲያ አሜሪካ) በማስተማር ዛሬ ቤተክርስቲያናችንንና ሀገራችንን በከፍተኛ ደረጃ የሚያገለግሉ አንቱ የተባሉ ምሁራንን አፍርተዋል፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በሐዲስ ኪዳንና በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ጉባኤ ዘርግተው ከማስተማራቸውም ሌላ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንደተቋቋመ የጊዜ ሰሌዳ ይዘው በዘመናዊ መልክ እንደ አንድ መምህር ከክፍል እየገቡ በማስተማር ምሳሌነታቸውን አሳይተዋል፡፡ እንደዚሁም በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በየጊዜው እየተገኙ ቃለ ምዕዳን ያሰሙ ነበር፡፡ 

     በስብከተ ወንጌል ተልዕኮ

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሳትና የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንደራሴ በመሆናቸው የስራ ብዛት ቢኖርባቸውም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመንቀሳቀስ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን ከመፈጸም አልተቆጠቡም፡፡ በዚህም እንቅስቃሴያቸው  በ1949 ዓ.ም በባሌ ክፍለ ሀገር በገደብ አውራጃ ፤ በዶዶላ ፤ በሲሮፍታ ፤ በሄቤኖ ፤ በኮኮስና በጋጫ እየተዘዋወሩ በሰጡት ወንጌል ስብከት 24 ሺህ የአዋማና ልዩ ልዩ እምነት ተከታዮችን በማሳመንና በማጥመቅ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች አድርገዋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከሀገር ውጪ ሐዋርያዊው ተልእኮዋን እንድትፈጽም በማብቃት በ1951 ዓ.ም በሰሜንና በደቡብ  አሜሪካ እየተዘዋወሩ ምዕመናንን በማስተማር አብያተክርስቲያናትን በመመስረት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አማንያንን የቤተክርስቲያኗ ተከታዮች ያደረጉ ሲሆን  እነዚህንም በየጊዜው በመጎብኝት በእምነታቸው እንዲጸኑ አድርገዋል፡፡

በሐረርጌ ሐገረ ስብከት ጳጳስ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ በትምህርታቸውና በስብከታቸው ወደ ክርስትና እምነት የተመለሱት ምዕመናን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ በመሄዱ እግዚአብሔርን የሚያመልኩባቸው አዳዲስ አብያተክርስቲያናት በመንግስት ርዳታና በምዕመናን አስተዋጽኦ እንዲሰሩ አድርገዋል፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1958 ዓ.ም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ድርጅት በመንበረ ፓትርያርኩ ሥር ከመሰረቱ በኋላ በየአጥቢያ ቤተክርስቲያኑና በየደብሩ ቅርንጫፍ የስብከተ ወንጌል ድርጅት በማቋቋም በየጊዜውም የሥራ እንቅስቃሴውን በዚያ በስብከተ ወንጌል  ድርጅት አማካይነት ምእመናን በቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ አስችለዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ በተለይም በከተሞች ውስጥ ሊገጥማት የሚችለውን ዘመናዊ አመለካከት አስቀድሞ በመገንዘብና ለወጣቶች እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዋና ጽ/ቤቱ በመንበረ ፓትርያርኩ ስር የሆነ የወጣቶች መምሪያ አቋቁመው በዚህ አማካይነት ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት ወጣቶቹ በሃይማኖትና በመልካም ስነ ምግባር የሚታነጹበት  ሁኔታ አመቻችተዋል፡፡ በእነዚህ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አማካይነት ዛሬ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች የሃይማኖት ትምህርት እየተማሩና ያሬዳዊ ቅኝት እያጠኑ ሰባኪያን ወንጌልና ዘማርያን እስከ መሆን በቅተዋል፡፡

ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር ጎን ለጎን መራመድ ትችል ዘንድ ሰባኪያን ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚሰለጥኑባቸው የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማትን በየሀገረ ስብከቱ እንዲቋቋሙ መሰረት ጥለዋል፡፡

  •  በውጭ ግንኙነት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የነበራትን ግንኙነት በማሳደግ በማጠናከር እንዲሁም አዳዲስ ግንኙነቶችን በመመስረት ረገድ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የፈጸሙት ተግባር አቻ የለውም፡፡

·      ገና በመምህርነትና በሊቀ ሥልጣናት ደረጃ በነበሩበት ጊዜ ቤተክርስቲያናችን ከኢትዮጵያ አበው መካከል ጳጳሳት መሾም እንድትችል በቤተመንግስትና በቤተክህነት የተጀመረው ጥረት ግብ እንዲመታ ከኢትዮጵየ ወደ እስክንድርያ በየጊዜው በተደረገው ጉዞ ቅዱስነታቸው ልዑካንን በመምራት ተገቢውን ድርድር በማድረግ ለቤተክርስቲያናችን የላቀ ድርሻ አበርክተዋል፡፡

·        የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአለም አብያተክርስቲያናት ጉባኤ መስራች አባል ናት፡፡ መስራች አባል እንድትሆን  ያደረጓት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1940 ዓ.ም በአምስተርዳም ሆላንድ በተካሄደው መስራች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን መልዕከኞች መርተው ተሳታፊ በመሆን ነበር፡፡ ከዚያን በኋላ የአለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በተከታታይ በተካሄደባቸው ሀገሮች ማለትም በ1949 በአሜሪካ ኤቫስን ከተማ ፤ በ1954 ዓ.ም በሕንድ ኒውደልሂ ፤ በ1960 በስዊዲን አብሳላ  በልኡካን መሪነት በመገኝት ብቁ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ የዚሁ ኮሜቴ ማዕከላዊ አባል ሆነው እንዲሰሩ የተመረጡትም በዚህ ብቃት ባለው ተሳትፏቸው ምክንያት ነበር፡፡

·        እንዲሁም የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ሚና  በመገንዘብና የቅዱስነታቸውን ታላቅ መንፈሳዊ መሪነት በመቀበል ሁለት ጊዜ በተከታታይ ከ3ቱ ፕሬዝዳንቶች አንዱ አድርጎ ስለመረጣቸው ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡ ለምሳሌ በ1961 ዓ.ም በአቢጃን የተካሄደው ጉባኤ በፕቴዝዳንትነት የመሩት ቅዱስነታቸው ነበሩ፡፡

·        ከዚያም ቀደም ብሎ በ1956 ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ አዳራሽ የተካሄደው የኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተክርስትያናት መሪዎች ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ከማድረግ ጋር  የኢትዮጵያ መልዕክተኞችን በመምራት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

·        በ1963 ዓ.ም ቅዱስነታቸው የዓለም አብያተክርስቲያናት ማኅበር ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ እንዲደረግ በመጋበዝ ለውጤታማነቱ ያልተቆጠበ ጥረት በማድረጋቸውም በላይ የጉባኤ ተካፋዮች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት በይበልጥ እንዲገነዘቡ አድርገዋል፡፡
·        ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ልዩ አህጉራት አብያክርስቲያናትን በመጎብኝት ከታላላቅ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመነጋገርና የውጭ ግንኙነትን በማስፋፋት ቤተክርስቲያኗ በሌሎች ዘንድ በአግባቡ እንድትታወቅ አድርገዋል፡፡
  •  በቅርስ አጠባበቅ
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በረዥም ታሪኳ ያፈራቻቸው የጽሁፍ የስዕል ፤የቅርጻ ቅርጽ የኪነ ጥበብ ታሪኮችን ተቃራኒ እምነት ያላቸው ኃይሎች አጋጣሚ ባገኙ ቁጥር እየተነሱ  ቢያወድሙባትም ፤ ከውድመት የተረፉና በየጊዜው የተከማቹ  በርካታ ቅርሶች አሏት፡፡ ቅዱስነታቸው ለእነዚህ ቅርሶች  ተገቢውን ጥበቃና እንቅስቃሴ  የሚያደርግ የቅርሳ ቅርስ  መምሪያ በመንበረ ፓትርያርክ ሥር እንዲቋቋም ከማድረጋቸው በላይ ቅርሶቹ በዘመናዊ ዘዴ የሚጠበቁበትን ስልት  ከመፈለግ አልተቆጠቡም፡፡ በዚህም መሰረት  ተጠባባቂ ፓትርያርክ ሳሉ በ1962 ዓ.ም በአሜሪካ ከሚገኝው  ብሔራዊ የሰብአዊ ጥናቶች መርጃ ድርጅት  የገንዘብና የመሳሪያ እርዳታ በመጠየቅ የብራና መጻህፍት  የማይክሮ ፊልም ድርጅት አቋቋሙ፡፡ በዚህ ስራ ልምድና እውቀት ካለው በአሜሪካ ሚኒሶታ  በቅዱስ ዮሀንስ ኒቨርሲቲ ከሚገኝ የማይክሮ ፊልም ድርጅት  ጋርም በመነጋገር የቴክኒክ ባለሙያ በማስመጣት የዘመን ጥርስ የበላቸው የብራና መጻህፍት ጨርሰው ሳይጠፉ ከየገዳማቱና ከየአድባራቱ በማሰባሰብ በማይክሮ ፊልም እንዲቀረጹ አድርገዋል፡፡ ይህን ስራ እንዴት እንደጀመሩት አስመልክተው  በሚኒሶታ ቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ማይክሮ ፊልም ድርጅት ኃላፊ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፡-

“ተጠባባቂ ፓትርያርክ በነበሩበት በ1962 ዓ.ም ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በውጭ ዓለም ብዙም ያልታወቁ በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት የሚገኙ መጻሕፍትና የታሪክ ቅርሱች የኒነ ጥበብ ውጤቶች በማክሮ ፊልም እንዲቀረጹ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ይህም ሃሳብ በተግባር ይተረጎም ዘንድ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን የሚቀርጽ የማይክሮ ፊልም ድርጅት እንዲመሰረት በጋለ ስሜት አበረታቱ” በማለት ተናግረዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በዚህ አይነት ያቋቋሙት የማይክሮ ፊልም ድርጅት በቤተክህነት ስር ሆኖ ሲሰራ  ከቆየ በኋላ ወደ ባህል ሚኒስቴር እንዲዛወር በመደረጉ አሁን የባህል ሚኒስቴር ይዞታና ሃብት ሆኗል፡፡ ነገር ግን አሁን ወደ መጀመሪያ ባለቤቱ የሚመለስበትን መንገድ መፈለግ እንደሚኖር እናምናለን፡፡ ቤተክህነትም ይህን ጉዳይ ለመንግስት ጥያቄ በማቅረብ ወደ ቀድሞ ቦታው ይመለስ ዘንድ መጣር መቻል አለበት፡፡
  •  በልማት
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ካከናወኗቸው ታላላቅ ተግባራት አንዱና ዋናው የልማት ኮሚሽን ማቋቋማቸው ነው፡፡ ጥቂት አሳና ሕብስት በረድኤቱ አበርክቶ የተራቡ ብዙ ሺህ ምዕመናንን የመገበው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ የተከተሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን በተቻላት አቅም በልማት መስክም ከመንግስት ጎን ተሰልፋ ረሃብን ፤ ድርቅን ፤  ድንቁርናንና በሽታን የምትዋጋበት መንገድ አስቀድመው ያልሙና ያስቡ ነበር፡፡

ይህ ሃሳብ በኅሊናቸው ተቀርጾ ሳለ ቅዱስነታቸው በሐምሌ ወር 1960 ዓ.ም የዓለም አብያተክርስቲያናት ጠቅላላ ጉባኤ በስዊድን  ኡብሳላ ቤተ ክርስቲያን በልማት ተሳታፊ የምትሆንበትን  ዘዴና ስልት ሲቀይስ በጉባኤው ላይ ተካፋይ ስለነበሩ ከዚያ ከተመለሱ በኋላ በተከታታይ ዓመታት ባደረጓቸው ጥረቶች  ሁኔታዎች ተመቻችተው በጥር ወር 1963 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በልማት ተካፋይነት” በሚል ርዕስ የምክክር ጉባኤ ተደረገ፡፡ የዚህም ጉባኤ ውጤት የኢትዮጵያ  ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን በታህሳስ 26 ቀን 1964 ዓ.ም ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ  አስተዳደር ሥር ራሱን ችሎ እንዲቋቋም  አስቻለ፡፡

ይህ ኮሚሽን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በ6 ሀገረ ስብከት በተቋቋሙት  የካህናት ማሰልጠኛዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ካህናትና በተለያዩ ልማት ነክ ትምህርቶች እያሰለጠነ በመላ ሀገሪቱ በማሰማራቱና የካህናት ህይወት ከመለወጡም ሌላ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢ ህዝቦች ድንገተኛ አደጋ ስለደረሰባቸው ወገኖች በአጠቃላይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን አቅሙ በፈቀደ መሰረት  የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ በማድረግ  የቤተክርስቲያንን መሰረታዊ ተልእኮ  በአጥጋቢ ሁኔታ እያሟላ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ይህ ድርጅት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ለቤተክርስቲያን ታላቅ ባለውለታ መሆናቸውን አጉልቶ ያሳያል፡፡

  •  የሰበካ ጉባኤ አደረጃጀት
 ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቤተክርስቲያን የመንግስት ጥገኛ ሆና የምታገኝው መተዳደሪያ ዘለቄታ የሌለው መሆኑን አስቀድመው በመገንዘባቸው ራሷን ችላ በራሷ ገቢ የምትተዳደርበት የሰበካ ጉባኤ አደራጅተው በቃለ አዋዲ እንዲመራ አድርገዋል፡፡ ከካህናትና ከምዕመናን መካከል  የተመረጡ የአስተዳደር ኮሚቴ አባላት የሚመራው ይህ ጉባኤ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ  በሁሉም አጥቢያ አብያተክርስቲያናት ተቋቁሞ ከምዕመናን በሚሰበሰበው ወርሀዊ መዋጮና ልዩ ልዩ ገቢ ለአገልጋይ ካህናትና የአስተዳደር ሠራተኞች ደመወዝ እየከፈለ በማሰማራት ቤተክርስቲያን በሁለት እግሯ እንድትቆም ያስቻለ ስርዓት ነው፡፡

አርቆ አሳቢው ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከልምድ በቀሰሙት ዕውቀት መሰረት ይህን ጉባኤ እንዲቋቋም ባያደርጉ ኖሮ አሁን ካለሁ ተጨማሪ በርካታ ችግሮች በየአጥቢያው ተከስቶ ማየት በቻልን ነበር ፤ ምዕመኑም በቤተክርስቲያን አስተዳርና ልማት የሚያደርገው ተሳትፎ እንዲህ የጎላ ባልሆነ ነበር፡፡
  •  ምግባረ ሰናይ ድርጅት
የተራበ ማብላት የተጠማ ማጠጣት የታረዘን ማልበስ አምላካዊ ትዕዛዝ መሆኑን የምታስተምር ቤተክርስቲያን የበጎ ሥራ ግንባር ቀደም ናት፡፡ በ1966 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር ተከስቶ የነበረው አስከፊ ድርቅ  ብዙ ወጎኖቻችንን  ለረሃብና ለሞት በዳረገበት ጊዜ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  አቅሟ የሚፈቅደውን የገንዘብ እርዳታ ብታደርግም  ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በዚህ ብቻ  መወሰን በቂ አለመሆኑን በመገንዘብ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት ቅጽር ግቢ አንድ የሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እንዲቋቋም በሰጡት መመሪያ በተጠቀሰው ረሃብ ምክንያት  እናትና አባቶቻቸው የሞቱባቸው 50 አዳጊ ሕጻናትን  ከወሎ መጥተው በዚህ ድርጅት እንዲረዱ አድርገዋል፡፡ በዚህ አይነት የጀመሩት ምግባረ ሰናይ ድርጅት  ከጊዜ በኋላ እያደገ መጥቶ ዛሬ የሕጻናት አስተዳደግ ጉባኤ የሚል ስያሜ አግኝቶ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በሚገኝው ርዳታ በርካታ የህጻናት ማሳደጊያዎችን በመመስረት ከ10ሺህ በላይ ሕጻናትን በማሳደግና በመንከባከብ ላይ ይገኛል፡፡

  • በሲመተ ጳጳሳት
ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንሐዋርያዊትና ማኅበራዊ ተልዕኮ እየሰፋ በመምጣቱ በእነዚህ ዓመታት በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሢመተ ጵጵስና ፤ ሊቀ ጳጳስና ፓትርያርክነት በቅተዋል፡፡ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ራሳቸው ከመምህርነት እስከ ፓትርያርክነት የደረሱት  በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ ሲሆን በእሳቸው የፓትርያርክነት ዘመን እየሰፋ የመጣውን የውስጥና ውጭ ሐዋርያዊት ተልእኮ ለማሟላት እንዲቻል በ1964 ዓ.ም እና 1968 ዓ.ም በድምሩ ዘጠኝ አበው ጳጳሳትን ሹመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አራቱ በውጭ አገር ለተመሰረተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲመደቡ ስድስቱ ደግሞ በሀገር ውስጥ ተመድበው እንዲሰሩ ተደርገዋል፡፡ አምስተኛው ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ከሾሟቸው ጳጳሳት ውስጥ ይገኛሉ ፤ አቡነ ቴዎፍሎስ አቡነ ጳውሎስን በጵጵስና ማዕረግ ከሾሙ በኋላ ደርግ ማንም እንዳይሾም የሚለውን ትዕዛዜን አላከበሩም በሚል ወደ እስር ቤት እንዳወረዳቸው እና በዚያው እንዳረፉ ዜና ሕይወታቸው ይናገራል፡፡ 

6ተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የእኝህን የወንጌል አርበኛ ፤ የተዋህዶ ዓይን ፤ የመአዘን ድንጋይ ፤ የጎጆ ምሰሶ ሆኑው ያለፉትን ፓትርያርክ ስራቸውንና ታሪካቸውን አውቀው ራሳቸውን ለተሻለ አገልግሎትና ቀንበር ለመሸከም ያዘጋጁ ዘንድ መልዕክታችን ነው፡፡

ግብዓት ፡- የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ አጭር የህይወት ታሪክ
 
ይቀጥላል……….(አለም ዓቀፍአዊ ስብዕናና ግንኙነት ፤ በሀሰት ስለመከሰሳቸው ፤ ስለተቀበሉት ሰማዕትነት… ከበርካታ ታሪካዊ ፎቶዎች ጋር ይጠብቁን……)
“የአባቶችን ታሪክ ማወቅ ራስን ማወቅ ነው”

2 comments:

  1. ስለ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ጠለቅ ያለ ታሪክ አንብቤ አላውቅም ነበረ። እሳቸው የጀመሯቸው ከላይ የተጠቀሱትን አዳዲስ ፈለጎች እግዚአብሔር ይውደድላቸው አይውደድላቸው የሚያውቀው ፈጣሪ እራሱ ነው። ሆኖም ይቅርታ አድርጉልኝና ከላይ ከተጠቀሱት አሥር የአዳዲስ ፈለግ ነጥቦች ውስጥ ወደ ስምንት የሚሆኑት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙ ፈለጎች ናቸው ብየ ለመቀበል ያዳግተኛል። በኢሳይያስ 39 ቁጥር 2 የተጻፈው መልእክት ከላይ በተዘረዘሩት የቅዱስ ፓትርያርኩ አዳዲስ ፈለጎች የተፈጸመ ይመስለኛል። በኢሳይያስ 39 ቁጥር 6 እና 7 የተጻፈውም ከፈለጎቹ በኋላ ተከትሎ በመጣው ዘመን ተፈጽሟል።

    ReplyDelete
  2. ይህን የመሰለ የታላቁን አባት ታሪክ ስላካፈላችሁን እናመሰግናለን። ቀጣዩን ክፍል በጉጉት እንጠብቃለን። እግዚአብሄር ይስጥልን።

    ReplyDelete