Monday, February 25, 2013

ለስድስተኛ ፓትርያርክነት የሚወዳደሩት ዕጩዎች ሰኞ ይታወቃሉ


(Reporter February 24 2013):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛው ፓትርያርክ ለመሆን የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚካሄደው ምርጫ በዕጩነት የሚቀርቡት ተወዳዳሪዎች ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ይፋ እንደሚሆኑ ታወቀ፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ዕጩ ፓትርያርክ እንዲሆኑ ከካህናትና ምዕመናን በተሰጠው ጥቆማ ላይ ተመሥርቶ ባደረገው ውይይት የለያቸውን ዕጩዎች በይፋ ባይገለጽም፣ ለየካቲት 16ቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

የካቲት 21 ቀን ለሚደረገው ስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዕጩ የሚሆኑ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት የካቲት 18 ቀን እንደሚታወቁ፣ ከምርጫውም በኋላ በዓለ ሲመቱ የካቲት 24 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል፡፡


በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለሦስት ዓመታት የመሩት አቡነ መርቆሬዎስ (1980-1983) ለሁለት ጌቶች በመገዛት ቀኖናዊ ስህተት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ መፈጸማቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ፓትርያርክም አይደሉም ብሏል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በአሜሪካ በስደት የሚገኙት አራተኛው ፓትርያርክና ሌሎች አባቶችን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፣ ከሃያ ዓመታት በፊት በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቀኖናዊ ስህተት የፈጸሙት የዚህን ዓለም ሹመት ከመንፈሳዊው ሹመት ጋር አዳብለው በመያዛቸው መሆኑን አሳይቷል፡፡

አቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ገሪማና አቡነ ኤጲፋንዮስ በተገኙበት መግለጫውን በንባብ ያሰሙት ንቡረእድ ኤልያስ አብርሃ፣ “ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳንን የፈጸሙ አባት፣ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5፡198 ላይ “ፓትርያርክ ራሱን ከክርስቶስ አገልጋይነት ሌላ ለንጉሥ ከሚሠሩ ሥራዎች በማናቸውም ሥፍራ መሾም አይገባውም፤ በዚህ ቢገኝ ከሹመቱ ይሻር፣ ጌታችን ‘አንድ አገልጋይ ለሁለት ጌቶች መገዛት አይቻለውም፣ አለዚያ ግን አንዱን ያሳዝናል፣ ሌላውንም ደስ ያሰኛል’ ብሏልና፤ የሚለውን በቅዱስ ወንጌልና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከለከለውን የዚህን ዓለም ሹመት ከመንፈሳዊው ሹመት ጋር በማዳበል እየሠሩ የጣሱት ቀኖና ሳያንስ የፓትርያርክነቱም ሥልጣን የጨበጡት “የገዢዎችን ኃይል ተጠቅመው፣ ሲኖዶሱን ተጭነውና መንፈስ ቅዱስን ተጋፍተው ነው፤” ብለዋል፡፡

አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ከመሆናቸው በፊት በጎንደር ሊቀ ጳጳስ ሳሉ በቀድሞው መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ሸንጎ አባል ሆነው መመረጣቸውና እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ማገልገላቸውን መረጃዎችና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይናገራሉ፡፡

ሥልጣናቸውን “ሕመም አድሮብኛል” በማለት ለሲኖዶሱ ነሐሴ 18 ቀን 1983 ዓ.ም. ማስረከባቸው የሚያስታውሰው መግለጫው፣ ሲኖዶሱ ጉዳዩን ካጠናና ቀኖናው የሚለውን ጠብቆ ከሥልጣን ካነሣቸው በኋላ አራተኛው የቀድሞው ፓትርያርክ “ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ፓትርያርክ አይደሉም” በማለት ውሳኔውን አብራርቷል፡፡ መግለጫው አያይዞ አራተኛው የቀድሞ ፓትርያርክ ባቀረቡት ጥያቄና በዚህ ቀኖና መሠረት እርሳቸውን አንስቶ ሌላ ፓትርያርክ ሾመ እንጂ በፓትርያርክ ላይ ፓትርያርክ አልሾመም፣ ሁለት ፓትርያርክ እየተባለ የሚነገረው አነጋገርም ሕጋዊነት የሌለው ፍጹም የስህተት አባባል መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶበታል፡፡

ሲኖዶሱ ውሳኔውን ባስተላለፈበት ጊዜ ዛሬ በአሜሪካ ያሉት አባቶችም ባሉበት፣ በተስማሙበትና በፈረሙበት ሁኔታ የተፈጸመ ሲሆን፣ የፈረሙበት ሰነድ በቤተ ክርስቲያን ተቀምጦ እያለ እውነትነት የሌለው ሌላ ታሪክን ለመተረክ ሲሞክሩ መሰማታቸው እጅግ ከፍተኛ ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው ብሏል፡፡

“አራተኛው ፓትርያርክና ከርሳቸው ጋር ባሉት አባቶች የተፈጸመው ስህተት ሁሉ በጽሑፍ፣ በሚዲያና በልዩ ልዩ ጉባኤያት ለሕዝቡ እንዲደርስ ይደረጋል፤” ያለው መግለጫው፣ ሕጉና ቀኖናውን ተከትሎ እየተከናወነ የሚገኘውን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ይፈጸም ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ ተሳትፎና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አድርጓል፡፡

No comments:

Post a Comment