በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን!
ከሁሉ አስቀድሜ ቅዱስነትዎ እግዚአብሔር ባወቀ ተመርጠው እንዲጠብቁ የተሾሙበት መንጋ አካልና ታናሽ የምሆን የመንፈስ ቅዱስ ልጅዎ ለምሆን ለኔ ቡራኬዎ ይድረሰኝ እላለሁ፡፡
በመቀጠልም የአገልገሎት ዘመንዎን ልዑል እግዚአብሔር የተቃና እንዲያደርግልዎ
ልባዊ ምኞቴን እየገለጽኩ፣ ይህችን አጭር
ደብዳቤ መጻፌ
ድፍረት ተደርጎ እንዳይቆጠርብኝ
እጅግ ከፍ
ባለ ትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ስለ ራሴ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የመንጋው አካል የሆንኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጅ ስሆን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ፭ተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍትን ተከትሎ ቀደም ሲል በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ተከስቶ ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል ጎራ በማስለየት የቤተክርስቲያናችን የበላይ አካል የሆነውን ቅዱስ ሲኖዶስ ያለያየና ያወጋገዘ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እልባት አግኝቶ፣ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ቀደመ ታሪኳ ወደ አንድነት እንድትመጣና የተጠራችለትን ሐዋርያዊ ተልዕኮ በፍቅርና በአንድነት ለመወጣት እንድትችል በእጅጉ ከተመኙትና ይፈልጉ ከነበሩት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ልጆችዎ መካከል አንዱ ነኝ፡፡
ስለ ራሴ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት የመንጋው አካል የሆንኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጅ ስሆን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ፭ተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍትን ተከትሎ ቀደም ሲል በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ተከስቶ ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል ጎራ በማስለየት የቤተክርስቲያናችን የበላይ አካል የሆነውን ቅዱስ ሲኖዶስ ያለያየና ያወጋገዘ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እልባት አግኝቶ፣ ቤተ ክርስቲያናችን እንደ ቀደመ ታሪኳ ወደ አንድነት እንድትመጣና የተጠራችለትን ሐዋርያዊ ተልዕኮ በፍቅርና በአንድነት ለመወጣት እንድትችል በእጅጉ ከተመኙትና ይፈልጉ ከነበሩት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ልጆችዎ መካከል አንዱ ነኝ፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን መካከል የተፈጠረውን መለያየት በማስወገድ የበላይ አመራሯን ሲኖዶሱን ብሎም ማኅበረ ምዕመናኑ ወደ አንድ የማምጣት ተግባር የመላው ምዕመን ፍላጎትና ፀሎት የነበረ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች በገሃድ የታየ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከእኔ ከታናሹ የመንፈስ ቅዱስ ልጅዎ ይልቅ ቅዱስነትዎና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጥልቅ በሚያውቁት ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን የተከሰተውን ልዩነት በማስወገድና መወጋገዝ በማንሳት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን መልሶ ወደ አንድ የማምጣት ሥራ ሳይጠናቀቅ ብፁዕነትዎ ፮ኛው የቤተክርስቲያናችን ፓትርያርክ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ 1.3 እንደጻፈው የሆነው ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነና ከሆነው ሁሉ አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ ፈቃድ እንዳልሆነ ያለጥርጥር አምናለሁ፡፡
በእኔ በታናሹ የመንፈስ ቅዱስ ልጅዎ እይታ በቤተ ክርስቲያናችን መካከል የተፈጠረውን ልዩነት አስወግዶ የቀደመውን አንድነት መልሶ በማምጣት ሒደት የቅዱስነትዎ ፮ኛ ፓትርያርክ ሆኖ መመረጥ እንቅፋትና ችግር ሳይሆን፣ በችግሩ አፈታት ሒደት ዙሪያ ሌላ ምዕራፍ የሚከፍትና በምዕራፉም ማለትም ቤተ ክርስቲያናችንን መልሶ ወደ አንድነት በማምጣት ጉዳይ ቅዱስነትዎን ግንባር ቀደም ተዋናይና መሪ የሚያደርግዎ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ይህንም ልዑል እግዚአብሔር በእርስዎ ላይ ሊጥል እንደወደደ ይረዳኛል፡፡
ቅዱስ አባታችን፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከምንጊዜውም የበለጠ ዛሬ በመሆንና ባለመሆን፣ በማድረግና ባለማድረግ መካከል መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ በታች የቤተ ክርስቲያናችን ራስ አድርጎ ሲቀባዎ ከተራራ የገዘፉ እጅግ ብዙና ውስብስብ ችግሮችን ልዑል እግዚአብሔር በሚሰጥዎ ሰማያዊ ጥበብ ፈትተው፣ የእግዚአብሔርን መንጋ አንድ አድርገውና አስተባብረው ይመሩ ዘንድ ያለበት አንድ ትልቅ ምዕራፍ የተከፈተበት እንደሆነ ያለአንዳች ጥርጥር አምናለሁ፡፡
ይህ ምዕራፍ የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ እንዳስተማረንና “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይህች ናት፤” የዮሐንስ ወንጌል 05፡02 ብሎ እንደተናገረ ለሁለት የተከፈለውን ቅዱስ ሲኖዶስ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት አንድ በማድረግ ይጀምራል፡፡ ደግሞም ስለ ፍቅር በእግዚአብሔር ቃል በተለያየ ሥፍራ እንደተጻፈ “እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም” መጀመሪያይቱ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 4.9 እና ፍቅር የሁሉ የበላይ መሆንዋን በሚገልፀው መልዕክቱ 1 ቆሮንቶስ 03.1-8 “በሰዎችና በመላዕክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ …ፍቅር ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፣ ፍቅር አይቀናም፣ ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም የራሱንም አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በደልን አይቆጥርም፣ የማይገባውን አያደርግም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ አመጻ ደስ አይለውም” የሚለውን ቃል በወንጌል ሐዋርያነት ለሚመሩት መንጋ በተግባር የሚያስተምሩበት ምዕራፍ እንደሆነ በእጅጉ እረዳለሁ፡፡
ይህ አዲስ ምዕራፍ በእንደራሴና በተወካይ ሳይሆን ለሁለት የተከፈለው ቅዱስ ሲኖዶስና ይህንኑ ተከትሎ የተከፈለው መንጋ እርሰዎ ይመሩት ዘንድ የተቀቡበት አንድ መንጋ ስለሆነ፣ መንጋውን አንድ የማድረግና በውስጡ የተፈጠረውን መለያየት የማስወገድና ውግዘት የማንሳት ሥራ በእርስዎ ተወካዮች አማካይነት የሚከናወን ተግባር ሳይሆን፣ ቅዱስነትዎ ራስዎ ሊሠሩት የሚገባ ግንባር ቀደም ተግባርና የአባታዊ ሥራዎ መጀመሪያ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ስለዚህም ቅዱስነትዎ ከሲመትዎ የመጀመሪያ ቀን ጀምረው አበክረው እንዲሠሩና የተከፈለውን መንጋ አንድ በማድረግ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ እንዲያጽፉ አበክሬ በትህትና እማጸናለሁ፡፡ ይህን ማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ፍቅርን በቃል ሳይሆን በተግባር የምታስተምር ለመሆኑ ሕያው ምስክር ከመሆኑም ባሻገር፣ ለቅዱስነትዎ የወደፊት ቀጣይ ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ መከናወን ትልቅ መሠረት የሚጥል እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ቅዱስነትዎ እንደሚያስተምሩኝ ይህ ተግባር ደግሞ ጌታችንና መድኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ እግር ሥር ተቀምጦ ያጠባቸውን ዓይነት ታላቅ ትህትና የሚጠይቅ እንደሆነ ይረዳኛል፡፡
ምንም እንኳን በግል ደረጃ በተከፈለው ሲኖዶስ ካሉ ብፁዓን አባቶች አንዱ ሌላውን የበደለበት ሁኔታ ያለ ባይመስለኝም (ቢኖርም እንኳ)፣ በዕለት ውስጥ ብዙ ጊዜ የምንደግመውንና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን “በደላችንን ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” የሚለው ይቅር መባባልን የሚያስተምረን ቃል፣ መንጋውን ወደ አንድ ወደ ማምጣት በሚያደርጉት ሒደት ግንባር ቀደም መርህ መሆን እንደሚገባው አምናለሁ፡፡
ስለሆነም የብዙዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ምዕመን ፍላጎት የሆነውንና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መልሶ የመገንባት ሥራን ቀዳሚ ተግባርዎ በማድረግ የአገር ውስጥ ሲኖዶስ፣ ስደተኛው ሲኖዶስ እንዲሁም በሌላ በኩል የሸዋ፣ የጎጃሜ፣ የጎንደሬ፣ የትግሬ፣ የወሎ፣ የኦሮሞ የሚሉ ክፍፍሎች ሁሉ ታሪክ ሆነው፣ በክርስቶስ ደም ላይ የተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን አንድ ሆና አማናዊ ተልዕኮዋን የምትወጣበትን ስልት ከፕትርክናዎ የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እንዲሠሩበት፣ እጅግ አጭር በሆነ ጊዜ ለእነዚህ ችግሮች እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ባወቀ ረድቶዎት መፍትሔ እንዲያበጁ፣ በእርቀ ሰላሙ መራቅና በቤተ ክርስቲያን መከፈል ልቡ ባዘነበት ምዕመን ልብ መልሰው ደስታን እንዲዘሩ እኔ ከሁሉ ታናሽ የምሆን የመንፈስ ቅዱስ ልጆዎ እማጸናለሁ፡፡
በመቀጠል በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ውስጥ በእጅጉ ሥር እንደሰደደ የሚነገርለትን በዘመድ አዝማድ መሳሳብ፣ በወንዝ ልጅነት መጓተትና በቤተ ክርስቲያኒቱ የአመራርና የሥልጣን እርከን ላይ መሰባሰብን በማስቀረትና ይህም ዳግም የማይፈጠርበትን ሁኔታ በመፍጠር፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና አመራር በእውነት ለነፍሳቸው ባደሩና አገልግሎታቸውን ጠንቅቀው በተረዱ አገልጋዮች ይከናወን ዘንድ ሁኔታዎችን ማስተካከል እጅግ ከፍተኛ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ትልቅና ከባድ ሥራ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ከባድም ቢሆን የዚህ ተግባር በአግባቡ አለመተግበር የነገይቱን የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር በእጅጉ ስለሚጎዳ ቅዱስነቱዎ ልዩ ትኩረት ስጥተው እንደሚያስተካክሉት አምናለሁ፡፡
በአንድ ወቅት በቤተ ክርሰቲያናችን አስተዳደር ውስጥ እንደሰፈነ የሚነገረው በጎ ያልሆነ ሥነ ምግባር (ጉቦኝነት) አሰራር ላይ “አንድ ሰው ጉዳይ እንዲፈጸምለት ሲፈልግ አምስቱን አዕማደ ሚስጢር፣ ሰባቱን ምስጢራተ ቤተክርስቲያን … ታውቃለህ? ይባላል፤” ይህ ማለት ለጉዳይ ማስፈጸሚያ አምስት ሺሕ ብር፣ ሰባት ሺሕ ብር ማለት ነው ፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያናችን የእምነት መሰረት የሆኑት ሚስጥራትና ሌሎችም ለእንደዚህ ዓይነቱ ኢክርስቲያናዊ የሆነ ተግባር አምሳያና መግለጫ መሆን እጅግ የሚያሳዝን ተግባር ነው፡፡ ቅዱስነቱዎ ለዚህም ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት በእግዚአብሔር ዘንድ አስፀያፊ የሆነው ጉቦና መማለጃ ለቤተ ክርስቲያናችን ብቻ ሳይሆን ለአገርም ዕድገት ችግርና ፀር እየሆነ የመጣ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር ጓዳ ከዚህ መልካም ያልሆነ ሥነ ምግባር በማፅዳት፣ በአገር አቀፍም ጭምር በስፋት ለሚንፀባረቀው ለዚሁ መልካም ያልሆነ ሥነ ምግባር ቤተ ክርስቲያን መፍትሔ እንዳላት የምታሳይበትን መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥሩ እምነቴ ከፍ ያለ ነው፡፡
ቅዱስነትዎ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንዲመሩ የተመረጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ከአገራችን ጠቅላላ ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ የቅዱስነቱዎን ሚና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ሳይገደብ በአገር አቀፍም ደረጃ የጎላ ያደርገዋል፡፡ ምንም እንኳን በአገራችን ሕገ መንግሥት መሠረት ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩና አንዱ በአንዱ ሥራ ጣልቃ የማይገቡ ቢሆንም ሕግ ሲጣስ፣ በደል ሲፈጸም፣ ነገሮች ያለአግባብ ሲከናወኑና ሲደረጉ እንዳልሰሙ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ሊያልፉ የማይገባና እንደ ቆራጥ የሃይማኖት አባት ወቅቱን የጠበቀ ምክርና ብሎም ተግሳፅ የመስጠት ተግባርና ኃላፊነት ጭምር እንዳለብዎ እረዳለሁ፡፡
ቅዱስ አባታችን፣ ከላይ የጠቀስኩዋቸውና የዘረዘርኩዋቸው ነጥቦች ሁሉ እርስዎ የማያውቋቸውና ያልተረዷቸው ነገሮች ናቸው የሚል አንዳች የሆነ ሐሳብ የለኝም፡፡ ይልቁንም እንደ አንድ ታናሽ የመንፈስ ቅዱስ ልጅዎና እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል የቅዱስነትዎ ምርጫና በዓለ ሲመት ሲከናወን በውስጤ ያለውን ሐሳብ ለመግለጽ ፈልጌ እንጂ፡፡ በመጨረሻ በዚህ አጭር ደብዳቤ ካደረኩት የቃላት አመራረጥ እንዲሁም ባለማወቅ ቅር ያሰኘሁበት ነገር ካለ አባት ልጅን ይቅር ማለት የተገባ ነገር ነውና ቅዱስነትዎ ይቅርታ እንዲያደርጉልኝ እጅግ ከፍ ባለ ትህትና እጠይቃለሁ፡፡
አክባሪና ታዛዥ የመንፈስ ቅዱስ ልጅዎ
የጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻ seifesa@yahoo.com (ሰይፈ ገብርኤል)
kale heiwot yasemalen.
ReplyDeleteK, tadi
" ... ምንም እንኳን በአገራችን ሕገ መንግሥት መሠረት ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩና አንዱ በአንዱ ሥራ ጣልቃ የማይገቡ ቢሆንም ሕግ ሲጣስ፣ በደል ሲፈጸም፣ ነገሮች ያለአግባብ ሲከናወኑና ሲደረጉ እንዳልሰሙ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ሊያልፉ የማይገባና እንደ ቆራጥ የሃይማኖት አባት ወቅቱን የጠበቀ ምክርና ብሎም ተግሳፅ የመስጠት ተግባርና ኃላፊነት ጭምር" አለብዎ::
ReplyDelete" ... ምንም እንኳን በአገራችን ሕገ መንግሥት መሠረት ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩና አንዱ በአንዱ ሥራ ጣልቃ የማይገቡ ቢሆንም ሕግ ሲጣስ፣ በደል ሲፈጸም፣ ነገሮች ያለአግባብ ሲከናወኑና ሲደረጉ እንዳልሰሙ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ሊያልፉ የማይገባና እንደ ቆራጥ የሃይማኖት አባት ወቅቱን የጠበቀ ምክርና ብሎም ተግሳፅ የመስጠት ተግባርና ኃላፊነት ጭምር" አለብዎ::
Delete