from http://www.melakuezezew.info
ድሜጥሮስ መስታወት ነው፡-በመስታወት ከዓይን ጉድፍ ከጥርስ እድፍ አይተው እንደሚያጸዱበት ሁሉ ባሕረ ሐሳብንም የተማረ ሰው ዓለም ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ እስከ ምጽአት ድረስ የሚሆነውን ቁጥር ያውቃልና፡፡ ባሕረ ሐሳብ ማለት ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ነው፡፡ አንድም ሐሳብ ባሕር ይለዋል ዘመን ያለው ቁጥር ሲል ነው፡፡
ድሜጥሮስ መነጽር ነው፡- መነጽር የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን አጉልቶ፣ የተበተነውን ሰብስቦ እንዲያሳይ እርሱም የተበተኑ አጽዋማትን በዓላትን አቅርቦ ያሳያልና፡፡
ድሜጥሮስ ጎዳና ነው፡- በጎዳናው ተጉዘው ከቤት እንደሚደርሱ ሁሉ፣ ባሕረ ሓሳብም ወደ ኋላ ያለፉትን ወደፊትም የሚመጡትን አጽዋማት በዓላትን ለይቶ ያሳውቃልና፡፡
ድሜጥሮስ ተራራ ነው፡- በተራራው ጫፍ ላይ በወጡ ጊዜ ምንጩ ሜዳው፣ ግጫው፣ ኮረብታው እንደሚታይ ሁሉ ድሜጥሮስም የአጽዋማት በዓላትን ኢየዓርግ ኢይወርድ ጠንቅቶ ጽፏልና፡፡
ድሜጥሮስ መስተገብረ ምድር (በግብርና የሚተዳደር) ነው፡- ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ፡-
ድሜጥሮስ አባቱ አርማስቆስ ይባላል፡፡ አርማስቆስ ደማስቆ የሚባል ወንድም ነበረው ፡፡ደማስቆ ልዕልተ ወይን የምትባል ሴት ልጅ ነበረችው፡፡ አባቷ በሚሞትበት ጊዜ ለወንድሙ ለአርማስቆስ አደራ ሰጥቶት ሞተ፡፡ ልዕልተ ወይን ከድሜጥሮስ ጋር አፈር ሲፈጩ፣ ውኃ ሲራጩ በአንድነት አደጉ፡፡
ቅዱስ ድሜጥሮስ ደኮ ታጥቆ፡ እርፍ አርቆ፣ ተክል አጽድቆ ይኖር ነበር፡፡ ያጎቱ ልጅም በሕፃንነትዋ አባትና እናቷ ስለ ሞቱባት፣ በድሜጥሮስ እናትና አባት ቤተ እየኖረች አብረው አድገዋል፡፡ ሁለቱም ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን በደረሱ ጊዜ ዘመኑ አሕዛብ የበዙበት ክርስቲያኖች ያነሱበት ጊዜ ነበርና ሕንፃ ሃይማኖት ከሚፈርስ ሕንፃ ሥጋ ይፍረስ ብለው መክረው አጋቡአቸው፡፡
ሰርጉ ተሰርጎ ሲበላ፣ ሲጠጣ ተዋለና ወደ ማታ ገደማ ሥርዓተ መርዓት ወመርዓዊ ያድርሱ ብለው መጋረጃ ጥለው ሕግ እንዲፈጽሙ ጥለዋቸው ወጡ፡፡ መኝታቸውም ላይ እንዳሉ አስቀድማ ሙሽራዋ ብድግ ብላ ተነሥታ ወንድሜ ለመሆኑ ይህን ነገር ያደረግኸው የእሷ ዝምድና አይረባኝም፣ አይጠቅመኝም ብለህ ነውን? ብላ ጠየቀችው፡፡ እሱም እኔስ ያንቺ ዝምድና አይረባኝም፣ አይጠቅመኝም ብዬ ሳይሆን የእናት አባቴን ፈቃድ ለመፈጸም ብዬ ነው ሲል መለሰላት፡፡ አሁንስ ቢሆን ፈቃድሽ ከሆነ ለምን አንተወውም አላት፡፡ እሷም አኔስ ፈቃዴ ነው እንተወው አለችው፡፡ እንግዲያውስ የተለያየን እንደሆነ እኔንም ለሌላ ያጋቡኛል፣ አንቺንም ለሌላ ይድሩሻል፡፡ የተጋባን መስለን ሳንለያይ አብረን እንኑር፡፡ ልጅ ባንወልድ እንኳን መካን ሆነው ነው ይሉናል እንጂ አልተጋቡም አይሉንም አላት፡፡ ተስማምተው በአንድ አልጋ በአንድ ምንጣፍ እየተኙ አንድ ልብስ እየለበሱ 48 / አርባ ስምንት/ ዓመት ሙሉ በንጽሕና ኑረዋል፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል እየመጣ በቀኝ ክንፉ ለድሜጥሮስ ግራ ክንፉን ለልዕልተ ወይን አልብሷቸው አድሮ ጠዋት ከመካከላቸው ተነሥቶ ሲሄድ በአምሳለ ጸአዳ(ነጭ) ርግብ ይታያቸው ነበር፡፡
ድሜጥሮስ ደኮ ታጣቂ፣ እርፍ አራቂ፣ ተክል አጽዳቂ ነበርና ወደ ተክል ቦው ገብቶ ላለ፣ የወይን ዘለላ ያለ ጊዜዋ አብባ አፍርታ አግኝቶ እኔ ልመገባት አይገባኝም ብሎ ቆርጦ ወስዶ ለሚስቱ ሰጣት፡፡ እሷም ይህንንስ እኔ ልመገባት አይገባኝም በመሶበ ወርቅ አድርገህ ወስደህ ለሊቀ ጳጳሱ ሰጥተህ በረከት ተቀብለህባት፣ ተመርቀህ ና አለችው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተገናኙ ናቸውና ቃላቸው አንድ ሆነ፡፡ እሷም እንዳለችው ወስዶ ለእስክንድርያው 12ኛ ሊቀ ጳጳስ ለቅዱስ ዩልያኖስ ሰጥቶ ተመረቀ፡፡
ሊቀ ጳጳሱ ዩልያኖስ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ደግ ሰው ነበርና የሚሞትበት ቀን በደረሰ ጊዜ መልአኩ መጥቶ “አንተ ዩልያኖስ የምትሞትበት ጊዜ ስለደረሰ በወንበርህ የሚተካ እንድታገኝ አንተም እዘን ሕዝቡም ይዘኑ” አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ዩልያኖስ ሕዝቡን የራቀውን በደብዳቤ የቀረበውን በዐዋጅ ሰብስቦ እኔ አረጀሁ የምሞትበት ጊዜ ደርሷል፡፡ በቅዱስ ማርቆስ ወንበር የሚተካ እንድታገኙ ወደ እግዚአብሔር አመክቱ ጸልዩ፣ እዘኑ ብሎ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቶ ሰደዳቸው፡፡ መልአኩ በድጋሚ ወደ ዩልያኖስ መጥቶ “ያለ ጊዜዋ ያፈራች አንዲት የወይን ዘለላ፣ በረከት አገኛለሁ ብሎ በመሶበ ወርቅ አድርጎ ይዞልህ የሚመጣ ሰው አለ፡፡ ካንተ ቀጥሎ የሚሾመው እሱ ነው” ብሎ ነገረው፡፡ ሕዝቡም ሊቀ ጳጳሱ በቀጠራቸው ቀን ተሰብስበው መጡ፡፡ አባታችን እንደምን ያለ ሰው አገኘህልን አሉት? የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ ምልክት ነግሮኛል አላቸው፡፡ ምልክቱም፡- “ያለ ጊዜዋ ያፈራች አንዲት የወይን ዘለላ በረከት ለመቀበል ብሎ በመሶበ ወርቅ አድርጎ ይዞልኝ የሚመጣ ሰው አለ፡፡ ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው እሱ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡ ሕዝቡም በዚህ ተደስተው ወደ የቤታቸው ሄዱ፡፡
በማግስቱ ዩልያኖስ ጉባኤ ዘርግቶ ሲያስተምር ከቀድሞው ይልቅ ዘገየባቸው፡፡ “አባታችን ምነው ከቀድሞው ይልቅ ዘገየህብን?” አሉት፡፡ እሱም “ያ ያልኳችሁ ሰው እሰኪመጣ ድረስ ብዬ ነው” አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ዩልያኖስ ድሜጥሮስ ከርቀት ሲመጣ አሻግሮ አይቶ ለሕዝቡ ያልኳችሁ ሰው መጣ ብሎ ነገራቸው፡፡ ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው፡፡ አይሆንም እምቢ አሻፈረኝ ይላችኋል እናንተ ግን ቢሆን በውድ ባይሆን እንኳን በግድ ሹሙት እንዳትለቁት አላቸው፡፡ ምነው አስቀድሞ ነገራቸው ከእርሱ ፊት ባልነገራቸው ነበር ቢሉ ቅዱሳን ክብራቸውን በሰው ፊት ቢገልጹባቸው አይወዱምና ነው፡፡
ድሜጥሮስም ሊቀ ጳጳሱ ዘንድ በደረሰ ጊዜ እጅ ነስቶ ቆመ፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ሲያየው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንዴት አለህ? አለው፡፡ እሱም እግዚአብሔር ይመስገን ብሎ ወይኑን አበረከተ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ዩልያኖስም ድሜጥሮስን ባርኮት አልዋለም አላደረም ዕለቱኑ ዐረፈ፡፡
ድሜጥሮስም ሊቀ ጳጳሱን ቀብሮ ሳይውል ሳያድር ዕለቱን ልሂድ ብሎ ተነሳ፡፡ ሕዝቡም አባታችን ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው እሱ ነው ብሎናልና አንሰድህም አሉት፡፡ እንዲያውም ወንበር ያለሹም አያድርምና ተሾምልን አሉት፡፡እርሱም ንጹሕ፣ ድንግል በሚቀመጥበት በማርቆስ ወንበር እንደ እኔ ያለ ሕጋዊ በተጨማሪም ያልተማርኩ ስሆን እንዴት እሾማለሁ? ብሎ አይሆንም አላቸው፡፡ እነርሱም አባታችን ነግሮናል አይሆንም አሉት፡፡ ድሜጥሮስም አባታችን የተማሩ፣ ድንግል፣ ንጹሕ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ ያልተማርኩ ሕጋዊ ነኝ እንደምን ይሆንልኛል? ከእኔ የተሻለ ሌላ መርጣችሁ ሹሙ እንጂ አላቸው፡፡ እነርሱም ያባታችን ቃል አይታበልም ቢሆን በውድ ባይሆን በግድ አንለቅህም አሉት፡፡ እንግዲያውስ ሕጉን ሥርዓቱን ንገሩኝ አላቸው፡፡ አልተማርኩም ብትለን ነው እንጂ አባታችንስ አንቀጸ ብፁዓንን፣ አንቀጸ አባግዕን አንብቦ ተርጉሞ ይነግረን ነበር አሉት፡፡ ከቤተ መዛግብት መጽሐፍ አምጡልኝ አለ፡፡ ከዚያ ቀድሞ እንኳንስ ትርጓሜውን ንባቡን አያውቅም ነበር፡፡ መጽሐፉን እስኪያመጡለት ድረስ በቃሉ አንብቦ ተርጉሞ ተሹሟል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ብሉይና ሐዲስ ተገልጾለታል፡፡ በሀገራቸው ሊቀ ጳጳስ በተሾመ ጊዜ ሰባት ቀን ቀድሶ ያቆርባቸዋል፡፡
ቅዱስ ድሜጥሮስም ቀድሶ በሚያቆርብበት ጊዜ ሄዶ ከደጀ ሰላም ይቀመጣል፡፡ ሕዝቡ ለመቁረብ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ የሕዝቡ ኃጢአት “በብርሌ ካለ ጠጅ እንደገባ ሣር” ሆኖ እየታየው አንተ በቅተሃል ግባ አንተ አልበቃህም አትግባ እያ ይከለክላቸው ነበር፡፡ ምእመናን ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ሲመጡ የበቁ የሆነ እንደሆን ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው መላእክተ ብርሃን ከበዋቸው ያያቸዋል፡፡ እናንተ ግቡ ሥጋ ወደሙን ተቀበሉ ከትሩፋቱም ጨምሩበት ይላቸዋል፡፡ ያልበቁ የሆነ እንደሆነ ጨለማ ለብሰው፣ ጨለማ ተጎናጽፈው መላእክተ ጽልመት ከበዋቸው ያያቸዋል፡፡ እናንተ ተመለሱ ሥጋ ወደሙን አትቀበሉ ንስሐ ግቡ ብሎ ይከለክላቸዋል፡፡ እነዚያ የተከለከሉ ሰዎች “እጨጌነት ከሳዱላ” እንዲሉ እሱ የማይገባውን ከሚስቱ ጋር በአባታችን በቅዱስ ማርቆስ መንበር ተቀምጦ የእኛን ኃጢአት በምን ዐውቆ ይከለክለናል እያሉ አሙት፡፡ አንጎራጎሩበት፡፡ በዚህ ጊዜ በእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ እነዚህ ሰዎቸ በማይረባ ነገር በሐሜት ተጎድተዋልና በአንተና በሚስትህ መካከል ያውን ምስጢር ግለጥላቸው አለው፡፡
ፈቃደ እግዚአብሔር ከሆነማ እሺ ብሎ ሕዝቡን የራቀውን በደብዳቤ የቀረበውን በአዋጅ ሰብስቦ በአደባባይ እንጨቱን እንደ ደመራ አስደምሮ ሊቀ ዲያቆናቱን እኔ እስክ መጣ ድረስ ሕዝቡን አታሰናብት አቆይልኝ አለው፡፡ ዕለቱም ጰራቅሊጦስ ነበር፡፡ በሀገራቸው ልማድ በዘጠኙ በዓላት ሊቃነ ጳጳሳት ቅዳሴ ይገባሉ፡፡ ቀድሶ ወጥቶ የተከመረውን እንጨት እሳት አስነድዶ “ወጸለየ ድሜጥሮስ ነዋህ ሰዓተ በዲበ እሳት፣ አንድ ሰዓት ከእሳቱ ላይ ቆሞ ጸለየ” ያን ጊዜም ሚስቱ በምቅዋመ አንስት( በሴቶች መቆሚያ ) ቆማ ነበርና እርስዋን አስጠርቆ ስፍሒ አጽፍኪ፣ ልብስሽን ዘርጊው አላት ዘረጋችው፡፡
ቅዱስ ድሜጥሮስም እሳቱን በእጁ እያፈሰ በልብሷ ላይ አድርጎ ሂጂ ምእመናኑን ሦስት ጊዜ ዞረሽ እጅ ነስተሽ አምጪው አላት፡፡ እሷም እሺ ብላ “እሱም በልማደ አዳም እኔም ሴት ሆኜ በልማደ ሔዋን እንዳልተዋወቅን ምስክራችን ይህ ነው” እያለች ሕዝቡን ሦስት ጊዜ ዞራ እጅ ነስታ ብታፈሰው እሳቱ ሰውነቷን ሊፈጃት ይቅርና ከለበሰችው ልብስ ከዘሀው ከማጉ አንድስ እንኳ አልጠቆረም፣ አልቀነበረም፡፡ ይኸውም በዚህ ዓለም አንድ ልብስ ለብሰው አንድ ምንጣፍ አንጥፈው በአንድ አልጋ እየተኙ ሲኖሩ በኃጢአት መውደቅ እንዳላገኛቸው፣ ንጽሐ ጠባይ እንዳላደፈባቸው ያጠይቃል፡፡
ሕዝቡም ይህን አይተው አባታችን ይህ ነገር የተደረገበት ምክንያት ምን እንሆነ ምስጢሩን ግለጥልን አሉት፡፡ እሱም እኔ እከብርበት፣ እገንበትና እታፈርበት ብዬ አይደለም፡፡ እናንተም ታውቃላችሁ ይህች ሴትና እኔ ከተገናኘን 48 /አርባ ስምንት/ ዘመናችን ነው፡፡ ይህን ያህል ዘመን አብረን ስንኖር እኔ እሷን በልማደ ሔዋን አላውቃትም እሷም በልማደ አዳም አታውቀኝም፡፡ ከልብሷ ዘሃ አንዱ እንዳላረረ፣ እንዳልጠቆረ፣ እንዳልቀነበረ ሁሉ በኔና በሷ መካከል ያለውም ንጽሐ ጠባይ ያላደፈ መሆኑን ያሳያል አላቸው፡፡ እነሱም ተደንቀው አባታችን ሳናውቅ በከንቱ አምተንሃል ብለው ወድቀው ማረን አሉት፡፡ እርሱም ይቅር ስለ እግዚአብሔር አላቸው፡፡ ይቅር ካልክስ ናዝዘህ ኃጢአታችንን አስተስርይልን አሉት፡፡ እሱም በናዘዛቸው ጊዜ በሰውነታቸው ያለ ኃጢአት አንደ ሸማ፣ እንደ መጎናጸፊያ ተጠቅልሎ በፊታቸው ሲወድቅ አይተውታል፡፡ ከዚህ በኋላ የቅዱስ ድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳስነት ጸና፡፡ አሥራ ሁለተኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ሆነ፡፡ ልዕልተ ወይንም ከማኅበረ ደናግላን ተቆጠረች፡
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ደሜጥሮስ፡-
§ ነነዌ፣ በዓተ ጾም /ዐቢይ ጾም/፣ ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ
§ ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ፣ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ
§ ርክበ ካህናት፣ ጾመ ድኅነት ከረቡዕ
§ ዕርገት ከሐሙስ
§ ስቅለት ከዓርብ፣ ዕለታት ባይወጡ /በእነዚህ ዕለታት ቢውሉ/ በወደድኩ ነበር እያለ ይመኝ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የተመኙትን መግለጽ ልማዱ ነውና፤ መልአኩ ወደ ድሜጥሮስ ታዞ መጥቶ “ድሜጥሮስ ነገር በሐሳብ ብቻ ይፈጸማልን? ቢያደርጉት ነው እንጂ” ብሎ ነግሮት ከመዓልቱ 7 /ሰባት/ ሱባኤ ከሌሊቱ 23 /ሃያ ሦስት/ ሱባኤ ገብተህ ይገለጽልሃል፡፡ ይህንንም በሠላሳ በሠላሳ ገድፈህ በተረፈው ታገኘዋለህ ብሎታል፡፡
ይህንን የሌሊት 23 ሱባኤ ቢቆጥሩ 161 ይሆናል፡፡ ከዚህ በላይ 150ውን በአምስት 30 ገድፈህ 11ይቀራል፡፡ ይህንን አበቅቴ በለው ብሎታል፡፡ ጥንተ አበቅቴ የተባለ ይህ ነው፡፡ የመዓልቱን 7 ሱባኤ ቢቆጥሩ49 ይሆናል፡፡ ከዚያ ላይ ሠላሳውን ገድፈህ 19ኙን መጥቅዕ በለው ብሎታል፡፡ ትርጓሜውም ደወል ማለት ነው፡፡ ደወል ሲደወል የራቀው ይቀርባል የተበተነው ይሰበሰባል፡፡ በመጥቅዕም በዓላትና አጽዋማት ይሰበሰቡበታልና፡፡ ይህን 11 አበቅቴና 19 መጥቅዕ ቢገጥሙ ሠላሳ ይሆናል፡፡ መጥቅዕ ቢያንስ ከሠላሳ አይወጣም ከሠላሳ አይወርድም፡፡ “ ኢየዓርግ እም 30 ወኢይወርድ እም 30 ወትረ ይከውን 30” እንዲል፡፡
ስለምን የሌሊቱን ሱባኤ አብዝቶ የመዓልቱን አሳነሰው? ቢሉ ፡-
1. በመዓልት የተጣላ ሲያስታርቅ፣ የታመመ ሲጠይቅ፣ የሞተ ሲቀብር፣ ሲፈርድ፣ ሲተች፣ ሲመክር፣ ሲያስተምር፣ ቤተ እግዚአብሔር እጅ ሲነሳ ይውል ነበርና፤ በሌሊት ግን ይህ ሁሉ የለበትምና፡፡
2. በመዓልት እግር ከመሄድ፣ እጅ ከመዳሰስ፣ ዓይን ከማየት አይወሰንም ሌሊት ግን ከዚህ ሁሉ ይወሰናልና፡፡
3. የድሜጥሮስን ደግነት ለመመስከር ነው፡፡
ከዚህ በኋላ ቅዱስ ድሜጥሮስ የአጽዋማትና የበዓላት ኢየዓርግ ኢይወርዳቸው ተገልጾለት በሰባት አዕዋዳት አውዶ፣ በአንድ ዐቢይ ቀመር ወስኖ፡ በማኅተም አትሞ በሮም፣ በሶርያ፣ በአንጾኪያ ላሉት ለሦስቱ ሊቃነ ጳጳሳት አራተኛ የኢየሩሳሌም ላለው ኤጲስ ቆጶስ ጽፎ ሰደደላቸው፡፡
እነርሱም ተቀብለው ሐዋርያት በዲድስቅልያ ካስተማሩት ጋር አንድ ሆኖ ቢያገኙት ደስ ብሎአቸው ተቀብለው አስተምረውታል፡፡ ሠለስቱ ምዕትም ጉባኤ ሠርተው አስተምረውታል፡፡ ቅዱስ ድሜጥሮስም ይህን ባሕረ ሐሳብ ተናግሮ ዐርፏል፡፡ ይህን የባሕረ ሓሳብ መጽሐፍ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሊማረው ይገባል ይልቁንም ካህን፡ ዲያቆን ወዘተ . . . ሊማረው ይገባል፡፡
የቅዱስ ድሜጥሮስ ረድኤት፣ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን አሜን፡፡
አዲሱ ዓመት የደስታ ፤የብልጽግና ፤ የንስሐ ፤ የፍቅር ፤ የአንድነት ያድርግልን -አሜን
ምንጭ፡-
1. የባሕረ ሐሳብ መጽሐፍ ከመጽሐፈ ሰዓታት
2. አሥራት ገ/ማርያም፣ የዘመን አቆጣጠር፣ 1987 ዓ.ም.
3. አቡሻኸር መጽሐፍ፣ 1962 ዓ.ም.
4. ሐመር መጽሔት
Amen Kale Hiywot Yasemalin. We copy this post in our website: www.holyfathersundayschool.blogspot.com to reach to others in other dimentions. And we acknowledged and refer your site on it.
ReplyDeleteGod Bless You.