Tuesday, September 13, 2011

አቦይ ስብሀት


‹‹ጓደኛ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ››

የሰሞኑ የሕወሐት ሰዎች አጀንዳ “ማህበረ ቅዱሳን” ሆኗል፤ይህ በ1987 በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ላይ ያደረጉትንም ያስታውሰናል፤ሕወሐት የሥነ ምግባር እና የሞራል መሰረት የሆኑ ዕሴቶችን በማርከስ፣የነቀዘ ትውልድ ለማብቀል ቤተ ዕምነቶቻችንን የነውረኞች እና የሌቦች ዋሻ እንዲሆኑ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት እና ድጋፍ ተጠናክሯል::

በሃጂ መሃመድ አወል ረጃ እና በግራዝማች ሀዲስ መካከል የነበረውን አለመግባባት ተጠቅመው በታላቁ አንዋር መስጊድ ፍጅትን አነገሱ፤የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችን ሰብስበው ከርቸሌ ወረወሩ፤እጅ አልሰጥም አሉ በሚል ሽፋን የታወቁ የእስልምና መሪንም አስወገዱ፤በዚህ መልክ የእስልምና ምክርቤቱን አዳክመው ምን እንደተከተለ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይበልጥ ያውቀዋል፤እንኩዋን ለመሪነት በመስጊድ ደጃፍ ሊያልፉ የማይገባቸው የእስልምና ምክርቤቱን ተቆጣጥረው እስከቅርብ ግዜ ድረስ ቆይተዋል፤ ፤ዛሬ እኚህ ሰው በይፋ በሙስና ተወንጅለው በሙስሊሙ ማህበረሰብ ከፍተኛ ትግል ስፍራቸውን ለቀዋል፡፡


ከላይ ያለው ያለፈ ታሪክ ከ17 ዓመት ቆይታ በኋላ እኛ ላይ እንደማይደገም ምንም ማረጋገጫ የለንም ፡፡አሁን በቤታችች እየተከናወነ ያለው ይህን የመሰለው ስራ ነው፡፡ ይህን ያልኩት ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ ይህን የመሰለ ሸፍጥ የሰራ መንግስት ለእኛም ወደ ኋላ እንደማይል ለማሳሰብ ነው፡፡ አሁን ቤተክርስትያናችን ያለችበትን ክፍተት ተጠቅመው ሁሉም ጠላቶቸዋ ከውስጥም ከውጭም ያሉት በትብር እየሰሩባት ይገኛሉ፡፡


የሕወሀት ታጋዮች አቦይ የሚሏቸው ሌሎች ደግሞ የጥላቻው ፊት አውራሪ በማለት ሚጠቅሷቸው አቶ ስብሀት ነጋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ጳጳሳትን መወንጀል ፤ ቤተክህነቱን የማይረባ በማለት የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ቤተክርስትያንን ማጥቃት የ2003 መሻገሪያ የ2004 መቀበያ እቅዳቸው አድርገውታል፡፡ ሁሉንም ስብስብ በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ተልመው የተነሱት ገዢዎች አሁን ፊታቸውን በተጠናከረ መንገድ ወደ ማህረ ቅዱሳንና ወደ ቤተክርስትያናችን አዙረዋል፡፡ አቦይ ስብሐት በሚዲያ፤ በጋዜጦች፤ በተለያዩ መድረክ ላይ ስለ ቤተክርስትያናችን፤ ስለ ጳጳሳት፤ ስለቤተክህነት የሚናገሩት ነገር ለገባን እና ለተረዳን ሰዎች ነገ ቤተክርስትያናችን ላይ መስራት ለሚያስቡት ሸፍጥ እና ተንኮን የማንቂያና፤ የመጀመሪያ ደውል ነው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ሲናገሩ በዘፈቀድ ሳያስቡት የተናገሩት ሳይሆን ከበስተጀርባ የተጠነሰሰ ሴራ እንዳለ፤ ጊዜውን ጠብቆ ሊያፈነዱት ያሰቡት Time Bomb እንዳለ ያሳየናል፡፡ በተጨማሪ የተሰላ እና የተለካ አካሄድ መሆኑ ይገባናል፡፡
አቦይ ስብሐት ስለ ማኅበረ ቅዱሳን፤ቤተ ክህነቱና ስለ ጳጳሳቱ የተናገሩት
 1.  ለቤተ ክህነቱ አስተዳደራው ብልሹነት ተጠያቂው ቤተ ክህነት እንጂ መንግሥት አይደለም፤
 2. ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ፦ የቤተ ክህነት ዕዳ ነው፤ የቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ብልሽት ያውቃል ነገር ግን ዝም ይላል፣ ብልሽቱ እንዲስተካከል አይሠራም፣ የሚሠሩትን ያደናቅፋል፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ መድረክ ነው፤ …
 3.  ጳጳሳቱ “ለሃይማኖታቸው አይረቡም”
 4.  ቤተ ክህነት ከመንግሥት ሥር ወጥቶ አያውቅም፤ ምሳሌ፦ አጼ ኃ/ሥላሴ “ቅዱስ ተብለው ጽላት ተቀርጾላቸዋል”፤
 5. ለቤተ ክህነት በመንግሥት ሥር መውደቅ ተጠያቂዋ ራሷ ቤተ ክህነት ናት፤
 6. ቤተ ክህነቱ “ወደ ሞት አፋፍ እየሄደ ነው”
 7. ስለ ቤተ ክህነት እንደዚህ መሆን “አማኙ ሐቁን የመስማት መብት” አለው፤
 8. ሌሎች ሃይማኖቶች እንደ ቤተ ክህነት ለምን እንደዚህ አልሆኑም? ......  የሚሉት ናቸው።
ቤተክርስቲያን በእነ አባ ጳውሎስ መንደርተኛና ቤተሰባዊ አስተዳደር ስትመዘበርና በዘመኑ ታህድሷዊ ምንፍቅና ስትወረር? ቅዱስ ሲኖዶስ በቁሙ ሲሞትና ጳጳሳቱ በማንም  ሲንጒጠጡና ሲዋረዱ? ቤተክርስቲያናችን ህጋዊና ህገወጥ ተብላ ስትከፋፈል? ወዘተ መችነው በክርስቲያናዊ ድፍረት እውነቱን ተናግረን፣ ከእውነት ጋር ቆመን፤ እንደ ክርስቲያን ለክርስቶስና ፤ ክርስቶስ በደሙ ለዋጃቸው ቤቱና ልጆቹ በደል የምንመሰክረውና የነፃነት አዋጅን የምናውጀው?

ማህበረ ቅዱሳን 

የማህበረ ቅዱሳንን ማንነት ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሁሉ ማለት ይቻላል ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከአገር ቤት እስከ ውጭ አገር ያለ ሁሉ ማን እንደሆነ መንግስትም ጭምር ያውቃሉ፡፡ ምን እንደሚሰራ ያደረገው አስተዋጽኦ ምን እንደሆነና አባላቱም እነማን እንደሆኑ በገሃድ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ድብቅ አጀንዳ እንዳለው ለማስመሰልና ከዚሁ ጋር በማያያዝ ማስደንበር የሚፈልጓቸውን ሰዎች (የሚደነብር ካለ) ለማስደንበር የማህበሩን ስም ማጥፋት ተገቢ አይደለም፡፡ እስኪ አሁን ማን ይሙት የኢህአዴግን ጠባይ የሚያውቅ ኢትዮጵያዊ አቶ ስብሓት እንደሚሉት የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ቢሆን ኖሮ አስራ ዘጠኝ አመት ሙሉ ይቆያል?

ማህበረ ቅዱሳን ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ በስተቀር ቅንጣት ታክል ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲያራምድና ሌሎች እንዲጠቀሙበት የሚያስችል መዋቅራዊ አደረጃጀት የለውም፡፡ የአባላቱም ስብስብ ለማንም የእጅ አዙር አገዛዝ የሚመች አይደለም፡፡ ኢህአዴግ እውነቱን ያውቀዋል ግን ስጋቶች አሉበት፡፡ የስጋቱ ምንጭ ማህበሩ በአገር ውስጥ ከገጠር ቀበሌ (አጥቢያ) እስከ ከተማ የተዘረጋ መዋቅር መያዙ በውጭ አገር በአፍሪካ፣ በአውሮፓ በሰሜን አሜሪካና በአውስትራሊያም የመንፈሳዊ አገልግሎቱ እጅ የረዘመ መሆኑና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የተማሩ አባላት መያዙ ናቸው፡፡ ማህበሩ ድንገት እስከ አደረጃጀቱና አባላቱ ወደ ተቃውሞ ፖለቲካ ሸርተት ቢል ምን ይውጠናል ነው ጨዋታው፡፡ የተደራጀ ኃይል ያሸንፋል ማንም የግራ ክንፉ አቀንቃኝ ስለሚያውቃት የተደራጀን ኃይል (ለምንም ይደራጅ) እንደ ስጋት መቁጠር የባለጊዜዎች የማንቂያ ደውል ናት፡፡እድሜያቸው ያስተማራቸው ነገር ቢኖት አንድ ሆኖ መታየት፤ በማህበር መንቀሳቀስ ለእነሱ ጥሩ አለመሆኑን ብቻ ነው፡፡ 

በተለይ የህወሓትን አመሰራረት ቅድመ ታሪክ የሚያውቅ ሰው ለምን ገዢው ፓርቲ ማህበረ ቅዱሳንን ይሰጋል? የሚለው ግልጽ ይሆንለታል፡፡ በ1963ዓ.ም እንደተመሰረተ የሚነገርለት ማገብት (ማህበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) የተመሰረተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ነበር፡፡ የማህበሩ ተልእኮም የተለያዩ የበጐ አድራጐት ስራዎችን በክረምት ወደ ትግራይ በመሄድ ማከናወን የሚል ነበር፡፡ በሂደት ሙሉ በሙሉ ወደ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በመቀየር ለተሐህት/ህወሓት መመስረት መሰረት ሆነ፡፡ ስለዚህ ማህበረ ቅዱሳን የኔ ስራ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው ሲል ይቺን የራሳቸውን ታሪክ በተሞክሮ የሚያውቁ ኢህአዴጋውያን እንዴት ይመኑት፡፡ ሌባ እናት ልጇን አታምንም እንዲሉ፡፡

አሁን ግን 1960ዎቹ ውስጥ አይደለንም፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ የመጠላለፍ ፖለቲካ አይገባውም፡፡ እርስ በእርሱ ቢኮራረፍና ቢጣላ እንኳ በለቅሶና በእውነተኛ ይቅርታ የሚያምን እንጂ በሸፍጥ ወንድሙን ለማራድ የሚያደባ አይደለም፡፡ ታሪክ ተቀይሯል፡፡ ባልተረጋገጠ መረጃ ማህበሩን ያለግብሩ ስም በመስጠት አለቆቻቸውን ያስደሰቱ መስሏቸው ለመወንጀል ማኮብኮባቸው ብዙ ሺህ የማህበሩ አባላትና አገልግሎቱን የሚያውቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኦርቶዶክሳውያንን የሚያስቆጣ ነው፡፡  

እንግዲህ እግዚአብሔር በጌዴዎን ላይ አድሮ ያደረገው ታላቅ ታዓምር ለእኛም ምሳሌ ሊሆነን ይገባል፡፡ በዋናነት በጌዴዎን ታሪክ ልንማር የሚገባን ሀይል የእግዚአብሔር እንጂ የነገስታቱ እና የወታደሮቹ አለመሆኑን ነው፡፡ መፍራትም የለብን፡፡ መፍራት ካለብን እግዚአብሔርን እንጂ ጉልበተኞችን አይደለም፡፡ ገዥዎችንም ማክበር እንጂ መፍራት እንዳለብን  ቅዱስ መጽሐፍ ላይ አልተጠቀሰም፡፡  የትኛውንም ኢፍትሃዊ እና አግባብ ያልሆኑ ነገሮች ለመቃወምም ሆነ ላለመቀበል ፈሪዎች መሆን የለብንም፡፡ በሀገሪቷ ላይ ህግ ሊሰራ የሚችለው ከላይ ያለው ባለስልጣኑም ከታች ያለው የሀገሪቷ ዜጋ እኩል ሲመለከቱት እና ሲተገብሩት እንጂ አንዱ ወገን እየናደው አይደለም:: ዛሬ በማን አለብኝነት የምንሰራው ስራ የምንናገረው ነገር ነገ ልንጠየቅበት የምንችልበት መሆኑን መገንዘብ ያሻናል::

በአሁኑ ወቅት ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችነን በእግዚአብሔር ኃይል ልንፈታቸው እንችላለን፡፡ የግድ ቁጥራችን እልፍ አላፍት መሆን አይኖርበትም፡፡ የግድም ሚሊዮኖች በተርታ መሰለፍም አይጠበቅብንም ‹‹..ከአንተ ጋር ያለው ህዝብ በዝቶአል፡፡ ስለዚህ እስራኤል እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም..››መጽሐፈ መሳፍንት ም.1፡፡ ያለውን ቃል ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ብዛትን እነደ ትልቅ ነገር አድርገን እናየዋለን፡፡ ይሄ ግን ስህተት ነው፡፡እውነታው በሃይል ሳይሆን በእግዚአብሔር መመካት ነው፡፡ ህግ ሲጣስ፣ ጎጠኝነት ሲንሰራፋ፣ ጭቆና ሲበረታ አንድም ሰው ቢሆን ..ይሄ ህገ ወጥነት ነው.. ብሎ መቃወም አለበት፡፡ የግድ ሺዎች አብረውት እስኪሰለፉለት መጠበቅ አይኖርበትም፡፡ እምነት እንጂ ቁጥር በእግዚአብሔር ዘንድ ቦታ የለውም፡፡ እንሆም ይህንን አይነት ጠንካራ እምነት ይኖረን ዘንድ እግዛአብሄር አምላክ ይርዳን፡፡ አሜን ይርዳን፡፡

1 comment:

 1. እግዚአብሄር ሆይ እምነት ጨምርልን፣

  ReplyDelete