Sunday, September 25, 2011

የሀዋሳ ደ/ም/ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አዲስ ሰበካ ጉባኤ ተመረጠለት

  •   በምርጫው ሥነ ሥርዓት ከ1100 በላይ ምዕመናን ተገኝተዋል፡፡

  • እነ ያሬድ አደመ አመጽ ለማስነሳት ስላልቻሉ ከገዳሙ ሰ/ት/በት በሕገ ወጥ መንገድ የዘረፉትን ንዋያተ ማኅሌት ይዘው የግብር አጋሮቻቸው ወደ ሚገኙበት ማረሚያ ቤት አቅንተዋል፡፡
  •  የሰጣችሁንን አደራ ያለ ማንም ተጽእኖ እና ጣልቃ ገብነት በንጹሕ መንፈስ ማከናወናችንን እንገልጻለን ….. የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት
  • ተስፋዬ መቆያ በክብረ መንግስት ህገ ወጥ ጉባዔ እያካሄደ ነው፡፡

በተሃድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች በተፈጠረ አመጽ ለበርካታ ወራት ያለ መደበኛ ሰበካ ጉባኤ የቆየው የሀዋሳ ደ/ም/ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በምዕመናን ከፍተኛ ተሳትፎ በዛሬው ዕለት አዲስ ሰበካ ጉባኤ ተመርጦለታል፡፡

መነሻውን ከዛሬ 15 ወራት በፊት ከሰኔ 11-13/ 2002 ዓ/ም በተስፋ ኪዳነ ምህረት ፀረ- ኤችኤይ ቪ/ኤዲስ ማህበር (በቤተ ክርስቲያን እውቅና የሌለው በደቡብ ክልል ኤች አይ ቪ ኤድስ መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በተሰጠው ፈቃድ የሚንቀሳቀስ) ለ3ቱ ሃይማኖት ተከታዮች (ለኦርቶዶክስ ፣ ለፕሮቴስታንትና ሙስሊም) አዘጋጀሁት ባለው”ጉባኤ” በተፈጠረው አለመግባባት የተነሳ የሀዋሳ ምዕመናን ጉዳይ የመጨረሻ እልባት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡


ከላይ የተጠቀሰውን “ጉባኤ” በመቃወም አካሄዱ የተሳሳተ ነው፣ የቅዱስ ሲኖዶስንም መመሪያ የጣሰ ነው፣ ተሰፋ ኪዳነ ምህረት ፀረ- ኤች ኤይ ቪ/ኤዲስ ማህበር በቤተ-ክርስቲያን እውቅና የሌለው በመሆኑ እና መንፈሳዊ ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት ውጭ ማካሄዱ ትውፊትን የሚጻረር በመሆኑ ሊፈቀድ አይገባም ሲሉ የሐዋሳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ፣ ምእመናን፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ጉባኤውን እንዲያስቆሙ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ፀሐይ መልአኩን በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መልስ በማጣታቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አቤቱታ ቀርቦ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጉባኤውን ማገዱ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎ የተሐድሶው ቡድኑ ከወ/ሮ እጅጋየሁ እና ከአባ ጳውሎስ ጋር ያለውን የዓላማ እና የጥቅም ትስስር በመጠቀም በወሰደው ደጋግ ምዕመናን የማሳደድ እርምጃ በርካታ አሉታዊ ውጤቶችን አስከትሏል፡፡ ከነዚህ መካከል የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

1ኛ. ምእመናንና ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ የነበሩት የሀዋሳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ አባ ገ/ዋህድ ከሓላፊነታቸው ተነሱ፡፡


2ኛ. የሐዋሳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤ አባላት በግፍ ተበተኑ፡፡

3ኛ. የሐዋሳ ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሰንበት ትምህርት ቤት ስራ አመራር ተወግዶ በጋሻው ደሳለኝ እና ግብር አበሮቹ የራሳቸውን ተላላኪዎች አስቀመጡበት፡፡

4ኛ. ሰላማዊ ምእመናን ሁከት ፈጣሪ ተብለው ተከሰሱ፡፡

5ኛ. ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ ምእመናን እና ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የስም ማጥፋትና የማሸማቀቅ ሰፊ ዘመቻ ተካሄደ፡፡

6ኛ. ምእመናን ተደበደቡ፡፡

7ኛ. እጅግ ፀያፍና አስነዋሪ ድርጊቶች በቅጽረ ቤተክረስቲያን ተከናወኑ፣ ገንዘብ ተመዘበረ፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ እንደ ጌታቸው ዶኒ ያሉትን አሸባሪዎች የቤተክርስቲያንን መዋቅራዊ አሰራር በመናድ ጭምር በመሾም ችግሩን በማባባስ ቅዱስ ፓትርያርኩ የተጫወቱት አፍራሽ ሚና በቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ የማይረሳ ነበር፡፡

ከብዙ ጥረት በኋላ ግን የግንቦት 2003 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ሽብር ፈጣሪዎች ላይ እርምጃ ከወሰደ በኋላ ቅን የቤተክርስቲያን ልጆች ሀገረ ስብከቱን በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡የሀዋሳ ደ/ም/ ቅዱስ ገብርኤል ገዳምን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በአዲስ መልክ ማቋቋም የዚሁ ሥራ አካል ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በ07/01/04 ዓ.ም የተዋቀረው አስመራጭ ኮሚቴ ዛሬ ጠዋት ከቅዳሴ በኋላ እጩዎችን በማቅረብ የመጨረሻዎቹን የሰበካ ጉባኤ አባላት አስመርጧል፡፡

የተመረጡት ተወካዮች እና ያገኙት ድምጽ

1ኛ. አባ ሠርፀወልድ ገ/ኢየሱስ 633 ድምጽ

2ኛ. ዲ/ን ምትኩ ምንሾ 525 ድምጽ

3ኛ. መ/ር ሄኖክ ፈንቴ 520 ድምጽ

4ኛ. መሪጌታ አክሊሉ ዓይናለም 518 ድምጽ

5ኛ. ወ/ሮ አስቴር ሰይፉ 719 ድምጽ

6ኛ. አቶ በላቸው ታደሰ 513 ድምጽ

7ኛ. አቶ ስዩም ጌታሁን 474 ድምጽ ሲሆን


የሰንበት ት/ቤት ተወካይ ህጋዊ የሰንበት ት/ቤት አመራር ሲመሰረት እንደሚመረጥ በምርጫ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡


በዚሁ ወቅት የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ‹‹ ሰላማችን ቢደፈርስም ለብዙ ጊዜ ሲጠበቅ ለነበረው ዕለት ስላደረሰን አግዚአብሔርን እናመሰግናለን፤ የረዳን እግዚአብሔር ነው የሰጣችሁንን አደራ ያለ ማንም ተጽዕኖ እና ጣልቃ ገብነት በንጹሕ መንፈስ ማከናወናችንን እንገልጻለን ›› በማለት እግዚአብሔርን አመስግነው የተጣለባቸውን መንፈሳዊ አደራ በብቃት መወጣታቸውን ለሕዝበ ክርስቲያኑ አሳውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ምዕመናን እግዚአብሔር ላደረገላቸው በጎ ነገር በእልልታ እና በልቅሶ ” ንሴብሆ ለእግዚአብሔር” ብለው ዘምረዋል፡፡

ይሄ በጎ ሥራ ያላስደሰታቸው እና ጥቁር ጨርቅ በመያዝ የአመጽ ሰልፍ ለማድረግ እየተዘጋጁ የነበሩት እነ ያሬድ አደመ በወቅቱ በሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ በዓል ምክንያት በጸጥታ ኃይሎች ማስጠንቀቂያ በመሰጠቱ ጥረታቸው መምከኑን በመረዳት ከደብሩ ሰ/ት/ቤት የዘረፉትን አልባሳት እና ከበሮ በመያዝ የግብር አጋሮቻቸው ወደ ሚገኙበት ማረሚያ ቤት በማምራት ሲጨፍሩ ውለዋል፡፡ ቤት በመከራየት ‹‹የገብርኤል ተገንጣይ ኦርቶዶክሳዊያን›› የሚባል የእምነት ተቋም ለመክፈት የፕሮቴስታንት ድርጅት እያስተባበራቸው መሆኑም ታዉቃል፡፡

በተያያዘ ዜና የተሐድሶው ቡድን በሀዋሳ በዚህ መለኩ በመመታቱ የተበሳጨው ተስፋዬ መቆያ ያለ ሀረገ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ በክብረ መንግስት ከተማ ጉባኤ በማካሄድ ላይ መሆኑን ከቦረና ሀገረ ስብከት የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ተስፋዬ መቆያ ለረጅም ጊዜ የተሐድሶ ሥራውን ለማደራጀት በሰሜን አሜሪካ የቆየ ሲሆን እዛው እያለ በስልክ በርካታ የአመጽ ትዕዛዛትን ሲያስተላልፍ እንደነበረ የሚታወቅ ነው፡፡
እነዚሁ አጉራ ዘለል ሰባኪያን (በጋሻው ደሳለኝ ተስፋዬ መቆያ ትዝታው ሳሙኤል በሪሁን ወንደሰን) ከ12-14/01/04 ዓ.ም ያዘጋጁትን ጉባዔ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ቢያግዱትም በህገ ወጥ መንገድ ቀጥሏል፡፡የአከባቢው ጸጥታ ኃይሎች ድርጊቱን እንዲያስቆሙ ቢጠየቁም “ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋል እርምጃ እንወስዳለን” በማለት የእንቅስቃሴው ደጋፊዎች መሆናቸውን በድርጊት በመግለጻቸው ትዝብት ውስጥ ወድቀዋል፡፡ከዚህ በፊት በጋሻው ለተመሳሳይ ዓለማ ወደ ሜጋ ከተማ ተንቀሳቅሶ ለግማሽ ቀን በእስር ከቆየ በኋላ ምንም ነገር ሳይተነፍስ ከተማውን ለቆ እንዲወጣ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን!!!!!

Posted on September 25, 2011 by ገብር ኄር
ማቴዎስ አጥምዛ (gebrher33@gmail.com)

1 comment:

  1. ere mindinew betekristiyan lay yemideregew ere tilk tselot yasfelgal egziabher betekirstiyanin yitebikiln yetemeretutm bemenfes kidus mirit endiseru egziabher yirdaln amen

    ReplyDelete