Friday, September 2, 2011

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እና ፊሊጶስ



  • የፊልጶስ ጥያቄ እና የጃንደረባው መልስን በሚገባ ማስተዋል ያስፈልጋል፡
  • እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ሲጀመርም ለአገልጋዮችም ሆነ ለምእመናኑ አርአያ ሊሆኑ አልቻሉም
  • ስለአንዳንድ ሰባኪያኖች ግን ከፈጣሪ መንገድ ይልቅ አለማዊ (አጋንታዊ) መንገድን እየተከተሉ ነው
  • የሚደረገው ክርክር መሰል ምልልስ የእየራሳቸውን እምነት ተከታዮች ከማደናገሩም ባሻገር እናገለግለዋለን የሚሉትን ፈጣሪያቸውን ጭምር የሚያሳዝን እየሆነ ነው
  • ማንም ሰው ወደ አምልኮ ስፍራዎች የሚሄደው እንደ ጃንደረባው ተደስቶ ለመመለስ እንጂ ልቡ ተሰብሮ ለመመለስ አይደለም
  • የሁሉም እምነት ተከታይ የፊልጶስን አይነት ሰባኪን (አስተማሪን) እንጂ እርስ በእርሱ የማይከባበር እና የሚሰዳደብ ሰባኪን አይፈልግም
  • የተጠቀሱት ሃይማኖት መሪዎች በሙሉ ከእግዚአብሔር ይልቅ ቄሳርን የሚያገለግሉ እና የሚፈሩ ናቸው፡የእረኝነት ተልእኮአቸውን ከመውጣት ይልቅ የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ አስፈፃሚ በመሆን ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ናቸው
  • አንዱ አንዱን ለማውገዝ ካሴት እስከማውጣት እና መጽሐፍ እስከማሳተምም ደርሰዋል
  • ሀገሪቱ የሚያምነውም የማያምነውም መሆኗን በቅድሚያ መገንዘብ ያስፈልጋል




..የጌታም መልአክ ፊልጶስን፡- ተነስተህ በደቡብ በኩል ከእየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው፡፡ ተነስቶም ሄደ፡፡ እነሆም ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግስት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳለም መጥቶ ነበር ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነብዩን የኢሳያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፡፡ መንፈስም ፊሊጶስን፡- ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፡፡ ፊልጶስም ሮጦ የነብዩን የኢሳያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው፡፡ እርሱም፡- የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው፡፡ ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፡፡ ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፡-

እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ ህይወቱ ከምድር ተወግዳለችና፤ ትውልዱንስ ማን ይናገራል?

ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ፡- እባክህ ነብዩ ይህን ስለማን ይናገራል? ስለራሱ ነውን ወይስ ስለሌላ? አለው፡፡ ፊልጶስም አፉን ከፈተ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፡፡ በመንገድም ሲሄዱወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም፡- እንሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው፡፡ ፊልጶስም፡- በፍፁም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል አለው፡፡ መልሶም፡- ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ፡፡ ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፤ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረደ፤ አጠመቀውም፡፡ ከውሃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና ፊልጶስ ግን በአዘጠን ተገኘ፤ ወደ ቂሳርያም እስከመጣ ድረስ እየዞረ በከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር፡፡.. የሐዋርያት ስራ ም.8 ቁ.26-40

እነሆ የሐዋሪያት ስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያው ጃንደረባ እና የፊልጶስ ግንኙነት ዛሬ በሀገራችን በተለይም በእምነት ተቋማት ዘንድ ላለው አሳዛኝ ችግር አስተማሪ ይሆናል በሚል ነው የዛሬው የፁህፌ ይዘት በዚህ ላይ ያደረኩት፡፡

እንደሚታወቀው በሀገራችን በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታይ ያላቸው የክርስትና እና የእስልምና እምነቶች አሉ፡፡ በክርስትና ውስጥ የኦርቶዶክስ ክርስትና እና የፕሮቴስታንት ክርስትና እምነት ተከታዮች ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን በእነዚህ እምነት ጥላ ስር የሚገኙ የተወሰኑ ሰባኪያኖች በአሁኑ ወቅት ማንን እያገለገሉ እንደሚገኙ የገባቸው አይመስልም፡፡ ከጥቂት የእግዚአብሔር አገልጋዮች በስተቀር ሌላው ወይ ቄሳርን፣ ወይ ገንዘብና ዝናን ወይ ዲያብሎስን አሊያም ደግሞ ሶስቱንም በአንድነት እያገለገሉ ያለ ይመስለኛል፡፡ የዚህ አይነቱ ግብር እንኳን በመንፈሳውያን ቀርቶ በአለማውያንም ቢሆን ፀያፍ ነው፡፡

የክርስትናም ሆነ የእስልምና እምነት መጽሐፍ እና ትእዛዛት እንኳን ሰባኪያኖች ምእመናኖችም ቢሆኑ ለሌሎች አርአያ እንጂ መሰናከያ እንዳይሆኑ በጥብቅ ያስተምራል፡፡ ይሄ በሁለቱም ያለ እውነት ሆኖ ስለአንዳንድ ሰባኪያኖች ግን ከፈጣሪ መንገድ ይልቅ አለማዊ (አጋንታዊ) መንገድን እየተከተሉ ነው፡፡ ይሄ ድርጊታቸውም በአሁኑ ወቅት ብዙ ምዕመናንን ከቤተ አምልኮ ስፍራዎች እያሸሸ እንደሆነ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡

በአንዳንድ የኦርቶዶክስ የእስልምና ሰባኪያኖች፤ በአንዳንድ የፕሮቴስታንት ሰባኪያኖች እና በአንዳንድ የኦርቶዶስክ ሰባኪያኖች፤ በአንዳንድ የእስልምና እና የፕሮቴስታንት ሰባኪያኖች መካከል የሚደረገው ክርክር መሰል ምልልስ የእየራሳቸውን እምነት ተከታዮች ከማደናገሩም ባሻገር እናገለግለዋለን የሚሉትን ፈጣሪያቸውን ጭምር የሚያሳዝን እየሆነ ነው፡፡ ይሄ ለሃገርም ቢሆን የሚጎዳ ነው፡፡ ሀገሪቱ የሚያምነውም የማያምነውም መሆኗን በቅድሚያ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ስላሴ እንዳሉት ሀገር የጋራ ነው፤ ሃይማኖት የግል ነውና፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ በተመሳሳይ እመነት ውስጥ ያሉ ሰባኪያኖች እርስ በእርሳቸው በአለማዊ ሚዲያ ሳይቀር መወነጃጀላቸው ነው፡፡ የእነዚህ ሰባኪያን ድርጊት ለአለም መማሪያ እና መዳኛ ከመሆን ይልቅ መዘባበቻ ከሆነም ውሎ አድሮአል፡፡ አንዱ አንዱን ለማውገዝ ካሴት እስከማውጣት እና መጽሐፍ እስከማሳተምም ደርሰዋል፡፡ በእርግጥ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ የተሳሳቱት ሰባኪያኖች ብቻ አይደሉም፡፡ እንዲያውም የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የየእምነቶቹ የበላይ አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ሲጀመርም ለአገልጋዮችም ሆነ ለምእመናኑ አርአያ ሊሆኑ አልቻሉምና ነው፡፡ የተጠቀሱት ሃይማኖት መሪዎች በሙሉ ከእግዚአብሔር ይልቅ ቄሳርን የሚያገለግሉ እና የሚፈሩ ናቸው፡ የእረኝነት ተልእኮአቸውን ከመውጣት ይልቅ የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ አስፈፃሚ በመሆን ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጽሐፍቶችን ከመስበክ ይልቅ የመንግስትን የትራንስፎርሜሽን እቅድ መስበክ የሚቀናቸው ነው፡፡ እናም ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ... በሚልም ሰባኪያኖም እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ ቄሳርን፣ ገንዘብን፣ ዝናን፣ ሰይጣንን... ማገልገልን እንደ አማራጭ ውሰዱ፡፡

ከላይ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እና የሐዋርያው ፊልጶስ ግንኙነት ሁሉም ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ጊዜ የነቢዩን ኢሳያስ የትንቢት መጽሐፍ ሲያነብ ሳለ፤ ፊልጶስ በጌታ መንፈስ ተገፍቶ ወደ ጃንደረባው በመጠጋት ..በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?.. ሲል ጠየቀው፡፡ ጃንደረባውም ..የሚመራኝ ሳይኖር ይሄ እንደት ይቻለኛል?.. ብሎ ሲመልስለት ፊልጶስ ያደረገው ነገር ቢኖር ጃንደረባው ተሳፍሮበት ወደነበረው ሰረገላ በመግባት ሀዋርያዊ ተልእኮውን መወጣት ነው፡፡ አዎ.. የፊልጶስ ጥያቄ እና የጃንደረባው መልስን በሚገባ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ካስተዋልነው በኋላ ደግሞ ልናመርበት ግድ ይለናል፡፡

እነሆም እናንተ በአለማዊ እና በግል ጉዳይ ተጠምዳችሁ ያላችሁ ሰባኪያን ሆይ፡- መንፈሳዊ ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባችኋል፡፡ ከቶስ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁራን ያለ አስተማሪ ለእኛ እንዴት ሊገለጥልን ይችላል? እናንተ ካላስተማራችሁን እንደ ፊልጶስ ካልተረተራችሁልን ቅዱስ ቃሉን እንዴት ልናስተውለው እንችላለን?

ሌላው በጣም አሳዛኝ ጉዳይ የፈጣሪን መንገድ እሰብካለው የሚል ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላደረበት ካልሆነ የሚያቃልለው እራሱን ብቻ ሳይሆን ፈጣሪውንም ጭምር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሊሰብክ የተዘጋጀው ያልገባውን እውነት እንደሆነም ያሳብቅበታል፡፡ እርስ በእርስ የሚሰዳደብ የፈጣሪ አገልጋይም በየትም ቦታ የለም፡፡ በመንፈሳዊያን ዘንድ ልክ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እዛና እዚህ ሆኖ መወነጃጀል ምእመናንን ማሰናከል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ ..የሰውን ልጅን ከምታሰናክል የወፍጮ ድንጋይ በአንገት ታስሮ ወደ ባህር ብትወረወር ይሻልሃል.. ይላል፡፡ ይሄ እውነት ያልገባው ሰባኪ ምን ሊሰብክ ወደ አውደምህረቱ እንደሚወጣ ማሰቡ በራሱ ይከብዳል፡፡ የሁሉም እምነት ተከታይ የፊልጶስን አይነት ሰባኪን (አስተማሪን) እንጂ እርስ በእርሱ የማይከባበር እና የሚሰዳደብ ሰባኪን አይፈልግም፡፡ ወደ ፈጣሪው መንገድ የሚመራውን እንጂ ወደ ጥላቻ የሚነዳውን ሰባኪ አይፈልግም፡፡ ማንም ሰው ወደ አምልኮ ስፍራዎች የሚሄደው እንደ ጃንደረባው ተደስቶ ለመመለስ እንጂ ልቡ ተሰብሮ ለመመለስ አይደለም፡፡ ይበልጥ የፈጣሪውን መንገድ አውቆና ገብቶት ይመለስ ዘንድ ነው ወደ ቤተ አምልኮ ስፍራዎች የሚሄደው፡፡ የፈጣሪ አገልጋይ ነን፤ የእውነት መንገድ ሰባኪነን እስከአላቸው ድረስ በድርጊታቸውም ፈጣሪያቸውን መምሰል እንደሚጠበቅባቸው ማስተዋሉ አስፈላጊ ነው፡፡ አሊያ ሁሉም ነገር ግብዝነት ይሆንና ከጊዜ በኋላም የሚያደምጣቸው አንድስ እንኳ አታገኙም ሌላው ቀርቶ የማይኖሩትን ህይወት መስበኩስ ቢሆን እንዴት አድርጎ ነው ሰሚን ሊለውጥ የሚችለው?

የሆነ ሆኖ የየትኛውም እምነት ሰባኪ በድፍረት ለመስበክ ከመሞከሩ በፊት እራሱን መለወጥ መቻል አለበት፡፡ ..እኔን ምሰሉ.. የሚለውን የፈጣሪውን ቃልም ሊተገብረው ይገባል፡፡ ይሄ ከሆነ በኋላ ነው ሌሎችን ለመለወጥ ሌሎችን ለማሳመን መ..ድ ያለበት፡፡ እነሆም እግዚአብሔር አምላክ ለእንዲህ አይነቶቹ ሰባኪያኖች ራሳቸውን ለመለወጥ የሚያስችል ልቦና ይስጣቸው፡፡ አሜን ይስጠን፡፡

2 comments:

  1. አስፈሪውን ጊዜ እንዴት እንዋጀው ብለው እረኞቹ እንደ ፀሐፊው ቢያስቡበት ምንአለ? እስቲ ሁላችንም ሱባዔ እንያዝ ቀን ወስናችሁ መልዕክት አስተላልፉልን፡፡ በመስካየ ህዙናን እነ ጋሽ ታዬ እነ ጋሽ ላቀው ምነው ጨከናችሁ? መልዕክታችሁ በያለንበት እንዲደርሰን በታላቅ ጩኸት እንጠራችኋለን፡፡ የሱባዔ ቀን ስጡን እባካችሁ እባካችሁሁሁ!!!!

    ReplyDelete
  2. አስፈሪውን ጊዜ እንዴት እንዋጀው ብለው እረኞቹ እንደ ፀሐፊው ቢያስቡበት ምንአለ? እስቲ ሁላችንም ሱባዔ እንያዝ ቀን ወስናችሁ መልዕክት አስተላልፉልን፡፡ በመስካየ ህዙናን እነ ጋሽ ታዬ እነ ጋሽ ላቀው ምነው ጨከናችሁ? መልዕክታችሁ በያለንበት እንዲደርሰን በታላቅ ጩኸት እንጠራችኋለን፡፡ የሱባዔ ቀን ስጡን እባካችሁ እባካችሁሁሁ!!!!

    ReplyDelete