Sunday, September 25, 2011

አባ ሰረቀ፤በመስቀል-ደመራ በዓል አከባበር ላይ በአደባባዩ እንዳይገኙ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

  • “እኔ ችግር [የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ] ካለብኝ ከመምሪያ ሓላፊነቴ መነሣት ብቻ ሳይሆን ከቤተ ክርስቲያንም ልወገድ ይገባኛል፤”/አባ ሰረቀ ለመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ አስተዳደር ጉባኤ፣ ለበዓል አከባበር ዐቢይ ኮሚቴ፣ ለሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ እና ለጸጥታ ኀይል የጋራ ስብሰባ ከተናገሩት/::
  • ውሳኔው  ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነንና ሕገ ወጦቹን እነ ጌታቸው ዶኒን፣ በጋሻው ደሳለኝን፣ አሰግድ ሣህሉን፣ ግርማንና የመሳሰሉትን እንደሚያካትት ተገልጧል፡ 
  • ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣‹ ‹‹ወጣቱ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚያስጠብቅ ነውበአካል ወጣቱን አይቻለሁ፤ ጥሩ ዝግጅት ላይ ነው ያለው ››
(ደጀ ሰላም፤ መስከረም 14/2004 ዓ.ም፤ ሰፕቴምበር 25/2011)፦ በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም በመላው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች፣ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ደሴ ከተማ የ12 አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ የተቃውሞ መግለጫ የወጣባቸው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል መስከረም 16 ቀን 2004 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በሚከናወነው የመስቀል-ደመራ በዓል አከባበር ላይ እንዳይገኙ ውሳኔ ተላለፈባቸው፤

 
ውሳኔው በክብረ በዓሉ ወቅት “ሐውልቱ እስከ መቼ?” በሚል ርእስ ያሳተሙትንና በመኖሪያ ቤታቸው ያከማቹትን ‹መጽሐፍ› ለማሰራጨት ተዘጋጅተዋል የተባሉትን ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነንና ሕገ ወጦቹን እነ ጌታቸው ዶኒን፣ በጋሻው ደሳለኝን፣ አሰግድ ሣህሉን፣ ግርማንና የመሳሰሉትን እንደሚያካትት ተገልጧል፡፡ ውሳኔው የተላለፈው መስከረም 11 እና 12 ቀን 2004 ዓ.ም የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የበዓል አከባበር ዐቢይ ኮሚቴ ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ አስተዳደር ጉባኤ፣  አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት እንዲሁም ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር አባላት እና ፖሊስ ጋራ ባካሄደው የምክክር ስብሰባ ላይ ነው፡፡
ክብረ በዓሉ በወጣለት መርሐ ግብር መሠረት ሰዓቱን ጠብቆ በጊዜ እንዲፈጸም በምክክር ስብሰባው ላይ በአጽንዖት የተመለከተ ሲሆን በመድረኩ እና በአካባቢው ልዩ ልዩ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ አካላት ብቻ ስማቸውንና የተግባር ድርሻቸውን የሚገልጽ ባጅ እንዲዘጋጅላቸው ታዝዟል፡፡ ከቤተ ክርስቲያናችን ዐበይት በዓላት መካከል ከፍተኛ የቱሪስቶች ቁጥር የሚታይበት እና ሰፊ የብዙኀን መገናኛ ሽፋን የሚሰጠው የመስቀል-ደመራ ሥነ በዓል የመስቀሉን ብርሃን ለዓለም የምንሰብክበት እና የሃይማኖታችንን ጥንታዊነት የምንመሰክርበት በአጠቃላይ የአገራችንን መልካም ገጽታ የምንገነባበት እንደሆነ ዐውደ ትርኢቱን በሚያቀርቡት ወጣቶች ዘንድ ግንዛቤው እንዳለ በስብሰባው ተሳታፊዎች ተገልጧል፡፡
ለዐውደ ትርኢቱ ልምምድ በሚደረግባቸው አምስት ማእከላት ተዘዋውረው መመልከታቸውን የተናገሩት የአዲስ አበባ እና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ-ሰላሌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ “ወጣቱ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚያስጠብቅ ነው፤ በአካል ወጣቱን አይቻለሁ፤ ጥሩ ዝግጅት ላይ ነው ያለው፤ ቁጥራችን እንዳይበዛ የሚያደርጉት በቀድሞው ሥርዐት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳንሄድ ይከለክሉን ከነበሩት ሰዎች ጋራ እንደምራቸዋለን፤” ብለዋል፡፡ ከብፁዕነታቸው ጋራ ወጣቶቹን ተዘዋውረው የጎበኙት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴም “በእምነት ጉዳይ ማንም አያዝዘኝም፤ ወጣቱ በርታ፤” በማለት የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ከየአጥቢያቸው ለሚላኩ ወጣቶች የቀን አበላቸውን/በሰው-ቀን ብር ዐሥር/ ከመሸፈን ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው አሳስበዋል፡፡
“የመስቀል ጥናት” ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ተወስዶ የሚካሄድ ቢሆንም ወጣቶቹ በበዓሉ ዕለት የድካማቸውን ፍሬ በሚያሳዩበት አደባባይ ላይ ዐውደ ትርኢታቸውን በሚገባ ሳያቀርቡ ከአደባባዩ እንዲወጡ መዋከባቸው ቅር ያሰኛቸው አጥቢያ አስተዳደሮች ለጥናቱ ወጪ እንዳይመድቡ አድርጓቸዋል፡፡ በዘንድሮው በዓል እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ለሚያቀርበው ዐውደ ትርኢት ተገቢ የመከወኛ ጊዜ /ሰዓት/ እንዲሰጠው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ ይህም ሆኖ በበዓሉ አከባበር ወቅት ተቃውሞ ከቀረበባቸው ግለሰቦች አንዳቸውም በመድረኩ እና በአካባቢው ከተገኙ ወጣቶቹ አደባባዩን ለቅቀው ሊወጡ እንደሚችሉ በአንድነት አመራሮቻቸው ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና ለበዓል አከባበር ዐቢይ ኮሚቴው በማስታወቃቸው የተጠቀሱት ግለሰቦች በአደባባዩ እንዳይገኙ ተወስኗል፡፡
በትንቱ የጋራ ስብሰባ በውሳኔው ከልክ ያለፈ ማዘናቸውን የገለጹት አባ ሰረቀ፣ እኔ ችግር [የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ] ካለብኝ ከመምሪያ ሓላፊነቴ መነሣት ብቻ ሳይሆን ከቤተ ክርስቲያንም ልወገድ ይገባኛል፤” በማለት በተለይም ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ የአስተዳደር መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ጥበብ በእምነት ጋራ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል፡፡ የሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራር በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም ባወጡት የጋራ መግለጫ እና እርሱን ተከትሎ በተለይም በአባ ሰረቀ፣ በአጥማቂ ግርማ፣ በሕገ ወጥ ሰባክያኑ በጋሻው እና አሰግድ ላይ አጠናቅረው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዲሁም ለቋሚ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ባስረከቡት ማስረጃ ጉዳይ ላይ ከመስቀል-ደመራው በዓል አከባበር በኋላ የተደረሰበት ውሳኔ እንደሚገለጽላቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የዋና ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት አማካይነት ተገልጦላቸዋል፡፡
የጋራ ስብሰባው ስምምነት እና ውሳኔ በአስተዳደር መምሪያው ሓላፊ የተገለጸላቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከፍተኛ ቅሬታ ቢያድርባቸውም እንደተቀበሉት ተዘግቧል፡፡ ይሁንና መስከረም ዘጠኝ ቀን 2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ የሰንበት ት/ቤቶች ተጠሪዎች እና የክፍለ ከተማ አመራር ተወካዮች በተገኙበት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በተደረገ ውይይት፣ “. . .ከቤተ ክርስቲያን የሚያባርረው ከዚህ በፊት የነበረው ዘመን ነው፤ ማንም ማንንም ችግር አለበት ብሎ መናገር አይችልም፤ ብትሰሙኝ ቀደም ብዬ መምሪያ [ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን በሚመለከት] ልኬ ነበር፤” በማለታቸው ፓትርያርኩ በውሳኔው ላይ ያላቸውን አቋም በመቀየር ጉዳዩ ቀጣይ የውዝግብ ምንጭ ሳይሆን እንደማይቀር ተሰግቷል፡፡ ምናልባትም ከዚህ ጋራ በተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ በተገመተ ምክንያት የሰንበት ት/ቤቶች ክፍለ ከተማ አንድነት አመራር አባላት ትንት፣ መስከረም 14 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲቀርቡ ተጠርተው እንደነበር ተነግሯል፡፡
በመስቀል-ደመራ ክብረ በዓል የጋሞ ሕዝብ ወጣቶችን ጨምሮ በቁጥር ከ5000 ያላነሱ  የአምስት ክፍ ከተሞች ሰንበት ት/ቤት አባላት ዐውደ ትርኢት እና ዐውደ መዝሙር ያቀርባሉ፡፡ የዐውደ ትርኢቱ ዐቅድ እንደ ቀድሞው ከማደራጃ መምሪያው የተሰጠ ሳይሆን በየክፍለ ከተሞቹ የአንድነት አመራሮች የታቀደ ነው፤ ይህም በማደራጃ መምሪያው እና በሰንበት ት/ቤቶቹ መካከል የሥራ ግንኙነት ለመቋረጡ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ክፍለ ከተሞቹ ሐምሌ 24 ቀን 2003 ዓ.ም የጀመሩትን ቅድመ ዝግጅት በመቀጠል - የሰሜን ክፍለ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም፤ የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች በጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል፤ የምዕራብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፤ የምሥራቅ አዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች በደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች በጃቴ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ጥናታቸውን በማሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ 

No comments:

Post a Comment