Thursday, September 1, 2011

የዘመናችን የአርዮሳውያን ግብር



ኦልማን የተባለ የታሪክ ፀሃፊ በ379 በቁስጥንጥንያ የነበረውን የሃይማኖት ሁኔታ እንደሚከተለው ገልፆታል፡፡ 

ሃይማኖታዊ ጉዳይ እንደማንኛውም ተራ ወሬ ስራ መፍቻና የቀልድና የመዝናኛ ጉዳይ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ቲያትር ቤት ውስጥ የነበረው ሁኔታ ወደ ቤተክርስቲያን መጣ ፤ የቤተክርስቲያን ብቸኛ ሃብት ተደርጎ ይታይ የነበረው ጉዳይ ወደ ቲያትር ቤት አዳራሽ ተወሰደ ፤ በአንድ ወቅት የተሻለ ክርስቲያናዊ ትርጉም ይሰጠው የነበረና ወደ ቀልድ መድረኮች የማይመጣው የቤተክርስቲያን ምስጢር በአደባባይ የብዙወች መዘባበቻ ፣ ከንፈር መምጠጫ ሆነ፡፡ 


በቁስጥንጥንያ መንበር ላይ የተቀመጡት አርዮሳውያን መሪወች ይህ እንዲሆን የሚያበረታቱ ለሃይማኖትም ጉዳይ ደንታ ቢሶች ነበሩ፡፡ የቤተክርስቲያን የነበረውን ህዝብ ፣ ታላቅ ከበሬታ ይሰጠው የነበረውን ጉባኤ አቃለሉት ፤ ናቁት ፤ ነዋሪዋቹም እውነተኛ የነበረውን ነገር እርቃኑን አስቀሩት ፤ ቅዱስ የነበረው አለማዊ በሆኑ ሰዋች ከንፈር ተቃለለ ፤ ከዚህ ሁሉ በጣም የከፋው ፣ ሊቆጣጠሩት ያልቻሉት ቤተክርስቲያንን ማቃለልና መዘባበቻ ማድረግ ሰዋቹን ደስታ የሚሰጣቸው ነገር ሆነ ፤ ደስታ ብለው በቆጠሩት ነገር ላይ ጊዜያቸውን ማባከን ተያያዙት ፤ ቤተክርስቲያንን ወደ ቲያትር መድረክነት ፣ ሰባኪወቻቸውንም ወደ አክተርነት ለወጧቸው፡፡ ሕዝቡንም ከቤተክርስቲያን አውጥተው በአዳራሽ እንዲሰበሰብና የቀደመ ማንነቱን ቀስ በቀስ እንዲረሳ አደረጉት ፤ ተሳካላቸውም፡፡ 

ሰባኪው ሕዝቡን ያስደስታል ብሎ ካመነ እንደምርጫቸው እራሱን ለመለወጥ ችግር አልነበረበትም፡፡ እንደወደዱም አድርጎ ያዝናናቸዋል ፤ ያስቃቸዋል ፤ ደስታ ከተባለም እንዲሁ ያስደስታቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር የሚደረገው በቤተክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ለጆሯቸው ደስ የሚላቸውን ነገር እንጂ ከእግዚአብሄር የሆነው ነገር ይነገራል ተብሎ ፈፅሞ አይታሰብም፡፡ አቀራረቡም ቲያትር ቤት ውስጥ እንደሚያዩት ውዝዋዜና ዳንስ ነገርም የተቀላቀለበት አይነት ዝላይ የሚመስል አደገኛ ጨዋታ ነበር፡፡ኮሜድያኑ ወደ መድረክ አደባባይ እንደሚወጣ ሁሉ በቤተክርስቲያን አደባባይ ሲወጣ ፦ ልክ በቲያትር ቤቶቻቸው እንደለመዱት ቅልጥ ባለ ጭብጨባ ታጅቦ ነበር የሚወጣው ፤ ያሳዝናል ፤ የሰባኪወቹም ቁጥር ደግሞ በሕዝቡ ቁጥር ልክ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሰባኪወቹም ይህንን አድናቆት ነፍሳቸው ይወደው ነበር ፤ ወደ መድረክ ሲወጡ እንዲጨበጨብላቸው የራሳቸው ቲፎዞወች በየጉባኤው የተለያየ ቦታ ያስቀምጡ ነበር፡፡ የቤተክርስቲያን የአምልኮት መፈፀሚያ እቃወችም ነገስታቱና መኳንንቱ ከቅምጦቻቸው ጋር ይገለገሉባቸው ነበር፡፡ የተቀደሰውና ሰወቹን ሁሉ የሚመራው የእግዚአብሄር ቃል ና የወንጌል ህግ ተረስቶ ማንኛውም ሰው ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ከሚለምነው ለማኝ እስከ ንጉሱ ድረስ ለድህነት የሚጠቅመውን የሕይወት ኑሮ መኖር ሳይሆን ጥቅስ መወራወርን ኑሮየ ብለው የተያያዙበት ጊዜ ነበር፡፡በየጎዳናው ፣ በየገበያው ፣ በየበረንዳው ከሕፃኑ እስከ አዛውንቱ ከአብና ከወልድ ማን ይበልጣል የሚል ተግዳሮት ሲነጋገሩ መስማት የተለመደ ነበር፡፡ አርዮሳውያን የቁስጥንጥንያን ቤተክርስቲያን ከ325 – 379 ያወረሷት ሃብት ይሄ ነበር፡፡

ሰኔ 30/2003 ምንጭ ፦ አስራት ገብረ ማርያም ትምህርተ መለኮት 1983 /ገፅ፦ 65 – 115/


በእኛም ዘመን የተነሱብን እኝህን የመሰሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ለቤተክርስትያናችንና ስለ ተዋህዶ እምነታችን መልካም ነገር ሰርተን ማለፍ ቢያቅተን እንኳን ህጓን እና ስርዓቷን ጠብቀን እና አስጠብቀን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡ 

No comments:

Post a Comment