Monday, March 30, 2015

የአ/አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ሹመት ፓትርያርኩንና ረዳት ሊቀ ጳጳሱን እያወዛገበ ነው




  • ረዳት ሊቀ ጳጳሱ የፓትርያርኩን ምደባዎች በደብዳቤ ተቃውመዋል
  •   ቋሚ ሲኖዶሱ፤ጠቅ/ሥራ አስኪያጁ ያቀረቡትን አቤቱታ መመልከት ጀምሯል
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ ስኪያጅ መሾማቸውን ተከትሎ ከሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተገለጸ፡፡ኹለቱ ሥራ አስኪያጆች ለሀገረ ስብከቱ መመደባቸው የተገለጸው፣ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ ከፓትርያርኩ ልዩ /ቤት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በደብዳቤ በተሰጠ መመሪያ ነው፡፡የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እንደኾነና ከረዳት ሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ የሚመደቡ ሓላፊዎችን የመምረጥና የመመደብ ጉዳይ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ መያያዙን፣ በዚኽም መሠረት ሲሠራ እንደቆየ በመመሪያው የተጠቀሰ ሲኾን፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለኹለቱ ሥዩማን ሥራ አስኪያጆች ምደባቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲያደርሷቸውና ሥራቸውን እንዲጀምሩ ይደረግ ዘንድ ይጠይቃል፡፡

Saturday, March 14, 2015

በእንተ ዝቋላ


በቅርቡ ኢትዮጵያ ነክ ከኾኑና የተለያዩ መገናኛ ብዙኀንን ካጨናነቁ ዜናዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳምና የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ በገዳሙ ውስጥ ሊፈጽመው ያቀደውና በኢትዮጵያ ቴሌቭዢን ያስነገረው ማስታወቂያ ነው። ማስታወቂያው በአማርኛና በኦሮሚኛ ክፍለ ጊዜያት መነገሩም ጉዳዩ በግብታዊነት ወይም በጥቂት ሰዎችጠብ ጫሪነትየተፈጸመ ድርጊት ሳይኾን በዕቅድና በጥናት የተደረገ መኾኑን ያሳያል። ባይኾንማ ኖሮ ከፍተኛ የሳንሱር ሕግ አለው በሚባለው የኢትዮጵያ ቴሌቭዢን እንዲህ ዓይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊያስከትል የሚችል ርዕሰ ጉዳይ ባልቀረበ ነበር።

Monday, March 9, 2015

የእምነት ተቋማትንና የአምልኮ ቦታን የሚመለከት ሕግ ሊወጣ ነው


 * በግለሰብ ቤት አምልኮን መፈጸም አይፈቀድም፡

(አንድ አድርገን የካቲት 30 2007 ዓ.ም)፡- ባሰላፍናቸው ሃያ አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ በርካታ የእምነት ተቋማት የተቋቋሙበት ዓመታት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ወደ መንግስት ተጠሪ ቢሮ ያቀረበው(በጊዜው አቶ ጌታቸው እና ወ/ሮ ሮማን ገሥላሴ በተጠሪነት ሲያገለግሉት የነበረው )ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከአንድ ሺህ በላይ አዲስ እምነት ለማቋቋም ጥያቄዎች ለፌደራል ጉዳዮች እንደቀረቡ እና  ከነዚህ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት የእምት ተቋም ለማቋቋም የጠየቁ ቡድኖች ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ሊያሟሉ ይገባሉ ያላቸውን መስፈርቶች ማሟላት በመቻላቸው ፍቃድ እንደተሰጣቸው ያትታል፡፡

Sunday, March 8, 2015

በሐውልቱ ላይ ለሚደረጉ ማናቸውም ተግባራት ያገባናል!


(አንድ አድርገን የካቲት 29 2007 ዓ.ም)፡- የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ከመነሳቱ እንስቶ ያለው ሂደት በውዝግብ በጥያቄዎች የተሞሉ ነበሩ ፤ መንግሥት የባቡሩን ፕሮጀክት በሚቀርጽበት ጊዜ አማራጭ የባቡር መስመሮችን ሳይመለከት ቀጥታ ወደ ስራ ከገባ በኋላ የመጣ ክስተት በመሆኑ ብዙዎችን ሲያነታርክ ሲያነጋግር ሰንብቷል ፤ ሐውልቱ ከመነሳቱ እና ከተነሳ በኋላ ብዙ ጥያቄዎች መልስ ባያገኙም በማኅረሰቡ ዘንድ ሲጠየቅ  ነበር ፤ ሀውልቱ በሚነሳበት ወቅትም ረብሻ እና ብጥብጥ እንዳይነሳ በማለት በርካታ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊሶች ሐውልቱ በሚነሳበት ጊዜ ከፍተኛ ጥበቃ ሲያደርጉም ነበር፡፡

ቤተክርስቲያን ባልተካተተችበት ኮሚቴ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቦታው ሊመለስ ነው

  • የኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ አልተካተተችም ፤
  • ሐውልቱ እንዴት ወደ ቦታው እንደሚመለስ ቤተክርስቲያኒቱ የምታውቀው ነገር የለም፡፡
(አንድ አድርገን የካቲት 29 2007 ዓ.ም)፡- ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ምክንያት ከቦታው ተነስቶ የነበረው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቦታው ሊመለስ መሆኑ ተሰማ፡፡ ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ላይ የአዲስ አበባ መንገዶች  ባለስልጣን እንደገለጸው በ2007 ዓ.ም ውስጥ ሐውልቱ ወደ ቦታው እንደሚመለስ በሥራ አስኪያጁ በኩል  መናገሩ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀውልቱን ለማስመለስ መንግሥት የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ከተሞች መንገዶች ባለሥልጣን በጋራ እንዲሰሩ እና በሁለት ወር  ባልበለጠ ጊዜ የመመለሱን ሥራ እንዲያከናኑ ኮሚቴ ማቋቋሙ ታውቋል፡፡ አሁንም በብዙዎች ጥያቄ እየተነሳ የሚገኝው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሐውልቱ አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ አለመካተቷ ነው፡፡

Friday, March 6, 2015

ዜና ሠናይ .... ‹6›


Diakon Abayneh Kasse
በእንተ እሳት ዘደብረ ዝቋላ አሁን እሳቱ አደጋ ሊፈጥር ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ሌሊቱን ሙሉ በስፍራው ኾነው ሲጠባበቁ ያደሩት ሰዎች እንደገለጡት ከኾነ ከእንግዲህ በተለየ ተአምራዊ ሁኔታ ካልኾነ በስተቀር ያንን አስፈሪ እና አውሬ እሳት ዳግም የሚያዩት አይመስልም፡፡ እሳቱ ከገደሉ ውስጥ እንደተቀበረ ቀርቷል፡፡ ይኽንን ዜና ያሰማን ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው፡፡ ትናንት ከሩቅ ሲታይ ያመሸው ጭስ እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ ደብዛውን አጥፍቶ አድሯል፡፡ አሁን በዓይን የሚታይ ምንም ነገር ባይኖርም የተዳፈነ እሳት ላይኖር የሚችልበት አመክንዮ ግን የለም፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ሰዓት ከመስቀል አደባባይ ተነሥተው ጉዳዩን ለመከታተል ወደስፍራው የሚያመሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ኅብረት አባላት እየተሰባሰቡ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ ደርሰው የድርሻቸውን አበርክተው እስኪያረጋግጡልን ድረስ ጸሎታችን ሊገታ አይገባውም፡፡ እባብ ያየ በልጥ በረየ እንዲሉ አበው ከዚህ ቀደም ያየነው ጠፋ ሲሉት የሚያገረሽ እሳት ብዙ አስከፍሎናልና ከዚያ መማር አለብን፡፡ አሁንም የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፯ .. ከሦስት ቀን በፊት ተነሥቶ የነበረው እሳትም እንደዚሁ ጠፋ ተብሎ ካዘናጋ ወዲያ ገንፍሎ የተነሣ ስለነበር ከቅርብ ቀን ተሞክሮው እናውቀዋለን፡፡ ለዚህም ነው  የሰው ኃይል ወደ ደብረ ዝቋላ እየተመመ ያለው፡፡ እግዚአብሔር የሰማነውን እውነት ካደረገው የሚቀረን ነገር ስለወደፊቱ ማሰብ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሰው ልብ እየደነገጠ፣ ተባባሪ አስተባባሪ እየጠፋ ስቃይ ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ 


ለዚህም ደግሞ የገዳሙ አስተዳደር ልክ እንደ ልማት ዘርፍ እንቅስቃሴው በዚሁ ጉዳይ የሚመለከታቸውን አካላት እያስተባበረ አስፈላጊውን መርሐግብር /ፐሮጀክት/ ቀይሶ ሊሠራ የሚችል ብሔራዊ ዕውቅና ያለው ጉባኤ ማቋቋም ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ዓይነት ኑሮ ለመግፋት እንገደዳለን፡፡ ከዚህ በፊት ጥቆማ ያደረግሁባቸው መንገዶች ሁሉ ተግባራዊ ሊኾኑ የሚችሉት ሥራየ ብሎ የሚሠራ አካል ሲዋቀር ብቻ ነው፡፡  

ቸር ዜና ያሰማን፡፡