Sunday, March 8, 2015

ቤተክርስቲያን ባልተካተተችበት ኮሚቴ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቦታው ሊመለስ ነው

  • የኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ አልተካተተችም ፤
  • ሐውልቱ እንዴት ወደ ቦታው እንደሚመለስ ቤተክርስቲያኒቱ የምታውቀው ነገር የለም፡፡
(አንድ አድርገን የካቲት 29 2007 ዓ.ም)፡- ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ምክንያት ከቦታው ተነስቶ የነበረው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቦታው ሊመለስ መሆኑ ተሰማ፡፡ ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ላይ የአዲስ አበባ መንገዶች  ባለስልጣን እንደገለጸው በ2007 ዓ.ም ውስጥ ሐውልቱ ወደ ቦታው እንደሚመለስ በሥራ አስኪያጁ በኩል  መናገሩ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀውልቱን ለማስመለስ መንግሥት የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ ከተሞች መንገዶች ባለሥልጣን በጋራ እንዲሰሩ እና በሁለት ወር  ባልበለጠ ጊዜ የመመለሱን ሥራ እንዲያከናኑ ኮሚቴ ማቋቋሙ ታውቋል፡፡ አሁንም በብዙዎች ጥያቄ እየተነሳ የሚገኝው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሐውልቱ አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ አለመካተቷ ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ይህ ሐውልት ከቦታው ሲነሳ ቤተክርስቲያን ፤ ሕዝብ እና የሚመለከታቸው አካላት ያልመከሩበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሚነሳበት ወቅትም በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገፆች ፤ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ሬድዮን ጣቢያዎች ወሬው በመመላለሱ ምክንያት በስተመጨረሻም መንግሥት በሚመለከተው አካል አማካኝነት መልስ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ በወቅቱም እንዴት እንደሚነሳ እና መቼ እንደሚነሳ ለሕዝቡ ግልጽ ያለመደረጉ ይታወቃል፡፡ መጀመሪያ ሐውልቱ ከቦታው ሲነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ምንም የምታውቀው ነገር እንደሌለ ከሚመለከተው አካልም ምንም አይነት ደብዳቤ ያልደረሳት ሲሆን አሁንም ከመጀመሪያው ስህተት ባለመማር መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱ የሐውልቱን ወደ ቦታው የመመለስ ሂደት ላይ ታሳታፊ ያላደረጋት መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡


No comments:

Post a Comment