Friday, March 6, 2015

ዜና ሠናይ .... ‹6›


Diakon Abayneh Kasse
በእንተ እሳት ዘደብረ ዝቋላ አሁን እሳቱ አደጋ ሊፈጥር ከማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ሌሊቱን ሙሉ በስፍራው ኾነው ሲጠባበቁ ያደሩት ሰዎች እንደገለጡት ከኾነ ከእንግዲህ በተለየ ተአምራዊ ሁኔታ ካልኾነ በስተቀር ያንን አስፈሪ እና አውሬ እሳት ዳግም የሚያዩት አይመስልም፡፡ እሳቱ ከገደሉ ውስጥ እንደተቀበረ ቀርቷል፡፡ ይኽንን ዜና ያሰማን ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው፡፡ ትናንት ከሩቅ ሲታይ ያመሸው ጭስ እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ ደብዛውን አጥፍቶ አድሯል፡፡ አሁን በዓይን የሚታይ ምንም ነገር ባይኖርም የተዳፈነ እሳት ላይኖር የሚችልበት አመክንዮ ግን የለም፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ሰዓት ከመስቀል አደባባይ ተነሥተው ጉዳዩን ለመከታተል ወደስፍራው የሚያመሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ኅብረት አባላት እየተሰባሰቡ ነው፡፡ እነርሱ ደግሞ ደርሰው የድርሻቸውን አበርክተው እስኪያረጋግጡልን ድረስ ጸሎታችን ሊገታ አይገባውም፡፡ እባብ ያየ በልጥ በረየ እንዲሉ አበው ከዚህ ቀደም ያየነው ጠፋ ሲሉት የሚያገረሽ እሳት ብዙ አስከፍሎናልና ከዚያ መማር አለብን፡፡ አሁንም የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፯ .. ከሦስት ቀን በፊት ተነሥቶ የነበረው እሳትም እንደዚሁ ጠፋ ተብሎ ካዘናጋ ወዲያ ገንፍሎ የተነሣ ስለነበር ከቅርብ ቀን ተሞክሮው እናውቀዋለን፡፡ ለዚህም ነው  የሰው ኃይል ወደ ደብረ ዝቋላ እየተመመ ያለው፡፡ እግዚአብሔር የሰማነውን እውነት ካደረገው የሚቀረን ነገር ስለወደፊቱ ማሰብ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሰው ልብ እየደነገጠ፣ ተባባሪ አስተባባሪ እየጠፋ ስቃይ ውስጥ መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ 


ለዚህም ደግሞ የገዳሙ አስተዳደር ልክ እንደ ልማት ዘርፍ እንቅስቃሴው በዚሁ ጉዳይ የሚመለከታቸውን አካላት እያስተባበረ አስፈላጊውን መርሐግብር /ፐሮጀክት/ ቀይሶ ሊሠራ የሚችል ብሔራዊ ዕውቅና ያለው ጉባኤ ማቋቋም ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ዓይነት ኑሮ ለመግፋት እንገደዳለን፡፡ ከዚህ በፊት ጥቆማ ያደረግሁባቸው መንገዶች ሁሉ ተግባራዊ ሊኾኑ የሚችሉት ሥራየ ብሎ የሚሠራ አካል ሲዋቀር ብቻ ነው፡፡  

ቸር ዜና ያሰማን፡፡


1 comment:

  1. egzabhar ystlen char wer slasamhan egezabher ybarkh!! aman!!

    ReplyDelete