Saturday, March 14, 2015

በእንተ ዝቋላ


በቅርቡ ኢትዮጵያ ነክ ከኾኑና የተለያዩ መገናኛ ብዙኀንን ካጨናነቁ ዜናዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳምና የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ በገዳሙ ውስጥ ሊፈጽመው ያቀደውና በኢትዮጵያ ቴሌቭዢን ያስነገረው ማስታወቂያ ነው። ማስታወቂያው በአማርኛና በኦሮሚኛ ክፍለ ጊዜያት መነገሩም ጉዳዩ በግብታዊነት ወይም በጥቂት ሰዎችጠብ ጫሪነትየተፈጸመ ድርጊት ሳይኾን በዕቅድና በጥናት የተደረገ መኾኑን ያሳያል። ባይኾንማ ኖሮ ከፍተኛ የሳንሱር ሕግ አለው በሚባለው የኢትዮጵያ ቴሌቭዢን እንዲህ ዓይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊያስከትል የሚችል ርዕሰ ጉዳይ ባልቀረበ ነበር።

ያም ኾነ ይኽ ካልጠፋ ቦታ ለስምንት መቶ ዓመታት ያኽል ክርስቲያናዊ ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጸምበት በነበረው ቦታ ላይ ከገዳሙ ተልዕኮ ጋር ምንም የሚያመሳስለው ወይም የሚያቀራርበው ገጽታ የሌለውን የእሬቻ በዓል እናከብራለን ብሎ መነሣት ከጤናማ አእምሮ የሚፈልቅ አሳብ አይደለም። በሌላ በኩልም ከእምነት ጋር በተያያዘ መልኩ የሚከሰቱ ግጭቶች የሚያስከትሉትን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ያለመረዳት ውጤት ወይም ቢረዱም ሊፈጠሩ ከሚችሉ ቀውሶች አንዳች ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ከማሰብ ሊከሰት ይችላል። በሌላ መልኩም በአኹኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ የገጠማትን የአስተዳደር ክፍተት በማየት ገዳሙ ባለቤት እንደ ሌለው በመገመት ሊኾን ይችላል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ እምነቷን በግድ ተቀበሉ ብላ ያስተማረችበት ጊዜ የለም። ምናልባት አንዳንድ ባለ ሥልጣናት በእምነት ሽፋን ሕዝቡን ለመያዝ ካህናተ ደብተራዎችን ይዘው የፈጸሟቸው በደሎች ሊኖሩ ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን እንደ ተቋምም ኾነ እንደ ተልዕኮዋ አካል አድርጋ አስተምህሮዬን ተቀበሉ ብላ አላስገደደችም፤ አታሰገድድምም። ከእምነት ተልዕኮዋ ባሻገርም የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ስትፈጽምእናንተ ከእምነቴ ውጪ ስለኾናችሁ ይኽን አገልግሎት ማግኘት የለባችሁምበማለት ያገለለችው አካል ወይም ኅብረተስብ የለም። ለዚኽም በጠበል ቦታዎቿ አገልግሎት የሚያገኙ ጠበልተኞችን ማየቱ ብቻ ይበቃል። የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ጠበል ከመላው ኢትዮጵያ የሚመጡ ሕመምተኞች ፈውስ ድኅነት ያገኙበታል። በዚህም በዘመናዊ ሕክምና መፍትሄ ላላገኙና ዘመናዊ ሕክምና የሚጠይቀውን ወጪ መሸፈን ለማይችሉ ታማሚዎች የገዳሙ ጠበል የሚያበረክተው አስተዋፅዖ በገንዘብ የሚተመን አይደለም። ከዚህም በላይ በተለያዩ መንሥዔዎች የአእምሮ ጭንቀት ላገኛቸው ሰዎች ዝቋላን የመሰሉ ከዓለማዊው ጫጫታ የራቁ በጽሙናና በአርምሞ የተሞሉ ገዳማት ከየትኛውም ዘመናዊ የአእምሮ ሕክምና መስጫ ተቋም የበለጠ ፍቱን ናቸው።

በመኾኑም ዝቋላ ገዳም ሀብትነቱ አንዳንድ የአመለካከት ችግር ያለባቸው ሰዎች እንደሚሉት የአንድ ብሔር የአንድ አምነት ብቻ አይደለም። በገዳሙ ያሉት ማኅበረ መነኮሳትም ከአንድ ወንዝ የተውጣጡ ሳይኾኑ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ጎሳና ቋንቋ ያልለያቸው እምነት ያስተሳሰራቸው የክርስቶስ ፍቅር የሳባቸው ናቸው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአእምሮ አድማስን ሰፋ አድርጎ ማሰብ የተሳናቸው ወይም በጥቂት አስረጂ ብቻ የአንድ አስተሳሰብ ተገዢ የኾኑትን ሰዎች በተሳሳተ መንገድ መምራት የሚሹ ሰዎች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንየአማራ እምነትእያሉ ሌላውን ከእምነቱ ወደ ኋላ ለማሸማቀቅ ሲተጉ ይስተዋለሉ። ይኽ ግን ታሪክ ይቅር የማይለውን ስሕተት ያስተከትላል። ለመኾኑ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት አማራ ኦሮሞ ትግረ ወላይታ ከምባታ ጉራጌ….. የሚሉ የብሔር ብሔረሰቦች ክፍፍል ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ የንግሥት ሕንደኬ በዥሮንድ የኾነ ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱን ሲመለስም በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በሐዋርያው ፊልጶስ እጅ ተጠምቆ መመለሱን ይነገረናል እንጂ የብሔር ቆጠራ ውስጥ አልገባም። ከዚያስ አማራ የሚባለው ብሔረሰብ ወደ ሥልጣን የመጣው በስንተኛው ክፍለ ዘመን ነው? አማራ የሚባለው ብሔር በትረ መንግሥቱን ከመጨበጡ በፊት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በምሥራቅ እስከ የመን፣ በምዕራብ እስከ ኑብያ፣ በደቡብ እስከ መቋዲሾ መስፋፋቱን ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊዎች ይነግሩናል። ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የኢትዮጵያ እምነት ብቻ አይደለችም። ጥንታውያን (ኦሪየንታል) የሚባሉ ኮፕቲክ (ግብፅ) ሶርያ፣ አርመንና ሕንድ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸው። ይኽ ደግሞ አኹን በዘመናችንም የሚታይ እውነታ ነው። ከኾነ እንዴት አድርገው ነው ኦርቶዶክስን የአማራ እምነት ነው። አማሮች ከሀገራችን ውጡ ብሎ በገዳም ያሉ መነኮሳትን መረበሽ የተጀመረው? ኦርቶዶክስስ የአማራ ተባለ። እስልምናስ? ፕሮቴስታንትስ? ካቶሊክስ? በእውነቱ ይኽ ከእንጭጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ የመነጨ እውነታን ወደ ጎን ያገለለ አባባል ነው።


በቅርቡ በግብፅ ከተከሰተው መንግሥት ግልበጣ ጋር ተያይዞ የሙስሊም ብራዘር ሁድ ፓርቲ ወደ ሥልጣን በመጣበት ወቅት ተመሳሳይ ችግር በግብፅ ተከስቶ ነበር። አንዳንድ አክራሪ የእስልምና እምነት ተከታዮችክርስቲያኖች በተለይም የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሀገራችን ይውጡብለው ተነሡ። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ክርስቲያኖችን በአሰቃቂ ኹኔታ ገደሉ፤ አብያተ ክርስቲያናቱን አቃጠሉ። መላ ሀገሪቱን አወኩ። በዚህ መካከል ነው በእስልምናው ዓለም አንጋፋና እጅግ ታዋኪ የኾነው የአል አሕዛር ዩኒቨርስቲ መሪ የነበሩት እስላማዊ ሊቅ በግብፅ ታሪክ ውስጥ ኮፕቶች ቀዳማውያን ናቸው፤ እነርሱ ከእስልምና በፊትም በዚህች ምድር ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። ደግሞም የግብፅ ታሪክ ያለ ኮፕቶች ጎደሎ ነውበማለት በዚያ አስጨናቂ ወቅት ይኽን እውነት የተናገሩት።

በኢትዮጵያችንም ያለው እውነታ ይኸው ነው። ኢትዮጵያ የአሁኑን ቅርጿን የያዘችው በብዙ ሂደቶች ውስጥ አልፋ ነው። በተለያዩ ዘመናት መስፋትና መጥበብ ገጥሟታል። በምድሪቷ የሚኖሩ ዜጎቿ ፍልሰት አግኝቷቸዋል። አንዱ ሌላውን አስለቅቆ ሌላው የነበረበትን ቦታ ይዟል። ስሙን ቀይሯል። ይኽ እውነታ በተለይ ከኦሮሞ መስፋፋት ጋር በስፋት የሚታይ ነው። ሁሉም ብሔረሰቦች ዛሬ እየኖሩ ባሉበት ቦታ ያልነበሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። በመኾኑም የአንድ ብሔረሰብ ታሪክ ያለ ሌላው ብቻውን ጎደሎ ነው። ብሔሮች ታዋግተዋል፣ ተፋልሰዋል፤ ተጋብተዋል፤ በሥልጣን ተሳስረዋል፤ በአንድነት የጋራ ጠላት ተዋግተው የጋራ ታሪክ አኑረዋል። እነዚህን ለዘመናት አብረው የኖሩትን ሕዝቦች አንተ ውጣ አንተ ግባ፤ አንተ ይገባሃል፤ አንተ አይገባህም የምንል ከኾነ በሠለጠነው ዘመን ላይ ኾነን እጅግ ወደ ኋላ የቀረን ሕዝቦች እንኾናለን።


እነዚህ ሕዝቦች በመኖር ዘመናቸው ውስጥ በኖሩባቸው አካባቢዎች ያኖሯቸው የታሪክ፣ የእምነትና የባህል አሻራዎች አሏቸው። አሁን ያለው ትውልድ ከጠባብ የብሔርተኝነት ስሜት ርቆ እነዚህን የቀድሞ ትውልድ አሻራዎችን መጠበቅ ይኖርበታል። ይኽ በሌሎች አገራት የሚታይ እውነታ ነው። ግብፅ በዐረቦች እጅ እስከ ወደቀችበት ድረስ በተለያዩ ሀገሮች ተገዝታለች። ግሪኮችና ሮማውያን ለብዙ ዘመናት አስተዳድረዋታል። እንዲያውም ግብፅ ለሮም ኤምፓየር እንደ ምግብ ጎተራው ኾና ታገለግል ነበር። ሮማውያን በግብጻውያን ክርስቲያኖች ላይ ብዙ መከራ አድርሰውባቸዋል። ዐረቦች ሀገሪቱን ከያዙ በኋላ ግን እነዚህ ቀድሞ ሀገሪቱን አስተዳድረው የነበሩ ሕዝቦች ያኖሯቸውን የታሪክ አሻራዎች አላጠፏቸውም። በአሁኑ ጊዜ የፈርዖን ቤተ መንግሥቶች፣ የነገሥታቱ የመቃብር ቦታዎች፣ የክርስቲያኖች ገዳማት፣ የቅዱሳን አጽም፣ የሮማውያን ቤተ መንግሥት በእስላማዊው የግብፅ መንግሥት ልዩ ጥበቃና ጥገና እየተደረገላቸው ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። አንዳንድ አክራሪ የእስልምና ቡድኖች ተነሥተው በእነዚህ የታሪክ አሻራዎች ላይ ጥቃት ሊያደርሱ ሲነሡ የመከላከል ርምጃውን የሚሠራው እስላማዊው የግብፅ መንግሥት ነው።

በኦሮሚያ ክልል ቢሮ ውስጥ የሚሠሩ ባለ ሥልጣናት ከዚህ ሊማሩ ይገባቸዋል። ኦሮሚያ በተባለው ክልል ውስጥ አማሮች፣ ጉራጌዎች፣ ወርጂዎች፣ አርጎባዎች፣ ሶማሌዎች ኖረዋል። ሁሉም የራሳቸውን አሻራ በምድሪቱ አኑረዋል። በሌሎች ክልሎችም የኦሮሞ ሕዝብ ያኖራቸው አሻራዎች አሉ። ይኽ የሕዝብ ዓለም አቀፍ የአኗኗር ስልት ነው። አንዱ ያለ ሌላው ጎደሎ ነው። ሙሉ የምንኾነው ስንተባበር ብቻ ነው።

ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ጻድቁ የተጋደሉበት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምሕረት ከእግዚአብሔር የለመኑበት ነው። ጻድቁ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ናቸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አስተምህሮዋን ጠብቀው ሥርዓቷን አክበረው ለሕልውናዋ መጠበቅ ዘመናቸውን ሙሉ በፆም በጸሎት የተጋደሉትን አባት በስማቸው ገዳም መሥርታ፣ ጽላት ቀርፃ፣ ገድል ጽፋ ቀን ሰይማ ታከብራቸዋለች። ዝቋላ ለኦርቶዶክሳውያን ተራ ተራራ አይደለም። ቅዱሱ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሰመረ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት፣ ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን የተቀበለበት፣ በኪደተ እግሩ የቀደሰው የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት ቅዱስ ስፍራ ነው። ይኽ ገዳም የዓለም ሀብት ነው። በመኾኑም የክልሉ መንግሥትም ኾነ ማዕከላዊው መንግሥት የቱሪዝም ቢሮ የከፈቱት በየቢሮው ላሉት ባለ ሥልጣናት አምነትና አመለካከት የሚመቹትን ቅርሶችና መዳረሻዎች ለመጠበቅ ሳይኾን ሕዝቡ በመኖር ሂደት ያስቀመጣቸውን ቁሳዊና መንፈሳዊ እሴቶች ለመጠበቅ እስከ ኾነ ድረስ የዝቋላ ገዳም ከነሙሉ ክብሩ እንዲጠበቅ የሚገባውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።


ሕዝቡ አንጀቱ ካረረ መንፈሱ ከተረበሸና ራሱን ለሰማዕትነት ካዘጋጀ በኋላ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የምስራቅ ሸዋ ዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ኀላፊዎችእናንተ ሰላም ፍጠሩ፤ [በክብረ በዓሉ] ከተለመደው ውጭ አንዳችም የሚደረግ አይኖርም፤ ጥበቃውም እንዲጠናከር ይደረጋል፤ የተላለፈውን ዘገባ አጣርተን በኦሮምኛ እና በአማርኛ ማስተባበያ እንዲሰጥበት እናደርጋለን፡፡›› ማለታቸው እየተሰማ ነው። መልካም ነው። ግንአጣርተንሲሉ ምኑን ነው የሚያጣሩት? በመንግሥት ቴሌቪዥን የተነገረን ማስታወቂያ ለማጣራት ምን ጊዜ ይፈጃል? ወይስ ከሕዝቡ ጥያቄ ፋታ ለማግኘትና የሕዝቡን ስሜት ለማርገብ? አሁን መፍትሄው ጊዜያዊ የማርገቢያ ምላሽ መስጠት ሳይኾን ሥር ነቀል ርምጃ መውሰድ ነው። ርምጃውም ዝቋላ የዓለም የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቋሚ ቅርስ መኾኑን አምኖ ተገቢውን ክብር መስጠትና በውስጡ የሚኖሩ አበውና እማት መነኮሳት ሳይረበሹ በመረጋጋት እንዲኖሩ ዋስትና መስጠት ነው።

ከዚህ ውጪ ‹‹ለእኛ ዐዲስ ነገር ነው፤ እዚኽ ቦታ ኢሬቻ የለም፤ በአራት ወይም በስምንት ዓመት አንዴ ዝናም እምቢ እንዳይለን ገዳሙን አስፈቅደን ከምንፈጽመው ሥርዐት ውጭ በተነገረው መልኩ የሚከበር በዓል የለም፡፡ ያስተላለፉት መጠየቅ አለባቸው፡፡›› በሚለው የአባ ገዳ ተወካዮች አባባልም ውስጥ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ነገር አለ። ዝናም አልዘንብ ቢል ቤተ ክርስቲያን ስለ ዝናብ መዝነብ የምትፈጽመው የምሕላ ጸሎት አላት። በዚያ ምሕላ ላይ በጸሎቱ የሚያምኑ ኹሉ ተገኝተው መሳተፍ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ በተከበረው የገዳሙ ክልል ውስጥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓተ ጸሎት የተለየ ሌላ ጸሎት እንዲደረግ ገዳሙም መፍቀድ አይችልም። ይኽ ማለት መስጊድ ሄደን ቅዳሴ እናስቀድስ እንደ ማለት ነው።
በኢየሩሳሌም ዴር ሡልጣን ገዳም ከግብፆች ጋር ሊፈታ ያልቻለ ውዝግብ ውስጥ የገባነው በዓመት አንድ ቀን የትንሣኤን በዓል ለማክበር መብራት አብርተን በእናንተ በኩል እንለፍ ተብሎ በተጀመረ ጣጣ ነው። ትውልድ ያልፋል፤ ትውልድ ይተካል። ከዚህን በፊት አባቶቻችን በየዋሕነት እሺ ብለው ተቀብለው አስተናግደው ውለው ሲያበቁ ግን ሕልውናችንን ጥያቄ ውስጥ እስከ ማስገባት የደረሱ አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። የገዳሙ ማኅበረሰብ አርቆ ማሰብን ገንዘቡ ሊያደርግ ይገባዋል። ዛሬ ሰላም ለመፍጠርና ያሉባቸውን ወከባዎች ለማስታገስ ብለው በቀላሉ የማይነቀሉ እሾሆችን መትከል የለባቸውም።

መላው ሕዝበ ክርስቲያንም ዘላቂ መፍትሄ ከመፈለግ ውጪ የነገር እሳት በተነሳ ቁጥር ያንን ለማጥፋት የምናደርገው ጊዜያዊ ሩጫ ወንዝ አያሻግረንም። በመኾኑም እንደ ሰደድ እሳት በሀገራችን የሚንቀሳቀሰው የጎሳ ፖለቲካ ሳይከፋፍለን በአንድ በክርስቶስ መስቀል አንድ ኾነን ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ ገጽታ ልንወያይ ይገባናል። የአብያተ ክርስቲያናቱና የገዳማቱ ቦታ በሕግ ታውቆ ሊከበር ይገባል። የጥምቀተ ባሕርና የመስቀል ደመራ ቦታዎች የመቃብር ስፍራዎች በሕግ የተረጋገጠ የሰነድ ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል። ለዚኽም የተማረው የኅብረተስብ ክፍል ከፍተኛውን ድርሻ መውሰድ ይጠበቅበታል። አሁን ከላይ ብቻ መጠበቅ የሚያዋጣበት ጊዜ አይደለም። ቤተ ክርስቲያንን የጠበቋት እምነተ ጽኑዓን የኾኑ ምእመናን ናቸው። ዛሬም እነርሱ ናቸው። ከዚህ ውጪ መላው የኢትዮጵያ ገዳማት ማኅበረሰብ እግዚአብሔር በረድኤት ሀገራችንን አብያተ ክረስቲያናቱን ይጠብቅልን ዘንድ ከምን ጊዜውም በላይ በጸሎት ሊተጉ ይጠበቅባቸዋል። እግዚአብሔር ይረዳናል።
በቀሲስ ስንታየሁ አባተ


4 comments:

  1. እግዚአብሔር እንደዚህ ያሉ ልብ ብርሃን የሆኑ የቤተከርሰቲያን ልጆችን አያሳጣን ለጸሐፊው ዕድሜንና ጤናን ይስጥልን

    ReplyDelete
  2. ቀሴስ እድሜና ጤና ይስጥልን ፣እንዲሕ ፌት ለፌት የሜጮሁ አባቶች አያሳጣን።

    ReplyDelete
  3. አባቴ ቀሲስ እግዚአብሔር እንደርስዎ ያሉትን አባቶች ያቆይልን፡፡ እግዝአብሔር በእድሜ በጤና ይጠብቅልን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የታላቁን የአባታችንን የፃድቁን ገዳም ይጠብቅልን፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን፡፡ አሜን፡፡

    ReplyDelete
  4. እግዚአብሔር አምላክ የአባታችንን የፃዲቁን ገዳም ይጠብቅልን፡፡ ቸር ወሬ ያሰማን፡፡ አሜን፡፡ የትምወርቅ

    ReplyDelete