Thursday, March 5, 2015

ለደብረ ከዋክብት የመፍትሔ ሀሳቦች ‹4›


ደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከተገደመ ፰፻፸፯ ዓመታት እንዳስቆጠረ የገዳሙ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በበርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶች እንደሚገኙት ገዳማት እና አድባራት በሀገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ ተራሮች አንዱ በሆነው በዝቋላ ተራራ ላይ ከመመሥረቱ ባሻገር ከላይ ከአናቱ በፈዋሴ ድውያን የጠበል ሐይቅ ዙሪያውን ከእግረ ተራራው ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ እንደ መሥራቹ እንደ አቡነ ገብረመንፈስቅዱስ የጸጋ ልብስ በተንዘረፈፈ አጸደ ሐምል የተሸለመ ዐቢይ ቅዱስ ገዳም ነው፡፡
 
በመጋቢት ቀን ፳፻፩ .. ተራራውን በእኔ እበልጥ እኔ በልጥ ፉክክር ከወዲህም ከወዲያም ብቅ ብቅ ብለው በፍቅር ተጠጋግተው ያደጉ እንደ አርዘ ሊባኖስ እና የኢትዮጵያ ጥድ ያሉ ዕድሜ ጠገብ ሀገር በቀል ዛፎች እንዲያ በእሳት ነድደው ገዳያቸው ሳይታወቅ ደመ ከልብ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ዳግመኛም በመጋቢት ቀን ፳፻፬ .. ጠፋ ሲሉት እንደገና እየተቀሰቀሰ በቀላሉ አልበርድ ያለ እሳት የቻለውን ያኽል ደን ድምጥማጡን ማጥፋቱ አይዘነጋም፡፡  የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፯ .. ደግሞ ሌላ እጅግ አሳዛኝ ጥፋት በተለመደው እሳት ተከሰተ፡፡

 
እንደተሰማው ከሆነ ከሌሎቹ ጊዜያት በአጠረ ፍጥነት እሳቱ ወደ ሰማንያ በሚደርሱ ራሳቸውን ባዘመቱ ቀናተኛ ምእመናን እና ጥቂት የፖሊስ አባላት ርብርብ ተግ አለ የሚል በጎ ዜና ሰማን፡፡ እሳቱ የተነሣበት አቅጣጫ ተሳላሚው በእግር በመኪና በሚገባባት አቅጣጫ ሲሆን የተሻለ የደን ክምችት የሚገኝበት እንደሆነ የሚያውቁት ያስረዳሉ፡፡ ብዙም ከፍ እጅግም ዝቅ ሳይል በተራራው ወገብ አካባቢ የተነሣው እሳት ብዙ ሳያጠፋ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ደግ ቢሆንም እስከ መቼ? የሚለው ጥያቄ ግን የምእመናን እና የአባቶች መነጋገሪያ ኾኗል፡፡

ከመናገሻ ከተማችን ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ይኽ ታሪካዊ እና ቅዱስ ስፍራ ስንት ጊዜ ነደደ? እንዴት መፍትሔ ሳይበጅለት ቀረ? ተጠያቂው ማን ነው? በ፮ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ጊዜ ተቃጠል ማለት በየ፪ ዓመቱ የመንደድ ጥቃት እየደረሰበት እንደሆነ ያመላክታል፡፡ እናስ መጨረሻው ምን ይሆን?
እሳት በብዙ ክንያት ሊነሣ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ተፈጥሯዊ ምክንያት እንዳለ ሁሉ ሰው ሠራሽ ምክንያትም አለ፡፡ ከቦታው ቅዝቃዜ አንጻር ሲታይ ደግሞ በመጀመሪያው ዓይነት ከሚነሣው እሳት ይልቅ በሁለተኛው ምክንያት የሚነሣው እሳት ያዘነብላል፡፡ እናስ ምክንያቱ ይታወቅ ዘንድ ምን ያኽል ተደከመ? የምርመራው ውጤትስ የት ደረሰ? እንዴት አጥፊዎቹ ሳይገኙ ቀሩ

ዛሬ በሀገራችን ደን የዓይን ረሃብ እየሆነ ይገኛል፡፡ ሲሆን ዕድሜ ጠገብ ዛፎች በአዳዲስ ዛፎች የሚተኩበት ስልት ሊቀየስ በተገባው፡፡ ይባስ ብሎ ከዓመት ዓመት ደን እንደ ጧፍ እየነደደ ዝም ማለት የግራ ግራ ነው፡፡ አሁንም የቀሩት የተረፉት ዘመን እንዲሻገሩ የሚከተሉት የመፍትሔ ሀሳቦች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

. አጥፊዎችን ማወቅ እና ተገቢውን ፍትሐዊ ውሣኔ መስጠት
ዛሬ እነዚህን አጥፊዎች ፈልጎ በማግኘት ተመጣጣኝ የሆነ እና አስተማሪ የሆነ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ካልተደረገ ለነገ ምንም ዓይነት ዋስትና አይኖረንም፡፡ ይኽ ካልሆነ እነርሱ ያጠፋሉ፣ እናም ዝም ይባላሉ፣ ደግመው ደጋግመው ያጠፋሉ፡፡ ይኽም ይቀጥላል፡፡ ነገ በገዳሙ ውስጥ ያሉትን አበው፣ እመው መናንያን መነከሳትን እና መነኮሳዪያትን ሊያቃጥሉ እንደማይችሉ በምን እናውቃለን? ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ አሁን ይበቃል መበላ አለባቸው፡፡ እሳት በጥይት አይቆምም፡፡ እሳት እንዲቆም በዚህ በኩል ፍትሕ ርትእ ሊሰጥ ይገባል፡፡ የሁሉም ዓይኖች የሚያዩት ተራራ ኾኗል፡፡ ስለሆነም ልዩ ግብረ ኃይል ተሰይሞ ይኽንን በሀገር ላይ የተፈጸመ ወንጀል የሚያጣራ እና ለፍትሕ የሚያደርስ ሥልጣን ተሰጥቶት እንዲሠራ መደረግ አለበት፡፡ ሕዝቡም ተባባሪ እንዲኾን በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ሊደረግ ያስፈልጋል፡፡ ይኽ ካልተደረገ ግን ጉዳዩ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችልበት ሁኔታ እንዳይፈጠር እሰጋለሁ፡፡


. የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎችን በገዳሙ ዙሪያ ማስቀመጥ
ዛሬ የደረስንበት ዘመን የተለያዩ የእሳት ማጥፊያ ዘዴዎች እና መሣሪያዎች የተፈለሰሙበት ነው፡፡ ከዝቋላ ገዳም ጋር እንደ ኣይን እና ሽፋሽፍት በሆነችው ደብረ ዘይት የጦር አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከልብ ካለቀሱነውና ነገሩ ቃጠሎው እንደተነሣ ብድግ ብለው ድምጥማጡን ሊያጠፉት እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ ታዲያ ለእነዚህ በራሪ አካላትም ሆነ ለሰው እጅ የሚመጥን የሚረጭ ንጥረ ነገር (ኬሚካል ) ከእነ መከላከያ ልብሱ ማሰናዳት ይገባል፡፡

የግብርና ሚኒስትር እና የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት ይኽንን ቅድመ ሁኔታ ከመከላከያ ሚኒስትር ጋር በመሆን ማዘጋጀት ይከብዳቸው ይሆን? መቼስ የደኑን ጥቅም ለእነርሱ መንገር "ለቀባሪው ማርዳት" ነው፡፡ እየሆነ ያለው ግን ገዳሙና ሕዝቡ ይወጡት የሚል ይመስላል፡፡ ዝቋላ የሀገር ሀብት ነው፡፡ እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባልና፡፡ ወጪም ካለው ሕዝቡ ቸር ነው፡፡ ቢጠየቅ ያሟላል፡፡
 
የእሳት መከላከያ እና ማጥፊያ ድርጅትም ቢሆን እጁን አጣጥፎ ቁጭ ሊል የሚገባው ሊሆን አይችልም፡፡ በዋነኛነት ሥራው የእርሱ ነውና፡፡ ከፍተኛ የደን ክምችት ያለባቸው ስፍራዎች እነማን ናቸው ከተባለ በቀዳሚነት ሊጠቀሱ የሚችለሉት ገዳማት ናቸው፡፡ በእነዚህ ቅዱሳት መካናት ያሉት ዕጽዋት ከፍተኛ እንክብካቤ ይሻሉ፡፡ ለዚህም በጣና ገዳማት፣ በአሰቦት ገዳም እና በዝቋላ ገዳም እየሆነ ያለው ቋሚ ምስክር ነው፡፡ ስለሆነም ሥራዬ ብሎ በጥናት እያስደገፈ ሥራውን በአግባቡ ሊወጣ ይገባዋል እንጂ እንደማንኛውም ሕዝብ ዜና ቃጠሎ አዳማጭ ሊሆን አይገባውም፡፡
 

. አስፈላጊ የመከላከያ መም መሥራት
በተወሠኑ የርቀት ልዩነቶች እሳት በተነሣ ጊዜ ከአንዱ ወደሌላው እንዳይዛመት አደናቃፊ መም መሥራት ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ መሞች በሣር እና በሌሎች እሳት አቀጣጣይ በሆኑ ዕጽዋት እንደይያዙ እና በደለል እንዳይሞሉ በየጊዜው ማጽዳት፡፡ ለዚህም የሚገባውን የሰው ኃይል መመደብ፡፡
 
. ጠንካራ ጥበቃ ማድረግ
ከሰል አክሳዮች እና ሌሎች የጥፋት ተልእኮ ያላቸው ኃይሎች እንዳይተናኮሉ በተመረጡ ቦታዎች ጠንካራ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡
እነዚህን እና ሌሎችም ተጨማሪ የመከላከያ እና ቁጥጥር መፈትሔዎች በማድረግ ይኽን ታላቅ ገዳም ከተደጋጋሚ ቃጠሎ ማዳን ይቻላል፡፡ ችላ ከተባለ ግን ነገ የሚሆነው ከዚህም የከፋ ይሆናል፡፡ የአንድ ጊዜ ቃጠሎ ብዙ ሊያስተምረን ሲገባ ደግመን ደጋግመን ያንኑ ስህተት መደጋገም የለብንም፡፡ ከትናንት ወዲያም መቃጠል፣ ትናንትም መንደድ፣ ዛሬም መክስልለመሆኑ መንደድ ስንት ጊዜ ነው? መንግሥት ለጉዳዩ ባለቤት ሆኖ ቅድሚያ ከጀመረው እልፍ አእላፍ ምእመናን እና በጎ አድራጊዎች ከጎኑ እንደሚሰለፉ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለዚህም ባለቤትነቱን ሊያሳይ ይገባል፡፡

ከዲ/ን አባይነህ ካሴ

No comments:

Post a Comment