Thursday, September 8, 2011

ምን ዓይነት ለውጥ ለቤተ ክርስቲያን?



 (ለግልጽ ውይይት የቀረበ)
by Deje Selam on  September 8, 2011
  • ቤተ ክርስቲያንን ችግር በግልጽ አውጥቶ መነጋገር ገመና እንደመግለጥ የሚቆጠርበት ጊዜ አልፏል
  • አሁን የምንደብቀው፣ ብንደብቀውም የሚጠቅመን ገመና የለም
  • እጅ መጠቋቆሙ ለውጥ አያመጣም
  • ምእመናንን በስፋት ወደ አስተዳደር ማምጣት የዘላቂው መፍትሔ አካል ተደርጎ መታየት ይኖርበታል
  • በያዝነው መንገድ ከቀጠልን ግን የዛሬ አምስት ዓመት የምንነጋገርው ከአሁኑ በባሰ አዘቅት ውስጥ ሆነን እንደሚሆን ለመገመት ነቢይነት አይጠይቅም።
  • በትዕግስት አንብቡት፤ ሚዲያዎችን ጨምሮ ለአባቶችም ለምእመናንም በማድረስ ተባበሩን።
(ደጀ ሰላም፤ ሰፕቴምበር 3/211)፦ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጨርሶ መደበቅና ማስተባበል እንኳን ከማይቻልበት ደረጃ የደረሰው የቤተ ክርስቲያናችን ውስጣዊ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል። እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ ነገሩን በተቻለን ቅርበት ስንከታተል ቆይተናል። በየሚዲያው የሚወጡትን ጽሑፎች፣ ዜናዎች እና ቃለ ምልልሶችንም ሳያመልጡን ለመረዳት ሞክሬያለሁ። ሆኖም በሚዲያ የሚቀርቡት ብዙዎቹ አስተያየቶች ችግሩን በተረዱት መጠን ወይም መልክ በማንጸባረቅ ላይ የተወሰኑ ናቸው። ችግርን በትክክል መረዳት የመፍትሔው ግማሽ እንደመሆኑ ውይይቱ የሚወደድ ነው። የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከት የሞከሩ ፀሐፊዎችና ተናጋሪዎች ቢኖሩም ቅሉ ብዙውን ጊዜ ሐሳቦቹ ቅንጭብ በመሆናቸው አጠቃላይ ውጤታቸው በግልጽ የሚታይ አይደለም። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሷን ችግር የምትመረምርበት ተቋማዊ ዝግጅት የሌላት ሆና ትታያለች። ምእመናንና ሌሎች ተቆርቋሪ ዜጎችም ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አስተዋጽዖ የሚያደርጉበት ዕድል ዝግ ነው ማለት ይቻላል።


እነዚህ ችግሮች ሲያብሰለስሉን ቆይተዋል። ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመሆኑ በፊት በየደረጃው በአስቸኳይ ቀጥተኛና ጥልቅ ውይይት መደረግ እንዳለበት እናምናለን። እንደ ዜጋ፣ ከዚያም በላይ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጅ የራሳችንን ሐሳብ ለማካፈል ቀርጠን ስንጽፍ የቆየነው ከዚህ በመነሣት መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻችን ይታወሳል። ይህን ሐሳባችንን ሌሎች ሚዲያዎችም እንደሚያስተናግዱት ተስፋ እናደርጋለን። ወደ ሐሳቡ ከመግባታችን በፊት ሦስት ነገሮችን በማሳሰቢያ መልክ መግለጽ እንወዳለን።

አሁን የምንደብቀው፣ ብንደብቀውም የሚጠቅመን ገመና የለም። የቤተ ክርስቲያንን ችግር በግልጽ አውጥቶ መነጋገር ገመና እንደመግለጥ የሚቆጠርበት ጊዜ አልፏል። ችግሩን ለመረዳት፣ መፍትሔ ለመፈለግ እስከጠቀመን ድረስ ማናቸውንም ነገር በግልጽ መጥቀስ እንደበጎ ሊታይ ይገባዋል ብለን እናምናለን። እንደተለመደው በመሠረታዊው ችግር ላይ ሳይሆን በእንጭፍጫፊ እና ሁለተኛ ደረጃ እንከኖች ላይ ጉልበታችንን፣ ጊዜያችንን አናባክን።


የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊና መንፈሳዊ ችግር እኛ ሰዎች የፈጠርነው ችግር ነው። ስለዚህ ችግሩን የመፍታት ቀዳሚ ኃላፊነት ያለብን እኛው ነን። በዚህ ዓላማችን እግዚአብሔር እንዲረዳን እንማጸናዋለን፣ ያለጥርጥርም ይረዳናል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አሁን የገባችበት ቀውስ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነና የእኛ ጥረት ለውጥ እንደማያመጣ ማሰብ በሰውም፣ በታሪክም ይሁን በፈጣሪ ፊት ከኃላፊነት የሚያድነን አይሆንም። ስለዚህ ነገሩ የግልና የጋራ ኃላፊነታችንን የመወጣት ኅሊናዊና አገራዊ ግዴታ ነው።

አንዳንድ ሰዎች አሁን እየታዩ ያሉትን ችግሮች አምኖ ተቀብሎ ስለ መፍትሔ ከመነጋገር ይልቅ እጅ በመጠቋቆም ወይም በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ ጠንካራ ተሞክሮዎችን ብቻ በማንሣት የራሳቸውንም የአድማጮቻቸውንም ትኩረት ሲያባክኑ ይታያል። እነዚህን ሰዎች “ታሪክ ውስጥ ከመደበቅ ወጥታችሁ እውነትን ተጋፈጡ፤ እጅ መጠቋቆሙ ለውጥ አያመጣም” ልንላቸው ይገባል። አሁን የተረት ጊዜ አልፏል። አሁን ያለችውና የምንነጋገርባት ቤተ ክርስቲያን በተቋማዊ ቅርጿ ከጥንታዊቷ የተለየች ናት። በቀደመው ዘመን የነበረ ጥሩ ነገርም ለአሁን ችግር መቅረፊያ ትምህርት እንጂ የአሁኑን መሸፈኛ ወይም ማረሳሻ ሆኖ መቅረብ የለበትም። እንዲህ ማድረግ አሁን ያለው ችግር እንዲባባስ ጊዜ መስጠት ነው።

ለውይይት እንዲረዳን በአራት ጭብጦች ላይ እናተኩራለን። የችግሩ ተቋማዊ አድራሻ፣ የችግሩ ምንጭ፣ ያለው ችግርና የሚያስከትለው አደጋ፣ ምን ዓይነት ለውጥ እንደሚያስፈልገን ማለትም አዝጋሚ ወይስ አብዮታዊ? የሚሉትን ጭብጦች እናነሣለን። በሚገባ የሚታወቁ ችግሮችን ወደመዘርዘር ሳንገባ እያጠቃለልን ለማቅረብ እንሞክራለን። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያተኮርነው በውስጣዊ ችግሮች ላይ ብቻ ነው። ግምገማውን የተሟላ ለማድረግ ውጫዊ ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ እንረዳለን። ሁሉንም ነገር በዚህ አጭር ጽሑፍ ማጠቃለል ግን የሚሞከር አልሆነልንም። ውስጣዊውንም ቢሆን በጨረፍታ ነው።

ውይይታችንን ለመጀመር ብዙ አማራጮች አሉን። የችግሩን መጠን፣ በማስከተል ላይ ያለውን ጉዳትና ያዘለውን አደጋ መተንተን የበለጠ ተገቢ ይመስለናል። የምንመርጠው የመፍትሔ አቅጣጫም በዚህ ላይ የተመሠረተ ይሆናል። በችግሩ ስፋት፣ ባሕርይ እና አደጋ ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤና አቋም ካልያዝን በመፍትሔዎቹ ላይ መስማማት አንችልም። እዚህ ላይ በሁሉም ላይ ፍፁም አንድ ዓይነት መረዳትና መግባባት መፍጠር አለብን። ሙሉ በሙሉ ግን ይቻላል ማለታችን አይደለም።


የችግሩ ተቋማዊ አድራሻ
አሁን ቤተ ክርስቲያንን እንደጎርፍ ያጥለቀለቁትን ችግሮች በተቋማዊ አድራሻቸው ብንመድባቸው ስምንት ዋና ዋና ቦታዎችን እናገኛለን። እነዚህ ተቋማት እንደየደረጃቸው ቁልፍ የአመራር እና የአፈጻጸም ሚና የሚጫወቱ ናቸው። ያለእነዚህ ተቋማት የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ሕይወት ማሰብ አይቻልም። የአንዱ በሽታ የሌላውም ሕመም ነው፤ የአንዱ መዳከም ለሌላው ውድቀት በር ከፋች ነው። ተቋማቱ በዓላማቸው፣ በሥራ እሴቶቻቸው እና በራዕያቸው አንድ ዓይነት እንደሆኑ ይታመናል። ወይም የአንድ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ብልቶች እንደመሆናቸው መጠን እንደዚያ እንዲሆኑ ይጠበቃል። አስቸኳይ ትኩረትና መሠረታዊ ለውጥ የሚፈልጉት ተቋማቱ የሚከተሉት ናቸው።

  1. ቅዱስ ሲኖዶስ፣
  2. ቅ/ ፓትርያርኩ፣
  3. ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣
  4. አኅጉረ ስብከት፣
  5. አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳደር፣
  6. ሰበካ ጉባኤ፣
  7. ማኅበረ ካህናት እና
  8. ሕግጋተ ቤተ ክርስቲያን፣
ስለ እነዚህ ተቋማት ዝርዝር ድክመት መጻፍ ሰፊ ቦታ የሚወስድ ነው። አብዛኛውም ተደጋግሞ የተነገረ ነው። ቀዳሚዎቹን ሰባት ተቋማት አስተሳስረው የሚይዙት መጠባበቂያዎች ሕግጋት ናቸው። ሕግጋት ስንል በተለይ አስተዳደርን፣ የአስተዳደር ዘይቤን የሚመለከቱትን ነው። አሁን ከሰፈነው ዝብርቅርቁ የወጣ የሚመስል፣ ጠያቂና ተጠያቂ የማይለያዩበት፣ የዕውቀትና የሥራ ጥራት መለኪያ ደብዛው የጠፋበት ሁኔታ በመነሣት የችግሮቹ አንዱ ምንጭ ከሕግጋትና ከአፈጻጸማቸው ጋር የተቆራኘ እንደሆነ አያጠራጥርም። (ሕግጋትን እንደ አንድ “ተቋም” መመልከት በማኔጅመንትም ይሁን በኅብረተሰብእ ሳይንስ የተለመደ ነው።) እዚህ ላይ በሥራ ላይ የሚገኘው ቃለ ዐዋዲም ይሁን ሌሎች መመሪያዎች/ ሕጎች ከነድክመቶቻቸውም ቢሆን በተግባር ላይ አልዋሉም። አንድ ሕግ ተግባር ላይ ሊውል ካልቻለ ሕጉ ራሱ ችግር ሊኖርበት እንደሚችል አመላካች ነው። ችግሩ “የአፈጻጸም ነው” ማለት ወደ ምን ዓይነት የስሕተት አዙሪት እንደሚከት ከኢሕአዴግ መማር ይቻላል።

የችግሩ ምንጭ
ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ተቋማት ከሥራና ከመፍትሔ ማዕከልነት ወደ ብክነትና ወደ ችግር መፈልፈያነት የተለወጡበት ብዙ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ታሪካዊ፣ ግላዊ፣ ቡድናዊ፣ ተቋማዊ እና ውጫዊ ሁኔታዎች የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ። ዝርዝሩን ለማወቅ ጠለቅ ያለ ጥናት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ግን የታዘብናቸውን ከመዘርዘራችን በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር ሁሉ በአሁኑ ፓትርያርክ የተፈጠረ አድርጎ መረዳት የተሳሳተ መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን። አሁን ተባብሶ ገነፈለ እንጂ ችግሮቹ ቀድሞም የነበሩ ናቸው። ችግሮቹን ከታሪካዊ መሠረታቸው ለመረዳት ካልሞከርን የመፍትሔ አማራጫችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራን ይቻላል። አቡነ ጳውሎስ ከመንበራቸው ቢነሱ ችግሮቹ በአንድ ቀን ተንነው አይጠፉም። በእርግጥ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ዕድል ይሰጣል። አሁን በምንታዘበው መልኩ ግን አቡነ ጳውሎስን ራሳቸውን በውድም በግድም የመፍትሔው አካል ማድረግ ይቻላል፤ ይገባልም።


1. የተቋማዊ አሠራር ባህል አለመዳበር
በታሪካዊና በግለሰባዊ ምክንያቶች የተነሣ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የተቋማዊ አሠራር ባህል አልዳበረም። ከተጻፈ ሕግና መመሪያ ይልቅ ልማድ ወይም የአንድ መንፈሳዊ አባት/ ካህን ቃል የበለጠ ይከበራል። ይህ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አስተዳዳሪ ድረስ የሚታይ ባህል ነው። ሰዎች ይህን የሚያደርጉት በቅንነት ወይም ደግሞ የግል ፍላጎታቸውን (ጥቅማቸውን) ለማስከበር ሊሆን ይችላል። በምንም መነሻ ያድርጉት ግን ባህሉ የምናከብራቸው ካህናት ቃልና ፍላጎት ሕግን እንዲተካ መንገዱን አመቻችቷል። በዚህም ምክንያት በሕጉና በመመሪያው መሠረት ብቻ እሠራለሁ የሚለው አገልጋይ በየትኛውም የቤተ ክርስቲያናችን ተቋም ረጅም ጊዜ መቆየት አይችልም። በሰበካ ጉባኤ አባልነት እንኳን በዚህ መንገድ መሥራት ትልቅ ተጋድሎን ይጠይቃል።

በአጠቃላይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሕዝቡ ውስጥ የዳበረው አመለካከት የሚቀበላቸውን ሰዎች ቃል ከሕግ ባላይ እንዲያከብር የሚያበረታታ ነው። አንድ የምናከብረው ካህን የሃይማኖት ሕጸጽ ቢገኝበት ፈጽሞ አንታገሰውም፤ የሃይማኖት ሕጸጽ ካልተገኘበት ግን የፈለገውን ሕግ እየጣሰ ቤተ ክርስቲያንንና በዙሪያው ያሉ ምእመናንን ቢጎዳ እንኳን ቃሉን ከማክበር አንቆጠብም። አንዳንድ ጊዜ የምንሰማው ጉድ ሰውየው ሃይማኖቱን ቢክድ ከሚሰማን የበለጠ የሚያሳዝን እና የሚያሳፍር ነው። ነገር ግን ስለቤተ ክርስቲያን ሕግም ይሁን ስለ ኅሊና ብሎ ይህን መሰሉን ሰው “ተመለስ” ብሎ የሚገስጽ ሰው ከሺህ አንድ አይገኝም። ሕግ አውጪም፣ ሕግ ተርጓሚም፣ ሕግ አስፈጻሚም አንድ ሰው፣ አንድ አካል የሆነበት ተቋም ከቀውስ የሚታደገው አይኖርም።

ይህ የተሳሳተ አመለካከት፣ እምነትና ባህል በረጅም ጊዜም ቢሆን መቀየር ይኖርበታል። ይህም ለአባቶች የምንሰጠው መንፈሳዊ ክብር መነሻና ትርጉሙ ምንድን ነው? የክብራችን መጀመሪያና መጨረሻስ የት ነው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ዘላቂ ትምህርት እንደሚያስፈልገን ያሳያል። 

2. የተጠያቂነት አለመኖር
በተራ ቁጥር አንድ የተገለጸው ችግር እዚያ አያቆምም። ሕግ የሚጥሱ ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራርና ባህልም የለም። ይህም ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ የተንሰራፋ ባህል ነው። ለዚህ አራት ምክንያቶች አሉ። አንዱ ምክንያት ተጠያቂነትን አስገዳጅ የሚያደርግ የሕግና የተቋም መደላድል የለም። ሁለተኛው ምክንያት በተጠያቂነት እና በይቅርታ ጽንሰ ሐሳቦች ዙሪያ ጥርት ያለ አመለካከትና ግንዛቤ በብዙዎች ዘንድ የለም። ሦስተኛ ምክንያት በተለይ ካህናትንና አገልጋዮችን ተጠያቂ ማድረግ ለእነርሱ ያለንን ክብር እንደመካድ አልፎም ቤተ ክርስቲያንን እንደመዳፈር ይወሰዳል። ሁሉም በስሜትና በቆራጥነት “ካራውን” የሚመዘው የሃይማኖት ሕጸጽ ሲባል ነው። አራተኛውምክንያት የመጠቃቀምና የመሸፋፈን ስትራቴጂ ነው። ሌባ ሌባን እንደማይከስ ሁሉ (ትርፉን እንካፈል ይላል እንጂ) በቤተ ክርስቲያንም “ደብቀኝ እደብቅሃለሁ” የሚለው የጥቅም ትስስር የገነነ ነው።

በፍርድ ቤትም ይሁን በአስተዳደራዊ መድረክ በተጠያቂነት መቅረባቸው አግባብ አይሆንም የምንላቸው ሰዎች ካሉ እነርሱን መጀመሪያውኑ ከአስፈጻሚነት የሥራ ምድብ ማራቅ ያስፈልጋል። ፓትርያርኩን ከዕለታዊ የሥራ አስፈጻሚነት በማራቁ ሐሳብ ጠቃሚ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። አንድ ፓትርያርክ በብር ማባክን፣ በሠራተኛ ምደባ በትንሹም በትልቁም ስሙ ሊነሳ፣ እርሱም እዚህ ውስጥ ሊገባ ፈጽሞ አይገባውም። ለፓትርያርኩም ለቤተ ክርስቲያኒቱም አይበጅም።

3. ሙያ፣ ባለሙያ እና ዓላማ
በታሪክ እንደምናነበው ቤተ ክርስቲያንን ከጠበቋት ጥንካሬዎች አንዱ ሙያንና ባለሙያዎቿን ማክበሯ ነው። ዛሬ ይህ በቦታው የለም። ሲጀመር አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት ራዕያቸው፣ ግባቸው፣ ዓመታዊ ዒላማቸው ወዘተ. ምን እንደሆነ በተጨባጭ የሚታወቅ ነገር ጥቂት ነው። አንድ አጥቢያ ወይም ሀገረ ስብከት ዕቅዱ ምንድን ነው? ዕቅዱ በምን ይመዘናል? ዕቅዱን እንዴት ያስፈጽማል … ከጥቅም ጋር ካልተያያዙ የማይታሰቡ ናቸው። ቢሮ መግባት፣ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆሞ መስበክ፣ ሕንጻ መገንባት ብቻውን የሥራው መጀመሪያም መጨረሻም የሚመስለው ይበዛል። ውድድሩ የበለጠ ገቢ መሰብሰብ እንጂ ሌላ መመዘኛ የለውም።

የዚህ አንዱ መሠረታዊ ችግር ሙያ እና ባለሙያዎች በቤተ ክርስቲያን ቦታ አለማግኘታቸው ነው። ሙያና ባለሙያ ሲባል በአብነት ትምህርት ቤቱ ዕውቀት መስክ ብቻ አይደለም። ከዚያ የባሰውና ቤተ ክርስቲያኒቱን እገደል አፋፍ ያቆማት እንዲያውም የሌላው ዕውቀት፣ ሙያና ሙያተኛ በቤተ ክርስቲያን መጥፋቱ ነው። ዛሬ በሥራ አመራር፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሶሲዎሎጂ ወዘተ ዓለም እጅግ ተራምዶ፣ ሁሉም ዓይነት ተቋማት የዚህ በረከት ተቋዳሾች ሆነው ቤተ ክርስቲያን ግን አሁንም በጾም ላይ ትገኛለች፤ ጾሙ ከተፈታ ስንት ዘመን አልፎት። እኛ ዘንድ አሁንም ካህን መሆን ወይም የነገረ መለኮት ዕውቀት ብቻውን ለማንኛውም ሥራ እንደሚያበቃ ይቆጠራል።

የትርጓሜ መምህሩ፣ የዜማው ሊቅ፣ የብሉይና የሐዲስ አስተማሪው ሁሉ የየራሱ ሙያ አለው። እነዚህ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን እንዲዘሩ አልተከበሩም፣ አልረዳናቸውም። ይብሱን ደሞ ቁምስናና ጵጵስና የአስተዳደር ሙያ ባለቤትነት ማዕረግ ተደርጎ ይቆጠራል። እነዚህ ሰዎች ጥሩ አመራር ባለመስጠታቸው በእነርሱ ብቻ አይፈረድባቸውም። ከዚህ የበለጠ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕውቀት፣ ልምድ እና ልምድ እና “ኤክስፖዠር” የላቸውም። ምናልባት በተወሰነ መልኩ ጥሩ ሥራ የሚሠሩ ቢኖሩም እንኳን በግል ብቃታቸውና ቀናነታቸው እንጂ በባለሙያነታቸው አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ብሩህ ልብ ያለው ቀና ሰው ደግሞ ብዙ ጊዜ አይገኝም።

ዛሬ ችግሩን ሁሉ እንዲፈታ የምንጠብቅው ቅዱስ ሲኖዶሳችን ብዙ ዕድሜያቸውን በገዳም ሕይወት ያሳለፉ ብፁዓን አበው የሚገኙበት ነው። ለእነዚህ አባቶች ንጹሕ ሙያዊ መረጃ፣ ትንተናና አስተያየት የሚሰጡ የየዘርፉን ባለሙያዎች አልመደብንላቸውም። ቀሪዎቻችን በየትምህርት ቤቱና በየሥራ ቦታችን የምናየው የሥራ ሒደት፣ የሰው ኀይል አስተዳደር፣ የሀብት አጠቃቀም ሳይንስ ለእነርሱ የምናስበውን ያህል ቅርብና ቀላል ሊሆን አይችልም። ምንም እንኳን መንፈሳዊ አባቶቻችን ቢሆኑም ሁሉ የተገለጠላቸው ቅዱሳን እንዳልሆኑም መርሣት አይገባም ነበር። እነርሱ ራሳቸውም ቢሆኑ “ሁሉን እናውቃለን” ሳይሉ ባለሙያዎችን በዙሪያቸው መሰብሰብ ይገባቸው ነበር። ይሄ ነገር በሁሉም ደረጃ መኖር ያለበት ሆኖ ይሰማናል። 

4. የምእመናን መገለል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ የአምልኮ ሥርዓት ምእመናንን በእጅጉ የሚያሳትፍ ነው። ከቅዳሴ የበለጠ የተከበረ ሥርዓት የለንም። ቅዳሴ ግን ያለ ምእመናን የተሟላ አይሆንም። የቅዳሴ ሥርዓቱ እያንዳንዱ ሂደት ምእመናን ያሉበት ነው፤ ከአሐዱ አብ ቅዱስ እስከ አሜን። የዘመናዊቷ ቤተ ክርስቲያን (መንበረ ፕትርክና ካገኘን ወዲህ ያለው ማለታችን ነው) ተቋማዊ አስተዳደር ግን በመዋቅሩም ይሁን በይዘቱ የካህናት፣ ይልቁንም የመነኮሳት ፍጹም የበላይነት የተንሰራፋበት ነው።

ቃለ አዋዲው (የቤተ ክርስቲያኒቱ ከአጥቢያ እስከ ሲኖዶስ የምትተዳደርበት ዋናው ሕግ) ለምእመናን ቦታ መስጠቱ የሚካድ ባይሆንም በመዋቅሩ ከታች ወደላይ ስንጓዝ የምእመናን ውክልናና ተሳትፎ በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ ሔዶ ደብዛው ይጠፋል። ከፍ ባሉት መድረኮች ለስሙ የሚወከሉት ምእመናን ይህ ነው የሚባል ዕውቀትና ልምድ ማካፈል የማይችሉ፣ ከአባቶች ቡራኬ ለመቀበል እንጂ የሐሳብ ፍጭት ለማካሔድ የማይችሉ ናቸው። ስለዚህ እንዳሉ መቁጠርም የሚቻል አይደለም። በአጥቢያ ደረጃ የሰበካ ጉባኤዎቹ አደረጃጀት ዞሮ ዞሮ በአስተዳዳሪዎቹ ፍጹም የበላይነት ሥር የሚወድቅ ነው። አስተዳዳሪዎቹ ደግሞ ቀደም ሲል በተጠቀሱት ምክንያቶች ትርጉም ያለው ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው ናቸው። በሰበካ ጉባኤ ለማገልገል ገብተው ተማርረው የወጡ ባለሙያ ምእመናን ብዙ ናቸው። ዛሬ አብዛኛው ምእመን በአጥቢያው ጉዳይ መሳተፍ የሚፈልግ አይደለም። ለምን ብሎ ነገሩን መመርመር ያስፈልግ ይሆናል።


የቤተ ክርስቲያኒቱን ማዕከላዊ አንድነት ከመጠበቅ አኳያ አሁን ያለው አሠራር የሚያስተምረን ነገር እንዳለ እናምናለን። ነገር ግን ምእመናንን በስፋት ወደ አስተዳደር ማምጣት የዘላቂው መፍትሔ አካል ተደርጎ መታየት ይኖርበታል። የቤተ ክህነቱ ሰዎቹ የተማሩ፣ ሌላው ምእመን ያልተማረ (ጨዋ) የነበረበት ማኅበረሰባዊ እውነታ ተቀይሯል። ዛሬ ዕውቀትን ከነገረ መለኮት መስክ አስፍተን ብንገመግም ብዙ ዕውቀት ያለው በቤተ ክህነት ሰዎች አካባቢ ሳይሆን በጥንቱ “ጨዋ” ምእመን ዘንድ መሆኑን እንገነዘባለን። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ይህን እውነት የሚቀበልና የሚጠቀምበት መሆን አለበት። የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር “ለጥቁር ራሶች” (ክህነት የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን በሽሙጥ የሚጠሩበት ስም ነው) በሩን እንዲከፍት ዘመኑ ያስገድደዋል።

ያለው ችግርና የሚያስከትለው አደጋ

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉትን ችግሮች በጥልቀት መመርመር ራሱን የቻለ ጥናት ይጠይቃል። በዚህ ጽሑፍ ለማንሣት የሚቻለው መሠረታዊ ችግር ይታይባቸዋል የምንላቸውን አካባቢዎች (ርእሰ ጉዳዮች) በአንኳሩ መጥቀስ ነው። መጀመሪያ ችግሮቹን ከዚያ አደጋዎቹን በአጠቃሎ እንጠቅሳለን። እነዚህም፦

ሀ. የክህነትና የሥልጣነ ክህነት አሰጣጥ (ከዲቁና እስከ ጵጵስና)፤
ለ. የዘመናዊ አስተዳደር መዋቅር፣ ዕውቀት፣ ሕግና አሠራር ያልዳበረበት አመራር (ከአጥቢያ እስከ ቅ/ሲኖዶስ)፤
ሐ. ብልሹ የካህናትና የአገልጋዮች አስተዳደር (ከሙዳየ ምጽዋት ቀበኛው አንስቶ ወሲባዊ ጥቃት እስከሚፈጽፈመው ድረስ
    ተንደላቆ የሚኖርበት አስተዳደር)፤

መ. ከፍተኛ የሀብት ብክነት እና ምዝበራ (ሀብት ሲባል ገንዘብ፣ ጊዜ፣ ዕውቀት፣ ጉልበት ያካትታል)፤
ሠ. ሥር የሰደደ በወንዝ፣ በብሔር፣ በገንዘብ እና በጥቅም ላይ የተመሠረተ አሠራር፤
ረ. አገሪቱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ እና ምእመናን የደረሱበት ዘመን የሚመጥን ሕግና አሠራር የሚፈጥር፣ የሚተገብር አካል
   በቤተ ክህነቱ አለመኖር፤
ሰ. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ፍላጎቶችን አቻችሎ መምራት የሚችል አመራር መታጣት፤
ሸ. ቤተ ክርስቲያኒቱን በባለቤትነት (ከፈጣሪ በተሰጠው አደራ መሠረት) የሚመራ፣ ስለወደፊቱ የሚጨነቅ፣ የሚያቅድ፣

የሚሠራ አመራር/ ትውልድ አለመፈጠሩ፤
ቀ. የመንፈሳዊነት እጦት በተለይ በአገልጋዮች ዘንድ (ይሄ ለመለካት የሚያስቸግር ነው፤ ደሞ ሁሉንም የሚመለከት አይደለም። ብዙ እውነተኛ መንፈሳዊ ሰዎች አሉ። አብዛኛው ግን በሥራው ተገልጦ ስናየው የምንታዘበው ሌላ ነው።) መኖር፤ የሚሉት ናቸው። ወጣም ወረደ፣ በዚህም አልነው በዚያ፣ ችግሮቹ ሁሉ ከእነዚህ የሚወጡ አይደሉም። ከዚህ የሰፋ፣ የችግሩን ክፋት የበለጠ የሚያሳይ ዝርዝር ሊሰጡ የሚችሉ ብዙዎች ይኖራሉ።

ለመሆኑ እነዚህ ችግሮች የደቀኑብን አደጋ ምንድን ነው? በእኛ አስተያየት፣ በአደጋዎቹ ላይ የሚኖረን አመለካከት የቤተ ክርስቲያናችንን መጻዒ ዕድል ሊወስን የሚችል ነው። እንዲሁ ለውይይት ያህል አሁንም አንኳር የምንላቸውን አደጋዎች እንዘርዝር። አንዳንዶቹ አደጋዎች ከወዲሁ መድረስ መጀመራቸውን ልብ ይሏል።

  • የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት ሊፋለስ ይችላል፤ ይህም ለውስጣዊ የሃይማኖት አንጃ (የመናፍቃን ቡድን) መፈጠር በር ይከፍታል፣
  • የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ማዕከላዊነት ሊናጋ ይችላል። (አጥቢያዎች፣ ወረዳዎች እና አህጉረ ስብከቶች በማዕከሉ ማለትም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አልመራም በሚሉ ቡድኖች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ። ልዩነቱ በጳጳሳት ዘንድ መድረሱን፣ የጳውሎስ የመርቆርዮስ መባል መጀመሩን ልብ ይሏል። ሌላስ ሊከተል አይችልምን? )፤
  • ቤተ ክርስቲያን በብሔር እና በፖለቲካ ልትከፋፈል ትችላለች (አልደረሰም ለማለት ያስደፍረናል?)፤
  • ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ያቆየቻቸው ጠቃሚ ትውፊቶች፣ ቅርሶች እና ታሪኮች ያለ ባለቤት ይቀራሉ፤ የወሮበላ መነገጃ ይሆናሉ። ይህም ከተጀመረ ሰንብቷል።
  • ልዩነቶቹ ወደ ምዕመናን ሊወርዱ ይችላሉ። ይህም አደገኛ ግራ መጋባት ይፈጥራል። ችግሩ ለአገርም ሊተርፍ ይችላል።
  • ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ ውስጥ ያላት ተደማጭነት፣ አስተዋጽዖ እና ክብር ጠፍቶ ለአሸማቃቂ የሐፍረት ታሪክ መልስ ለመስጠት የምንገደድበት ሁኔታ ይመጣል። ከዚህ ከፊሉ መፈጸሙን ልብ ይሏል።
  • ከሁሉም በላይ ደግሞ (እግዚአብሔር አይበለው እንጂ) የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ሕይወትና ክብር ይወድቃል፤

እነዚህን ማስቀረት ካልተቻለ ፈጣሪም፣ ታሪክም፣ አገርም፣ ልጆቻችንም ተባብረው እንደሚወቅሱን ቅንጣት ያህል አንጠራጠርም። እግዚአብሔር ይህንን ለሰው የማይቻል የሚመስለንን ውድቀት አሸንፈን የምንወጣበትን ጥበብ፣ ትዕግስትና እምነት እንዲሰጠን ዘወትር እንጸልያለን።


ደጀ ሰላማውያን፣ አንባቢዎች ከእኛ በበለጠ የሚያውቁትን የችግር በመዘርዘር ሐዘን ውስጥ ከትተናችሁ እንዳንሔድ ስለመውጫውም የምናስበውን እናካፍል።


ምን ዓይነት ለውጥ፤ አዝጋሚ ወይስ አብዮታዊ?
 ቤተ ክርስቲያን ለውጥ አያስፈልጋትም የሚል ሰው የሚገኝ አይመስለንም። ካለም እኔ የምንጽፈው ለእርሱ አይደለም። እሱ በምቾት እንቅልፉ እንዲቀጥል እንተወዋለን። “ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ” የሚባለው ፕሮጀክትም የእዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም። ከፍ ብሎ የተጠቀሱት ችግሮች ሲቀረፉ “ተሐድሶ” የሚባለው ነገርም ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል። አሁን በአጽንዖት መጠየቅ የምንወደው የሚያስፈልገው ለውጥ ምን ዓይነት ነው? የሚል ነው። ከብዙ ሰው ጋር ስንወያይ - ከጳጳሳትም ከምእመናንም ጭምር ብዙዎች የአፈታቱን አቅጣጫና ፍጥነት ሳያስቡበት እናገኛቸዋለሁ። በደምሳሳው ግን አዝጋሚ የሆነ የችግር አፈታት ሒደት የሚመርጡ ናቸው። ሲፈሩም ይታያሉ። “አዝጋሚ ለውጥ ስንት ዓመት የሚፈጅ ነው?” ሲባሉም ቁጥር መናገር ይከብዳቸዋል። በእኛ አመለካከት ደግሞ የችግሩ ስፋት፣ ጥልቀት እና የሚያስከትለው አደጋ ሲታይ “አዝጋሚ” የሚባለው አቅጣጫ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” የሚያሰኝ እንዳይሆን ስጋት ይገባናል።

ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው አደጋዎቹ መታየት ጀምረዋል። አንዳንዶቹ ደንድነዋል። ችግሮቹ በረጅም ዘመን የተጠራቀሙ እንደመሆናቸውም በረጅም ሒደት ብቻ ይፈቱ ቢባል በእነዚሁ ችግሮች ተጠልፎ እመንገድ መቅረት ይኖራል። በጠቅላይ ቤተ ክህነቱም፣ በአጥቢያም የሚቀርቡ ሐሳቦች እየተኮላሹ የሚቀሩት በዚሁ በተደላደለው በሽታ እየተጠለፉ ነው። (“አብዮት” የሚለውን ቃል ከደም መፋሰስ ወይም ከዓመጻ ጋራ እንዳይያያዝብን እንማጸናለን። “ሥር ነቀል” የሚለውን ቃል መጠቀም አልፈቀድንም። ችግር ችግሩን ብቻ እየመረጠ የሚነቅል ከሆነ እንኳን ባልከፋ።)

እኛ እንደምንለው፣ ቤተ ክርስቲያን የአሥር ዓመት መሠረታዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ወይም አብዮት መጀመር ይገባታል። አብዮት በሚለው ፈንታ ሌላም ስም መስጠት ይቻላል። ዘገምተኛ ለውጥ የሚሉት ሰዎች በዚህ ከተስማሙ እኛ ከስሙ ቅሬታ የለንም። ነገር ግን በአዝጋሚ አካሄድ ከተባሉት ችግሮች በ10 ዓመት ሩቡን እንኳን መፍታት አይቻልም። ስለዚህ አብዮታዊ ወይም መሠረታዊ እና ፈጣን ለውጥ ይሻላል።

ለውጡ ፈጣን መሆን የሚገባው በምን ምክንያት ነው?

ሀ. በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጡት አደጋዎች እየተፈጸሙ፣ በብዛትም፣ በዓይነትም፣ በሚያስከትሉት ውጤትም እየጨመሩ
    መምጣታቸው በገሐድ መታየት በመጀመሩ፤
ለ. ችግሮቹ እርስ በርስ የሚመጋገቡና የሚደጋገፉ በመሆናቸው፣ አንዱን ሳይነኩ ሌላውን ማቡካት ትርፉ ድካም ስለሆነ እንዲሁም፣
ሐ. አሁን የተንሰራፋው ሥርዓት ብልሹ ቢሆንም ተቋርቋሪዎች እንደማያጣ በመረዳት፤ ለእነዚህ ተቆርቋሪዎች ረጅም ጊዜ መስጠት ለውጡን ያለጥርጥር ስለሚያደናቅፍ ነው።

ከችግሮቹ መጠን አኳያ 10 ዓመት ብዙ አይደለም። ለውጡ አብዮታዊ እንዲባል የተመረጠበትም ምክንያት ከጊዜው ይልቅ በሂደቱ የማይመለስ መሆን እና በሚፈልገው መንፈሳዊ ቆራጥነት ነው። በጥበብ፣ በማስተዋል፣ ነገር ግን በተቻለ ሰብዓዊ ፍጥነት መጓዝ ይጠይቃል። የቀረውን ደሞ ለቤቱ ከእኛ በላይ ቀናዒ የሆነው አምላካችን ይሞላልናል።

ይህንንስ አልን፤ “በ10 ዓመት ምን ምን ይሠራ?” የሚል ጥያቄ ይኖራል። እኛ ነገሩን ሁሉ ማወቅ አይቻለንም። እናውቃለን ብንልም እየዋሸን ነው። ይልቅ አንኳር አንኳር ጥቆማዎች እንስጥ።

የ10 ዓመት ለውጥ አመላካቾች

  • በመጀመሪያው ዓመት የሲኖዶስ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ መክሮ፤ አንድ የለውጥ ጉባኤ ኮሚቴ ይሰይም።
  • ይህ ኮሚቴ ከአራት ወር ባልበለጠ ጊዜ የቤተ ክህነቱ ተቀጣሪ ያልሆኑ ነጻ ባለሙያዎች ብቻ የሚገኙበት፣ ከ10 የማይበልጡ ሰዎች ያሉበት የጥናት ኮሚቴ ያቋቁም። ለኮሚቴውም የሚያስፈልገውን ያህል ገንዘብ፣ ያለምንም ስስት፣ ጠቀም ያለ በጀት ይመደብለት። ይህ የጥናት ኮሚቴ ምን ምን እንደሚሠራ በዝርዝር በጽሑፍ ይሰጠው። በአጠቃላይ ሥራው ያለውን ችግር ዘርዝሮ፣ በክፍል በክፍል ተንትኖ ማቅረብ ነው። ከዚሁም ጋራ የመፍትሔ አማራጮችን ያቀርባል። ይህንንም የሚያደርገው በሳይንሳዊ የጥናት ዘዴዎች፣ መረጃ ሰብሳቢዎችን አሰማርቶ፣ ተንታኞችን ቀጥሮ፣ ለመፍትሔ አማራጮች ወጥቶ ወርዶ (ካስፈለገው ሌላም አገር ተጉዞ) ይሆናል። እዚህ ውስጥ ማንኛውም የቅ/ ሲኖዶስ አባል ወይም የቤተ ክርስቲያን ሠራተኛ ለአስረጅነት ካልሆነ በኮሚቴ አባልነት ባይገባ ጥሩ ነው እንላለን። በመረጃ ስብሰባውና ትንተናው የተማሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ተሳትፎ ብዙ ይጠቅማል። ይህ የጥናት ኮሚቴ ሦስት ወራት ለዝግጅት፣ ከ8-12 ወራት ለዋናው ሥራ ይሰጠው።
  • የጥናት ጉባኤው ውጤቱን ለውይይት ያቀርባል። ውይይቱም በየደረጃው የሚካሄድ ይሆናል። በሁሉም አጥቢያ ማድረግ የማይቻልም የማያስፈልግም ይሆናል። ከካህናት፣ ከአብነት መምህራን፣ ከገዳማውያን፣ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችና መምህራን፣ ከሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ ከተለያዩ ማኅበራት ጋራ በተናጠልም በጋራም በጥናቱ ላይ ተወያይቶ ሐሳቦችን ማዳበር።
  • የጥናት ጉባኤው በውይይቶቹ የተገኙትን ነጥቦች አጠቃሎ ተንትኖ ከጥናቱ ጋራ በአባሪነት ያስቀምጣል። ከጥናቱና ከውይይቶቹ በመነሣትም የመጨረሻ የውሳኔ ሐሳቦችን ከአማራጮች ጋራ ያቀርባል። ይህም ከየአኅጉረ ስብከት የሚውጣጡ ተካፋዮችና ሁሉም ብፁዓን አበው በሚገኙበት የመጨረሻ ውይይት ይካሄድበታል። ብፁዓን አበው በዚህ ጉባኤ እንዲገኙ የሚገባው የጥናቱን ግኝት እንዲሰሙና ለመጨረሻ ውሳኔያቸው እንዲያግዛቸው ነው።
  • በመጨረሻ ጉዳዩ ለውሳኔ ለቅዱስ ሲኖዶስ ይቀርባል። ጉባኤው ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት በጋራ ለሦስት ቀን ሱባኤ ይይዛል። ከዚያም የመፍትሔ አማራጮቹን አስቀምጦ ወደ ቀጣዩ የተግባር እንቅስቃሴ ይገባል።
  • በተመረጡት አማራጮች መሠረት አዲሱን ሂደት የሚመራ፣ የሚቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን ያለው ጊዜያዊ አካል ይቋቋማል። ይኸው አካል ከአንድ ዓመት ያልበለጠ የትግበራ ዝግጅት፣ ጊዜና በጀት ይሰጠዋል። በዚህም ጊዜ ሕጎችን የመከለስና አዳዲሶቹን የማዘጋጀት፣ አወቃቀሮችን የመፈተሽና የመቀየር/ የማሻሻል ሥራ ያከናውናል፤ ሙከራ የሚደረግባቸውን አጥቢያዎች፣ አኅጉረ ስብከት ይመርጣል፤ በጀቱን አቅርቦ ያጸድቃል። በውስጣዊ አሠራርና ሕግ ሳይሆን በሌሎች አማራጮች የሚፈቱ ችግሮችን ለምሳሌ የተለያዩ አባቶችን የማስታረቅ፣ ከመንግሥትና ከሌሎች አካሎች ጋራ ያለውን ግንኙነት የሚመለከቱ አካሄዶችን አርቅቆ ለጳጳሳቱ የለውጥ ጉባኤ ያቀርባል። እርሱም በተራው ለሲኖዶሱ እያቀረበ ሂደቱ ይቀጥላል።
  • የሙከራ ትግበራው ከ6-9 ወራት ተካሂዶ፤ በገለልተኛ ወገን ግምገማ ይደረጋል። ከግምገማው ውጤት በመነሣት በሕጎቹ፣ በአሠራሮቹ ወዘተ ላይ ማስተካከያ ተደርጎ ሪፖርት ይቀርባል። ከዚህ በመነሣት ቅዱስ ሲኖዶሱ በሕጎቹና አሠራሮቹ ላይ መክሮ ያጸድቃቸዋል፤ የሥራ መመሪያም ይሆናሉ
  • በአዲሶቹ አመለካከቶች፣ ሕጎች፣ አሠራሮች ላይ በየደረጃው በየክፍሉ ሥልጠና ይሰጣል። ጊዜያዊ አካሉም የሥራውን ሪፖርት አቅርቦ፣ ቀጣይ ሥራዎቹን ለሚመለከታቸው አካላት አስረክቦ ይሰናበታል፣ ይበተናል።
  • በአምስተኛው ዓመት በሁሉም አኅጉረ ስብከትና የወረዳ ቤተ ክህነት ደረጃ አዲሱ አሠራር ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ መዋል ይጀምራል። ይህ ዓመት ከሞላ ጎደል የሙከራ ጊዜ ነው የሚሆነው። ሌሎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማትም በየፊናቸው የየራሳቸውን አዲስ አሠራር እንዲሁ ይጀምራሉ። በዓመቱ መጨረሻ ተቋማቱ በአዲሱ አሠራር ላይ ሪፖርታቸውን ያቀርባሉ። ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሪፖርቱን መርምሮ የቀጣዩን አምስት ዓመት አፈጻጸም ዕቅድ ይነድፋል። ሁለተኛው አምስት ዓመት/ ምዕራፍ አሁን ያለው ብልሹ አሠራር ከሥሩ መነቀል የሚጀምርበት ነው። ከፍተኛ ትግስት፣ ጥበብና ጽናት ይፈልጋል። ወሬው ወደ ተግባር የሚቀየርበት ስለሚሆን ውጊያውም ያይላል።
  • በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ቤተ ክርስቲያናችን በአስተዳደራዊና በመንፈሳዊ ቁመናው ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገርበትን ዘመን በቁርጠኝነት ለመቀበል የምትዝጋጅበት ነው።

ይህ አሥር ዓመት ለብዙ ሰዎች በጣም ረጅም እንደሚመስል እናውቃለን። ነገር ግን ሥራ ከተሠራባቸው ረጅም አይደሉም። እጅግ ቀርፋፋ የሆነ አስተሳሰብና አሠራር ለረጅም ዘመናት በሰፈነበት ተቋም ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ለመጀመር ከዚህ ያጠረ ጊዜ የሚበቃ አይመስለንም። ከዚህ ባጠረ ጊዜ (ዋናው ጊዜ የመጀመሪያው አምስት ዓመት ነው) የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ ሕይወት የሚነካ መሠረታዊ ለውጥ መጀመር ከተቻለ ደስታችን ነው።

እንግዲህ እኛ ያለንን አካፈልን። አንዳች የሚረባ ነገር እንዳለበት ከእኛ በተሻሉ ሰዎች ልብ ያድርና ለፍሬ ይበቃል። የደካማ ሰዎች ከንቱ ጩኸት ከሆነም እንዲሁ ይቀራል። ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል የምንለውን በማስተዋል የምንነጋገርበትና የምንፈጽምበት የመንፈስ ቆራጥነት ካለን ይህን ዘመን እንሻገረዋለን። በያዝነው መንገድ ከቀጠልን ግን የዛሬ አምስት ዓመት የምንነጋገርው ከአሁኑ በባሰ አዘቅት ውስጥ ሆነን እንደሚሆን ለመገመት ነቢይነት አይጠይቅም።

የአባቶቻችን አምላክ ይርዳን። አሜን።

No comments:

Post a Comment