Friday, September 9, 2011

ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ


እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ ዘመነ ማቴዎስም፣ ዘመነ ማርቆስም፣ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡
ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍ «የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልእከተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጅ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ» ተብሎ በኢሳይያስ እንደ ተነገረ የነቢዩ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነሥቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ ለኃጢአት ሥርየት እየሰበከ መጣ ብሎ በዘመነ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ገልጾታል፡፡ /ማር.1.40፤ኢሳ.40.3-4/፡፡ 

የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተክርስቲያን አበው የበዓላቱን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ አባቶች ደንግገዋል፡፡ / ድርሳነ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1ጠ 3/ ይህንንም በዓል አባቶቻችን በርእሰ ዓውደ ዓመት ማክበር እንደሚገባ አስበው ያደረጉት ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ሆኖ አይደለም፡፡ ለአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዓውደ ዓመት «ቅዱስ ዮሐንስ» ይባላል፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡ 

ከዚህ በመቀጠል በዓሉ በተለያየ ስያሜ ስለመጠራቱና ትርጓሜያቸውን እንመለከታለን፡፡ 

ዘመን መለወጫ 

አስቀድመን ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ማንነትና የዘመን መለወጫ መግቢያው ላይ በስሙ ስለመጠራቱ ተመልክተናል፡፡ ዘመን መለወጫ ደግሞ ለምን እንደተባለና ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ያትታሉ፡፡ ሲያትቱም ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱንም ጠንቀቀው ቢቆጥሩት 364 ቀናት ይሆናል፡፡ ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትን ፈጠረ ይላልና /ሔኖክ.21.49/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድረገው የአቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡/ኩፋ.7.1/ 

በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡ 

እንቁጣጣሽ 
ዓመታት ተፈጽመው አዲስ ዓመት ስንጀምር ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ፣ እንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜው አመጣጥ ወይመ ጥንተ ታሪክ በመጀመሪያ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪካ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪካ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኃ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡ ሁለተኛው የሀገራችን ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ዜና ጥበብ እየሰማች ስታደንቅ ትኖር ነበር፡፡ በጆሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ዓይታ ለመረዳት ስለፈለገች በግመሎች ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ በኢየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ ከንጉሡ ሰሎሞንም ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገጸ በረከት ከሰጠችው በኋላ ብዙ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ላይ ሰውሮ ሁሉንም ገለጸላት፡፡ ቤተ መንግሥቱንም በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ ዕቃዎችን ሁሉ አስጎበኛት፡፡ ሲያበቃ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ አበረከተላት/ሰጣት/፡፡ ወሩም ወረኃ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው መጥቷል፡፡ አሁን ከሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት ደርሶ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሚከበረውም መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ አንድም «ዕንቁ ዕፅ አወጣሸ» ብሎ የአበባውን መፈንዳትን ያስረዳናል፡፡ 


በዚህ በአዲሱ የአራተኛው ሺሕ መግቢያ ላይ እንገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አራተኛውዓመተ ምሕረት ያሳለፈቻቸውን መልካም ሥራዎችና የደረሰባትን መጥፎ ሥራዎችን አልፋ አሁን ላለው ትውልድ ደርሳለች፡፡ ይሕ ትውልድ ደግሞ በአራተኛው ሺሕ ዓመት እምነቷን፣ ሥርዓቷን፣ ትውፊቷን አውቆ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለበት፡፡ 

ለዚህም የሚረዳውን ገዳማትና አድባራትን በማጠናከር ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ዘመናዊ አስተዳደር በመዘርጋት ከእኅት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ጥሩ ግንኙነት በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል፡፡ 

ሺሕ ዓመቱ ሲለወጥ በዋዜማው ላይ በምንገኘኝበት ወቅት በእነዚህ ነገሮች ላይ ተቀራርቦ በመሥራት የሰው ዘር በሙሉ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
by ተዋህዶ ሀይማኖታችን
በዳዊት ደስታ 

No comments:

Post a Comment