ሰው በልጇ ስም እያፈረ እንዴት አማልጂኝ ብሎ ይለምናል እንዴትስ በረከቷን ይሻል....ቀሲስ አሽናፊ ገብረማርያም
መልስ ከታምራት ፍስሀ
“(ከቀሲስ አሽናፊ ገብረማርያም )ሰላም ለሁሉ፤-እንኳን አደረሳችሁ፡፡ እመቤታችን በምድር ላይ ጌታችን ኢየሱስን ወልዳ አቅፋ አጥብታው አዛው ታዛው እቅፏ ውስጥ አስተኝታው አጥባው አልብሳው አጉርሳው ስማው…. በተግባር በኑሮ ሰብካው አገልግላው በብዙ መከራ ለኛ ሰጥታናለች፡፡ ኢየሱስን የምትወዱ ከእመቤታችን ጋር በተግባር እየተባበራችሁ ነውና በርቱ! ተሰድባለች ከመቅደስ ተባራለች ከሃገር ተሰዳለች በትትና ስለራሷ ስላልተናገረች በዙ ነቀፌታን ታግሳለች፡፡ ሰው በልጇ ስም እያፈረ እንዴት አማልጂኝ ብሎ ይለምናል እንዴትስ በረከቷን ይሻል”
መልስ ከታምራት ፍስሀ
በእውነት ይህን መልእክት አንድ የፌስቡክ ጉደኛየ እንድመለከተው ሲፅፍልኝና ሳነበው በጣም አዘንኩ በተለይ የፅሁፉ ባለቤት የቤተክርስቲያናችን መምህር መሆኑን ሳስብ ደግሞ ተናደድኩ፡፡ እውነት ግን እንዲህ ብሎ መልእክትን ማስተላለፍ ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? እንደዚህስ ማለት ምን ይሰራል? ይህስ በስህተት የተባለ ይሆን? ወይንስ ይህ በማር የተለወሰ መርዝ ነውን? በዚህም ምክንያት በአንድ ወቅት “ኢየሱስ የሚለውን ስም ሽሽት” በሚል የሰጠሁትን አስተያየት ትንሽ አሻሽየ አወጣሁት፡፡ “ኢየሱስ” ብሎ መጥራት እውቀት የሚመስላቸው ነገር ግን
“ጌታችን መድሃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብሎ መጥራት ደግሞ ስህተት መስሎ የሚሰማቸውን ምን ትሏቸዋላችሁ?ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ፣ የነገስታት ሁሉ ንጉስ ፣ የጌቶች ሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስታስተምር የኖረችና የምትኖር ናት ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም ከስሞች ሁሉ የሚበልጥ የተወደደ ስም ነው ፤ የተወደደ አምላክ ጌታችን መድሃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ በምድር የሚኖሩትን ፍጥረታት በጥበቡ የፈጠረ ነው ፤ እርሱ ለአብርሃም የተገለጠ ፣ ለሙሴ ህግን የሰጠ ፣ ቀይ ባህርን የከፈለ ፣ ዮርዳኖስን ያሻገረ ፣ ወደ ምድር የወረደ ፣ ወደ ሰማይም የወጣ ፣ ለመፍረድም የሚመጣ እርሱ ነው ፣ በእርሱ የሚያፍር ከሰይጣን በቀር ማንም የለም ፤ይህንንም ማንም ሳይሆን ተዋህዶ እናታችን አስተማረችን፡፡ እኛማ ኦርቶዶክሶች በስሙ ተጠምቀናል ፣ ስጋውን ደሙን በልተን ጠጥተን ተባርከናል ፣ ለስሙ ቅዳሴ ቆመናል ፣ በስሙ ህይወታችን ይጠበቃል ፣ ስለ ስሙ ኦርቶዶክሳዊ ሰማእታት ነፍሳቸውን ሰጡ ፣ ደማቸውን አፈሰሱ ፣ ቁልቁል ተቸነከሩ ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ ፣ በምጣድ ተቆሉ ፣ በወፍጮ ተፈጩ ፣ እንደ አክርማ ተሰነጠቁ ፡፡ ይህን ያስተማረች ፣ የመሰከረችና ለዘላለም በስሙ ተደግፋ ሳትናወጥ የምትቆመው ተዋህዶ እምነታችን ናት ፡፡ የትኛውም የእምነት ድርጅት ፣ የትኛውም ባለስልጣን ፣ የትኛውም ሰባኪ ስለስሙ ከእርሷ የበለጠ ሊመሰክር አይችልም፡፡ የተዋህዶ ሰማእታት በደማቸው የመሰከሩትን ምስክርነት ማንም ሰባኪ ነኝ የሚል በወሬ አዲስ ምስክርን ሊመሰክር አይችልም፡፡”የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኢየሱስን አትሰብክም ፡ በስሙም ታፍራለች” የሚሉ በእውነት አካሄዳቸውን ከመናፍቃን ጋር ያደረጉ ሰነፎች ናቸው፡፡ እኒህ በወሬ እንጂ በህይወት ስለስሙ አልሰበኩምና እነርሱ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ትሉኛላችሁ እኔ ግን አላውቃችሁም እላቸዋለሁ “ ከሚባሉት ወገኖች ናቸው፡፡ ተዋህዶ ግን ከመሰረቷ እስከ ጉልላቷ እርሱን ትሰብካለች ፡ ስሙም ጉልበቷና ሃይሏ ነው ፡ ልጆቿም በህይወት ይህን ይመሰክራሉ ፡፡ ነገር ግን አካሄዱን ከዲያቢሎስ ጋር ያደረገ ይህን ይቃወማል፡፡
ታዲያ እናንተ ሰነፎች ይህን ማስተዋል ያቃታችሁ ፦ ተዋህዶ ኢየሱስ ብቻ ከማለት ስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድሃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስላለችው ነውን? ወይንስ አርዮሳዊ እንዲያፍር እግዚአብሄር ወልድ ቃል አምላክ ብላ ስለጠራችው ነውን? ወይንስ አህዛብ እንዲያፍሩ ለሚጠራጠሩም ምስክር እንዲሆን ከሶስቱ አካል አንድ አካል አካላዊ ቃል መድህን አለም ኢየሱስ ክርስቶስ ስላለችው ነውን? ወይንስ ኢየሱስ ጌታ ነው ከማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የጌቶች ጌታ የነገስታት ንጉስ የአማልክት አምላክ ስላለችው ነውን? ወይንስ ኢየሱስ ማለት መድሃኒት ማለት እንደሆነ ይህም ስም በእስራኤላውያን ዘንድ የተለመደ እንደሆነ ክርስቶስ ማለት ግን መሲህ ይህም አንድ ብቻ እንደሆነ የእግዚአብሄር ልጅ አንድ እንደሆነ የሚገልፅ መሆኑን የሚያመለክት እንደመሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ስንል መድሃኒት የሆነው መሲህ ፣ ስለ ሰወች ልጆች ሃጢአት የሞተው ትሁት ፣ ወደሰማያት ያረገው ገዥ ፣ ለመፍረድ የሚመጣ ፈራጅ እርሱ አንድ እንደሆነ እንደሚናገር እንዴት ረሱት? ይህስ ምስክርነት እንዴት ይዘነጋል? ወይንስ ኢየሱስ ጌታ ነው ሲባል በአለም ብዙ ጌቶች እንዳሉ ስናውቅ ፣ ተዋህዶ ግን ይህን ሲባል ለመግለፅ የፈለግነው አንዱን ክርስቶስን እንደሆነ ለማጠየቅ የጌቶች ጌታ (የሁሉም ጌታ) ማለቷ ይህ ከዚያኛው አይበልጥምን? ወይንስ ማንን ደስ እንዲለው ነው “ኦርቶዶክስ ኢየሱስን አትሰብክም ፡ ስሙንም ትፈራለች“ የሚሉት? ከውጭ ሆኖ በተስፋ ወደ ተዋህዶ ለመመለስ ከራሱ ጋር እየታገለ ያለውን ሰው ለማራቅ ይሆንን? ወይንስ የተዋህዶ ንኡሳን ክርስቲያኖች በመጠራጠር ከተዋህዶ እንዲለዩ ነውን? ወይንስ እኒህ ራሳቸውን ከተሃድሶ ጎራ ያደረጉ ተዋህዶ ስለ ክርስቶስ የምትመሰክረውን ምስክርነት እናድስ ለማለት ይሆንን? እኛስ ራሳቸውን ከፍ ከፍ እንደሚያደርጉ ፃፎችና ፈሪሳውያን የተወደደውን የአምላካችንን ስም እንደ ተራ ሰው ስም አድርገን አንጠራም፡፡
እናንተ የማታስተውሉ እስኪ መልሱልኝ ፦ አንድን ንጉስ ንጉስ ከተባለ በኅላ ለንግስናው የተሰጠውን ማእረግ ሽራችሁ በስሙ ብቻ ካልጠራሁ ትላላችሁን?ይህንስ ካላላችሁ የነገስታት ንጉስ የሆነውን እንዴት ናቃችሁት? ወይንስ እናንተ ራሳችሁን መንፈሳዊ የምታደርጉ ለመንፈሳዊ አባቶቻችሁ የሰጣችሁትን ማእረግ ለአምላክ ትሽሩታላችሁን? ለራሳችሁ ከስማችሁ በፊት ማእረጋችሁን ቀጥላችሁ ዘማሪ ፡ ቀሲስ ፡ ወንጌላዊ ፡ ፓስተር ወዘተ ካልተባልን የምትሉ ስትሆኑ የጌቶች ጌታ ለሆነው አምላክ እንዴት ይህን ትነፍጋላችሁ? ወይንስ “እኛኮ ልጆቹ ነን እንደ ሩቅ ሰው ማእረጉን መጥራት አይገባንም” የምትሉ ፡ አይደለም ለልጅነት ለባርነት እንኳን የማንጠቅም ሃጢአተኞች እንደሆንን ረሳችሁት? ለባርነት እንኳን የማንጠቅም እንደሆን ከተፃፈ ታዲያ ባርያ ለጌታው የሚሰጠውን ክብር አታውቁምን? እንግዲያስ በየትኛው የፅድቅ ደረጃ ላይ ሆናችሁ ይህን ትህትና እረሳችሁት? ነገር ግን የትኛውም የፅድቅ ደረጃ ላይ አይደላችሁምና ትህትናን አታውቋትም፡፡
እኛስ በቀደመው ዘመን ተጠርጣሪወች አንዳንዶቹ ይህ ክብር ይግባውና ወንበዴ ነው እንደአሉት ፡ አንዳንዶች ነብይ ነው እንደአሉት ሳይሆን ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ጥቂቶች የህያው የእግዚአብሄር የባህርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሄር እንተ እንደሆንክ እናምናለን እንዳሉት እናምናለን እንታመናለን፡፡ የቀደሙት የተዋህዶ ቅዱሳንም ይህን ክብሩን ሳያፍሩ ለአለም ለመግለጥ በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል ፀሎት ላይ እመቤታችንን ሊያመሰግኑ ሲነሱ “ የአሽናፊ የእግዚአብሄር እናት ሆይ ሰላምታ ላንቺ ይገባሻል” ብለው “ የኢየሱስ እናት” ብለው ለመናፍቃን ቦታ እንዳይተው “የእግዚአብሄር እናት ሆይ” አሏት፡፡ስለዚህም እኛ ኦርቶዶክሳውያን የቅዱሳን ልጆች እንሆን ዘንድ እንፋጠናለንና የተወደደውን የአምላካችንን ስም ስንጠራ በፍፁም ክብር እንደ ቀደሙት አባቶቻችን አጠራር ራሳችንን ዝቅ አድርገን ጌታችን መድሃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብለን እንጠራዋለን፡፡ይህን ስንል ግን ተዋህዶ ይህን የስም አጠራር ስለትህትና ፣ ስለአምላክ ክብርና ስለ ክርስቶስ ምስክርነት ዘወትር ትጠቀምበታለች እንጂ “ኢየሱስ” ማለት ልክ አይደለም ማለት አይደለም፡፡
እኛስ መቼም መቼም በእመቤታችን ልጅ ስም አናፍርም፡፡ አፍረንም አናውቅም፡፡ ተዋህዶም ሆኖ በእመቤታችን ልጅ ስም ያፈረ ማንም እንደማይኖር ለሁሉ እንመሰክራለን፡፡ እውነተኞቹ የተዋህዶ ልጆች እመቤታችንን አማላጅ የሚሏት ለመማለድ ፍቅሩ እጅግ ብዙ የሆነውን አምላካችንን መድሃኒታችንን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አምነው አይደለምን? ስለሰው ልጅ ባለው እጅግ የበዛ ፍቅር ቅዱሳንን በፊቱ ቆመው ስለ ሰወች ልጆች ሁሉ ለማማለድ እንዲቆሙ ያዘጋጀልን እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን “እመቤታችን” ብለን ለንግስትነቷ የምንጠራት ንጉሱን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለወለደችልን አይደለምን? ታዲያ እመቤቴ አማልጂኝ ብሎ ንግስቲቱን ለምኖ የንግስቲቱን ልጅ ንጉሱን የሚጠላ ማነው? ስለዚህም ማንም “በእመቤታችን ልጅ ስም ያፍራሉ” ብሎ አይናገርብንም፡፡
እንግዲህ እኛም ተዋህዶ እንዳስተማረችን የተወደደ አባታችንን እንዲህ እያልን ለሁሉ እንመሰክራለን ፦ ክብር የሚገባው ጌታችን አምላካችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ህይወታችን ነው ፣ ሰላማችንና እረፍታችን እርሱ ነው ፤ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ የጥበባት ሁሉ ምንጭ እርሱ ነው ፤ መጀመሪያ የሌለው አልፋ መጨረሻም የሌለው ኦሜጋ እርሱ ነው ፤ እርሱ ሁሉን የሚወድ ነው ፤ እርሱ የአለም መድሃኒት ነው ፤ እርሱ የወደቁትን የሚያነሳ ፣ የተዋረዱትን የሚያከብር ለድሃ አደጉ አዛኝ የምንዱባን ረዳት ነው ፤ አለምን በቃሉ የፈጠረ እርሱ ነው ፤ አለምን ሊያድን ወደምድር የወረደ የድንግል ልጅ እርሱ ነው ፤ ወደ ሰማይ የወጣ እርሱ ነው ፤ ለመፍረድም የሚመጣ እርሱ ነው ፤ እርሱን አምነን አንዳች ነገር አይጎድልብንም ፤ እርሱ ሁሉ ነገራችን ነው ፤ ትምክህታችን እርሱ ነው ፤ መደገፊያችን እርሱ ነው ፤ አበዳሪያችን እርሱ ነው ፤ ምስጢረኛችን እርሱ ነው ፤ እርሱ አባታችን ነው ፤ እርሱ እናታችን ነው ፤ ከእኛ በላይ ለእኛ የሚያስብ እርሱ ነው ፤ በጨለማ የሚያበራልን ብርሃናችን እርሱ ነው ፤ እርሱ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ በስልጣን ፣ በፈቃድ ፣ በልእልና የተካከለ ነው ፤ እርሱ እድፍ ጉድፍ የሌለበት ንፁህ ቅዱስ የእግዚአብሄር ልጅ እግዚአብሄር ነው ፤ እርሱ በድንግል ማርያም ማህፀን በተፀነሰ ጊዜ በሰማይ በምድር የሞላ በኪሩቤልም ዙፋን የነበረ ነው ፤ እርሱን በምን ቃል እንገልፀዋለን? እርሱን በማን እንመስለዋለን? ክርስቶስ ሆይ በእውነት ላንተ ምስጋና ይገባሃል፡፡ ቸር አባት አንተ ነህና በቸርነትህ ስለእናትህ ስለቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ብለህ ምስጋናችንን ተቀበል፡፡ እያልን እንደ አባቶቻችን እናመሰግናለን፡፡ ይህንንም ማንም ሳይሆን ተዋህዶ እናታችን አስተማረችን፡፡ እኛም ይህን ከመመስከር ቸል ብለን የእናታችንን ውለታ አንረሳም፡፡ ነገር ግን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተዋህዶን ሊተቹ የሚነሱትን እግዚአብሄር ልቦና ይስጣቸው፡፡ አሜን፡፡
ቃለ ሕይወት ያሰማልን! ፕሮቴስታንቶች አላዋቂ ሳሚ እንደሆኑ መች አወቁትና የያዝነውን ወርቅ አደናግረው ሊያስጥሉን የማይቆፍሩት ምን አለና ? ብቻ እግዚአብሔር ይጠብቀን እናትና ልጅ ምንምና እህት አለያይተዋል አለዋቂ መሆናቸውን ስለማያውቁ ለመመርመር እንኳን አያስቡም ፡፡
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን! ፕሮቴስታንቶች አላዋቂ ሳሚ እንደሆኑ መች አወቁትና የያዝነውን ወርቅ አደናግረው ሊያስጥሉን የማይቆፍሩት ምን አለና ? ብቻ እግዚአብሔር ይጠብቀን እናትና ልጅ ምንምና እህት አለያይተዋል አለዋቂ መሆናቸውን ስለማያውቁ ለመመርመር እንኳን አያስቡም ፡፡
ReplyDelete