Wednesday, February 20, 2013

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን አንቋሸዋል የተባሉ በእስር ተቀጡ

  •  ፍርድ ቤቱ ለእያንዳንዳቸው 6 ወር ፈርዶባቸዋል፡፡
  •  መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ጀርባ የመሸጉት ቡድኖችን ይወቋቸው፡፡
(አንድ አድርገን የካቲት 13 2004 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን የሚያንቋሽሽና የሚያስተሃቅር ወንጀል ፈጽመዋል ወይም የወንጀል መቅጫ ህጉ ቁጥር 32/1ሀ ና 492/ሀ ላይ የተመለከተውን የህግ ድንጋጌ ተላልፈዋል የተባሉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ፡፡
ዐቃቢ ሕግ በመሰረተው ክስ ዲያቆን ሀብቴ ተፈራ እና ዲያቆን ጓዴ ሳህሉ የሚል የመታወቂያ ስም ያላቸው ተከሳሾች የኦርቶዶክስ ተዋህዶን ሃይማኖት የሚያቃልል ጽሁፍ የያዘ ፓምፕሌት ይዘው ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ደብረ ታቦት ከተማ በመሄድ ባሰራጩት ጽሁፍ “እንደ እንቧይ ካብ  በገዛ ራሱ  የፈራረሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የተሰኝው እምነት ከንቱ መዋቅር ነው ፤ እሁድ እንደ ማንኛውም የስራ ቀን ነው ፤ ቤተክርስቲያንን የሚመሩ ጳጳሳት ዝሙታን ናቸው…” የሚሉ እና የመሳሰሉት ጽሁፎች በየቦታው ሲበትኑ እንደነበርና ይህም በሰውና በሰነድ ማስረጃ ከበቂ በላይ ተረጋግጧ ተብሏል፡፡

ተከሳሾቹ በጠበቃቸው አማካኝነት ባቀረቡት መቃወሚያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋዶ ሃይማኖት ተከታዮች መሆናቸውን ‹‹ኦርቶዶክስ›› የሚለው ስያሜ አያስፈልገንም ፤ ሰንበት ቅዳሜ ነው ? ወይስ እሁድ ? ነው የሚለው ሃይማኖታዊ አመለካከት እንጂ ወንጀል አለመሆኑን ፤ ይዘውት የተገኙት ጽሁፍም ቤተክርስቲያኗ ወደ ጥንቱ ትክክለኛ አምልኮ ስርዓት እንድትመለስ ጥሪ የሚያደርግና ይህም ሕገ መንግስታዊ መብት መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል፡፡
የተከሳሾቹ ምስክሮችም “የተበተነውን ጽሁፍ ለእኛ ደርሶን አንብበነዋል ፤ መዋቅሩ ፈርሷል ማለት ከሃይማኖት ጋር የሚያገናኝ ነገር አይደለም ፤ ሕገ - መንግስቱን የተከተለ አስተሳሰብ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ፈርሷል የተባለውም አሜሪካ ያለው ሲኖዶስና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሲኖዶስ እርስ በእርስ ስለተወጋገዙ እንጂ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን አያንቋሽሽም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ክሱ የቀረበለት የደብረ ታቦር ወረዳ ፍርድ ቤት የከሳሽና የተከሳሽ ወገኖችን ክርክር ከሰማና የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ከተመለከተ በኋላ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ የመቀበልና የማስተማር መብት ቢኖረውም የሌሎችን ሃይማኖት እንዲነቅፍ ወይም እንዲንቋሽሽ  ሕገ-መንግስቱ አይፈቅድም ሲል በተከሳሾቹ ሃይማኖትን የሚያንቋሽሽ  ወይም የሚያቃልል ተግባር መፈጸማቸው በአቃቢ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በተገቢው ሁኔታ በመረጋገጡ እና ተከሳሾችም የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ናቸው ተብለዋል፡፡
ተከሳሾቹም በጠበቃቸው አማካኝነት ቅጣቱ በገንዘብ እንዲሆንላቸው የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ከወንጀሉ አፈጻጸም አንጻር የገንዘብ ቅጣቱ ተከሳሾቹንም ሆነ መሰሎቻቸውን ወይም ሌላው ሊያስተምር እንደማይችል በማመኑ የተከሳሾችንም የቅጣት ማቅለያ መርምሮ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው በ6 ወር ቀላል ቅጣት እንዲቀጡ ወሰኗል፡፡ ተከሳሾች በውሳኔው ይግባኝ ቢሉም የደቡብ ጎንደር የደብረ ታቦር ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የአማራ ብሔራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የበታች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ፍሳኔ አጽድቋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአመት በፊት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጀርባ  ኤልያስ ወደ ምድር ወርዷል ፤ ትክክለኛ ሰንበት ቅዳሜ እንጂ እሁድ አይደለም ፤  የአሁኗ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ስርዓተ ቤተክርስቲያን ትክክለኛ አለመሆን ፤ ስለ አማላጅነትና መሰል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጋር የሚጣረስ ሃሳብ ያላቸው ቡድኖች መነሳታቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ እነዚህ ቡድኖች  “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።” ትንቢተ ሚልክያስ  4፤5 “ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናናል” የማርቆስ ወንጌል 9 ፤12 የሚሉትን የመጽፍ ቅዱስ ቃል መሰረት በማድረግ ነብዩ ኤልያስ ወደ ምድር ጳግሜ 5 2003 ዓ.ም እንደመጣ ይሰብካሉ ፡፡ ቦታው መሃል አራት ኪሎ መሆኑ እና በርካቶችን ውስጥ ውስጡን በፓምፕሌትና በተለያዩ በራሪ ወረቀቶች በመሳብ ላይ ይገኛሉ ፡፡  ቦታው ድረስ ሄደን እንደተመለከትነው ስማቸውን መጥቀስ የማያስፈልግ ጥቂት በህዝብ ዘንድ ታዋቂ የሆኑ አርቲስቶች ፤ ቆብ ያጠለቁ መነኮሳትና ለማገልገል የሚፋጠኑ ወጣቶች በቦታው ላይ መመልከት ችለናል ፤ ጉባኤ የሚያካሂዱትም በሳምንት በተወሰኑ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት አንስቶ እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት መሆኑን ለማወቅ ችለናል ፤ ሰዎቹ እንዳያያዛቸው ሰይፍ ቢመጣ የሚመለሱም አይመስሉም ፡፡ የኦርቶዶክስ ተከታዮች መስለው ይህን የመሰለውን ስራ የሚሰሩትንና መንጋውን ወዳልሆነ መንገድ የሚመሩትን ቡድኖች ቤተክህነቷ በሃላፊነት ተከታትላ እርምጃ የሚወሰድበትን መንገድ ማመቻቸት አለባት ብለን እናምናለን ፡፡(ይህ ጉዳይ ሰፊ ስለሆነ ከማስረጃዎች ጋር ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን)፡፡
ቸር ሰንብቱ

1 comment:

  1. ብላቴናዋ ከጀርመንFebruary 20, 2013 at 10:42 AM

    ሰላም አንድአድርገኖች እንደምን ከረማችሁ ለምታቀርቡልን መረጃዎች በቅድሚያ እያመሰገንኩ ነገርግን በማስረጃ የተደገፈ ነገረ ካላችሁ የሰዎቹን ማንንነት በፎቶ ወይም የተቀረጸ ነገርካለችሁ ብታወጡት መልካም ይመስለኛል ታማኝነትንም ታተርፉበታላችሁ ብየ አምናለሁ በተፈግን በርቱ ስራችሁን የቤተክርስቲያን አምላክ ይባርክላችሁ !አሜን

    ReplyDelete