ከአጥናፉ አለማየሁ
(አንድ አድርገን የካቲት 6
2005 ዓ.ም)፡- አንድ ፓትርያርክ ከስልጣን ቢወርድ ወይም በስጋ ዕረፍት ቢለይ በ1991 የወጣውና በሥራ ላይ የሚገኝው ሕገ ቤተክርስቲያን
የሚከተለውን ይላል
ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ
1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የቤተክረስቲያኒቱ ሕግና ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት ተመርጦ ይሾማል፡፡2. ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ፓትያርክ ምርጫ የሚወሰነው ቁጥር መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡3. ለፓትርያርክነት የሚመረጡ እጩዎች ለሊቃነ ጳጳሳት ፤ ከጳጳሳት ከኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሲሆን ብዛታቸው ከሶስት ያላነሰ ከአምስት ያልበለጡ ይሆናሉ፡፡4. አስመራጭ ኮሚቴው ዕጩዎቹን ጠቁሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀርባል፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ምርጫው እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡5. መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተክህነት ጠቅላይ ስራ አስኪያጅ የመምሪያና የድርጅት ሃላፊዎች ፤ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች ፤ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ከየአህጉረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በእድሜ ከ40 ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምዕመናን ተወካዮች ፤ እንዲሁም እድሜያቸው ከ22 እስከ 40 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ ፤ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤ የሚወከሉ ከአንድ ሀገረ ስብከት 12 ሆነው በሥጋወ ደሙ የተወሰኑ ፤ በሕገ ቤተክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው፡፡6. የምርጫ አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ይሆናል፡፡7. የተመረጠው ፓትርያርክ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ቀኖናውን ሊጠብቅና አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተክርስቲያኒቱን ሊያስተዳድር ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡8. ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያወጣል፡፡
እንግዲህ ከአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ ስድስተኛውን የቤተክርስቲያኗን ፓትርያርክ ለመሰየም ከዚህ በኃላ የሁለት ሳምንታት እድሜ ብቻ ይቀራል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ “ሀይሁብ መርሐ ርቱዕ ለቤተክርስቲያን” ማለትም ለቤተክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ እግዚአብሔር የወደደውንና የፈቀደውን ያስቀምጥ ዘንድ ከየካቲት አንድ እስከ ስምንት የአንድ ሱባኤ ጸሎት ምህላ ካወጀ ዛሬ ስድስተኛውን ቀን ይዟል፡፡
እንዲያም ቢባል ግን የፕትርክናው
ምርጫ እየተካሄደ ያለው በሁለት ጎራ በተከፈሉ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች እና ምዕመናንን አንድ በማድረግ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡
ተደጋግሞ እንደተወሳው ከራሳቸው ከአባቶች መካከል የተወሰኑት ሳንታረቅ የምን ፕትርክና እያሉ በሚቃወሙበት ሰዓት መሆኑ ፤ ከምርጫው ይልቅ ዕርቅ ይቅደም የሚሉ ጩህቶች
አሁንም እየተሰሙ በሚገኙበት ወቅት መሆኑ ፤ በተለያዩ አገራት የሚገኙ በውጭ ሲኖዶስ ስር የሚገኙ የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን ከእንግዲህ
በኋላ ከእናት ቤተክርስቲያናቸው ጋር መለያየታቸው ቁርጥ በሆነበት ጊዜ መሆኑ ፤ ባለፉት 21 ዓመታት በገጠማቸው የተለያዩ ችግር
ምክንያት ከዚህም ከዚያም አንሆንም በማለት “ገለልተኛ” በሚል ስም እየተጠሩ ያሉት እንደወጡ በዚያው እንዲቀሩ በሚመስል ሁኔታ ነው
ተመራጩን ፓትርያርክ ወደ ስልጣን ለማጣት ዝግጅቱ እየተካሄደ ያለው፡፡
እርግጥ ነው ብዙ የተደከመበት ዕርቀ
ሰላም በሰንካላ ምክንያት እስከተቋጠበት ጊዜ ድረስ አንድነትን ለማምጣት የተደረገው ጥረት ቀላል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ እናም በዚህ
ሁሉ ፓትርያርክ ይሆኑ ዘንድ ፈተናቸው ቀላል አይሆንም፡፡
የምርጫው ሂደትና አስመራጮቹ
ታህሳስ 10 ቀን 2005 ዓ.ም
የተቋቋመው ኮሚቴ ይፋ ካደረጋቸው መርሐ ግብሮቹ ባሻገር ፤ በራሱ በአስመራጭ ኮሚቴው ማንነት ላይ ጥየቄዎች ሲነሱ መቆታቸው ይታወሳል፡፡
ይሁንና በዚህ በኩል ጉልህ የሆነ ክፍተት እንደሌለ ከስብስቡ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ መሰረት አስራጭ ኮሚቴው ከሚከተሉት አካላት የተወጣጣ መሆኑ ይጣወቃል፡፡ ከሊቃነ ጳጳሳት ፤ ከጠቅላይ ቤተክህነት ሰራተኞች ፤ ከአድባራና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፤ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከማኅበረ ቅዱሳን ሲሆኑ በጥቅሉ 13 አባላት ያሉበት ኮሚቴ ነው፡፡
እንደዚህ ኮሚቴ መግለጫ ማንም የቤተክርስቲያኒቱ
ምዕመን የሚፈልገውን እጩ መጠቆም እንደሚችል ማሳወቁ እና የ6ተኛ ፓትርያርክ መራጮች ቁጥር ካለፉት አምስት የፓትርያርክ ምርጫ ቁጥር
ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑንና አምስቱን እጩዎች የሚመርጠው ይፋ
የሚያደርገውም ይህው አስመራጭ ኮሚቴ ነው፡፡ ይሁንና በዚህ በኩል አንዳንድ አስተያየቶች እየተሰሙ ይገኛሉ ፡፡ የተቃውሞ ድምጾቹ
አስመራጭ “ኮሚቴው አምስቱን
ዕጩዎች እንዴት እንደሚመርጥ ግልጽ አይደለም” ከሚለው ይጀምራል፡፡ ይህም አሰራር አስመራጭ ኮሚቴው ከሶስት ያላነሰ ከአምስት ያልበለጠ እጩ ያቀርባል በሚለው የምርጫ
ደንብ መሠረት በራሱ ወንፊት አበጥሮ ፤ ሕገ ደንቡን አክብሮ ለሲኖዶስ እንደሚያቀርብ እንጂ ይህንን ሁሉ አልፎ ተጠቋሚዎችን ለማቅረብ
ስለመቻሉ የተባለ ነገር አለመኖሩ ፉክክሩን ቀላል ያደርገዋል የሚሉ አልታጡም፡፡
ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አስተያየት
ያላቸው ወገኖች ደግሞ የአምስቱ እጩዎች አመራረጥ በምርጫ ሕገ ደንቡ
ላይ በግልጽ መቀመጡን ያስረዳሉ፡፡ ለምርጫ የሚጠቆመው ጳጳስ ወይም ኤጲስ ቆጶስ ዜግነቱ ኢትጵያዊ የሆነ የውጭ ሀገር ዜግነት ካለውም የውጭ
ዜግነቱን ሰርዞ ወደ ኢትዮጵያዊነቱ የተመለሰ ፤ ዕድሜው ከ50 ዓመት ያላነሰና ከ70 ዓመት ያልበለጠ ከቤተክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤቶች ቢያንስ በአንድ ጉባኤ የተመረቀ ፤ ቢቻል ሁለገብ ትምህርት ያለው ሆኖ ከከፍተኛ መንፈሳዊ ተቋማት ዲፕሎማ
ወይም ድግሪ ያለው ፤ ሙሉ አካል ያለውና ጤንነቱ የተሟላ ፤ ግዕዝ የሚያውቅ
ሆኖ ቢቻል ከአለም አቀፍ ቋንቋዎች አንዱን የሚያውቅ ፤ በቅድስና ሕይወቱ ፤ በግብረ ገብነቱ የተመሰገነ ፤ መንፈሳዊና
ማኅበራዊ አገልግሎቱ በመፈጸም በቂ አስተዳደር ችሎታና ልምድ ያለው መሆን እንደሚገባው በፓትርያርክ ምርጫ ደንቡ ላይ መሥፈሩን ያመለክታሉ፡፡
የተጠቀሱት ነጥቦችና ኮሚቴው የሚገመግምበት ሚዛኑ ምን ይሁን ምን የታወቀ ነገር የለም ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምርጫው ሂደት በዕጣ
እንደማይሆን ነው የታወቀው፡፡ ከተጠቀሱን ነጥቦች ውስጥ “በቅድስና ሕይወቱ ፤ በግብረ ገብነቱ የተመሰገነ” የሚለው ነጥብ ኮሚቴው በየትኛው ሚዛን እንደሚመዝነው አይታወቅም፡፡
ሌላው የድምጽ ቆጠራ ጉዳይ ነው፡፡
በድምጽ ቆጠራው ወቅት እኩል
ድምጽ ቢገኝ አሰራሩ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አልተቻለም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥር 800 መራጮች እንደሚገኙ
በአኅዝ ከመቀመጡ በስተቀር መራጮች ላይ የሚኖር የምረጡኝ ዘመቻ ተጽህኖ
ይኖር አይኖር እንደሆነ አልተነገረም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡
እንዲሁ ሁሉ አስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው
መግለጫ ግርታን የፈጠረ አንድ ነጥብ ተነስቷል፡፡ በመግለጫው ገጽ ሁለት በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 17 ቁጥር 2 መሰረት የቤተክርስቲያኒቱ
መሪ በሞት በተለዩ ጊዜ ከ40 እስከ 80 ቀናት ባለው ጊዜያት ውስጥ አዲስ ፓትርያርክ ይመረጣል ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ይህ
ሕገ ቤተክርስቲያኗ አምስት ፓትርያርኮችን ስትመርጥ እንደተሰራበት በመግለጽ ፡፡ አሁንም 6ተኛ ፓትርያርክ የምትመርጠው በዚሁ
ሕግ መሰረት እንደሆነ ያትታል፡፡ ነገር ግን አምስተኛው ፓትርያርክ የተመረጡት 4ተኛው ፓትርያርክ በህይወት እያሉ ነውና አሁንም ሌላ የህግ መፋለስ
የሚታይበት አካሄድ እየተሄደ እንደሆነ ሰዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡
የቀረቡትን እጩዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ
የሚያቀርበው አስመራጭ ኮሚቴው ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአስመራጭ ኮሚቴው ተጣርተው በቀረቡለት እጩ ፓትርያርኮች ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የካቲት 16 ቀን ይሰበሰባል፡፡ ይሁንና ለስድስተኛ ፓትርያርክ
ምርጫ አምስት አባቶች እንደሚቀርቡ እንጂ አምስቱ እጩዎች ለመጨረሻ ምርጫ ከስንት ተጠቋዎች ተመርጠው እንደሚቀርቡ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡
መሰል ችግሮችና ኮሚቴው የሚሄድባቸው
መንገዶች ምን ይሁኑ ምን የሚያውቀው ኮሚቴውና ኮሚቴው ብቻ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment