Tuesday, February 5, 2013

ልዩ ልዩ


ስም ማጥፋት

(ጥር 28 2008 ዓ.ም)፡- ዛሬ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ማታ ከሁለት ሰዓቱ ዜና በኋላ ሽብርተኝነትንና ሃይማኖትን በተመለከተ አወዛጋቢ ፊልም ያቀርባል ፤ የፊልሙ ማጠንጠኛ “ኢስላማዊ መንግስት” ለመመስረት እቅድ ነበረን የሚሉትን ሰዎች በዶክመንተሪ መልክ ለህዝብ ማቅረብ ነው ፤ ይሄ ፊልም በቴሌቪዥን እንዳይተላለፍ በሽብርተኝነት የተከሰሱት ሰዎች ጠበቃ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ የይታገድልን ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል ፤ ጥያቄያቸውም መልስ እንደማያገኝ ይገመታል ፤ትላንት ማታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ሽብርተኝነትና አደጋውን በሚመለከት ቃለ መጠይቅ ባደረገላቸው ወቅት “አንዳንድ ክርስትያኖችና ሙስሊሞች” እያሉ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውሏል ፤ በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ የሙስሊም ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ሰዎች በቃሊቲ እንዳሉ ይታወቃል ፤ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ አሸባሪ ወይም አክራሪ ተብሎ የታሰረ አንድም ክርስትያን ወይም የክርስቲያን ተቋም በሌለበት ሁኔታ “አንዳንድ ክርስትያኖች” በማለት የሚሰጥ አስተያየት ተገቢ ነው ብለን አናስብም ፤ “ሊበሏት ያሰቧትን …” በሚያስብል መልኩ በሆነውም ባልሆነውም ቦታ ስም መጥራት ከስም ማጥፋት አይተናነስም ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናው በመጨረሻ የፓርላማ ንግግራቸው “ይህ የአክራሪነት አመለካከት አፈር መልበስ አለበት” ብለው ነበር ፤ አፈር መልበስም ካለበት በዚህ ጎራ የቆሙትንና ያልቆሙትን ሰዎች መለየት የመጀመሪያ ስራ መሆን ሲገባው ሰው ሃይማኖቱን ስለጠበቀ እና በአግባቡ ስለተከተለ ያልሆነ ስም መስጠት ተገቢ ብለን አናምንም




የእርምጃው ውጤት

ቤተክህነት ውስጥ ያለውን ጉዳይ ተጨባጭ ካልሆኑ ድረ-ገጾች በመሰብሰብ ለገበያ ማሻሻጫ ስራ ማዋል ከተጀመረ ሰንበትበት ብሎ ነበር ፤ ባለቤት የሌለው ቤት ይመስል የሚጻፈውን እና የሚወራው ቤተክህነት መልስ ሳትሰጥ ዝም ብላ ስታልፍም ነበር ፤ ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ቤተክህነት ባቀረበችው ክስ ምክንያት ቅዳሜ ጥር 25 የታተሙ መጽሄቶች አንዳቸውም ይሄ ነው የሚባል ነገር ያለመጻፋቸው የተወሰደው እርምጃ ትክክል መሆኑን ያመለክታል ፤  የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ባልሰሩት ስራ እና ባላሰቡት ነገር ስማቸውን የሚያጠፉ የመጽሄትና የጋዜጣ አሳታሚዎች ወደፊት ተጠያቂነት እንዳለ አውቀው ከስራቸው እንደሚታቀቡ አመላክቷል ፤ ወደፊትም ቤተክህነት የመገናኛ ብዙሃን ስለ ቤተክርስቲያኒቱ የሚጽፉትን የሚያወሩትን ወሬ ሁላ በመከታተል ጥሩውን የማመስገን እና ትክክለኛ ያልሆነውን ዘገባ የማረም ሃላፊነቷን መወጣት መቻል አለባት ፤ ምዕመኑ በሆነውም ባልሆነውም ዘገባ ግራ መጋባት ስለሌለበት የሚመለከተው ክፍል ስራውን ስራዬ ብሎ መያዝ መቻል አለበት ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚወጡትን ዘገባዎችን እያባረሩ ክስ መመስረት ብቻ ሳይሆን ቤተክህነት በየወቅቱ ያሉ ዜናዎችን ለምዕመኑ የማድረስ መንገድ ቀይሳ መንቀሳቀስ ይኖርባታል፡፡ በየጊዜው  የሚወጡትን መረጃዎች በዝምታ ማለፍ ከመስማማት ስለሚቆጠር አይንና ጆሮዋን መገናኛ ብዙሃን ላይ ማሳረፍ መቻል አለባት እንላለን ፤ እንደ ግብጽ ኮፕት ክርስቲያኖች ቤተክርስቲያኒቱ የራሷ ሬዲዮ ቴሌቪዝን እና ተደራሽ ጋዜጦችና መጽሄቶች ሲኖሯት የዛኔ ምዕመኑ ውሃውን ከምንጩ ይጠጣል ብለን እናምናለን…..
አጉስታ ጽዮን ማርያም
ጥር አስራ አራት ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ይህ ነው ባልተባለ እሳት ቤተክርስቲያኒቱ መቃጠሏን መዘገባችን ይታወቃል ፡፡ በወቅቱ በደረሰውን አደጋ ምክንያት ህዝበ ክርስቲያኑ ቤተክርስቲያኒቱ ከተቃጠለችበት ቀን አንስቶ በህብረት ቀን ከሌት በመስራት በቀናት ውስጥ ቤተክርስቲያኒቱን እንደገና ከበፊቱ በተሸለ በመስራት ጥር 21 ቀን የሚከበረውን የእመቤታችንን ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀት መከበሩን ማወቅ ተችሏል ፤በተአምር ከእሳት የተረፉት ታቦታት ጥር 20 ቀን ማታ ለጊዜያዊ ካረፉበት ቦታ ወደ አዲሱ ቤተመቅደስ ዞረዋል፡፡  ቤተክርስቲያኒቱ በፊት ከነበረችበት ቦታ ላይ ትንሽ ቦታ በመጨመርና ውስጣዊውን መጠነኛ የዲዛይን ለውጥ በማድረግ ቤተመቅደሱ አይንን በሚስብ መልኩ መታነጹን በቦታው ሄደን መመልከት ችለናል ፤ በጊዜው በርካቶች በጊዜው የተጠየቀውን ነገር በማሟላት ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸው ታውቋል ፤ ምንጣፍ ፤ መጋረዣ ፤ መስቀል ፤ የተለያዩ የቅዱሳን ስእሎች ፤ አራት ትላልቅ ድምጽ ማጉያዎች ፤ የመቅደስ በሮችና መስኮቶች  ፤ የተለያዩ አልባሳት በስጦታ መልክ ሲያቀርቡ ተስተውሏል፡፡ በፊት አንድ የድምጽ ማጉያ ብቻ የነበራት ቤተክርስትያን በአሁኑ ሰዓት በአራቱም አቅጣጫ ትላልቅ የድምጽ ማውጫ መሳሪያዎች ተገጥመውላታል ፤ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ሆነው የሚያስቀድሱ ምዕመናን ሙቀት እንዳያስቸግራቸው ኮርኒሱ በልዩ ባለሙያዎች በተለየ መልኩ ተሰርቷል ፤ የቤተክርስቲያኒቱ የውስጥ መብራቶች ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዘመናዊ በሆኑ መብራቶች ተተክተዋል ፤ ባጠቃላይ በአሁኑ ሰዓት ነገሮች ወደ ነበሩበት ቦታ ተመልሰዋል፡፡ ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

1 comment:

  1. እንድ አድርኝ ምነው በሁሉ ቦታ ጥልቅ ጥልቅ አላችሁ ሙስሊም እንደዚ አያደርግም ባላችሁ ነው ምነው እዚሁ ድህረ ገጸ ላይ እኮ ነው ቤተ ክርስቲዬን አቃተሉ ምን አደረጉ ስትሉ የነበረው አሁን ከመንግስት ጋር ስትጛጬ ለአክራሪ ምስሊም ማገዝ መደገፍ አብራችሁ አሸባሪ መሆን ፈለጋችሁ ስይጣንም ከ መንግስት ጋር ቢጋጭ ለሰይጣን ልታግዙ ነው አስተውሉ ዛሬ የተናገራቸሁትን መልሳችሁ እንዳትልሶት

    ReplyDelete