ለፓትርያሪክነት የተጠቆሙት
ዕጩዎች ዛሬ ይለያሉ
(አዲስ አድማስ ቅዳሜ የካቲት 9
2005 ዓ.ም)፡- ፡- የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ፤ ካህናትና ምእመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ሊኾን ይገባል የሚሉትን ዕጩ እንዲጠቁሙ ያወጣው የስምንት ቀን መርሐ ግብር አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ለፓትርያሪክነት
የተጠቆሙት ዕጩዎች ቅዳሜ ይለያሉ፡ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ቅን
መሪ እንዲሰጥ፣ የወደደውንና የፈቀደውን በመንበረ ፕትርክናው እንዲያስቀምጥ ካህናትና ምእመናን አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ የታዘዘው የአንድ ሳምንት የጸሎት ሱባኤ
እስከ ምርጫው ፍፃሜ የካቲት 21 ቀን
2005 ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት ተላልፏል፡፡ ዐዋጅም መፈጸሙ ተነግሯል፡፡ በምርጫው መሪ ዕቅድ መሠረት፣ የካቲት 9 ቀን ካህናትና ምእመናን የዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማ የሰጡበትን ቅጽ የያዘው የታሸገ ሣጥን
ተከፍቶ ተጠቋሚዎቹን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ የአስመራጭ ኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ
ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማው ካህናት፣ ምእመናንና ገዳማውያን ሳይቀሩ በንቃት መሳተፋቸውን የተናገሩት ሓላፊው አቶ
ባያብል ሙላቴ፤ ጥቆማውን ኮሚቴው በዕጩነት ለሚለያቸው አምስት አባቶች ዋነኛ ግብአት አድርጎ እንደሚጠቀምበት
ገልጸዋል፡፡ ኮሚቴው የካቲት 9 ቀን
ለጥቆማው አቀባበል በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ካህናትና ምእመናን የጠቆሟቸው አባቶች ለፓትርያሪክነት ለሚመረጡ ዕጩዎች የተቀመጡትን መመዘኛዎች ማሟላት አለማሟላታቸውን ከግል መረጃዎቻቸው ጋር
እያነጻጸሩ የመለየትና የማጣራት ሥራዎች እንደሚሠራ አቶ ባያብል አስረድተዋል፡፡
ሓላፊው አያይዘውም በፓትርያሪክነት መመዘኛው መሠረት ተጠቋሚዎቹን የመለየትና ተጨማሪ የማወዳደር ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ፣ ኮሚቴው የካቲት 16 ቀን
2005 ዓ.ም
ለተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ
የሚቀርቡትን አምስት ዕጩዎች ለይቶ የካቲት 14 ያስታውቃል ብለዋል፡፡
‹‹በአንድ ሰውም ይኹን በአንድ ሺሕ ሰው የተጠቆሙ የተለያዩ አባቶች ቢኖሩ ኮሚቴው የሚወስደው ለዕጩነት መጠቆማቸውን ነው፤›› የሚሉት አቶ ባያብል፣ ተጠቋሚው በዕጩነት ሊያዝ የሚችለው፣ በምርጫ ሕገ ደንቡ የፓትርያሪክነት መመዘኛውን አሟልቶ ሲገኝ እንጂ በብዙ ሰው ስለተጠቆመ ብቻ ባለመኾኑ የዕጩ ጥቆማውን ጥያቄ ከመምረጥ ወይም ምርጫ ሂደት ጋር ማሳሳት ተገቢ አለመኾኑን ገልፀዋል፡፡
ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ላይ የተጠየቁትን የድጋፍ ደብዳቤዎች አሟልተው የቀረቡ ዕጩ ጠቋሚዎች የተስተናገዱት በግላቸው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ባያብል፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች እገሌን ለዕጩነት ጠቁመናል ወይም እገሌን መርጠናል በሚል በቡድን የቀረቡ ማመልከቻዎችን ሳይቀበሉ መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ብፁዕ
አቡነ ሳሙኤልን በዕጩ ፓትርያሪክነት በመጠቆም እንዳቀረቡት የተገለጸው ደብዳቤ ተቀባይነት የሚኖረው፣ ደቀ
መዛሙርቱ በነፍስ ወከፍ የኮሌጅ ተማሪነታቸውን ከኮሌጁ አስተዳደር በተጻፈ ደብዳቤ አስደግፈው ለጥቆማ ሲቀርቡ እንደኾነ ሓላፊው አስረድተዋል፡፡
አስመራጭ ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት መግለጫው፣ የካቲት 21 ቀን በሚካሄደው የስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ የሚሳተፉት የመራጮች ብዛት 800 እንደኾኑ ካስታወቀ በኋላ በሂደት እየተለዩና ዕውቅና እየተሰጣቸው የተጨመሩ መራጮች መኖራቸው ተመልክቷል፡
በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቷ በሀገር ውስጥ ካሏት 53 አህጉረ ስብከት መካከል 790 መራጮች ይሳተፋሉ፤ ከሀገር ውጭ ባሏት ስምንት አህጉረ ስብከት ከእያንዳንዳቸው አራት (ከሥራ አስኪያጁ ጋር ካህናትን፣ ምእመናንን፣ ሰንበት ት/ቤቶችን የሚወክሉ አንድ አንድ) መራጮች፣ ከግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ጋር ባለው የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት አራት መራጭ ተወካዮች በአጠቃላይ ማስተካከያው እስከተነገረበት ጊዜ ድረስ 826 መራጮች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡
ዕጩ ፓትርያርኮችን
የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኮሚቴው አስታወቀ
(ሪፖርተር
የካቲት 10 2005 ዓ.ም) ፡- በየካቲት
ውስጥ ለሚካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ዕጩዎች እንዲሆኑ በካህናትና ምዕመናን ሲሰጥ
የነበረው ጥቆማ
መጠናቀቁንና አስመራጭ ኮሚቴውም በምርጫ ሕጉ
መሠረት ውይይት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው የአስመራጭ ኮሚቴ
ሰብሳቢ ብፁዕ
አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመንበረ ፓትርያርክ ባለፈው ዓርብ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ስድስተኛ ፓትርያርክ ይሆናል የሚሉትን በአካልና በፋክስ እንዲጠቁሙ በተላለፈው መሠረት በርካታ ካህናትና ምዕመናን ጥቆማቸውን ሲሰጡ
ሰንብተዋል፡፡
ከካህናትና ከምዕመናን የተገኘው ጥቆማ ለአስመራጭ ኮሚቴው በግብዓት የሚያገለግል መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፣ ዕጩ ፓትርያርኮችን እስከ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በሚያደርገው ውይይት ከለየ በኋላ የካቲት 16 ቀን ለሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንደሚያቀርበው አስታውቀዋል፡፡
የጥቆማ አሰጣጡና የጸሎት ጊዜው በሰላም መጠናቀቁን የገለጸው አስመራጭ ኮሚቴው፣ በቀሪው ጊዜም በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ፈጣሪያቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ አሳስቧል፡፡ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚደረገው ስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዕጩ የሚሆኑ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት የካቲት 18 ቀን እንደሚታወቁ፣ ከምርጫውም በኋላ በዓለ ሲመቱ የካቲት 24 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
ከካህናትና ከምዕመናን የተገኘው ጥቆማ ለአስመራጭ ኮሚቴው በግብዓት የሚያገለግል መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፣ ዕጩ ፓትርያርኮችን እስከ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በሚያደርገው ውይይት ከለየ በኋላ የካቲት 16 ቀን ለሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንደሚያቀርበው አስታውቀዋል፡፡
የጥቆማ አሰጣጡና የጸሎት ጊዜው በሰላም መጠናቀቁን የገለጸው አስመራጭ ኮሚቴው፣ በቀሪው ጊዜም በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ፈጣሪያቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ አሳስቧል፡፡ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚደረገው ስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዕጩ የሚሆኑ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት የካቲት 18 ቀን እንደሚታወቁ፣ ከምርጫውም በኋላ በዓለ ሲመቱ የካቲት 24 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
sewun sayhon EGZIABHERN yemiasdsitu melkam abat amilakachin ysiten amen!!!
ReplyDelete