Wednesday, February 20, 2013

አቡነ ሳሙኤል የምረጡኝ ዘመቻ ጀመሩ


በሳምንት ከ20 ሺህ በላይ በመታተም ለንባብ የሚበቃው ሰንደቅ ጋዜጣ የካቲት 13 2005 ዓ.ም በፊት ገጽ ይዞት የወጣው ዜና
  • 500 ሺህ ብር በአበል መልክ እንዲከፈል አድርገዋል
(አንድ አድርገን የካቲት 13 2005 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት  የተለዩት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን የሚተካ ስድስተኛ ፓትርያርክ ለማስመረጥ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ የፓትርያርክ ምርጫ ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያኒቷ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስና ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩት ወቅት ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው የነበሩት አቡነ ሳሙኤል  በቀጣዩ ምርጫ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው እንዲመረጡ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳትን ፤ የቤተክህነት አስመራጮችን ፤ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ስራ አስኪያጆችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በማግባባት ላይ መሆናቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለጉዳዩ በጣም ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ ለዚህ ይረዳቸው ዘንድ ከፍተኛ ገንዘብ መድበው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን በጥቅምት ወር በተካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተ ክርስቲያን 31ኛው ጉባኤ ወቅት ተሳታፊ ለነበሩ ቁጥራቸው ወደ 900 የሚጠጋ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተሰበሰቡ ተሳታፊዎች 500 ሺህ ብር በአበል መልክ እንዲከፈል አድርገዋል፡፡ ይህም ለሚካሄደው የፓትያርክ ምርጫ ይጠቅማቸው ዘንድ ያከናወኑት መሆኑን ተግባር መሆኑ ታውቋል፡፡
 አያይዘውም ገንዘቡ በሱማሌ እና አፋር ክልሎች ለሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲውል ከእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተገኝ እንደሆነ ተሳታፊዎቹም ከሀገረ ስብከታቸው አበል ተከፍሏቸው የመጡ መሆናቸው ነገር ግን አቡነ ሳሙኤል ተወዳጅነት ለማግኝት ሲሉ የልማት ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስነታቸውን በመጠቀም ገንዘቡን ለተሳታፊዎች እንዲበተን ማድረጋቸው ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህ የምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ድምጽ ለሚሰጡዋቸውና ከጎናቸው ለሚሆኑ ሰዎች ፓትርያርክ ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተሻለ ኃላፊነት ቦታ እንደሚሾሟቸው ለቤተሰቦቻቸው የውጭ እድል እንደሚያመቻቹላቸው ቤተክርስቲያኒቷ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የምታስገነባቸው ህንጻዎች ውስጥ የንግድ ቦታ እንደሚሰጧው ቃል እየገቡላቸው እንደሆነ መራጮች ገልጸዋል፡፡
አቡነ ሳሙኤል አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናትን እንዳግባቡና መንግስት ፓትርያርክ ሆኜ እንድመረጥ ይፈልጋል የሚለው አቡነ ሳሙኤል ተናግረውታል የተባለውን ወሬ በአሁነ ሰዓት በቤተክህነት ውስጥ በሰፊው እየተነዛ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትንና የቤተክህነት አመራሮችን  በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርን ሲሆን  አቡነ ሳሙኤል እያደረጉት ያለው ተግባር ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው የሃይማኖት አባት የማይጠበቅና ሃይማኖታችን የማይፈቅደው ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ፓትርያርክነት የሚገኝው በምረጡኝ ዘመቻ ሳይሆን በአምላካችን ፍቃድ ስለሆነ ምዕመናን ቤተክርስቲያኒቷን በበለጠ  መንገድ የሚያገለግላት ፓትርያርክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው በጸሎት ላይ መሆናቸው እና ጸሎታቸውን አጠናክረው እንድቀጥሉ እየመከሩ እንደሚገኙ ምንጮቻችን ይገልጻሉ፡፡
የአንድ አድርገን  ሃሳብ
በአሁኑ ወቅት እየተሰማ ያለው እና እየሆነ ያለው ነገር ምርጫውን በግለሰቦች በቡድኖች በውስጥና በውጭ ተጽህኖ ምክንያት መስመር እንዳይስት ስጋት መኖሩን ነው፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሕግን ከለላ በማድረግ አንድን አባት ብቻ ከፍ አድርጎ በመስቀል ሌሎቹን እንዳይቀርቡ የማድረግ ስራው ከተገፋበት ምርጫው ሳይታለም የተፈታ ሊያደርገው ይችላል ብጹዕ አቡነ ሳሙኤልን የሚደግፉ ከአራት በላይ አንጃ የፈጠሩ ቡድኖች መኖራቸው አስመራጭ ኮሚቴው ነገሩን ቆም ብሎ እንዲያስብ አድርጎታል የጥቆማውን ወረቀት በንጽጽር ውስጥ ሲገባም ከበስተጀርባ ሌላ  የመንግሥትም ይሁን የግለሰቦች አንጃ ምርጫውን መምራት የሚፈልግ መኖራቸውን አመላካች ምልክት አሳይቷል ገና የምርጫ ሕጉ ሳይወጣ እነዚህ ሰዎች መንግሥት አቡነ ሳሙኤል ፓትርያርክ ቢሆኑ እንደሚስማማ እና እሳቸው የመንግሥት ምርጫ መሆናቸውን ሲናገሩ ሲያስነግሩ ወሬውም ብዙሀኑ ጋር በአንድም በሌላም መንገድ እንዲደርስ ሲያደርጉ ነበር፡፡  ምርጫው የአቡነ ሳሙኤልና የአስመራጭ ኮሚቴ ፍጥጫ ብቻ እንዳይሆንም እንሰጋለን፡፡ 
ቸር ሰንብቱ

1 comment:

  1. አንድአድርገን!! በጣም ተከታታያችሁና በጣም ደጋፊያችሁ ነኝ አሁን ትንሽ ከመስመር ውጪ ልትሆኑ መሰለኝ በአቡነ ሳሙኤል ዙርያ ያነሳችሁት ነገር ስም ማጥፋት ነው የሚባለሁ እና ክፉውን ነገር ትታችሁ መልካሙን ነገር ብቻ ማየት ነው ሌላውን ለክርስቶስ መተው ነው "ወይፈድዮ ለኩሉ በከመ ምግባሩ..." ይልቁንም በኣባቶቻች በኩል ያለውን ደካማ ጎን ወደ አደባባይ ማውጣት ለመናፍቃን በር መክፈት ነው ክፉ ይሁን በጎ መራጩ እግዚአቤሔር ነው

    ReplyDelete