Sunday, February 10, 2013

ለስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ 800 መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ


-    ምርጫው  የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ይፈጸማል 
( Reporter:-  )የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛው ፓትርያርክ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደምትመርጥና 800 መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ አስታወቀች፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የካቲት 21 ቀን ለሚፈጸመው የፓትርያርክ ምርጫ የሚቀርቡት አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች የካቲት 18 ቀን ለሕዝብ ይፋ ይሆናሉ፡፡

ስድስተኛውን ፓትርያርክ የሚመርጡት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምርያ ኃላፊዎች፣ ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፣ ካህናት፣ ምዕመናን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መሆናቸውና ቁጥራቸውም 800 መሆኑን ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

ካህናት፣ ምዕመናንና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በሚያቀርቡት የአባልነት ማስረጃ በዕጩ ፓትርያርክ ጥቆማ ከየካቲት 1 ቀን እስከ የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ መሳተፍ እንደሚችሉ የገለጹት ሰብሳቢው፣ ካህናትና ምዕመናን ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁና ከየካቲት መባቻ ጀምሮ ለአንድ ሱባኤ የሚቆይ የጸሎት ጊዜ መታወጁንም አስታውቀዋል፡፡

የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን ተካሂዶ በዚሁ ዕለት ከምሽቱ 12 ሰዓት የተመረጠው አባት በመገናኛ ብዙኀን አማካይነት ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን፣ በዓለ ሲመቱም እሑድ የካቲት 24 ቀን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተጠቅሷል፡፡ የመራጮች ቁጥር ባለፉት አምስት ፓትርያርኮች ምርጫ ከታየው በእጅጉ ከፍተኛ መሆኑም ተነግሯል፡፡

ምርጫውን ቅዱስ ሲኖዶስ በምርጫ ሕጉ በወሰነው መሠረት የአራቱ እኅት አብያተ ክርስቲያናት [ግብፅ፣ ሶርያ፣ አርመን፣ ህንድ] የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር፣ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮችና በቋሚ ሲኖዶስ የሚመረጡ ምዕመናን እንዲታዘቡ መጋበዛቸውም ታውቋል፡፡

የመጀመርያውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን በ1951 ዓ.ም. የመረጠችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለፉት 53 ዓመታት አምስት ፓትርያርኮች ብፁዓን ወቅዱሳን አቡናት ባስልዮስ፣ ቴዎፍሎስ፣ ተክለሃይማኖት፣ መርቆሬዎስ  የመሯት ሲሆን፤ አምስተኛው ፓትርያርክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ (1928-2004) በመንበሩ ላይ 20 ዓመት ከቆዩ በኋላ ያረፉት ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደነበረ ይታወሳል፡፡  

No comments:

Post a Comment