Friday, February 22, 2013

የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫና አምስቱ እጩ ፓትርያርኮች



  • አስመራጭ ኮሚቴ አምስቱን እጩ ፓትርያርኮች ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረቡ ተሰማ፡፡
  • ቅዱስ ሲኖዶስ የስድስተኛውን ፓትርያርክ ምርጫ እንዲሳካ ሕዝበ ክርስቲያኑ ተሳትፎው እንዲያጠናክር ጠየቀ
  • “አንድነት ስለፈለጉት ብቻ የሚመጣ አይደለም” መግለጫው
  • አራተኛው ፓትርያርክና ከእሳቸው ጋር ባሉት አባቶች የተፈጸመው ስህተትን የሚያጋልጥ መረጃ በጽሁፍ በመገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ ጉባኤዎች ለሕዝቡ ይፋ ይደረጋል፡፡
 
(አንድ አድርገን የካቲት 15 2005 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኢርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን ሕግና ቀኖናውን ተከትሎ እየተከናወነ የሚገኝው ስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ሕዝበ ክርስቲያኑ እስከ አሁን ሲያደርግ የቆየውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጥሪውን አቀረበ፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ  አባቶች ፓለቲካዊ አስተሳሰባቸውን ትተው በኃይማኖት አጀንዳ ላይ ብቻ ለመስራት ፈቃደኞች ከሆኑ ቤተክርስቲያኗ እጇን ዘርግታ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ “ራሱን ቅዱስ ሲኖዶስ ብሎ የሚጠራው አካል ያወጣውን የሐሰት መግለጫ”  አስመልክቶ ትላንትና ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው ፤ ምርጫው በተሳካ መንገድ ይፈጸም ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ አስከ አሁን እያሳየ ያለውን የላቀ ተሳትፎና ትብብር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በሰሜን አሜሪካ የሚገኝው የቤተክርስቲያኒቱ ተከታይም ኢትዮጵያዊነቱን የሚገልጽበትን የአንድነት መንፈስ ሳያስተጓጉል የፓትርያርኩ ምርጫ እንዲሳካ ከቤተክርስቲያኒቷ ጎን መቆም አለበት ብለዋል ፡፡

ምዕመናንና ምዕመናት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶችን አንድነት ማየት እንደሚናፍቁ የተገነዘበ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቁሞ ፤ ይህ አንድነት ስለተመኙብ ብቻ ሳይሆን እውነትን በመከተል የሚገኝ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የአባቶች አንድነት ማረጋገጥ የሚቻለው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አባቶች የሚያስላልፉትን አፍራሽ ቅስቀሳ በማሰላሰል አለመሆኑን የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ፤ በአገሩ እና በመንበሩ ሆኖ ዓለም ከእሱ ጋር እየሰራ  ያለውን ቅዱስ ሲኖዶስ ተከትሎ በጥበብ በማስረዳትና በመውቀስም ጭምር  የሚሳሳቱትን በመመለስ እንደሆነ ጠቅሷ፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ በውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ ተከታዮቹ ከጎኑ እንዲቆሙ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የቤተክርስቲያኗ አራተኛው ፓትርያርክ የነበሩት አባት ከሕዝቡ የቀረቡ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግና በሌሎችም ምክንያቶች ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን ደረጃ በደረጃ  አጥንቶ ከስልጣናቸው ያስነሳ  መሆኑን መግለጫው አስታውሶ ፤ ውሳኔው የተላለፈውም በአሁኑ ወቅት በእነዚህ አባቶች እየተካሄደ ባለው ትረካ ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ሆኖ መገኝቱን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

መግለጫው እንዳመለከተው ፤ የሰሜን አሜሪካ አባቶች እየተከተሉት ያለውን ፓለቲካዊ አስተሳሰብ በመተው በኃይማኖት አጀንዳ ብቻ ለመስራት ፈቃደኞች ከሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ አሁንም ቢሆን እጇን ዘርግታ ልትቀበላቸው ዝግጁ ናት፡፡ ራሳቸው ስህተት ፈጽመው ሌላውን ለማሳሳት እያደረጉ ያለውን የቤተክርስቲያኗን ቀኖና መጣስ ስህተት በማቆም የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ለማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ስህተቱ ያለው የት እንደሆነ በማወቅ ለመምከር ሆነ የህሊና ዳኝነት ለመስጠት እንዲሁም በእነሱ የሀሰት ቅስቀሳ ግራ ላለመጋባት እውነተኛውን መረጃ ለሕዝብ ለማሳወቅ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በቀድሞ አራተኛ ፓትርያርክና ከእሳቸው ጋር ባሉት አባቶች የተፈጸመው ስህተትን የሚያጋልጥ መረጃም በጽሁፍ ፤ በመገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ ጉባኤዎች ለሕዝቡ ይደርሳል፡፡ ምዕመናን እውነቱን በማወቅ የቤተክርስቲያኒቱ ሉዓላዊ አንድነት እንዲጠበቅና ሰላም እንዲመጣ ተጽህኖ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊው ቀኖናን መሰረት አድርጎ ጊዜውን የዋጀ ሕገ ቤተክርስቲያንን  በመቅረጽና ፤ መዋቅሩን በማጠናከርና አገልግሎቱን ዓለማቀፋዊ ቅርጽ  በማስያዝ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ክብርና ለቤተክርስቲያኗ ህልውና መጠበቅ  ከመቼውም በላይ ጠንክሮ እንደሚሰራ ለሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ላሉ ምዕመናን አረጋግጧል፡፡

በሌላ ዜና የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴው ያስቀመጠውን መመዘና ያሟላሉ ያላቸውን አምስቱን እጩዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረቡ የውስጥ ምንጮች አስታወቁ ፡፡ውሳኔው በቅዱስ ሲኖዶስ ለውጥ ካልተደረገበት በቀር  ብፁዕ አቡነ ማቲያስ   ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፤ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ   ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ  እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል፡፡  በሁለት ቀን ውስጥ ይፋዊ መግለጫም ቅዱስ ሲኖዶሱ ወይም አስመራጭ ኮሚቴው ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃልም ፡፡ ብዙ ሲባልባቸው የነበሩት አቡነ ሳሙኤልና አቡነ ገብርኤል አለመካተታቸው “አንድ አድርገን” ከውስጥ ምንጮች ባገኝችው መረጃ መሰረት እጩዎቹ ያልታሰቡት ይሆናሉ ብላ ያስቀመጠችው ቅድመ ግምት የደረሰ ይመስላል፡፡ አሁንም 6ተኛው ፓትርያርክ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲያስ ይሆናሉ የሚል ብዙ ግምቶች ቢኖሩም ነገሩ ፍጹም ያልታሰበ ሊሆን እንደሚችልም ሃሳባቸውን የሚሰጡ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ እነዚህ አምስቱ አባቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ ለይቶ ሶስት እንደሚያስቀራቸውና በሶስቱ ላይ ብቻ ምርጫ እንደሚደረግ ይታወቃል፡፡




ይህ መረጃ ይፋዊ የአስመራጭ ኮሚቴው ወይም የቅዱስ ሲኖዶስ ስላልሆነ አምስቱን ለማወቅ የነገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔን መጠበቅ ግድ ነው
( ሲኖዶስ የሚጨምረውም የሚቀንሰውም ሊኖር ይችል ይሆናል)



 
እግዚአብሔር የወደደው ይሁን”

1 comment:

  1. EGZIABHER ybarkachihu!!! abetu AMLAK hoy ante ymertkachewun abat endefekadih siten amen.

    ReplyDelete