Tuesday, May 29, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን ያቀረበው ሪፖርት ላይ የ‹‹አንድ አድርገን›› ሐሳብ

(አንድ አድርገን ግንቦት 21 2004.)- ባሳለፍነው ሳምንት ማኅበረ ቅዱሳን በዋልድባ ገዳምና በወልቃይት  የስኳር ልማት ፕሮጀክት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ አምስት  አባላት ያሉት  ልኡካን ቡድን የጥናት ዘገባ አስነብቦናል፡፡

ገዳማትና የአብነት ት/ቤቶች የቤተክርስቲያኗ ህልውና መሰረት እንደሆኑ በመገንዘብ ማኅበረ ቅዱሳን ከ100 በላ የሚሆኑ የአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ፕሮጀክት አጥንቶ ምእመናን በማስተባበር እየተገበረ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ገዳማት ውስጥ የዋልድባ ገዳም አንዱ ነው፡፡ ማኅበሩ ፕሮጀክት አየተገበረበት የሚገኘው የዋልድባ ገዳምና የስኳር ልማት ፕሮጀክት ውዝግብን እንደ   ቤተክርስቲያኒቱ አካል ጉዳዩን በሰከነና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደተመለከተው ከጥናቱ ዘገባ መረዳት ይቻላል፡፡


ሪፖርቱ በይዘቱ፡- እንደ ቤተክህነቱ አጣሪ ኮሚቴ መንግሥትን ደስ ለማሰኘት፣ ራሱ መንግሥት እንኳን “እንደሱ አትናገሩልኝ፣ በገዳማውያንና በመንግስት መካከል ሆናችሁ አግባቡን፣ ስለ ፕሮጀክቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ እኔ አስረዳላሁ” በማለት የተቸውን የሰዱቃውያኑን ሪፖርት ይቃረናል፡፡ ይልቁንም መረጃዎችን በመሰብሰብና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በመተንተን ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ማኅበሩ  ይህን ሪፖረት ከማቅረቡ ቀደም ብለው በነበሩት ሳምንታት ከውስጥ የጨለማ ቡድኑ መሰሪ አካሄድ፣ የተሃድሶ መናፍቃን ጉዳዩን ፖለቲካዊ  ዓላማ ያለው በማስመሰል ከመንግስት ጋር ለማላተም በድረ ገጾቻቸው መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበረበት፣ መንግሥትም በተለያየ መንገድ ሲገልጸው የነበረውን ማኅበሩ “በአክራሪነት” የመፈረጅ ዝንባሌ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ በተነገረበትና ፓትሪያሪክ ጳውሎስ እነዚህን ሁሉ በማስተባበር የማኅበሩን ተቋማዊ ቀብር ለመፈጸም አጋጣሚዎችን እየጠበቁ እየተገዳደሩት ባለበት ሰሞን ነው፡፡ ከቤተክህነት  ይሁን ከመንግስት መግለጫ ጋር ፈጽሞ ሊገናኝ የማይችል የጥናት ግኝት ይፋ ማድረጉ ማኅበሩ ከራሱ ህልውና ይልቅ ለቤተክርስቲያን ህልውና ቅድሚያ በመስጠት አንድ እርምጃ መራመዱን ያሳየናል፡፡በዚህም ምእመናን ገዳሙ ስላለበት ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳትና ሃሳባቸውን ለመግለጽ መነሻ የሚሆን ታአማኒነት  ያለው መረጃ ማድረስ ችሏል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በዋልድባ ገዳም ክብርና ህልውና ላይ ስለተጋረጠው አደጋ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሃሳብ ማቅረብ ነው፡፡ለዚህም እንደ መነሻ የምናደርገው የማኅበረቅዱሳንን ጥናት ነው፡፡

1.     ጥናቱ ያስገኛቸው ጥሬ ሀቆች(Real Facts) 
  • መንግስትም ይሁን የቤተክህነቱ አጣሪ ኮሚቴ ይክዱት የነበሩትን በገዳሙ መነኮሳት ይቀርቡ የነበሩ ሥጋቶች እውነተኛነት አስረግጦልናል፡፡

ሀ.  ግድቡ  16.6 ሔክታር  ከገዳሙ ቅዱስ ቦታ ገብቶ እንደሚያርፍ በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል፡፡ይህ ቅዱስ ቦታ እህል አይዘራብሽ፣ እርሻ አይታረስበሽ፣ ኃጢዓት አይሻገርብሽ የሚል ቃልኪዳን የተገባለት ነው፡፡ይህንን ቃልኪዳን በመተላለፍ ነው ታርሶ፣ተቆፍሮ ግድብ ሊሰራበት 16.16 ሄክታር ገብተው ስራ የጀመሩት፡፡ በሕገመንግስቱ አንቀጽ8 ላይ “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ፡፡”ይላል፡፡ሃይማኖት ማለት የቤተክርስቲያኒቱ  የእምነት አስተምህሮ አይደለምን? በየትኛው ሃይማኖታዊ ሥልጣኑ ነው ይህንን ቃለ ውግዘት የሻረው?

ለ. አጽመ ቅዱሳን መነሳቱን አረጋግጦልናል: - መንግሥት የተነሱ አጽሞች የቅዱሳን ሳይሆኑ “ዘመድ የሌላቸው” ሙታን አጽም እንደሆነ ነግሮናል፡፡ማኅበረቅዱሳን ደግሞ ራሱ መንግስት የቅዱሳንን አጽም ማንሳቱን ማረጋገጡን ነግሮናል፡፡ የቅዱሳን አጽም ሊነሳ ሰለሚችልበትና ስለአፈጻጸሙ  ቤተክርስቲያኒቱ  ቀኖና ያላት ቢሆንም ይሄንን ታሳቢ ያላደረገ ኮሚኒስታዊ አካሄድ ተከትሏል፡፡


ሐ. 500 ሜትር ያህል መንገድ መቀደዱ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ያወጣው ሪፖርት መንግስት በመገናኛ ብዙኃን  የገዳሙን ቦታ አላረስኩም ሲል የገዳሙ መነኮሳት ደግሞ ታርሷል እያሉ የተወዛገቡበትን ቦታ ሪፖርቱ መታረሱን  በአይን እማኞች አረጋግጦልናል ፡፡በቅዱስ ቦታው “በገልባጭ መኪና አፈር ሲጋዝ፣ ሰራተኞችም ሲሰሩ መመልከታቸውን” መስክረውልናል፡፡ መንግስት የገዳሙን አባቶች አድአርቃይ ከተማ ላይ ስብሰባ ጠርቷቸው ነበር የገዳሙ አባቶች ግን የታረሰው ቦታ ላይ ካልሆነ አንሰበሰብም ማለታቸው ይታወሳል፡፡


መ. ሶስት አብያተክርስትያናት ይፈርሳሉ፡- በገዳሙ የሚተዳደሩት ማይ ሐርገፅ ጊዮርጊስ ዕጣኖ ማርያም እና ማይጋባ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያናትን ይፈርሳሉ ብሎናል፡፡ ከእነዚህ አብያተክርስቲያናት በተጨማሪ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ከሚነሱት የሰባት ቀበሌ ነዋሪ ከሆኑት ወደ ሰባት ሺህ ከሚጠጉ አባወራዎች  ሲነሱ የሚፈርሱትን 15 አብያተክርስቲያናት ሳይጨምር መሆኑ ነው፡፡
  • እንደሚታወቀው ዋልድባ ላይ ከቋርፍ ውጪ የሚመገቡት ምግብ የለም እነዚህ ይፈርሳሉ የተባሉት አብያተክርስትያናት በዓመት ሁለት ጊዜ የዋልድባ አባቶችበልደትና በቁስቋም ከቋርፍ ውጪ ምግብ በመብላት የሚያከብሩባቸው  ናቸው፡፡
  • መነኮሳቱ የራሳቸውን እና የገዳሙን ፍጆታ የሚውል ሰሊጥ ኑግና የመሳሰሉት የቅባት እህል የሚመረትባቸው አብያተክርስትያናት ናቸው፡፡
  • ገዳማውያኑ ሲታመሙ በእድሜ የገፉ አረጋውያን አባቶችና ጤናቸው የታወኩ መነኮሳት የሚያርፉበትና ድጋፍ የሚደረግላቸው ቦታዎች ናቸው ፡፡

ሠ. ከዚህ ጋር በተያያዘ የማኅበሩ ሪፖርት አጉልቶ ባያስቀምጠውም ገዳሙ የእርሻ መሬቱን እንደሚያጣ በተዘዋዋሪ መንገድ አስገንዝቦናል፡፡ አብያተክርስቲያናቱ የሚፈርሱት በጎርፍ መጥለቅለቅ መሆኑን ስለሚነግረን፣ በጎርፉ ምክንያት የእርሻ መሬቱንም ቢሆን መጠቀም አይቻልም፡፡ ለዚህም “ማባበያ” መንግስት በስድስት ወር የሚደርስ ሙዝ ተክል እሰጣችኋለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡

የማኅበሩ አጥኚ ቡድን የገዳማውያን ስጋት ካስቀመጠ በኋላ በስተመጨረሻበዚህ ፕሮጀክት ትግበራ ላይም በተጓዳኝ የታዩ ስህተቶች ወይም ጉድለቶች ናቸው” ብሎ ሁለት ነጥቦችን አጠይሞ በፈሊጥ ገልጾ፡፡

የመጀመሪያው ነጥብ “አስቀድሞ ከሚመለከታቸው ጋር በተለይም ከገዳማውያን ጋር በቂ ውይይትን አለማድረጉ” ያስቀምጣል፡፡ መንግስት የአንድ አባውራን ቤት “በልማት  ምክንያት” ለማፍረስ ሲፈልግ ግለሰቡን ለማሳመን ከአስር ላላነሱ ጊዜያት ውይይትና ምክክር እያደረገ ባለበት ሁኔታ ክብረ ገዳማት የሆነውን ከአርባ ሚሊዮን  በላይ ለሚሆኑ ምእመናን መመኪያ የሚሆነውን ዋልድባን ለማፍረስ ውይይት ማድረግ እንዳለበት እንኳን አላሰበበትም፡፡ ከፓትሪያሪኩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ጥቂት ሊቃነጳጳሳትና ካህናት የመንግስት ፈቃድ የሚፈጽሙ መሆናቸውን በተግባር ስለሚያውቀው የልብ ልብ ሰጥቶታል፡፡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት  “ኢህአዴግ ቤተክርስቲያንን ይንቃታል፡፡” የሲኖዶስ ውሳኔ እስከ ማስቀየር የሚያደርስ “አስፈሪ ግርማው” ቤተክርስቲያኗ ላይ እንዳጠላበት አውቋል፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ግሞ እንዲህ ይላል ‹‹ችግሩን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ አግባብነት ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ ይጠቀሳሉ›› መንግስት ችግሩን ለመፍታት የሄደበት መንገድ  ስህተት መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ ይገልጻል ፡፡

መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት የሄደበትን የስህተት ጎዳና ከሞላ ጎደል ይሄንን ይመስላል፡፡  የገዳማውያንን አቤቱታ ወደ አዲስ አበባ ይዘው የመጡትን አባቶች ከማዋረድ ይጀምራል እናንተ ደፋሮች የአንድን ሀገር መሪ ለማናገር መጣችሁ” የሚል ምላሽ የጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት ኃላፊው በመስጠት ተፈጥሮአዊ የሆነውን የመጠየቅ መብታቸውን ኦርቶዶክሳዊ ስለሆኑ ብቻ ከልክለዋቸዋል፡፡

መነኮሳቱ ግን የመጡበትን ላማ ሳናሳካ አንመለስም በማለት ለፓትርያርክ ልዩ  /ቤት ግልባጭ በማድረግ   በአድራሻ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በመጻፍ  በአስቸኳይ መልእክት መላካቸው ይታወቃል፡፡ ለቢዮንሴ ወረብ ያስቀረቡት አባ ጳውሎስ ከክብረ ገዳማት ዋልድባ የመጡትን መነኮሳት መስማት አልወደዱም፡፡ ከመንግሥትና ከቤተክህነቱ ምላሽ ያጡት ተወካዮቹ ጉዳዩ ሁሉንም ምእመናን የሚመለከት በመሆኑ ከቪኦኤ ጋር ቃለ መጠይቅ በማድረግ  የአደባባይ ሚስጥር እንዲሆን አደረጉት ፡፡

ከዚህ በኋላ ነው መንግስት ለማስተባበል የስኳር ልማት ሚኒስትር አቶ ባይ ፀሐዬን በኢቲቪ 2 ሰዓት ከእውነታው ጋር የሚጋጭ ቃለ መጠይቅ የተደረገው፡፡ የገዳሙን አባቶች “መግለጫ የሰጡትን አባት ፖለቲከኛ ናቸው፣ የደርግ ወታደር የነበሩ ናቸው” በማለት የመነኮሳትን ክብር አቃለሉት፡፡

በቪኦኤ የተናገሩት አባት የት እንደሚገኙ የገዳሙ አባቶች እንዲጠቁሙ ገዳማውያንን  በወታደሮች እንዲንገላቱ ተደረጉ፡፡ ቤተክህነቷ አጣሪ ኮሚቴ   የግድቡ ግንባታ በዋልድባ ገዳም ላይ የሚያስከትለው ችግር እንደሌለው እንዲመሰክሩ ለማድረግ ተሞክሯል ሰሚ ባያገኙም፡፡  ቀጥሎም በማይጸብሪ ከተማ  በቤተክህነቱ ውስጥ የተሰገሰጉትን ሰዱቃውያን  እና ጥቂት ከተማው ውሰጥ የሚኖሩ  መነኮሳትን እንዲሁም ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸውን የእስልምና እምነት አባቶችን አንድ ላይ ሰብስቦግድቡ ገዳሙ ላይ የሚያመጣው ችግር የለም” የሚል ባለ ስድስት ነጥብ አቋም መግለጫ በማውጣትየገዳሙ መነኮሳት ተስማሙ በማለት ለማታለል ተሞክሯል፡፡

ይህም ተቃውሞውን ሊያስቆመው ስላልቻለ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ብአዴን ባደረገው ስብሰባ  ህዝቡ እንደማይስማማበት እንቅጩን ነግሮአቸዋል ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የጠቅላይ ቤተክህነቱ ምክትል ስራአስኪያጅ አቶ ተስፋዬ  (መንግስት ደህንነት ቢሮ በስለላ ተግባር ላይ ተሰማርቶ ሲሰራ የነበረ) ለጎንደር ህዝብ ስለ ዋልድባ ማስረዳት ሲጀምርዝም በል አንተ ነህ ስለ ዋልድባ ለጎንደር ህዝብ ማስረዳት የምትሞክረው?”   በሚል መብረቃዊ ተግሳጽ ንግግሩ እንዲያቆም ተደርጓል፡፡ በዚህ የስብሰባ አዳራሽ ላይስኳር ተወዷል ህዝቡ እየተቸገረ ነው ምን ችግር አለ ፕሮጀክቱ ቢሰራ?” ማለቱም የወራት ትውስታችን ነው ፡፡

 በስተመጨረሻም ገዳሙ ላይ ስፍር ቁጥር የሌለው ወታደር በማፍሰስ ገዳማውያን በነጻነት እንዳይጸልዩ መቆጣጠር፣ መደብደብና ማንገላታቱን ቀጠለበት፤ የገዳሙንና የመነኮሳትን ክብር የሚነኩ ተግባራት ተፈጸሙ፡፡ በእኩለ ሊት ነፍጥ በታጠቁ ሰዎች 65 ሺህ ብር   የሚገመት ገንዘብ ገዳሙ ተዘረፈ ፡፡

በሰላማዊ መንገድ ችግሩ ሊፈታ እንደማይችል የተገነዘቡት የሰሜን ጎንደር ዳባት፣ደባርቅ፣በየዳ፣ጃናሞራና አድአርቃይ ወረዳዎች  ቁጥራቸው  በሺህ የሚቆጠር አርሶ አደሮች  ወደ ወልቃይት የስኳር ልማት ፕሮጀክት  አካፋ ዶማ ጦር ይዞ ሲነጉድ  “ቆይ በቃ ረጋ በሉ በጠረጴዛ ዙሪያ እንነጋገር መፍትሄ ይኖረዋል” በማለት እየሄደ ያለበት መንገድ እንደማያዋጣው ተገንዝቦ የፕሮጀክቱ ስራ ለማቆም ተስማማ፡፡ ይሄንን ይመስላል “ችግሩን ለመፍታት የተሄደበት መንገድ የአግባብነት ጥያቄ የሚያስነሳበማለት በሪፖረቱ ላይ የተገለጸው፡፡
2. ጥናቱ ያላተኮረባቸው ጉዳዮች

 ሪፖርቱን   መንግስት ያጠናው ጥናት ከመመልከት በዘለለ፤ መንግስት ከዋልድባ ውጭ ሌላ አማራጮችን እንዲመለከት የሚሞግት የአቀራረብ መንገድን አልመረጠም፡፡  እነዚህ አማራጮች ገዳሙን ለመታደግ ለሚደረጉትን ሁለንተናዊ ትግሎች አጋዥ ሊሆኑ ስለሚሆን አንባብያን ውይይት እንዲያደርጉበት መነሻ እንዲሆን ለማድረግ የሚከተሉትን ትኩረት አቅጣጫችን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህ ከጉዳዩ የጋር ተያያዥነት ያላቸው ጽሑፎች የምናስተናግድ መሆኑንም እንገልጻለን፡፡

    i ፕሮጀክቱ ከተተገበረ በኋላ የሚያመጣውን ተጽዕኖ (Project Overall impact)
. በገዳሙ ዙሪያ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ሰፈራ ይካሄዳል፡፡ ምንም እንኳ መንግስት ይሄንን አስመልክቶ የሰጠው ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም ምናልባት በሰፈራውና በገዳሙ መካከል ግድቡ ይኖራል ስለዚህም የሚያሳድረው ተጽእኖ አይኖርም የሚል መከራከሪያ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ሃሳብ ግን ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የግድቡ ርዝመት በዋልድባና በወልቃይት መካከል 720 ሜትር ብቻ ነው፡፡ ከአንድ ኪሎ ሜትር በታች ሲሆን ሰፈራው ከግድቡ ሁለትና ሶስት . ርቀት ላይ ቢሆን እንኳን ቁጥራቸው ወደ ሰማንያ የሚሆኑ ነዋሪዎች በገዳሙ የምነና ህይወት ላይ ቀላል የማይባል ተጸእኖ ያሳደራሉ፡፡

ለ. ስነ ምህዳር ተጽህኖ -ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት ትላልቅ ግድቦች ነባር ስነምህዳሩን የመቀየርና አሉታዊ ተጽእኖ የማሳደር ጠባይ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ተተግብሮ  ሲያልቅ አሁን የምናውቀው ክብረ ገዳማት ዋልድባ ስነ-ምህዳሩና ብዝኃ ህይወቱ  ሳይቀየር ይኖራል ?  በዚህ ዙሪያ እንደ ዶክትር ጌታቸው አሰፋ ያሉ የአካባቢ ጥበቃ ምሁራን ጽሑፍ እንደሚያስነቡን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሐ. ፕሮጀክቱ ተተግብሮ ሲያልቅ  ጫካው በሸንኮራ አገዳ ስለሚተካ ዋልድባ የስውራን በዓት መሆኑ ያበቃል፡፡ብህውትናና የተመስጦ ህይወት ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ አይኖረውም ማለት እንደምን  ይቻላል?

መ. የጎርፍ መጥለቅለቅ ይኖራል፡-ግድቡ የሚገነባበት አካባቢ ከፍተኛ ቦታዎች የሚበዙበት በመሆኑ ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ይኖራል፡፡ በዚህም ወደ ግድቡ የሚገባው የደለል መጠን ይጨምራል፡፡ የግድቡ ጥልቀት ሰለሚቀንስ ውኃ የመያዝ አቅሙም አብሮ ይቀንሳል፡፡ ከግድቡ ተርፎ ወደ ገዳሙ ሊፈስ የሚችልበት አጋጣሚ አለው፡፡ እንደ መከራከርያ የቀረቡት የሙላት መከላከያ (spil way) ይሰራለታል የሚለው መከራሪያ ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡
ማጠቃለያ
በአሁኑ ሰዓት  መንግስት ለልማት” በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች  ነዋሪዎችን በማማከር የሚነሱበትን  ራዎችን የሚሰራበት ሁኔታ እየተመለከትን ነው ፡፡ ይህን ያደረገ መንግሥት ዋልድባን የሚያህል ክብረ ገዳማትን ግሬደር ማረስ ከመጀመሩ በፊት ቤተክርስቲያኒቱን የሚወክሉትን አባቶችንና የገዳሙን መነኮሳት አለማማከሩ መንግስት ለቤተክርሰቲያናችን ያለውን ከልክ ያለፈ ንቀት ያሳያል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ከፓትሪያሪኩ ጀምሮ በየደረጃው የተሰገሰጉት ሰዱቃውያን ሃይማኖታዊ ስራ ከመስራት ይልቅ የመንግስትንም ፈቃድ  ለመፈጸም የተዘጋጁ ወይም ያዘጋጃቸው መሆናቸው ነው፡፡



የስኳር ልማቱ በገዳሙ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መጀመሪያ የሚመለከታት የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ናት ፤ ነገር ግን ጉዳቱ ሳይታያቸው ቀርቶ ሳይሆን ጉዳዩን ቤተክህነታችን አይቶ ዝም ቢል ማህበረ ቅዱሳን ቦታው ድረስ ሄዶ መመልከት መቻሉ እና የአቅሙን ሪፖርት ማቅረቡ ሊያስመሰግነው ይገባል ፤ ይህ ነገር መልካም ቢሆንም የተሻለ ጥናት ለማድረግ ከመንግስት እውቅና እስከተሰጠው ድረስ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ማለትም ፤ ከባህልና ቱሪዝም ቋሚ ኮሚቴ አባላት(የህዝብ ተመራጮች) ፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፤ ከአማራ እና ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ፤ ከከፍተኛ የሀይማኖት አባቶች ፤ ከታዋቂ ሰዎች ፤ ግድብ ስራ ከሚሰሩ ከባለሙያዎች(Engineers) ፤ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ፤ ፕሮጀክቱን ከቀረጹት ባለሙያዎች ፤ ፕሮጀክቱን ከሚያስፈጽሙት ሰዎች በተዋቀረ ኮሚቴ ጥናቱ ረዘም ያለ ጊዜ ተወስዶ ቢካሄድ የጥናቱ ተቀባይነቱ በመንግስት የጎላ ይሆናል የሚል እምነት አለን፡፡

የዋልድባን ችግር ለመፍታት ከቤተክህነቱ አንዳች የምስራች አንጠብቅም፡፡ማህበሩ የመንግስት ቡራኬ እየተቀበለና እየጠየቀ  መስራት አለመቻሉ ጥርስ ውሰጥ እንዳስገባው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል፡፡ ለቤተክርሰቲያኗ አስፈላጊ እንደሆነ በአሁኑ የግንቦት ርክበ ካህናት ማጠቃለያ አቋም መግለጫ ላይ ተመስክሮለታል፡፡ ቤተክህነቱ ተፈትኖ በወደቀበት የዋልድባ ጉዳይም ቢሆን የቤተክርሰቲያኒቱ አንድ ዓይን መሆኑን በሩቅ ሆነን መዓዛው ለሚሸተን አሳይቶናል፡፡ “አንድ አይና በአፈር አይጫወትም” እንዲባል ከማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ በላይ መጠበቅ ቤተክርስቲያኒቱን ለተሃድሶ መናፍቃንና ለሲሞናውያን አሳልፎ ለመስጠት የመፍረድም ያህል ነው፡፡

ቤተክርስቲያንን እስካሁን የጠበቃት በረድኤተ እግዚአብሔር አጋዥነት ምእመኑ ነው፡፡የዋልድባ ገዳም ህልውና አደጋ ውስጥ መግባቱን፣ የገዳሙና የገዳማውያን ክብር መደፈሩን ከዚህ በላይ መረጃ አያስፈልገንም፡፡ ፕሮጀክቱ ከተተገበረ ዋልድባ የሚባል የአንድነት ገዳም አጥተን፣ ወደ ህግ ገዳምነት ይቀየራል ወይም ወደ ደብርነት እንደሚደበር እስከሁን ያገኘናቸው መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ስለዚህ ለዋልድባ የሚበጀው መንግሥት ስራውን አቁሞ ሌላ ቦታ ላይ ፕሮጀክቱን መተግበር፤ ይሄ እስካልሆነ ድረስ የምእመናን ተቃውሞው ይቀጥላል፡፡

እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችን ይጠብቅ!

5 comments:

  1. really good analysis. May our Lord be with us and MK.

    ReplyDelete
  2. so, what is implication of your comment. if u draw alternate solution i'm ok, unlesss i think not need of your gossip.

    ReplyDelete
    Replies
    1. fesame asemesaye kaderea weyem menafeqe

      Delete
    2. minew beselamnew sidibu, sidib hatyat mehonun zengtehnew weys...?

      Delete
  3. it is ok, but what should b next? realy MK is the only one w/c should b responsible 2 show such facts? i think we all the CHRSTIANS......

    ReplyDelete