Wednesday, May 23, 2012

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዘጠነኛ ቀን ውሎ




ቅዱስ ሲኖዶስ የማኅበራት መተዳደርያ ደንብ ጥናት ዳግመኛ ተጠንቶ እንዲቀርብ አዘዘ
አርእስተ ጉዳይ-
·             በማኅበራት መተዳደሪያ ደንብ ዝግጅት ላይ የቀረበው ጥናት የጽዋ፣ የጉዞና የስብከተ ወንጌል ማኅበራት፤ የጽርሐ ጽዮን አንድነት ማኅበር፣ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበረና የማኅበረ ቅዱሳን ህልውና እንዲከስም የሚጠይቅ ነው
·             የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበዋል
·             የሰንበት /ቤቶች / ሊቀ ጳጳስ ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተና ጸሐፊውለመሪያው የማይመጥኑበሚል ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ ጠይቀዋል
·             ዕንቍ ባሕርይ በማ/ ላይ ተጨማሪ የክስ ደብዳቤ ለምልአተ ጉባኤው አሰራጭቷል፤ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ እና የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮች ዛሬ በቅዱስ ሲኖዶስ ፊት ቀርበው ያስረዳሉ

·             ብፁዕ አቡነ አብርሃም አቡነ ፋኑኤልን ቋቋሙ - “እኔ ወጪውን እችላለኹ፤ ከእኔና ከአንተ ማናችን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ እንደ ሠራ አጣሪ ተልኮ ይጣራ?”
§  ·የጨለማው ቡድን በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ በኮሚቴው የቀረበውን የጥናት መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ለማስገልበጥ እየተንቀሳቀሰ ነው
§  ·አባ ጳውሎስ የቀሲስ / መስፍንን አቤቱታመዋቅሩን ጠብቆ አልመጣምበሚል ለማዘግየት እየሞከሩ ነው፤ የዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ልኡካንንበነገር አቀጣጣይነትከሰዋል
§  ·የዕርቀ ሰላም ንግግሩ በሐምሌ ወር ይቀጥላል፤ አባ ጳውሎስና አባ ፋኑኤል አባ መልከ ጼዴቅን በፖሊቲከኛነት ከሰዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በበኩላቸውበውጭ ያሉት አባቶች ዕርቀ ሰላሙን ከልብ የሚፈልጉ ናቸው፤ ችግር ያለው እዚህ ቤት ነውበማለት ለፓትርያርኩ ወቀሳ ምላሽ ሰጥተዋል

(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 13/2004 ዓ.ም፤ May 21/ 2012)፦ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የነበረው መደበኛ ስብሰባ ርእሰ መንበሩ ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ ለማሕሌታይ ቅዱስ ያሬድ ክብረ በዓል ወደ አኵስም ጽዮን ማርያም በመጓዛቸው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ሌሎችም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ግንቦት 11እና 12 ቀን የነበሩትን በዓላት በተለያዩ አድባራትና ገዳማት ተገኝተው አክብረዋል፡፡ በተለይም በርካታ አባቶች በተገኙበት ትላንት በደብረ ሊባኖስ ገዳም የተከበረው ፍልሰተ ዐፅሙ ለጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓል የሚጠቀስ ነው፡፡
መደበኛ ስብሰባው ዛሬ ግንቦት 13 ቀን2004 . መዋሉ የተዘገበ ሲኾን ምልአተ ጉባኤው ‹በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሕግ ባለሞያዎች ተጠንቶ መቅረቡ› በተነገረለት ባለ 16 ገጽ የማኅበራት መተዳደርያ ደንብ ጥናት ሰነድ ላይ ሲነጋገርና ውሳኔ ባሳለፈባቸው ቃለ ጉባኤያት ላይ እየተናበበ ሲፈራረም ውሏል፡፡ (የጥናቱን ሙሉ ንባብ ከዚህ ሲጫኑ ያገኛሉ)
በ‹ጥናቱ› እንደተገለጸው የደንቡ ዋነኛ ዓላማ በቃለ ዐዋዲው እንደታዘዘው በአጥቢያ፣ በወረዳ፣ በአህጉረ ስብከትና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የተዘረዘሩ የአስተዳደርና የአገልግሎት መዋቅሮችን በማጠናከር አሁን በቁጥርም በዐይነትም በርክተው የሚታዩ ማኅበራት አባላት እንደየ ዕድሜያቸውና ሚናቸው የሚታቀፉበትን፣ የፋይናንስና ንብረት ሀብታቸው ለየአስተዳደር አካላቱ ገቢ ኾኖ ቁጥጥሩ የሚጠናከርበትን አሠራር ማመቻቸት ነው ተብሏል፡፡
ስለዚህም ከሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ት/ቤትና ከአጥቢያ ጀምሮ በየደረጃው በአስተዳደራዊ መዋቅሩ ውስጥ ከሚቋቋሙ የስብከተ ወንጌል፣ ልማትና ምግባረ ሠናይ አካላት ውጭ በራሳቸው የሚንቀሳቀሱና ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ የማትቆጣጠራቸው ሌሎች ማኅበራት እንዲቋቋሙ መፍቀድ ቤተ ክርስቲያንን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ‹ጥናቱ› ያሳስባል፡፡ ሰነዱ በ‹ጥናቱ› የሸፈናቸው ማኅበራት፡-የጽዋ፣ የመንፈሳዊ ጉዞ፣ የልዩ ልዩ ቋንቋዎች መዘምራን፣ የስብከተ ወንጌል፣ የገዳማትና አድባራት ልማት፣ የአንድነት ኑሮ፣ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ምሩቃንና የአገልጋዮች ኅብረት ምሩቃን ማኅበራት ናቸው፡፡
ሰነዱ ስለ ማኅበር በሰጠው ብያኔ የቤተ ክርስቲያን የማይለወጥ ስያሜ መኾኑን በማመልከት ዛሬ የሚታየውን የማኅበራት አደረጃጀት የኦርቶዶክሳውያን ትውፊት እንዳልኾነ ይከራከራል፤ ስለኾነም በዚህ ስም ሊጠሩበት እንደማይገባ ያሳስባል፤ በትውፊት የቆዩን ጽዋ ማኅበራትና የሐዋርያት አነዋወር ተምሳሌት የኾኑ የአንድነት ኑሮ ማኅበራት ህልውና ሳይቀር መቋረጥ እንዳለበትና አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘ ክበብ፣ ኮሚቴ ከሚለው ውጭ በማኅበር ስም መጠራት እንደማይገባቸው ይመክራል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀደም ሲል ለሚታዩ የብኩንነት፣ ምዝበራና አለመግባባት ችግሮች የማኅበራትን መብዛት በመንሥኤነት በማቅረብ ጥፋታቸውን የማጉላት ድክመት የሚታይበት ጥናቱ በቃለ ዐዋዲው የተመለከቱት የአስተዳደር መዋቅሮች ባልተጠናከሩበት ኹኔታ በማኅበራቱ ላይ ይህ መሰሉ አቋም እንዲያዝ መወትወቱ በምልአተ ጉባኤው አባላት ዘንድ ቅንነቱን አጠያያቂ አድርጎታል፡፡ ከዚህ የተነሣ ነው የምልአተ ጉባኤው አባላት የጥናቱ መነሻ በአጥኚነት ከተዘረዘሩት ግለሰቦች ጥቂት የማይባሉቱ “የግል ቂም፣ በቀልና ክፋት መወጫ” ሊኾን እንደሚችል እስከ መግለጽ የደረሱት፡፡
“ማኅበራት በአንድ በኩል በቃለ ዐዋዲው የተመለከተው ወርቃማው መዋቅር እንዲሠራ አለመደረጉ የወለዳቸው ናቸው፤” የሚሉ አንድ አስተያየት ሰጭ ‹ጥናቱ› ተግባራዊ ይደረግ ቢባል እንኳ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክና ከወቅቱ ዓለማዊ ኹኔታ አኳያ በልዩ ኹኔታ መታየት የሚገባቸው የማኅበራት ትውፊታዊና ሞያዊ አደረጃጀቶች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልም የሚከተለውን ቃል ተናግረዋል፡-“እኔ በዚህ ሐሳብ አልስማማም፤ ማኅበር ማለት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት ማለት ምን ማለት ነው? ቅዳሴ ማርያሙ ተሻረ እንዴ? ማኅበረ ቅዱሳን፣ ማኅበረ መላእክት፣ ማኅበረ ደናግል፣ ማኅበረ መነኰሳት፣ ማኅበረ ጻድቃን፣ ማኅበረ ሰማዕታት. . .የሚለው? ከአኢወማና ከአኢሴማ በቀር ሌላ ማኅበር አይኑር ያለውን የደርግ አብዮት ነው እንዴ የምናካሂደው?”
ጥቂት የማይባሉ ማኅበራት እንደ መያዶች (NGO’s) ሁሉ በመደበኛ መዋቅር ሊሠሩ ያልቻሉ ተግባራትን ክፍተት የመሸፈን ሚናቸውን እየተወጡ መኾኑን የሚናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው÷ ያሉትን ማኅበራት ህልውና ከማክሰም አስቀድሞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አሁን ከአጥቢያ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ድረስ በሰው ኀይልና በፋይናንስ አስተዳደር የሚታየውን ሞያተኛውን የሚያርቅ ምዝበራና ብኩንነት አስወግዶ በቃለ ዐዋዲው መሠረት የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር በካህናትና ምእመናን ኅብረት ማጠናከር እንደኾነ ይመክራሉ፡፡
አባ ጳውሎስ በንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ሰብሳቢነት፣ በአእመረ አሸብር ጸሐፊነትና መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤልን በመሳሰሉ ሰዎች አባልነት ተጽፎ የቀረበውን በምልአተ ጉባኤው ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ብርቱ ጥረት ያደረጉ ቢኾንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በምትኩ ሰነዱ ሌሎችም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሞያው ያላቸው ምእመናን ተጨምረውበት በሚያሠራ መንገድ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
ምልአተ ጉባኤው በማኅበረ ቅዱሳንና በሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ መካከል ያለውን ችግር እንደሚመለከትና የሃይማኖት ሕጸጽ አለባቸው ተብሎ ጥቆማ በቀረበባቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ በቀረበው የኮሚቴው ጥናታዊ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ ላይ የጀመረው ውይይት በነገው ውሎው እንደሚቀጥል ተገልጧል፡፡
ተስተካክሎና ተሟልቶ ከደረሰን መረጃ ለመረዳት እንደሚቻለው 46 ገጾች ባሉት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጥምር ኮሚቴ ጥናታዊ መግለጫና የውሳኔ ሐሳብ መሠረት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጅ ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ፡-
1) ከመንግሥት ጋራ በመተባበር አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ የሚነገራቸው፤
2) በራሳቸው ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን የተለዩና በአፍራሽ ዘመቻቸው በሕግ የሚጠየቁ፤
3) እንግዳ ትምህርት በማስተላለፋቸው ተጠርተው የሚመከሩና በተሰጣቸው ምክር የማይመለሱ ከኾነ ቀኖናዊ ርምጃ የሚወሰድባቸው፤
4) ቀኖናዊ ርምጃ የሚወሰድባቸው፤
5) ተጨማሪ ክትትል የሚደረግባቸውና በቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙኀን መገናኛ ኑፋቄያቸውን የማጋለጥ ርምጃ የሚወሰድባቸው በሚል ደረጃ ተለይተዋል፡፡
የኮሚቴው ሪፖርት መታየት ከጀመረበት ቀን አንሥቶ ግቢውን እያዘወተሩ የሚገኙት ቀኖናዊ ርምጃ እንዲወሰድበት የተወሰነው አሸናፊ መኰንንና በኮሚቴው ጥሪ ተደርጎለት ያልቀረበው በጋሻው ደሳለኝ ከንቡረ እድ ኤልያስ፣ እጅጋየሁ በየነና ኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ጋራ በመኾን የውሳኔ ሐሳቡን ለማስገልበጥ እየተጣጣሩ መኾኑ ተመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት በአባ ጳውሎስ በኩል ለቅዱስ ሲኖዶስ የሚቀርብ እንዴት እንወገዛለን?” ማመልከቻ አዘጋጅተው ነበር፡፡ ይህንኑ ማመልከቻ አባ ጳውሎስ በኀሙሱ የምልአተ ጉባኤው ውሎ ለማቅረብ ሞክረው የነበረ ሲኾን መዋቅሩን ጠብቆ ያልመጣ ነው በሚል ውድቅ ተደርጓል፡፡
ርእሰ መንበሩ አባ ጳውሎስ ለዚህ የምልአተ ጉባኤው ውሳኔ በዐይነት ለመመለስ ይመስላል አባ ፋኑኤል ያለ ሕግ ሥልጣነ ክህነቱን የያዙባቸው የዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ጸሐፊ የቀሲስ / መስፍን ተገኝ አቤቱታ በሚቀርብበት ጊዜም እኔን ቅድም እንዳላችኹን ይህም አቤቱታ መዋቅሩን ጠብቆ በቋሚ ሲኖዶስ በኩል የቀረበ አይደለም በሚል እንዳይታይ አድርገዋል፡፡ የዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት /ቤት አሁን አባ ፋኑኤል በቀሲስ / መስፍን ላይ በጥላቻ የተገፋ ያልተገባ ርምጃ እንዲወስዱ ያደረጋቸውን ተቃውሞ (ማእከላዊ አሠራርን በመጣስና መዋቅር በማፍረስ በቤተ ክርስቲያን አንድነት ላይ እየፈጠሩት ያለውን ሁከት) ጠቅሰው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ /ቤት ገልጠው ያመለከቱት የካቲት 5 ቀን2004 . እንደ ነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ከዚሁ ጋራ ተያይዞ አቡነ ፋኑኤልን አስመልክቶ በዕለቱ በታየው ጉዳይ ከብፁዕ አቡነ አብርሃም ጋራ ኀይለ ቃል የተመላበት ልውውጥ ተደርጓል፡፡ አቡነ ፋኑኤል ብፁዕ አቡነ አብርሃምን የሀገረ ስብከቱን ንብረት አስረክቡ ተብለው አላስረከቡኝም፤ የመንበረ ጵጵስናው ቤት የተገዛበት መንገድም ትክክል አይደለም በሚል ለማሳጣት ሞክረዋል፡፡
ብፁዕነታቸውም አቡነ ፋኑኤል ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ እንደ ሄዱ ወደ መንበረ ጵጵስናው መምጣት ሲገባቸው በመንደር ሄደው መቀመጣቸውን፣ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ያልመለሷቸውን ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያን እንደመለሱ አስመስለው ለቅዱስ ሲኖዶስ /ቤት የሐሰት ሪፖርት በማቅረብ ማታለላቸውን፣ ወደ መዋቅር ከገቡት አብያተ ክርስቲያን ጋራ በመኾን ማእከላዊነትን ለማስጠበቅና ቃለ ዐዋዲውን ለማስጠበቅ እንደማይሠሩ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የጣሰ ተግባር እንደፈጸሙ አብራርተው አስረድተዋል፤ በመጨረሻም እንዲህ በማለት አብራተዋል - እኔ ወጪውን እችላለኹ፤ ከእኔና ከአንተ ማናችን ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ እንደ ሠራ አጣሪ ተልኮ ይጣራ?” ውይይቱ በዚሁ ሳይቋጭ እንዲያድር ተደርጓል፡፡
በውይይቱ መሀል በነበረው ዕረፍት ከዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት ተወክለው ከመጡት ሦስት ልኡካን ጋራ የተገናኙት ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ እናንተ እነማን ናችሁ? ምን ትሠራላችኹ? ነገር ለማቀጣጠል እና ለማሸማቀቅ ነው የመጣችኹበማለት ለመቆጣት መሞከራቸው ተጠቁሟል፡፡ በአቅራቢያው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርኩ የሕዝቡን ጥያቄ መቀበል እንደሚገባቸው የተናገሩ ሲኾን ልኡካኑም ቅዱስ አባታችን፣ እኛ ሰላም ፍለጋ ነው የመጣነው በሚል ብርቱ ምላሽ እንደሰጧቸው ተዘግቧል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ግንቦት 10 ቀን2004 . በነበረው ስምንተኛ ቀን ውሎው በርካታ ጉዳዮችን የተመለከተ ቢኾንም በውሳኔ የቋጫቸው ጥቂቶቹን ናቸው፡፡ ምልአተ ጉባኤው በዕለቱ የሥራው መጀመሪያው ያደረገው ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በመተላለፍ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኮሚሽኑ የተንቀሳቃሽና ቁጠባ ሒሳቦች ላይ እንዳይፈርሙ ለባንኮች የጻፉት የእገዳ ደብዳቤ ተሽሮ አሠራሩ በነበረበት እንዲቀጥል ውሳኔ ያሳለፈበትን ቃለ ጉባኤ በመናበብ መፈራረም ነበር፡፡
በሌላ በኩል አባ ጳውሎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የባንክ ሒሳቦች ከማንቀሳቀስ ጋራም በተያያዘ ለሥራ ቅልጥፍና በሚል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጻፉት ማሳሰቢያም ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን የሚፃረር መኾኑ ሌላው የመነጋገሪያ ነጥብ መኾኑ አልቀረም፡፡ ፓትርያርኩ በቁ///326/301/04በቀን 14/7/2004 . ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጻፉት ደብዳቤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዘጠኝ የቁጠባና ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ቁጥሮች በመዘርዝር ቀደም ሲል በብፁዕ አባ ፊልጶስና በብፁዕ አባ ሕዝቅኤል ጥምር ፊርማ ሲሠራበት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በመቀጠልም አሁን ግን ለሥራ ቅልጥፍና ሲባል ሦስተኛ ሰው ኾኖ የሚፈርም አንድ አባት እንዲጨመር ማስፈለጉንና ለዚህም ብፁዕ አባ ገሪማ መጨመራቸውን፣ ከሦስቱ በተገኙት በሁለቱ ጣምራ ፊርማ ሒሳቡ እንዲንቀሳቀስ ለሚመለከታቸው ቅርንጫፍ ባንኮች እንዲተላለፍላቸው ጠይቀዋል፡፡
ደብዳቤው በግልባጭ የደረሳቸው የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 30 ቁጥር 17 እና 18 መሠረት÷ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት /ቤት ሥር በሚገኝ በኮሚሽን ወይም በመምሪያ ወይም በድርጅት ወይም በት/ቤት ወይም በሌላ የሥራ ዘርፍ ስም የተከፈቱትን የባንክ ሒሳቦች በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ከሁለቱ ከአንደኛው ጋራ በጣምራ ፊርማ ያንቀሳቅሳል፤ ስለሚል ሥራውን ለማቀላጠፍ በሚል ያለቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድና ውሳኔ የተጻፈው የብፁዕ አቡነ ገሪማ ፈራሚነት እንዲነሣ ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ ይጠይቃሉ፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስም ይህንኑ በመድገም አባ ጳውሎስ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ተመልክተው የማስተካከያ ደብዳቤ እንዲጻፉ ያሳስባሉ፡፡
ይኹንና ፓትርያርኩ ከምልአተ ጉባኤው ስብሰባ አንድ ወር በፊት ሕግን በመተላለፍ የፈጸሙትን ስሕተት በሁለቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማሳሰቢያ ሊያስተካክሉ ባለ መፍቀዳቸው በአጠቃላይ በዐርቡ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የቅ/ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በቃኝ፤ ከሓላፊነቴ መልቀቅ እፈልጋለኹ የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ከራሳቸው በተጨማሪ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ፊልጶስም መልቀቅ እንደሚኖርባቸው እዚያው ስብሰባው ላይ ነግረዋቸዋል፡፡ ለአባ ጳውሎስ ጫና ተጋላጭ የኾኑት አቡነ ፊልጶስ በዚህ ምልአተ ጉባኤ በሥራ አመራርና በውሳኔ አሰጣጥ በአቋም የመጽናት ክፍተት እንዳለባቸው ጎልቶ እየተነገረ ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በመኾን በተደራቢነት ከያዙት ሓላፊነት አንሡኝማለታቸው ተዘግቧል፡፡ በዋናነት የሰሜን ምዕራብ ሸዋ - ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕነታቸው ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በኋላ በያዙት የአዲስ አበባ /ስብከት አመራራቸው ወቀሳም ምስጋናም አስተናግደዋል፡፡ የአሁኑ የመልቀቂያ ጥያቄያቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካጋጠማቸው የጤና እክልና አሁን በዋና ሥራ አስኪጅነት አብረዋቸው የሚሠሩት ንቡረ እድ ኤልያስ በሚፈጽሙት ግልጽ የወጣ ሙስናና የአስተዳደር በደል ጋራ ሳይያዝ እንደማይቀር ተመልክቷል፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደሚናገሩት ለሁለቱ ብፁዓን አባቶች ከሓላፊነት የመልቀቅ ጥያቄ በአጀንዳ . (6) ማእከልን ጠብቆ አለመሥራት በሚል የተቀመጠው ርእሰ ጉዳይ ሌላው ምክንያት መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ከቀትር በፊት በነበረው የዕለቱ ስብሰባ የሻ ዕረፍት ላይ ለምልአተ ጉባኤው አባላት የተሰራጨውና በሕገ ወጥ መንገድ የሰንበት /ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾኖ የተሾመው / ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተ ያሰራጨው ደብዳቤ ከሻሂ ዕረፍት መልስ ከአጀንዳው ጋራ ተያይዞ ለተካሄደው የተጋጋለ ውይይት ምክንያት መኾኑ ተገልጧል፡፡
/ ዕንቍ ባሕርይ ተከስተ ማኅበረ ቅዱሳን እየፈጠረ ስላለው ሕገ ወጥ አካሄድ ይመለከታል በሚል ባዘጋጀው ሁለት ገጽ ደብዳቤ ማኅበሩን ከመምሪያው ጀምሮ በየደረጃው ላሉት የቤተ ክርስቲያን አመራሮች እንደማይታዘዝና በቤተ ክርስቲያን ስም ባስፋፋቸው ተቋማት በሚልዮን የሚቆጠር ብር መሰብሰቡን በመግለጽ ይከሳል፡፡ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ማኅበሩ እንዲፈጽማቸው ታዝዞአልታዘዝምበማለት እያረሳሳ ያቆያቸውን ውሳኔዎች ሥራ ላይ እንዲያውል ከመምሪያ ሠራተኞች ጋራ በመኾን አምነው በፈቃዳቸው ከፈረሙበት በኋላ የማኅበሩ አመራር አካላት በሰጧቸው ስውር አመራር በተጽዕኖ እንደ ፈረሙ በማስመሰል የማደራጃ መምሪያውን ክብ ማኅተም ከመምሪያው ነጥቀው በመውሰዳቸው ከሓላፊነታቸው መነሣታቸውን ደብዳቤው ያትታል፡፡
ይህ ኾኖ ሳለ ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳዩን በመግለጽ በቁጥር ማቅሥአ/45/02//04 በቀን30/8/04 . ሰንሰለቱን በጣሰ መንገድ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበው አቤቱታምየሐሰት ውንጀላመኾኑን በመግለጽ ማኅበሩ የመምሪያውንመሪዎችና ሠራተኞችበመናቅ ያለ ደረጃው የሚያቀርባቸው ደብዳቤዎች ተቀባይነት እንዳይኖራቸው የማያዳግም አመራር እንዲሰጥበት ይጠይቃል፤ እንደተለመደውም ደብዳቤውን በአድራሻ ለቅዱስ ሲኖዶስ /ቤት ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ግልባጭ አድርጓል፡፡
የደብዳቤው ውጤት ግን ዕንቍ ባሕርይ እንዳሰበው ሳይኾን የምልአተ ጉባኤውን አባላት ክፉኛ ያስቆጣ ነበር፡፡ ይህ ስሜት በመደበኛ ስብሰባው ላይ ለተከታታይ ሁለተኛ ቀን የታየ ነበር፡፡ ከአንድ ቀን በፊት ምልአተ ጉባኤው በማኅበራት ዙሪያ የተጠና ነው በተባለውና ፓትርያርኩ ባስያዙት አጀንዳ መሠረት በንቡረ እድ ኤልያስ በቀረበው ጽሑፍ መነሻነት ሲወያይ የመልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ መነሣትን፣ የዕንቍ ባሕርይ መተካትንና ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የጋለ ስሜት የተላበሱ አቋሞች ተራምደው ነበር፡፡
መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ በመንበረ ፓትርያርኩ ምርጫ ከተሾሙ ገና አንድ ዓመት እንዳልሞላቸው ያስታወሱት የስብሰባው ተሳታፊዎች እናንተው አስቀምጣችኋቸው አሁን ምን ስላደረጉ ተነሡ? ዕንቍ ባሕርይስ በየትኛው የተሻለ ብቃቱ ነው የሚሾመው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ዕንቍ ባሕርይ ከመምሪያው ጸሐፊ እና ከኀይለ ጊዮርጊስ ጥላሁን ጋራ በመኾን ሚያዝያ 19 ቀን 2004 . ምሽት ዋና ሓላፊውን ወደ አቡነ ገሪማ ቢሮ በመጥራት ማኅበረ ቅዱሳን የመስከረም 12 ቀን 2002 . ውሳኔዎችን 10 ቀናት ውስጥ እንዲፈጽም ትእዛዝ የሚያወርድ ደብዳቤ እንዲፈርሙ መገደዳቸው ለካ ቤቱ የሽፍታ ቤት ኾኗል የሚያሰኝ እንደ ኾነ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ተናግረዋል፡፡
ስለ ማኅበሩ የተሰነዘሩ አስተያየቶች ሲጠቃለሉ ማኅበረ ቅዱሳን አርቅቀንና አጽድቀን በሰጠናቸው መተዳደሪያ ደንብ የሚመሩ፣ በሞያቸውና በገንዘባቸው ያሳደግናቸው ልጆቻችን ናቸው፤ ይህን የምንነጋርበትን የመናፍቃን ወረራ መረጃ የሠራነው እኮ እኛ አይደለንም፤ እነርሱ ይህን ባይከታተሉ ቤተ ክርስቲያን የመናፍቃን መቀለጃና መጫወቻ ትኾን ነበር፤ ምንድን ነው ሁልጊዜ ነገር እየፈለጉ መጻፍና ማሳደድ? በፖሊቲካና በአስተዳደር ነገር እየተበተቡ መክሰስ? መቼስ ነው የሚቆመው? ማኅበሩን መበተን ቤተ ክርስቲያንን በድጅኖ የማፍረስ ያህል ነው፤ የሚሉ ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጋራም በተያያዘ በኀሙሱ ስብሰባ አባ ጳውሎስ ከኀይለ ጊዮርጊስ ጋራ መክረው ለአባ ገሪማ በስልክ በሰጠት መምሪያ በመታገዝ ዕንቍ ባሕርይ በሽፍታ ሥርዐት ከያዘው ሓላፊነት ተነሥቶ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ መመለስ እንዳለባቸው ጉባኤው ሐሳብ ሰጥቶ ነበር፡፡
በተከታዩ ዐርብ ስብሰባም ተመሳሳይ ሐሳቦች ተደምጠዋል፡፡ እንዲያውም የዋና ሓላፊው መነሣት ከእርሳቸው ዕውቅና ውጭ የተፈጸመ ሕገ ወጥ ተግባር መኾኑን ያስረዱት የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ዕንቍ ባሕርይ ተከሥተና ጸሐፊው / መኰንን ወልደ ትንሣኤ መምሪያው የሚመጥኑ ባለመኾኑ እንዲነሡላቸው ጠይቀዋል ተብሏል፤ ከእነርሱ ጋራ መሥራት አልችልም፤ መነሣት አለባቸው፤ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡
ብፁዕ አባ ገሪማ ሲኖዶሱ የአንድን መምሪያ ጉዳይ በዚህ መልኩ ማየት እንደማይገባው በመግለጽ ለመቃወም የሞከሩ ቢኾንም አባ ኅሩይ ከመምሪያው ዋና ሓላፊነት በሕገ ወጥ መንገድ የተነሡበትን ደብዳቤኮ ያጻፉት እርስዎ ነዎት፤ እርስዎ በጻፉት ደብዳቤኮ ነው የምንበጠበጠው፤. . .ይኸው ራሱ ዕንቍ ባሕርይስ አይደለም ወይ በደብዳቤ የጠየቀን፤ ይህን ማየት እንዴት ይሳንዎታል?” በሚል ምላሽ በብፁዓን አባቶች ተሰጥቷቸው ተቃውሟቸውን አንሥተዋል፡፡
በዕለቱ የማኅበሩ አመራር ተወካዮች ገብተው ለማስረዳት ዝግጁ የነበሩ ቢኾንም ዋና ሓላፊውን መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይንም መጨመር በማስፈለጉና ውይይቱ በሌሎች ሐሳቦች በመራዘሙ ለዛሬ እንዲቀርቡ ትእዛዝ ተሰጥቷል፡፡ በዛሬው ስብሰባ የማኅበሩ ተወካዮች የሚወነጀልበትን የኦዲት ሪፖርትና ሌሎች አሠራሮቹን ግልጽ በማድረግ ወደረኞቻቸውን ያሳፍራሉ፤ በማኅበሩ ህልውና ዐይን ቤተ ክርስቲያን እየገጠማት ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግርና መፍትሔውን ያብራራሉ፤ እንደ አባ ሰረቀ ሁሉ ዛሬም እነ ዕንቍ ባሕርይ የቅዱስ ሲኖዶሱን የወሳኝነት ሥልጣን በመሻርና የማኅበሩን መተዳደሪያ ደንብ በመተላለፍ የምክክር እንጂ የመወሰን ሥልጣን በሌለው የዕለት ስብሰባ የተላለፈውን የመስከረም 12 ቀን 2002 . መግለጫ ማስገደጃ የሚያደርጉበትን ዋታ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲሽረው በማድረግ አፈር እንደሚያለብሱት ይጠበቃል፡፡
በተያያዘ ዜና የዕርቀ ሰላም ሂደቱን አስመልክቶ በውጭ በሚገኙት አባቶች ተወካይ በቀረበው ሪፖርት ላይ ምልአተ ጉባኤው ተወያይቷል፤ ሂደቱ በመጪው ሐምሌ ወር እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ መደረሱም ተነግሯል፡፡ በውይይቱ ላይ ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ የሰሜን አሜሪካው አቡነ መልከ ጼዴቅ ሰሞኑን ክርስቲያኖች ሙስሊሞች ለሚያነሡት ጥያቄ ድጋፍ በመስጠት ተቃውሟቸውን እንዲያስተባብሩ ያስተላልፉትን ጥሪ በመጥቀስ ፖሊቲከኞች ናቸው የሚለውን ክሳቸውን አጠናክረዋል፤ አባ ፋኑኤልም ይህንኑ ክስ በማጠናከር የፖሊቲካ አጀንዳ ነው ያላቸው፤ ከፖሊቲከኞች ጋራ መነጋገር አያስፈልግም ማለታቸው ተገልጧል፡፡
ይህ ጉዳይ ወደፊት መጣራት እንደሚገባው ያሳሰበው ምልአተ ጉባኤው በዚህ ሳቢያ ግን የዕርቀ ሰላም ንግግሩ መቋረጥ እንደማይገባው አሥምሮበታል፡፡ መንበረ ፓትርያርኩን በመወከል ከሚነጋገሩት ልኡካን አንዱ የኾኑት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ በውጭ ያሉ አባቶች ዕርቀ ሰላሙን ከልብ የሚፈልጉ ናቸው፤ ችግር ያለው እዚህ ቤት ነው፤ በማለት ፓትርያርኩ እርሳቸውንም የውጭዎቹንም በመወቀስ ለተናገሩት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ ስብሰባ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጡረታን፣ ዝውውርንና ሹመትን በተመለከተ ጉራማይሌ አሠራሮች መኖራቸው ታይቷል፤ የውሳኔዎች አግባብነትም ጡረታ እንዲወጡ ከተደረጉት በመጋቤ ካህናቱ ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ ዝውውሩም ከገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊነት ወደ ሽሬ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት እንዲዘዋወሩ በተደረጉት ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ አብነትነት ተነሥቶ ተገምግሟል፡፡
በላሊበላ የሰባት ወይራ ሆቴል ጋራ በተገናኘ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና በቅዱስ ላሊበላ ደብር መካከል ያለው የይገባኛል ውዝግብ በፍ/ቤት ውሳኔ ለደብሩ የተሰጠ በመኾኑ በቀጣይ በውስጥ አሠራር (በመግባባት) እንዲፈታ፣ በአኵስም ሀገረ ስብከት በብፁዕ ሊቀ ጳጳሱና በአኵስም ጽዮን ማርያም ካህናት መካከል አለ የተባለው አለመግባባት በፓትርያርኩ አማካይነት እልባት እንዲያገኝ ከመግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ተጨማሪ ዜናዎችን ይከታተሉ
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

2 comments:

  1. አልፎ አይቼውMay 22, 2012 at 9:43 AM

    ይድረስ ለመምህር ዕንቍ ባሕርይ
    ከ1984 ዓም ጀምሮ ያለዕረፍት ቤተ ክርስቲያንን ለማፋት በትጋት እየሰራህ ነህ ልብ በ40 አመት ይገዛል ምናለ ራስህን ብትሆን? በአንድ ወቅት ለሽያጭ የተዘጋጀ ያን ሁሉ መጽሄት ሰርቀህና ደብቀህ ያስቀረከውና በአቡነ አብርሃም እጅ ከፍንጅ የተያዝከውን ረሳው? ነገሩ ተድበስብሶ ታለፈልህ እንዳንተ ያለው ሰው እንዴት አንድ መምሪያ መምራት ይችላል? የአንተንና የመሰሎችህን ጉድ ጊዜ ይፍታው ደግሞም አይቀርም፡፡

    ReplyDelete
  2. የአሥረኛው ቀን ውሎ ውሳኔ ወጥቶ ምነው በዘጠንኛው ቀን ሙጭጭ አላችሁ ፡፡ እውነትም በአሠራራችሁ ተኝታችኋል ያስብላል ፡፡

    ReplyDelete