Thursday, May 10, 2012

የጠ/ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች “የዳኛ ያለህ! ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዳኝነት ይታይላት” የሚል ጽሑፍ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አሰራጩ


    •  አቡነ ጳውሎስ ሃይማኖትን በመበረዝ እና በሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት መጠየቅ እና መወገድ ነበረባቸው::
    • ሊቃነ ጳጳሳቱ “ሰማዕታት፣ ነውረኞች፣ ዘገምተኞች እና ጥቅመኞች” በሚል በአራት ተከፍለዋል:
    • አቡነ ጳውሎስ የቅዱስ ሲኖዶስን ሕግ እና ውሳኔ እየሻሩ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ መምራታቸው ሊያሳፍራቸው እንደሚገባ ተነግሯቸዋል::
    • አቡነ ጳውሎስ የመጨረሻውን የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ይዘው ሊቃውንቱን በጡረታ በማግለልና በመርገጥ ሃይማኖት እየበረዙ፣ አዳዲስ መዋቅር እየከፈቱ ሀብቷ በዱርዬ ባለሥልጣናት እንዲወድም እያደረጉ መኾኑ ተገልጧል፡፡ ሰሞኑን በጠቅ/ቤተ ክህነቱ የተፈጸመውን የጡረታና ዝውውር ውሳኔ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያጤነው ሠራተኞቹ ጠይቀዋል፡፡
    • ከጥበቃ መደብ በቀጥታ ተነሥተው የመምሪያ ሓላፊ የኾኑና ሴቶችን በማነወር ሥራ የተጠመዱ ሓላፊዎች እንዳሉ ተጠቁሟል::
    • የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የቦርድ አባላት ያለሞያቸው በግል ወዳጅነት ተሰባስበው ኮሚሽኑን “እየመጠመጡት እና እየገደሉት ነው”::
(ደጀ ሰላም፤ ግንቦት 2/2004 ዓ.ም፤ May 10/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ማክሰኞ በጸሎት የተከፈተው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ትናንት ግንቦት1 ቀን 2004 ዓ.ም እንደሚጀመር ተጠብቆ የነበረ ቢኾንም እንዳልተካሄደ ታውቋል፤ ምክንያቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በዓለ ልደት ለማክበር በየአጥቢያው መሰማራታቸውና ከዚያም መልስ ፓትርያርኩ ለመሰብሰብ እንደማይችሉ በመግለጻቸው ነው ተብሏል፡፡ ስብሰባው ዛሬ እንደሚጀመር ተስፋ እየተደረገ ባለበት ኹኔታ ከሚያዝያ 30 ቀን ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች እንደተዘጋጀ የሚገልጽና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ለውስጥ በመሰራጨት ላይ የሚገኝ ጽሑፍ ለደጀ ሰላም ደርሷል፡፡


የጽሑፉ ይዘት በዋናነት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዐምባገነናዊ አስተዳደር፣ ሙስና እና ኑፋቄ ተሳስረውና ተመጋግበው የሚያደርሱትን ጥፋት የሚዘረዝር በሓላፊነትም አብዛኞቹን ጳጳሳት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ በተለይም“በነውረኛና ክፉ ፍቅር ተጠምደው ቤተ ክርስቲያኒቱን እያጠፏት ነው”ባሏቸው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እና አቡነ ገሪማ ላይ ያተኩራል፤ መላውን ጳጳሳት ሲገልጻቸው፡- ለቤተ ክርስቲያናቸው ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡና ሰማዕት የኾኑ፣ አንገት የሚያስደፋ ተግባር ያለባቸውና ቤተ ክርስቲያናቸውን መከላከል የማይፈልጉ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር መረዳት የተሳናቸው የዋሃንና ዘገምተኞች፣ በልዩ ልዩ ጥቅም የተያዙ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ቢዝነስ የሚሠሩ በማለት በአራት ከፍሏቸዋል፡፡


ደጀ ሰላም የጽሑፉን ምንጭ ለማጣራት ባደረገችው ጥረት የጽሑፉ ዝግጅት በዋናነት ሰሞኑን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከተፈጸመው የዝውውር እና ጡረታ ውሳኔዎች ጋራ የተያያዘ ሲኾን ከጽሑፉ አዘጋጆች ጥቂት የማይባሉት በመምሪያ ሓላፊነት ደረጃ ያሉና የነበሩ እንደ ኾኑ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ለ30ው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት እንደሚቻለው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ 18 መምሪያዎችና 403ሠራተኞች ያሉት ሲኾን ከእኒህም ውስጥ 338 ቋሚ 65 ደግሞ የኮንትራት ሠራተኞች ናቸው፡፡

በቅርቡ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በሁለት ዙሮች በተላለፈው ውሳኔ በአጠቃላይ26 ሠራተኞች በጡረታ እንዲገለሉ ተደርጓል፤ ከእኒህም ውስጥ በመቐለ፣ በሰላሌ - ፍቼ፣ በድሬዳዋ እና በኋላም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የቤቶች አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጋቤ ካህናት በመኾን የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ የኾኑት መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ሓላፊ የኾኑት በኵረ ትጉሃን ዓለም አታላይ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ምንጮቹ እንደሚናገሩት የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ሓላፊው በኵረ ትጉሃን ዓለም አታላይ ዕድሜያቸው ለጡረታ አልደረሰም፤ ያለጊዜያቸው በጡረታ ሰይፍ የተቆረጡት አላግባብ የሚደረጉ ዕቃ ግዥዎችን፣ ሌሎች ብኩንነቶችንና ምዝበራዎችን በመቃወማቸው ነው፡፡

የአቋቋም ሞያ ዐዋቂ፣ የወንበር መምህርና በየዐውደ ምሕረቱ ለአቡነ ጳውሎስ የሚዥጎደጎደውን የውዳሴ ዝናም በማስተባበር የሚታወቁት ሊቀ ማእምራን ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም ይመሩት በነበረው የካህናት አስተዳደር መምሪያ በዋና ሓላፊነት የተተኩት በዋልድባ ገዳም ላይ የተነሡ አቤታቱታዎችን በሽሬ፣ በማይ ፀብሪ እና በጎንደር ከተማ በተደረጉ ስብሰባዎች ለማስተባበል ሲሟሟቱ በብዙኀን መገናኛ የታዩት ንቡረ እድ ተስፋይ ተወልደ ናቸው - ውለታ መኾኑ ነው?

በዝውውር ውሳኔው ውስጥ ለብዙዎች አነጋጋሪ የኾነው በፊት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና በኋላ የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ የኾኑት ንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ - ሽሬ እንዳሥላሴ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በማድረግ ከአዲስ አበባ እንዲርቁ መደረጋቸው ነው፤ በምትካቸው በመንበረ ፓትርያሪክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰባክያነ ወንጌል አንዱና ማዕርገ ምንኵስና የሌላቸው መ/ር ሰሎሞን ቶልቻ የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ሓላፊ ኾነው ተሾመዋል፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ኾነው እየሠሩ ያሉት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ በቅኝት ስም በየአጥቢያው በመዞር እያፈሱት በሚገኘው የምእመናን ገንዘብ አገልጋይ ካህናትን እያስለቀሱ ነው፤ በየረር ቅድስት ሥላሴ እና በሌሎች የተለያዩ ቦታዎች የአብያተ ክርስቲያን መሬቶችን በግል ስማቸው እስከ ማዛወር መድረሳቸውም እየተነገረባቸው ነው፡፡ ንቡረ እዱ እንዲህ የሚያደርጉት ብቻቸውን አይደለም፤ አዲስ አበባ የቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው በሚል በወር እስከ ብር 10,000 ‹ደመወዝ› ፈሰስ እንደሚያደርጉላቸው ተጠቁሟል፡፡የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ሓላፊ የነበሩት፣ በአሰቦትና ዝቋላ ገዳማት ቃጠሎ የተዛባ መግለጫ ሲሰጡ የቆዩት ሊቀ ኅሩያን ዳዊት ለፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ‹ባጓደሉት ታማኝነት› ሳቢያ ፓትርያርኩ“መጋዘን አስገባልኝ” ብርቱ አገልጋዮችን ወደሚያገሉበት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት (በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት) አባል ኾነው ተዘዋውረዋል፤ በእርሳቸው ምትክ የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ መ/ር ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ሓላፊነቱን ቦታ እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሠራተኛው ከፍተኛ የሙስና ሐሜት እየተሰማባቸው የሚገኙት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያው ዋና ሓላፊ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ፣ የብቃት ጥያቄና በአሿሿማቸውም የአሁኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ እንደሚኾኑ የሚጠበቁት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ውብሸት ሌሎቹ የሠራተኛው ጽሑፍ ዒላማዎች ናቸው፡፡


የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ምክትል ሓላፊ የነበሩትና ሕገ ወጦቹ እነ በጋሻው ደሳለኝ በበጎ አድራጎት ስም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሊያካሂዱት ያቀዱት ‹ጉባኤ› እንዲታገድ የተንቀሳቀሱት ቀሲስ ሳሙኤል እሸቱ ከቦታቸው ተነሥተው በስዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ አስተዳደር ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ ተዛውረዋል፡፡ በእርሳቸው ቦታ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ምክትል ሓላፊ ተተክተዋል፡፡


ጡረታውም ዝውውሩም ቅንነት የጎደለው፣ መጥቀሚያና መበቀያ መኾኑን የሚናገሩት የቤተ ክህነቱ ምንጮች ዕድሜያቸው ለጡረታ ቢደርስም ፓትርያርኩ ለጡረታ አስወጪው ኮሚቴ በሰጡት ቀጥተኛ ትእዛዝ “እነርሱ አይውጡብኝ” ያሏቸው እንደ እነ ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገብረ ዐማኑኤል (የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ) እና ልዩ ጸሐፊያቸው አሰፋ ሥዩም በሥራቸው እንዲቀጥሉ ከተደረጉት መካከል እንደሚገኙበት ይናገራሉ፡፡


የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሊጣራ ይገባል ያሉትን የሃይማኖት ሕጸጽ በመጥቀስ በሃይማኖት በራዥነትም ከሰዋቸዋል፡፡ በ1988 ዓ.ም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮና የውጭ ግንኙነት” በሚል በታተመውና በወቅቱ በግፍ ከሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢነታቸው የታገዱት አለቃ አያሌው ታምሩ በከፍተኛ ደረጃ የተቃወሙትን መጽሐፍ ቀዳሚ እትም ላይ “ሁለት ባሕርይና ሦስት መለኰት” ተብሎ የወጣውን ከባድ ሕጸጽ በመጥቀስ አቡነ ጳውሎስ እንደ ቤተ ክርስቲያን ሕግ መከሰስ እና መወገድ ይገባቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይህ ባለመኾኑ ፓትርያርኩ “እመቤታችን ጥንተ ሰብሶ አለባት”ከሚሉት አባ ሰረቀ ጋራ እየተባበሩ ስለኾነ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን ተመልክቶ ይወስንበት ዘንድ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች “የዳኛ ያለህ” ብለዋል - በጽሑፋቸው፡፡


የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች በቀረበለት ማስረጃ መሠረት የአባ ሰረቀ የእምነት ሕጸጽ እንዲጣራ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ኮሚቴ ካቋቋመ በኋላ አባ ሰረቀ (Left Picture) “እውነትና ንጋት” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ መሰል “ጥራዝ”አቡነ ጳውሎስ እ.አ.አ በ1988 በአሜሪካ ፕሪንስተን ቴዎሎጂ ኮሌጅ “Filsata: The Feast of the Assumption of the Virgin Mary and the Mariological Tradition of the Ethiopian Othodox Tewahedo Church” በሚል ርእሰ ጉዳይ የሠሩትን የዶክትሬት ጽሑፍ (ዲዘርቴሽን) ጠቅሰዋል፡፡
አባ ሰረቀ በእርሳቸው ላይ ያሉትን ትኩረቶች ለማስቀየስ በመጽሐፍ መልክ ያወጡት ጥራዝ በቤተ ክህነቱ ሠራተኞች ፍና ተሣልቆ “SerekeLeaks” - ሰረቀሊክስ (ሐሳቡ ከዊኪሊክስ የተወሰደ ይመስላል) የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲኾን ዋነኛ ይዘቱ በሥራ ሓላፊነታቸው ወቅት የተጻጻፏቸው እና በሥራ ሓላፊነታቸው አማካይነት ያገኟቸው ዶሴዎች ናቸው፤ ከሥራ ሥነ ምግባር አኳያ አባ ሰረቀ ለግል ፍላጎታቸው ላሰቡት የሕዝብ ግንኙነት ፋይዳ የማይውሉና መጠበቅ የሚገባቸው ነበሩ፡፡

የኾነው ኾኖ አቡነ ጳውሎስ በዲዘርቴሽኑ መግቢያ ላይ እንዳሰፈሩት በነገረ ማርያም ላይ በዓለም ደረጃ (Ecumenical dialogue regarding Saint Mary)የአስተምህሮ አንድነት ለማምጣት (In search of a unifying Mariology) በማሰብ በሠሩት ጥናት (Academic project) ንጽሐ ጠባይ ያላደፈባት፣ ምንም ምን ነውር ያልተገኘባት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአዳም በዘር ቍራኛ የተላለፈው የውርስ ኀጢአት እንዳለባት መጻፋቸውን በዋቢነት አንሥተዋል፡፡

በአንዳንዶች አስተያየት ጥናቱ ለአካዳሚያዊ ዓላማ በአካዳሚያዊ ተቋም ውስጥ የተሠራ ነው፡፡ ይኹንና አቡነ ጳውሎስ ከኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖት ቀናዒነት አኳያ በየጊዜው በሚያሳዩት የላላ አቋም እና ግዴለሽነት ብዙዎች ሕጸጹ ከአካዳሚያዊ ተቋምና ዓላማ አልፎ የእምነት አቋማቸው እንዳደረጉት ያሳያል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያንና የሮም ካቶሊክ ተወካዮችበጥር ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ንግግር ሲያካሂዱ በነበረበት ሰሞን በተከበረው የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ባሰሙት ንግግር በ451 ዓ.ም በኬልቄዶን በተደረገው ጉባኤ መለካውያን የተወገዙበትንና እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከእነርሱም በኋላ እንደ እነርሱ ብዙዎች ቅዱሳን ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ወሳኝ ዶግማዊ ልዩነት “ለ1500 ዓመት የኖረ ጭቅጭቅ” ሲሉ ማቃለላቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጸሎተ ቅዳሴ ወቅት እንደ ሥርዐቱ ጀምረው የማይጨርሱበት ኹኔታም ይታያል፤ ነገሩ ከእርግና እና ሕመም በላይ ነው እየታየ ያለው፡፡ የአዘቦቱን ትተን ለአብነት ያህል በዐቢይ ጾም ወቅት በሆሳዕና እና በትንሣኤ ሌሊት በተከናወነው ጸሎተ ቅዳሴ በፓትርያርኩ ተጀምሮ በአቡነ ገሪማ ያለቀበትና ሌሎችም የድፍረት መተላለፎች የታዩበት ኹኔታ ተስተውሏል፡፡ ጉዳዩ ዛሬ በሚጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዋነኛ አጀንዳነት ሊቀርብ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

6 comments:

  1. ጳውሎስን ማስወገድ አይቻልም ወይ?

    ReplyDelete
    Replies
    1. I have been asking this same questions for sooooooooooooo many times. I think it is possible as far as we all are united.

      Delete
  2. May God give us true Ethiopian Orthodox patriarch like the previous ones.

    ReplyDelete
  3. What is Abuna Pawlos and Abuna Samuel fighting about?

    ReplyDelete
  4. To Anonymus of May 10, 2012 11:05PM

    It looks Abune Samuel is fighting for truth. He is just doing his job (Managing the "LIMAT KOMISION". This include safeguarding the assets of the comission.
    On the other hand Paulos is trying to take the asset(money) of the comission and use it for himself.

    In short I think Abune Samuel is working may be for the church but Paulos is working forhimself!!!

    That is why there can't be a reconciliation between these two people.

    ReplyDelete
  5. Hello! I know this is kind of off topic but I was wondering if you knew where
    I could find a captcha plugin for my comment form?
    I'm using the same blog platform as yours and I'm having problems finding one?
    Thanks a lot!
    Feel free to surf my web page ; GFI Norte

    ReplyDelete