Thursday, October 6, 2011

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መሻሻል- ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ



መግቢያ
(ቀሲስ ወንድምስሻ አየለ):- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ራስዋን የቻለች ዓለም አቀፍ ተቋም መሆኗ እንዲሁም ቀኖናዊነትን አጽንቶ የዛሬውን ትውልድ ለመምራት ጥብቅና ዘመናዊ አስተዳደር እንደሚያስፈልጋት ይታወቃል፡፡ ይህ አለመሆኑ በየአጋጣሚውና በሚገባውም በማይገባውም እየተመካኘ እየተነቀፈችበት እንዳለ ማስረጃው በየደጁ አለ፡፡ ከዚህም የተነሣ አመራሩና ምእመኑ የሚፈልገውን መንፈሳዊ ዓላማ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ከዘመኑ ጋር በተጣጣመ አቅም ማከናወን ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ይህን እንደሽፋን ሊጠቀምበት የሚፈልግ የተለየ የእምነት፤ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ፍላጎት ያለው ሁሉ ለራሱ ጥቅም እየገባ ያሻውን እንዲያደርግ ምቹ ሆኖ ቆይቶል፡፡ አሁን ደግሞ ይህ ጥፋት እንዲበቃ ሁሉም ወገን እየመከረበት ይገኛል፡፡ ስለዚህም ወሳኝ የሆኑ ማሻሻያዎችን በግልጽ መወያየትና ስምምነት የተደረሰበትን የተሻለ አደረጃጀት መፍጠር እንዲረዳ የድርሻዬን እነሆ ብያለሁ፡፡ ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ከብዙ መረጃዎችና አማካሪዎች ጋር በመሆን ባለብዙ ዘርፍ ምሁራንና ሊቃውንት ሊሳተፉበት የሚገባና በትልቅ መጽሐፍ ደረጃ ሊታተም የሚችል ጉዳይ እንደሆነ እያወቅሁ ነገር ግን ለመነሻ ብዙዎች በተናጠል በጥናትና በምክክር ደረጃ ያበለጸጉትን ሀሳብ አቀናጅቼ የራሴን ጥቆማ ብሰጥ ይረዳ ይሆናል ብያለሁና በቀናነት እንጠቀምበት፡፡




በመጀመሪያ ያልተለየ ችግር መፍትሔ ካለማግኘቱ ባሻገር ለሌሎችም ችግሮች ምክንያት ሊሆን ስለሚችል በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ባሉ ችግሮች ጠንካራ ግምገማ ሊደረግ ይገባል። በዚያውም ላይ በ፲፱፻፸፩ የጸደቀው የመጀመሪያው በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ሲሠራበት የነበረው “የአስተዳደር መምሪያ የውስጥ ደንብ” በመጀመሪያ አንቀጹ ታላቅና የተዘነጋ አዋጅ አስቀምጧል፤ «ይህ መምሪያ እንደሌላው መሥሪያቤት ሁሉ የጊዜውን የአስተዳደር ፈለግ ተከትሎ ይሠራበታል።» ክፍል ፩ ቁጥር ፩፡፡ በ፲፱፻፺፩ ዓም ጸድቆ እየተሠራበት ያለውም ቃለ ዓዋዲ ይህን በተመለከተ ሲናገር የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ፡-

  1.  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን /ንን ለመጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ፣ 
  2.  የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በሐዋርያዊ ተግባር ለማደራጀትና እንደዚሁም ችሎታቸውንና ኑሯቸውንም ለማሻሻል፣ 
  3.  ምእመናንን ለማብዛትና እንደዚሁም በመንፈሳዊ ዕውቀት ጎልምሰው በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው በክርስቲያናዊሕይወት እንዲኖሩ ለማድረግ፣ 
  4.  የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለማሻሻልና በማናቸውም ጉዳይ ራሷን ለማስቻል» በሚሉ ውብ ሐሳቦች የተንደረደረ ነው።


ከዚህ ብንነሣ እንኳን ሐሳቡ እያለ ለምን አልተሠራበትም? ለምን በየጊዜው የሚያስፈልገው አስተዳደራዊ ማሻሻያ አልተጠናም? ለተሳሳተ ዓላማና ጥፋት ምክንያት እንዳይገኝብንስ ለምን አልተደከመም? ብለን ስንጠይቅ ቀድሞ የተለጠፈብንን የኋላቀርነት ስያሜ እኛው የፈለግነው ወይም የምንፈልግ ወገኖች ያለን አስመስሎብናል። ስለዚህም ይህንኑ ተከትሎ ስለ ወንጌለ መንግሥት አካሄድና ለዚያም ስለሚያስፈልገው የሰው፣ የገንዘብና የአደረጃጀት ሁኔታ ገላጭ መመሪያዎችን ለማሰናዳት መሥራት በየጊዜው ሊጤን የሚገባው እንጂ አስተዳደርን የዶግማ ያህል እንደ ርስት መያዝ፣ ዘመኑ የሚጠይቀውንም ቀልጣፋና ምእመናንን የሚደርስ አሠራር ለመመሥረት ቸል ማለት ተገቢ አይደለም። ተገቢ አለመሆኑን ከተስማማን መፍትሔውን መፈለግ ደግሞ የቅንነትና ቁርጠኝነት ሚናውን የሚወጣ ሁሉ ሊያደርገው የሚገባ ተግባር እና ምናልባት በስጋት ደረጃ የሚቀመጡትን ችግሮችም ለመጋፈጥ መዘጋጀት የሚያስፈልግ ነው።

ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ዳሰሳ /SWOT analysis/

ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋን ለማሳካትና ራዕይዋን እውን ለማድረግ እስካሁን ያሳለፈቻቸውን ሂደቶችና አሁን ድረስ የዘለቁትን ችግሮች መዳሰስ ለዘላቂ ጥንካሬዋና ውጤታማነቷ ወሳኝ መነሻ ነው። በዚህም መሠረት የሰውና የሥራ ጠባይ የሚያመጡትን ትተን ለማሻሻያው ወሳኝ የሆኑት ላይ እናተኩራለን። የሰውና የሥራ ጠባይ የሚያመጣቸው የምላቸው የግለሰቦች የክብርና የነጻነት ፍላጎት፣ የምቾት/ የተሻለ አኗኗር ምኞት፣ የዕውቀት መለያየትና የሚያመጣው ጉድለት፣ ያልተሸፈኑ ኃላፊነቶችን መሻማት፣ ባለው ክፍተት ተጠቅሞ የወገንን ጥቅም ማስቀደም፣ ይህንም የመሰሉ ናቸው።

ውስጣዊ ሁኔታዎች፡ጠንካራና ደካማ ጎኖች

ጠንካራ ጎኖች፡-
  • የምእመናኑ፣ የአድባራትና ገዳማት ብዛት፡ የመንፈሳዊ ት/ቤቶች /የአብነትና ኮሌጆች/ ብዛት፡ የራሷ ሲኖዶስ መኖሩ፡ ዘመናዊ ሳይንስ የተማሩ ካህናትና ምእመናን መኖራቸው፡ ለማሻሻያው ወሳኝና ጠንካራ ጎኖቿ ናቸው፡፡
ደካማ ጎኖች፡-
  • ምእመናኑ በየሀገረ ስብከቱ በተለያየ ደረጃ የወቅታዊ ችግሮች ግንዛቤ፣ የቤተ ክርስቲያን /ኗን ጥልቅ ትምህርት ከተመሳሳይ ስህተት ለይቶ የማወቅ፣ በልዩ ልዩ ቅልቅል ባህሎች መጠለፍ፣ በዘመናዊነት ሰበብ ለሃይማኖት ግድየለሽ የመሆን ችግሮች፤ 
  • ለምእመናኑ አስተሳሰብና አኗኗር የሚመጥን የካህናትና የመምህራን ሥርጭትና ብቃት /ብዛትና ጥራት/ አለመኖር፤ 
  • የስብከተ ወንጌሉን ፍላጎት የሚደርሱ ዘዴዎች አለመደራጀት፣ /ቋሚ የጽሑፍ ዓምድ፣ ድረ ገጽ፣ የታቀዱ ማብራሪያ መጻሕፍት፣ የድምጽና ምስል ሕትመቶች፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ሥርጭት ፕሮግራሞች ገና የለም በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑ፤ 
  • ለምእመናን አንድነት የሚያግዝ አስተዳደራዊ መዋቅር አለመኖሩ፣ የአኅጉረ ስብከትና አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗ ውጤታማነትና ስኬት በግለሰቦች /ምእመናን ወይም ካህናት/ ላይ የተመሠረተ ከመሆኑ አልፎ አንዱ የጀመረውን ሌላው ሊያፈርሰው የሚችልበት ክፍተት ያለው መሆኑ፤ 
  • የአሥራት፣ በኩራትና መብዐ አሰባሰባችን በአጥቢያው ምእመናን ደግነት፣ በሰበካው አስተዳደር ትጋትና ታማኝነት፣ በወረዳውና ሀገረሰብከቱ ርቱዕነት እንጂ ምእመናንን የሚያስገድድ፣ ሰብሳቢዎችንም የሚቆጣጠር ወጥነት ያለው አለመሆን፤ 
  • የአድባራት፣ ገዳማትና አብነት ት/ቤቶች በዝርፊያና ቃጠሎ ለመጠቃት፣ ለስህተት ትምህርትና ለልዩ ልዩ መከፋፈል አደጋ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ መሆን 
  • በዚህ መጠን ተብሎ የማይለካ፣ በአስተዳደር ላይ ባሉት ሠራተኞች በአብዛኛው ከአካባቢያዊ ልጅነት ውጪ አለመተማመንና መጠራጠር፣ በአሠራር ፍቱንነት /efficiency of system/ አለማመን፤ በአድልዎ ለራስና ለወንዝ ወዳጅ ዕድሎችንና ጥቅምን ማካፈል፣ ለሹመትና ኃላፊነት ቦታዎች ወንዝንና ጎጥን ማስቀደም፡ ለዶግማና ቀኖና ችግር ባያጋልጥም አስተዳደራዊ ችግሮችን የሚያስቀጥል መሆኑ።
ውጪያዊ ሁኔታዎች
መልካም ዕድሎች
  • የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት በሕገ መንግሥቱ መሥፈሩ፣ የሌላ እምነት ተከታዮች በተለይም የአፍሪካም ሆነ የተቀረው ‹መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዓለም› ቤተ ክርስቲያንን ስለ እውነተኛ መንፈሳዊነቷ ተስፋ ማድረጉ፣ አኀት አብያተ ክርስቲያን በተለያየ ደረጃ ዘመኑን ለመዋጀት በመሞከራቸው ተሞክሮ ለመውሰድ መነሻ መሆናቸው፣ በልማት ተሳትፋ የኢኮኖሚ አቅሟን ለማዳበር የሚያስችሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸው፤
ስጋቶች 
  • የአክራሪ እስልምና ቡድኖች ቤተ ክርስቲያንን በኃይልና ሰርጎ በመግባት በስውር ለማጥፋት ሁለገብ ዕቅድና ዝግጅት ያላቸው መሆኑ፤ 
  • የተሐድሶ-ፕሮቴስታንቶች የዘወትር ዓላማ በሁለገብ አሠራር የቤተ ክርስቲያንን ወጥ ትምህርትና መገለጫዎቿን ትውፊቶች የማዳከም በሂደትም አጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኗን የመክፈል/ የማፍረስ እንቅስቃሴ በስፋት እየተሠራበት መሆኑ፣ 
  • የንግድና ፣ ኢንደስትሪው እንቅስቃሴ ሲሰፋ በሂደትም የከተሞች መስፋፋትና የአኗኗር ዘይቤ አለመመቸት ምእመናንን አሁን ባለው የአገልግሎትና አስተዳደር አፈጻጸም ማግኘት ያለመቻል ችግር፣ 
  • የዘመኑ አኗኗር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክንያት በሚፈጠር የጊዜ አጠቃቀምና መርሐግብር ለውጥ ምክንያት ውስብስብና ከዚያም ውጪ ለማሰባሰብ ውጥረት እየበዛበት የሚሄድ በመሆኑ ያለው የስብከትና አምልኮ ሥርዓት መርሐግብር በሂደት ጥናትና ክለሳ መፈለጉ ባለው የተሐድሶ አቀንቃኞች ለመጠለፍ መጋለጡ፤
የግምገማ  ማጠቃለያ
ከላይ ከተገለጹት ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር ሁሉንም/ ብዙዎችን ወገኖች ለማዳን፣ ግን ሁለገብ ጥንቃቄ ማድረግ የሚችል የማሻሻያ ረቂቆችን የሚያመነጭ የሊቃውንትና ምሁራን ውይይት የሚደረግበት ጉባኤ /በጥናትና ምርምር ማዕከል ደረጃ/ ያስፈልጋል።

በሌላ አባባል የሊቃውንት፤ የሳይንስ ምሁራንና የምእመናን የምክክር መድረክ ወይም ማዕከል ማቋቋም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

ከዚህም ጋር የምእመናንን አንድነት ለማጽናት ይቻል ዘንድ ማሻሻያው እስኪጠናቀቅ ከአጥቢያ አስተዳዳሪዎች፤ አበምኔቶች፤ ከቤተ ክህነት ኃላፊዎች፤ ከሒሳብ አንቀሳቃሾችና ከደኅንነት ጥበቃ ኃላፊዎች ጀምሮ ሥልጣናቸው ተገድቦ በማዕከላዊ አሠራር በምእመናን ሰፊ ተሳትፎ የሚመራ የስብከተወንጌልና የልማት ዕቅድ ሊኖር ይገባል። መጨረሻው ግቡ አንድ ቢሆንም ይህን ያገናዘበ በሦስት የተከፈለ የአስተዳደር ማሻሻያ ሂደት ቢጀመር መልካም ነው።
  1. አቅም ጥናት፡- ያለውን አቅም የሚያጠና በሊቃውንት ጉባኤ ውስጥ የተዋቀረ ክፍል ያለው የምእመናን፣ የአድባራት፣ የገዳማት፣ የጉባኤ ቤቶች፣ የካህናት፣ የመምህራን፣ የልማት ተቋማትና የቤትና ርስት መጠን መረጃዎችን በየመለኪያው ዓይነት ተዘርዝሮ ሊኖራቸው ከሚችለው ፍላጎት፤ ገቢና አሁን ካላቸው ወሳኝ ችግር ጭምር ቢበዛ በሁለት መንፈቅ ተጠንቶ በተከታታይ ቢቀርብ፣
  2. ማደራጀት፡-  አንድነቷን የሚያጸና፣ የሰው፣ የቁስና የንዘብ ሀብቷንና ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቷን በጊዜያዊነትና በቋሚነት ማደራጀት ያስፈልጋል። 
ጊዜያዊ ማደራጀት የሚያስፈልገው ለጊዜው የሰው ኃይልም ሆነ የቁስና ገንዘብ መጠባበቂያ/ትርፍ ያላቸው አድባራት፤ ገዳማትና አኅጉረ ስብከት ለወሳኝ ችግሮች መፍትሔ አሰጣጥ እንዲያግዙ፣ ምእመናንም ለወሳኝ ተቋማት መደራጀት የሙያ፤ የቁስና የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማደራጀት ነው። 
ቋሚ መደራጀት በራሳቸው አቅም የሚፈለገውን ተግባር ሊወጡ ለሚችሉ አኅጉረስብከትና ወረዳ ቤተክህነቶች ቋሚውን መዋቅር እንዲተገብሩ በማድረግ በአንድ በኩል ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ በሌላ በኩል አዲሱን መዋቅር ለመገምገም እንዲያግዙ ማድረግ ይቻላል። በሂደት ግን ሁሉም አኅጉረ ስብከቶች እየተገበሩት ቢገመገም፡ 
  1. ማወጅና መተግበር፡በሁለቱ ሂደቶች የተገኘውን የግምገማ ውጤት መሠረት በማድረግ በውጤቱ መሠረት የተከለሰውን መዋቅር በቃለ ዐዋዲና በሕገ ቤተ ክርስቲያን/ አካቶ በአዋጅ በማሻሻል በቀጣዩ ፫ ዓመት ተግባራዊ አድርጎ ማጠናቀቅ። በአዋጁ መሠረትም ያሉትን ክፍተቶች በማጥናት ሰፊ ግምገማ በመውሰድ ካስፈለገ አዋጆቹን ማሻሻል፣ በቂ ከነበረም በዚያው የሚቀጥልበትን ዝርዝር ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም የስነዳና መጻጻፊያ ቅጾች በማሳተም ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።   
  2. መከለስ፡ ምናልባት በአተገባበር ላይ የሚታዩ ውጤቶችና ጉድለቶችን ገምግሞ አንድ ጊዜ ለመከለስ በ፲ ዓመት ውስጥ ድጋሚ መገምገም ሊያስፈልግ ይችላል። 
መነሻ መዋቅር

ከዘመኑ አስተሳሰብ /ሳይንስ/ ጋር የሚጣጣምና ከዘመን አመጣሽ ፈተናዎች የሚከላከል መዋቅር ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ቢሆንም በቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ሆነ በጠቅላላ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ አስተያየት ሲሰጥና መለስተኛ ተግባራዊ ሙከራዎች በተበጣጠሰ መልኩ ሲሞከሩ ቆይተዋል። ይህ ደግሞ ድሮም ለሚሠሩት ኃላፊዎች የረዳ ቢሆንም ወጥነት ሊኖረው ባለመቻሉ ለሚሠሩት ሕመም ለዘራፊዎችም ጥሩ የዝርፊያ አማራጭ ከመፍጠር ያለፈ አልሆነም፡- በምሳሌ ለማሳየት የተለያዩ የአስተዳደር ማሻሻያዎች ሊቃውንቱን በጡረታና ተመሳሳይ ምክንያቶች ለማባረር መዳረጉ፤ የሕንጻ ግንባታ፣ የማሠልጠኛዎች በየሀገረስብከቱ መከፈት፣ የልማት ሥራዎች በየቦታው መሞከር ሥልጣን ላላቸው ሙሰኞች ተጨማሪ ምንጭ ነው የሆኑት። ስለዚህም ወጥ የሆነ ማሻሻያ ተደርጎ ከሰው ኃይሉ አደረጃጀትና ከቁጥጥር ሥርዓቱ ጭምር ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው።

በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኗ የመጨረሻ ከፍተኛው ሥልጣን ኖሮት ከሥራ አስፈጻሚው ጠቅላይ ቤተክህነት ሌላ ለአፈጻጸም አመቺ የሆኑ ሌሎች /ቤቶችም ለቅ/ሲኖዶስ ተጠሪ ሆነውለት እየመራቸውና እየተቆጣጠራቸው ልዩ ተግባራቸውን እንዲወጡ የሚያስችልና የሥራ መከፋፈል ክፍተትና ተደራራቢነትን ለማስወገድ የመዋቅር ማሻሻያ አስፈላጊ ይመስላል። የሚከተለው መዋቅር ለመነሻ ሳይረዳ አይቀርም፡-
  1. የሊቃውንት ጉባኤ፣ ከአስፈጻሚውም ሆነ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተመደቡ ኃላፊዎች ተጽእኖ ነጻ የሆነና ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ የዶግማና ቀኖና ጉዳዮችን በሚመለከት ሀሳብ የሚያመነጭና ከሲኖዶሱ ሲታዘዝ የውሳኔ ረቂቅ የሚያዘጋጅ የሳይንስ ምሁራንን ያካተተ ሆኖ ቢደራጅ፤
  2. ጠቅላይ ቤተክህነት፦ አሁን ያለው መዋቅር ተሻሽሎ ቢደራጅ፤
  3. የፓትርያርክ ልዩ /ቤት ይህ መዋቅር አሁን ያለ ቢሆንም ስም ይዞ የሲኖዶስንና የሥራ አስፈጻሚውን ኃላፊነት እየተጋፋ የግለሰቦችን ፍላጎት የሚያስፈጽም ሆነ እንጂ ተወስኖ የተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ግልጥ አይደለም፡፡ ስለዚህም በፓትርያርክነት ስም የማይገባበት ጉዳይ የለም፡፡ እንደ ማዕረጉ መጠንና ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስን እንደራሴነት እንዲወጣ በጸደቀለት ዕቅድ መሠረት በነጻነት እንዲሠራ የሚያመቻች ጽ/ቤት ሆኖ በሕግ ቢደራጅ፤
  4. ኦዲትና ኢንስፔክሽን የአስተዳደርና ፋይናንስ አፈጻጸም መመሪያዎችና ስልታዊና የየዓመቱ ዕቅዶችን የተከተለ የወርኃዊ አፈጻጸም ትክክልነት የሚከታተልና ይህንም ለቅ/ ሲኖዶስ ሪፖርት የሚያቀርብ ቢሆን፤
  5. መንፈሳዊ ፍርድ ቤት የእምነት ተከታዮቿ በፈቃዳቸው የሚመርጡት ክርክርም ሆነ የአስተዳደር ግድፈቶችን በአማራጭነት የሚዳኝና መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው ሕግ ተርጓሚ ቢደራጅ፡ ይህም ለስም ያለ ቢሆንም ሕገ መንግስቱ የፈቀደውን ሥልጣን ለመቀበል ብቁ ባለመሆኑ ዳግም ተደራጅቶ ለሲኖዶስ ተጠሪ ቢሆን፤
  6. የቅዱስ ሲኖዶስ /ቤት በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስን ሥራ የሚያመቻች፣ ውሳኔዎችን ወደሚመለከተው ክፍል የሚያስተላልፍና የ፭ቱ ጽ/ቤቶችን የዕቅድ አፈጻጸም የሚከታተል፣ ከተቻለም የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ፤ ሥልጠናና ምደባ የሚፈጽም ጽ/ቤት ይሆናል።

ስድስቱ ጽ/ቤቶች ለየራሳቸው ከቅ/ሲኖዶስ የጸደቀላቸውን ዕቅድና በጀት በነጻነት እየመሩ /የራሳቸው አስተዳደርና ፋይናንስኖሯቸው/  በጀታቸውንም በሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ተፈርሞ  ከተከፋፈለ በኋላ ቀጥታ ራሳቸው እያዘዙ እንዲሠሩ ማስቻል ያስፈልጋል።

ይህም በስፋት የታየውን ከልክ ያለፈ የፓትርያርክ ጣልቃ ገብነት እና አንበርካኪ አምባገነንነት አስቀርቶ ፭ቱ ጽ/ቤቶች ከፓትርያርኩ ዕውቅናና ፈቃድ መጠየቅ ውጪ በሲኖዶስ የጸደቀ ማንኛውንም ተግባር፣ ኃላፊነትና ዝርዝር ዕቅድ ተጽእኖ ከሚፈጥር የፋይናንስና አስተዳደር አሠራር ተነጥለው እንዲሠሩ ያግዛቸዋል። ብፁዐን ጳጳሳትም በጤንነታቸው፣ሕመማቸው፣ በሲኖዶሳዊ ተግባራቸውና ውክልናቸው (ለምሳሌ የአባቶች ዕርቅ ጉዳይ)፣ ይህንም የመሰሉት ኃላፊነቶች በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በሚንቀሳቀስ የሰው ኃይልና በጀት ይንቀሳቀሳል ማለት ነው።

 ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ /ቤት መምሪያዎች አብዛኛዎቹና መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ መዋቅራቸው እየተቃኘ ወደ ሀገረ ስብከትናወረዳ ቤተክህነት ይወርዳል።
  

 የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት /ቤት
በሦስት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጆች የሚመራ ሰፊ ተግባር ያለው ሆኖ

 የመንፈሳዊ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ
  • የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተልዕኮ፣
  • የትምህርት ተቋማት ተልዕኮ፣
  • የገዳማትና ሙዚየሞች አስተዳደር ተልእኮ፣
  • የሰበካ ጉባኤያትና ወጣቶች ማደራጃ ተልዕኮ፣

 የውጪ አኅጉራት መንፈሳዊ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ 

  • የሰበካ ጉባኤያት ማደራጃ መምሪያ፣
  • የስብከተ ወንጌል ማስተባበሪያ መምሪያ፣
  • የካህናት አስተዳደር መምሪያ፣

 የመንፈሳዊ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ 
  • የትሩፋትና በጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ተልዕኮ፣
  • የካህናት አስተዳደር ተልዕኮ፣
  • የዐቃቤ ሕግና ፍትሕ ተልዕኮ፣
  • የአስተዳደርና ፋይናንስ ተልዕኮ፣

ተልዕኮየሚለው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ የሆነና ሌሎች መምሪያዎች፣ ድርጅቶችና ልዩ ልዩ ማዕከላትን የያዘ እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡መምሪያዎችም በሥራቸው ክፍሎች ሊኖራቸው ይችላል።

  
አፈጻጸም
ቅዱስ ሲኖዶስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሉትን ስውርና ግልጥ ችግሮች ዓይቶ ለመጋፈጥ ጠቃሚ ውሳኔዎችን እየወሰነ ቢሆንም ታላቁ ችግር የሆነው ደግሞ አፈጻጸሙ ነው፡፡ ለዚህም ምእመናንም ድርሻቸውን የሚወጡበት አማራጭ ኖሮ ከፍተኛ ለውጥ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ማየት ተገቢ ነው፡፡ከየአቅጣጫው ከሚቀርቡ ትችቶችና ሂሶች አንጻር የሚከተሉት ጉዳዮች አፈጻጸሙ ላይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው።


  1.  የተሐድሶ አሠራር መወገዝ- የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት በመሸርሸር ዶግማዋንና ቀኖናዋን ለማጥፋት የተነሡት ተሐድሶዎች በስፋት ለመግባት የረዳቸውና ህልውናቸውንም የሚያስቀጥለው ደካማው አስተዳደር በመሆኑ የማሻሻያው ዋና እንቅፋት ወይም ጠላፊዎች ስለሚሆኑ እንደ አጠቃላይ በፍሬዎቻቸው የሚወገዙበትና አጠቃላይ መመሪያ የሚሰጥበት የምእመናንን ድርሻ ያካተተ ሆኖ እንዲታወጅና መረጃ ያለባቸው ደግሞ ሕጋዊ እርምጃዎቹ ያለማስተባበያ እንዲወገዙና እንዲተገበር ቢደረግ፤
  2.  የማኅበረ ቅዱሳን ቀጣይነት- ለፖለቲከኞችና ለተሐድሶዎች ራስ ምታት ሆኖ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ቀኖናዊት ቤተ ክርስቲያንን በታማኝነት ስላገለገለ ቢሆንም ቀኖናን ካለመውደድና ልቅ ባህል ማዳበር የሚፈልጉ ወገኖች በፖለቲካና በሌሎች ተራ ክሶች አላስፈላጊ የቤተ ክርስቲያንን የአገልግሎት አቅም እያባከኑ ስላሉ ማኅበሩ ባለው አቅም የአስተዳደር ማሻሻያውን በማገዝ በኩል ድርሻ ቢሰጠውና አሁን እየተሳተፈባቸው ያሉ ዘርፎችን በሂደት ለሚመሠረተው ጠንካራ አስተዳደር እያስረከበ በቤተ ክህነቱ ውስጥ በምልዓት የሚዋሐድበት ሁኔታ ቢፈጠር፤
  3.  የመንበረ ፓትርያርክ ቅጽረ ግቢ ጥበቃ- ይህ ጉዳይ ለማሻሻያው ሥራ አሳሳቢ መሆኑ ፓትርያርኩን የሚያስወቅስና በመንፈሳዊው ዐውድ መከሠቱ አሳፋሪ ጉዳይ ሲሆን በሲኖዶስ ደረጃ መታየት ባይኖርበትም ለዋናው ጉዳይ አፈጻጸም እንዲረዳ ውይይቶች በሰላም እንዲከናወኑና ቀጣይ አፈጻጸማቸውም እንዲሠምር የጠቅላይ ቤተክህነቱ ጥበቃ ሙሉ ለውጥ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ቢያንስ ለጊዜው መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ የግቢውን ጥበቃ ሊረከብ፤ የአስተዳደር ማሻሻያው ከተተገበረ ከዓመታት በኋላ ወደመደበኛ የጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ሊመለስ ይገባል፡፡
  4.  የታጠቁ የቤተ ክህነት ኃይሎች- ሕጋዊና ሕገወጥ የሆኑ መሣሪያዎችን የታጠቁ ክህነት ያላቸውና የሌላቸው በቤተ ክህነቱ መዋቅር ውስጥ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ ገጠር አጥቢያ ድረስ ያሉ ኃይሎች መኖራቸው ለምን እንደሆነ ለጊዜው ግልጥ ባይሆንም ለአስተዳደር ማሻሻያው ዕቅድ ግን ሁሉም ትጥቅ እንዲፈቱ፤ ወደፊትም ክህነት ያለው ሆኖ ትጥቅ ይዞ መገኘት በራሱ ከክህነት የሚያሽር መሆኑ በቀድሞው ቀኖና መሠረት ተግባራዊ ቢደረግ፡፡
  5.   ቀጣይ ፓትርያርክን በተመለከተ- ልዩ ልዩ ፍላጎት ያላቸው አካላት ወሳኝ ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚፈልጉበትና ዛሬም ሊታይ ይገባዋል የምለው የቀጣይ ፓትርያርክ ምርጫ ጉዳይ ሲሆን ለዕርቅ የሚደረገው ጥረት እየቀጠለ በተረጋጋ ሁኔታ ከወዲሁ ውይይት ቢደረግበት እንጂ ቀኑ ሲደርስ መጀመር ለአላስፈላጊ ጫናዎች መጋለጥ ነውና ቢታሰብበት፤
  6.  የመንግሥት ጣልቃ ገብነት- በ2001 ዓም ግንቦት ወር በተደረገው የአስተዳደር ማሻሻያ አማራጭ ሙከራ ጠንካራ አቋም ይዘው የነበሩ አባቶች ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በሀገሪቱ አሳፋሪና የመንግሥትን ሚና ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሲሆን እስካሁን ጉዳዩ ተጣርቶ 4 ኪሎ ላይ ለተፈጸመው ወንጀል ተጠርጣሪውን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ አለመቻሉ የወንጀል ተባባሪዎች የመንግሥት አመራሮች እንዳሉት ይጠቁማል፡፡ በአንጻሩም አሁን ለሚታሰበው መሻሻልም መንግሥት ሕግን የማስከበር ግዴታውን በተመለከተ ልዩ ዕቅድ አውጥቶ ገለልተኛ ሚናውን እንዲጫወት በቅዱስ ሲኖዶስ ማሳሰቢያና ግብዣ ቢቀርብለት፤       
  7.   ሶምሶን ንስሐ ይግባ፤ ፍልስጤማዊም ይደንግጥ- የፓትርያርክ ጳውሎስ አሳፋሪው ዘመነ ፕትርክና ሌላው ገጽታ የጵጵስና ክብር ከመጠን በላይ መቃለሉ ነው፡፡ ተጠንቶ እየተተገበረ ያለው ጥፋት ጊዜው ሲደርስ የሚገለጥ ሆኖ ለአሁን ግን ብፁዐን አባቶችን በሥነ ምግባር ችግር እያስፈራሩ ማንበርከክ የማሻሻያው እንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር በፈጣሪ ፊት ያለውን ተነሣሂነት ለመደምሰስ የሚሞክር ድርጊት ነው፡፡ ስለዚህም በደሊላ የተታለለ ሶምሶን ካለ ይጸጸት፤ በሕይወቱ ካጠፋቸው ጠላቶቹ ይልቅ በሞቱ ያጠፋቸው እንዲበዙ፡፡ የናዝራዊነታቸው ጠጉር መላጨቱና የራሳቸው መገለጥ ሳይሆን በንስሐቸው ፈጣሪያቸውና ምእመናኖቻቸው በደስታ ስለሚያከብሯቸውና ስለሚጠፉት ጠላቶቻቸው ያስታውሱ፡፡ ሕዝቡም የሚወዳቸውና የሚያከብራቸው በዚህ እንጂ በብልጣብልጥ አማራጭ አለመሆኑ ገሀድ ይሁን፡፡
  8.   አክአብና ኤልዛቤል ይገሰጹ- ስለእውነት መጣመምና ስለፍትሕ መጓደል ሳይሆን ስለክብራቸውና ጥቅማቸው የሚባክኑ፤ በንቀትና በጭካኔ የሚናገሩ መሪዎች በደጉ ሕዝብ ላይ መሾማቸው ለጊዜው ቢጎዳም በኤልያስ መንፈስ የሚሄደው ሲገለጥ ግን አንድ ሲሆን ሺዎችን የሚፈጅ ነውና ከወዲሁ እግዚአብሔርን እንዳወቁት መጠን እንዲያከብሩት ይገሰጹ፤ 
  9.   ናቡቴም ይጨክን ኤልዛቤል መክራ አክአብ ተስማምቶ ርስትህን ሊቀማ የሚመራህ ጨክኖብሀልና የኤልዛቤል ምክር ሳይፈጸም ላይመለስ በሚሸነግሉህ መታለል ሞኝነት እንዳይሆንብህ አሁን ጨክን፡፡ አስተዳደሩ እንዲሻሻል የድርሻህን ተወጣ፤ ገንዘብህ የት እንደዋለ ጠይቅ፤ ለምድ የለበሰውን ተኩላ፤ ክህነት የተሰጠውን አርዮስ፤ ከጠላት የተዋዋለውን ይሁዳ፤ ተሰሎንቄን የሚናፍቅ ዴማስን ለይተህ ዕወቅ፡፡ ከነቢያትና ሐዋርያት የተለየ አዲስ መሠረት የሚገነባውን ሰው በጴጥሮሳዊ ጥብዐት በነጎድጓዳዊው የዮሐንስ ፍቅርና ጥበብ እየተቃወምክ የቀደመውን ርስት ሃማኖትህን እስከሞት ድረስ ጠብቅ፡፡
  10.    ሥላሴ ይሙሉበት- በመቃብር ላይ የተጫነውን ድንጋይ ለማንሣት ከተባበርን ከዚህ ወዲያ ያለው ለሙቱ አካል ሕይወት መስጠት የፈጣሪ ድርሻ ነውና እርሱ ይፈጽመው፤ ለዚህም እንጸልይ፡፡ እርሱ ሲፈቅድ ከአልአዛር አካል ሰበኑን ፈትቶ የሚጥልም ይሾማልና በእርሱ እንታመን፡፡

ለማሻሻያው ደጋፊ የሆነ መረጃ
  • በ1976/77 ዓ.ም ቆጠራ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ ተከታይ የነበራት በ1999/2000 ቆጠራ 43 በመቶ ድርሻ የሆነባት፤
  • በ1984 ዓ.ም በሁሉም አውራጃዎች የተማረ ሰባኬ ወንጌል፤ በሁሉም አኅጉረ ስብከት ብስልና ከየዘርፉ ሊቃውንት ያሉበት፤ በየወንበሩ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ደቀ መዛሙርት የነበራት በ2000 ዓም ከአዲስ አበባና ዙሪያው ወረዳዎችና አጥቢያዎች በቀር ከ80 በመቶ በላይ ወረዳዎች ሙሉ ትምህርት የተማረ ሰባኬ ወንጌል የሌላቸው /አጫጭር ሥልጠና ባላቸው የተተኩበት/፤ ጥቂት የማይባሉ የአኅጉረ ስብከቶችና የጠቅላይ ቤተክህነቱ መምሪያዎች የታወቀ ሙያ በሌላቸው ብልጣብልጦች የተያዘባት፤ ወንበሮች ሁሉ ከ200 በታች ብዙዎቹም /የአቋቋምና የቅዳሴ/ ከ100 በታች ደቀ መዛሙርት የቀሩበት፤ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቃንም ከታላላቅ ከተሞች በተለይም ከአዲስ አበባ ላለመውጣት የተማማሉባት፡
  • በ2000 ዓ.ም ከ33 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ /ሲኖዶሱ ቁጥሩን ባይቀበለውም/፤ ከ400 ሺህ በላይ ዲያቆናት፤ መርጌቶችና ካህናት፤ ከ38 ሺህ በላይ አድባራትና ካህናት ይዛ በአማካይ 11 ካህናትና ዲያቆናትን ጨምሮ 860 ምእመናን በያንዳንዱ አጥቢያ ያሉባት፤
  • በ2005 ዓ.ም ከምእመናን የሚሰበሰብ አሥራት ከ1.24 ቢሊየን ብር በላይ፤ ከሕንጻዎች ኪራይና ልማቶች ገቢ ከ350 ሚሊየን ብር /አሁን ገቢ የሚደረገው ከ25 ሚሊየን ያነሰ ነው/ በላይ መሰብሰብ የምትችል፤ በ2007 በእጥፍ ማሳደግ የምትችለው አቅም ያላት ነች፡፡
  • ከላይ የተጠቀሰውን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት በጠቅላይ ቤተክህነት ደረጃ ብቻ በድምሩ ከ27000 ካሬ በላይ የሥራ ቦታ ያላቸው ከሰባት በላይ ሕንጻዎች የሚያስፈልጓት፣ አሁን ካለው የጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ እጥፍ የሆነ ስፋት ያለውና መንፈሳዊ ድባቡ የሚጠበቅ መንደር መገንባትም ሊያስፈለግ ይችላል፡፡ ለባለጉዳይ ካህናትና የአኅጉረ ስብከት ሠራተኞች እንዲሁም ከውጪ ሀገራት የሚመጡ እንግዶችን ማሳረፊያ/ማደሪያ ከተካተተ ተጨማሪ ሦስት ሕንጻዎች እስከ 6000 ካሬ የአገልግሎት ቦታ ያላቸው መገንባት ሊያስፈልጋት ይችላል፡፡

From Dejeselam
ቀሲስ ወንድምስሻ አየለ
ጅማ

No comments:

Post a Comment