Monday, October 31, 2011

ቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ዛሬም ይቀጥላል፤ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ በቋሚነት በሚመደብ ሊቀ ጳጳስ ይመራል

“እስከ መቼ ነው እርስዎ ሕግ እየጣሱ የሚቀጥሉት? የሚጠቅሱት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለእርስዎ አይሠራም ወይ? መጣራት የሚገባው ጉዳይ እንዳለ ሲኖዶሱ ካመነበት መጣራት በሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ልንነጋገር ይገባል 
 ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል  ለፓትርያርኩ 
  • ሊቀ ጳጳሱ ተደራቢ ሥራ ሳይኖራቸው የማደራጃ መምሪያው መዋቅራዊ አሠራር በሰው ኀይል እና በፋይናንሳዊ አቅሙ ለማጠናከር የሚያስችል መመሪያ የማስቀረጽ፤ በ1986 ዓ.ም የወጣውየማደራጃ መምሪያው ውስጠ ደንብ እና በ1994 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የጸደቀው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ከሚሻሻለው ቃለ ዐዋዲ፣ ሌሎች ሕጎች እና ከጊዜው ጋራ በማጣጣምእንዲሻሻል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተላለፈውን ውሳኔ የማስፈጸም፤ በዚህም ሕፃናትን፣ ወጣቶችንና ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ አስተባብሮ የመምራትሓላፊነት ይጠብቃቸዋል።
  • አባ ሰረቀ ከዋና ሓላፊነታቸው ተነስተው ሃይማኖታዊ ሕጸጻቸው እንዲመረመር የተላለፈው ውሳኔ የቤተ ክህነቱን ቢሮክራሲ (የሊቃውንት ጉባኤ መምሪያን ጭምር)ከፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ደጋፊዎች ለማጽዳት በቀጣይነት በመካሄድ ላይ ለሚገኘው ተጋድሎ አብነታዊ ርምጃ ተደርጎ ተወስዷል፤
  • “የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን በተመለከተ አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ጽሑፍ ተነጋግሮ መወሰን” በሚለው አጀንዳ ተራ ቁጥር ሰባት ላይ “የአጣሪ ኮሚቴው ጽሑፍ”ምንነት እና ፓትርያርኩ በንባብ እንዲሰማ ያዘዙት ‹ሪፖርት› በፓትርያርኩ እና በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መካከል ክርክር አሥነስቷል፤
  • ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ለሕገ ቤተ ክርስቲያን ተገዥ አለመሆናቸውን የተናገሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ምልአተ ጉባኤው የአቡነ ጳውሎስ ሐውልተ ስምዕ እንዲነሣ አሳልፎት የነበረው ውሳኔ አለመተግበሩን ጨምሮ በበርካታ የሙስና ጉዳዮች ዙሪያ ሲኖዶሱ መነጋገር እንደሚገባው ጠይቀዋል፤
(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 20/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 31/2011)፦ ጥቅምት 12 ቀን 2004 ዓ.ም የተጀመረውና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ 40 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እየተሳተፉበት የሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ምልአተ ጉባኤ ስምንተኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡ ሲኖዶሱ ትናንት እሑድ ሰንበት፣ ጥቅምት 19 ቀን 2004 ዓ.ም ከቅዳሜ ባሳደረው አጀንዳ ቁጥር ሰባት ላይ ለመወያየት ከቀኑ አምስት ሰዓት ጀምሮ ተገናኝቶ ለመወያየት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም ከ40 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል 19ኙ ብቻ በመገኘታቸው ምልአተ ጉባኤ ባለመሟላቱ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡

ምልአተ ጉባኤው ቅዳሜ ጥቅምት 18 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በአጀንዳ ተራ ቁጥር ሰባት ላይ እንደተመለከተው፣ “የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን በተመለከተ አጣሪ ኮሚቴው ባረቀበው ጽሑፍ {ላይ} ተነጋገሮ መወሰን” በሚለው ጉዳይ ላይ መካረር የታየበት ውይይት አካሂዷል፡፡ የጉባኤው ምንጮች እንደሚያስረዱት ለብዙዎቹ የምልአተ ጉባኤው አባላት እንደመሰላቸው፣ በአጀንዳው የሚቀርበው ሪፖርት የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት 131 ሰንበት ት/ቤቶች በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ጉዳይ በ14 ቪሲዲዎች፣ በአምስት የማስረጃ ጥራዞች እና ማስረጃውን በሚያብራራ 45 ገጽ መግለጫ ላይ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ኮሚቴ አቋቁሞ ባደረገው ማጣራት ላይ የቀረበ ሪፖርት እንደሆነ ይታሰብ ነበር፡፡

ይሁንና ፓትርያርኩ “የማቀርበው አለኝ” በሚል በሌላ ሰው እንዲነበብ ያዘዙት ሪፖርት ቀደም ሲል በውጭ ኦዲተር በተደረገው ማጣራት፣ “ቁሉቢ ኮንስትራክሽን” የተባለ ተቋራጭ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያለ አግባብ መውሰዱ፤ በዚህም መሐንዲሱን፣ በወቅቱ የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የነበሩትንና ራሳቸው ፓትርያርኩን ተጠያቂ በሚያደርግ አኳኋን ተረጋግጦ ያለፈውን ጉዳይ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በሚወነጅል መልኩ የተዘጋጀ ነበር ተብሏል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ያለ ቅ/ሲኖዶሱ ዕውቅና በራሳቸው ትእዛዝ ሰብስበውታል በተባለውና “እንደምንም ሠርታችሁ አምጡልኝ፤ ጉዳዩን እስከ ፀረ ሙስና ድረስ እንወስደዋለን” ባሉት ቡድን ተፈብርኳል የተባለው ይኸው ሪፖርት በምልአተ ጉባኤው ላይ እንዲነበብ አዝዘው ነበር፤ ወዲያው መነጋገሪያውን የተጫኑት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልም የተባለው ሪፖርት ሊነበብ እንደማይችል በማሳሰብ የታዘዘውን ሰው ያስቆሙታል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
አሁን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የተጠናቀረው የኮሚቴው ሪፖርት ቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝ ያልሰጠበትና የማያውቀው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “እስከ መቼ ነው እርስዎ ሕግ እየጣሱ የሚቀጥሉት? የሚጠቅሱት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ለእርስዎ አይሠራም ወይ? መጣራት የሚገባው ጉዳይ እንዳለ ሲኖዶሱ ካመነበት መጣራት በሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ልንነጋገር ይገባል፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ያሠሩት ሐውልት እንዲነሣ ሲኖዶሱ የወሰነው ውሳኔ መቼ ተተገበረ? በገንዘብ ጉዳይ እንነጋገር ከተባለ በመኪና ግዥ ሰበብ ከአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት የተመዘበረ ገንዘብ የለም? በጋምቤላ ተጠማቂዎች ስም የተመዘበረ ገንዘብ የለም? የአክሱም ሙዝየም ግንባታን እደግፋለሁ፤ ነገር ግን ከአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት ከብር 200 ሚሊዮን በላይ ተሰብስቧል፤ ግንባታው ያለ ጨረታ ለአንድ ሰው ሲሰጥ ሲኖዶሱ ላይ አቅርበው አጸድቀዋል? መነጋገር ካለብን እኒህን ሁሉ ጉዳዮች ማየት ይኖርብናል፤” በማለትም ብፁነታቸው ምልአተ ጉባኤውን አሳስበዋል፡፡

የብፁዕነታቸው ማሳሰቢያ እና ጥቆማ ሕጋዊ እና ትክክለኛ መሆኑን በመደገፍ የተናገሩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤልም በብፁዕነታቸው እና በፓትርያርኩ መካከል የተካረረ የቃላት ልውውጥ ሲደረግበት የነበረው አጀንዳ አድሮ በቀጣዩ ቀን እንዲታይ ባቀረቡት ሐሳብ የአጀንዳው ምንነት ተለይቶ ሳይታወቅ ጉባኤው ተነሥቷል፡፡ ይሁንና በቀጣዩ ቀን ማለትም ትናንት እሑድ ጥቅምት 19/2004 ዓ.ም ምልአተ ጉባኤ ባለ መሟላቱ ስብሰባው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ቀደም ሲልበተደረገው የኦዲት ማጣራት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ከሚባለው ውንጀላ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡእንደተዘገበ ይታወሳል፡፡

ስብሰባው ዛሬም በመቀጠል በእንጥልጥል ባደረው አጀንዳ ላይ እንደሚወያይ ይጠበቃል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 21 ቀን 2004 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ መርሐ ግብር የተያዘ ቢሆንም ገና ያልተወያየባቸው ከስምንት ያላነሱ አጀንዳዎች ይቀሩታል፡፡

እስከ አሁን ምልአተ ጉባኤው የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያን እና ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ ካሳለፈው ውሳኔ በተጨማሪ፦
  • የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብትና ልዩ ልዩ መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት በአእምሯዊ ሀብት/ንብረት እንዲመዘገቡ፤
  • የ30ው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርት እና የአቋም መግለጫን በማጽደቅ የአብነት ትምህርቱ ከዘመናዊው ሥርዓተ ትምህርት ጋር ተጣጥሞ ለመስጠት የሚያስችል ሥርዓተ ትምህርት እንዲያዘጋጅ የተወሰነውን ለማስፈጸምየትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ በጀት እንዲመደብለት፤
  • ለአብነት ት/ቤቶች እና ገዳማት የሚደረገው ድጎማ ተሻሽሎ እንዲሠራ፤
  • የተጀመረው የዕርቅ ሂደት እንዲቀጥል፤ እንዲሁም
  • የቃለ ዐዋዲው የተመረጡ ክፍሎች እንዲሻሻሉ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በመሆኑም ምልአተ ጉባኤው ቀሪ አጀንዳዎች ካላቸው አንገብጋቢነት አኳያ ዕንቅፋቶችን ታግሦበቀረቡበት አኳኋን ተወያይቶ የጋራ ውሳኔ እንደሚያሳልፍባቸው ተስፋ ይደረጋል፡፡

1 comment:

  1. Nigusie from Dz
    Igziabiher keabotochachin gar yihunlin

    ReplyDelete