- ወጣቶቹ “ሕዝብን ወደ ብጥብጥ የመምራት” እና “ሰውን የመደብደብ” ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፤
- ወጣቶቹ እርስ በርስ የማይተዋወቁ እና ከተለያየ አካባቢ የመጡ “የአዲስ አበባ ጥምቀት ተመላሽ ወጣት ማኅበር” አባላት ናቸው፤ ማኅበሩ ወጣቶቹ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲፈቱ ጠይቋል፤
- የሕገ ወጡ ቡድን አባላት (በጋሻው ደሳለኝ፣ በሪሁን ወንደወሰን፣ ትዝታው ሳሙኤል. . .) እና ለወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ቀራቢ የሆኑ ባለሥልጣናት ወጣቶቹ የዋስትና መብታቸውን ተነፍገው በእስር እንዲሰነብቱ እየተሯሯጡ ነው፤
“በተለያዩ ዘዴዎች ቤተ ክርስቲያንን ለመውረር ከውስጥና ከውጭ እየተከናወነ ባለው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተወያይቶ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ታሪካዊ ሚናውን እንዲጫወት” ለመጠየቅ ቅዳሜ ጥቅምት 11 ቀን 2004 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በመሰብሰብ ድምፃቸውን ካሰሙት ከ1000 የማያንሱ ወጣቶች መካከል ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙት ስምንት ወጣቶች ጥቅምት 13 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡
“ችሎ እና ተከባብሮ የኖረውን ሕዝብ ወደ ብጥብጥ በመምራት” እና “ሰው በመደብደብ” በሚሉ ሁለት የወንጀል ክሦች እንደሚፈልጋቸው ለፍ/ቤቱ አስረድቷል፡፡ በአዲስ አበባ ገርጂ፣ ሲ.ኤም.ሲ፣ ሃያ ሁለት እና ዑራኤል አካባቢ ሰፈሮች ነዋሪ መሆናቸውንና እርስ በርስ እንደማይተዋወቁ ለየራሳቸው የተናገሩት ወጣቶቹ በበኩላቸው፣ በዕለቱ በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተገኙት የተለያዩ የግል ጉዳዮቻቸውን ለመፈጸም በአካባቢው በሚያልፉበት ወቅት በአጋጣሚ ነው፤ ወደ ቅጽሩ ከገቡም በኋላ ተመልሰው ለመውጣት ስላልተፈቀደላቸው ቆይተው ሲወጡ መያዛቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል፡፡
ከወጣቶቹ አንዱም “[ይህስ ቢሆን] እኔ ቤተ ክርስቲያኔ ውስጥ ገባሁ እንጂ [ሌሎች እምነቶች] ጋራ አልሄድኩም፤ እንዴት ሕዝብን ወደ ሃይማኖት ብጥብጥ ለመምራት የሚል ውንጀላ ይቀርብብኛል?” በሚል የፖሊስን ክስ መቃወሙ ተገልጧል፡፡
ፖሊስ ተከሳሾቹ በዋስትና ቢወጡ ወደ ዐመፅ እና ብጥብጥ የሚመራ ተግባር ስለሚፈጽሙ፤ የድብደባ ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ (ትዝታው ሳሙኤል) በምን ዓይነት የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የማይታወቅ በመሆኑ የዋስትና መብት እንዳይሰጣቸው ጠይቋል፤ ዳኛውም ከስምንቱ ወጣቶች ስድስቱ (በመዝገቡ ከሦስተኛ እስከ ስምንተኛ ተራ ቁጥር የተመለከቱት) እያንዳንዳቸው የብር 600 ዋስትና አቅርበው እንዲወጡ፣ የተቀሩት ሁለቱ (በመዝገቡ በአንደኛ እና ሁለተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት) ደግሞ ለጥቅምት 16 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በዋስ እንዲወጡ ትእዛዝ የተሰጠላቸው ወጣቶች ቤተሰቦች የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ለፖሊስ ጣቢያ በመስጠት የዋስትና ሂደቱን ከጨረሱ በኋላ “ይፈለጋሉ” በሚል ወደ ማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ተወስደዋል ተብሏል፡፡
የሕገ ወጡ ቡድን አባላት በጋሻው ደሳለኝ፣ በሪሁን ወንድወሰንና ሌሎችም ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነንና ከወይዘሮዋ እኅት ጋራ በመፈጸሙት ጋብቻ የተዛመዷቸውን አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን (በቅርቡ በአፈጻጸም ድክመት ተገምግመዋል) በመጠቀም የጥምቀት ተመላሽ ማኅበር አባላት የሆኑት ወጣቶች የዋስትና መብታቸው ተነፍጎ በእስር እንዲሰነብቱ ከትናንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ እየተሯሯጡ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በጋሻው ደሳለኝና መሰሎቹ ሰሞኑን በተለምዶ ቺቺኒያ አካባቢ በሚገኘው ዮሊ ካፌና ሬስቶራንት “ልጆቹን ምን እናድርጋቸው?” በሚል ሲመክሩ ተሰምተዋል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ቁጥራቸው ከ3 - 7 የሆኑና በሕገ ወጦቹ ሐሰተኛ ቅስቀሳ ከሐዋሳ የመጡ ወጣቶች በተመሳሳይ ቀን (ጥቅምት 11) በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ ሲሆን ትናንት ፍ/ቤት ቀርበው የሰባት ቀን ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ተዘግቧል፡፡
No comments:
Post a Comment