Monday, October 31, 2011

“የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት” በሦስቱ አህጉረ ስብከት ሥር እንዲሆን አልያም እንዲዘጋ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ



 (ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 20/2004 ዓ.ም)፦
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን በሰሜን አሜሪካ ያሏትን ሦስት አህጉረ ስብከት “ከመንበረ ፓትርያኩ ጋራ ለማገናኘት” በሚል ተጠሪነቱ ለመንበረ ፓትርያኩ የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሆኖ ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና የተቋቋመው “የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጽ/ቤት” አገልግሎቱና ጥቅሙ በሚገባ ተመርምሮ በሦስቱ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ሥር እንደ አንድ የመረጃ ክፍል ሆኖ እንዲዋቀር፣ ይህ ካልሆነ ግን እንዲዘጋ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሰነ፡፡
  • በአጀንዳ ተ.ቁ ስምንት እንደተመለከተው ምልአተ ጉባኤው “ዝውውር የጠየቁ ሊቃነ ጳጳሳት” በሚል አጀንዳ ሥር በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና የካሊፎርኒያ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አዎስጣቴዎስ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ የላኳቸውን የቅሬታ ማመልከቻዎች በንባብ ካዳመጠ በኋላ ተወያይቶበታል፤ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ ሁለቱም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከቦታቸው እንዲነሡ ምልአተ ጉባኤውን ጠይቀው ነበር፤ ምልአተ ጉባኤውም፣ “ሁለቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና በሚመሰክር መልኩ ጉዳያቸውን በአካል መጥተው ማስረዳት ሲገባቸው አለመምጣቸው ተገቢ አይደለም፤ በመሆኑም በቀጣይ በአካል ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ” ሲል ትእዛዝ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡
  • ፓትርያክ አቡነ ጳውሎስ “የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ጉዳይ አጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት”በሚል በራሳቸው ትእዛዝ እንዲዘጋጅ ያደረጉት ሪፖርት ዛሬ ከቀትር በፊት በተካሄደው የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ መደናገርን ፈጥሯል፤ አጀንዳው በስብሰባው የተባበረ ድምፅ በደረሰበት ተቃውሞ ተቀባይነት ባለማግኘቱ አጀንዳው በራሱ ውድቅ ተደርጓል - “ይህ የሁላችሁ ሐሳብ ከሆነ ከእናንተ ቃል ውጭ አልሆንም፤ እንለፈው፤” (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ)

1 comment:

  1. ይህ የሁላችሁ ሐሳብ ከሆነ ከእናንተ ቃል ውጭ አልሆንም፤ እንለፈው፤” (ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ)

    ReplyDelete