Tuesday, October 18, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ተጀመረ


‹‹ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መሳካት ሁላችን እንፀልይ›› ከአንድ አድርገን

በአዲስ አበባ የመንበረ ፓትርያርክ የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ከተያዘለት መርሐግብር ዘግይቶ ቢጀመርም ቅዱስነታቸውን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃለ ጳጳሳትና ጳጳሳት የተገኙ ሲሆን በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ገዳም ካህናት በጸሎተ ወንጌል ተከፍቷል ከሁሉም በፊት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ አቅራቢነት ፡-


1ኛ. ሊቀ ትጉኃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኜ
2ኛ. መጋቤ ሰናያት አሰፋ ስዩም
3ኛ. ሊቀስዩማን ረደ አስረስ
4ኛ ንቡረዕድ ተስፋዬ ተወልደ
5ኛ. መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የጉባኤውን የጋራ የአቋም መግለጫ ረቂቅ አዘጋጆች ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በመቀጠልም በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ግብዥ ለጉባኤው የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት ቅዱስ ፓትርያርኩ ቀዝቀዝ ባለና የድካም ይሁን የህመም ባልታወቀ የእርጋታ ንግግር የጀመሩት በቅድሚያ በቅርቡ በሞት የተለዩንን አቡነ መርሐ ክርስቶስን፣አቡነ ኒቆዲሞስን፣አቡነ መልከ ጸዴቅን፣አቡነ ይሳቅን፣አቡነ በርናባስንና አቡነ ሚካኤልን በጸሎት እንድናስባቸው እጠይቃለሁ ብለው በጉባኤው ብፁዓን አበው እንዲታሰቡ አድርገዋል፡፡ አያይዘውም በድምጽ ማጉሊያ መበላሸት ምክንያት ያቋረጡትን እጅግ በጣም አጭር ንግግር ያደረጉ ሲሆን በዚሁ ንግግራቸው ይህ ዓለም ያለ አግባብ እንዳይራብ እንዳይጠማ እንዳይጉላላ ጠንክረን እንድንሰራ ሓላፊነት የተሰጠን ለእኔና ለእናንተ ነው:: እኔ እገሌን አላውቀውም እገሊትንም አላቀወቃትም እንድንል አልተፈቀደልንም:: በማለት ሁሉም በተሰጠው ሥልጣን ተጠያቂ እንደሚሆን አስታውሰው እግዚአብሔር የማይወደው ነገር እኔ እሻላለሁ እኔ እበልጣለሁ ማለትን ነው፡፡


እግዚአብሔር እንደዚህ ያለ ሩጫና መሽቀዳደም አይፈልግም ሲሉ በሚጠሩበት የማዕረግ ስም የሚኩራሩ መንፈሳዊውን ሩጫ ጥሎ ማለፍ አድርገውት በየትኛውም የቤተክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤቶች ሳይማሩ እራሳቸውን ሰባኪና ዘማሪ ፤ ካህናትና ፤ ዲያቆናት አጥማቂና ፈዋሽ ፤ አድርገው በማን አለብኝነት የሚፋንኑትን ወገኖች ወቅሰዋል፡፡

የከሰዓቱ ስብሰባ ስምንት ሰዓት እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ማሳሰቢያ ሰጥተው የጠዋቱ ውሎ በቅዱስነታቸው ጸሎት ተጠናቋል፡፡ ይህ ጉባኤ ቤተክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግሮች የሆኑትን ጉዳዮች ማለትም፡-
1ኛ. የተሃድሶን ጉዳዮች
2ኛ የአጉራ ዘለል ሰባኪያንን ጉዳይ
3ኛ የአባ ሰረቀን እናም የአቡነ ፋኑኤልን የወጭ ማተራመስ የቤተክርስቲያኒቱን አጠቃላይ አስተዳደራዊ ጉዳይ አጥብቀው እንደሚወያዩና ለጥቅምቱ የሲኖዶስ ስብሰባ የአጀንዳ ግባቶችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Posted  by ገብር ኄር                                                         
እስክንድር ሰይፉ 

No comments:

Post a Comment