Friday, October 21, 2011

ተሐድሶን ከማውገዝ እኩል ትጥቅ ያላቸውን ማስፈታት ያስፈልጋል፤ የመውጣት ምልክቱ ጫጫታ ነውና

(by Wendemsesha Ayele Kesis ) መምህር ዘመድኩን በቀለ በቪሲዲው አርማጌዶን ቁጥር ሁለት ላይ እንደተነተነው ከዓመታት በፊት ደሴ ላይ የተብራራው የመውጣት ምልክት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።  «የቤተክርስቲያን አስተዳደር መሻሻል ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ» በሚል ርእስ የጻፍኩት ክታቤ ላይ በአፈጻጸም ደረጃ በ፫ኛና አራተኛ ደረጃ ያስቀመጥኳቸው ጉዳዮች በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በቅጥር ያሉና ትጥቅ ያላቸውን ሰዎች ይመለከታል። ዛሬ ተሐድሶን ለማውገዝ ከሰፊና ሁለገብ ድካም በኋላ ሊሳካ ይመስላል። ይሁን እንጂ በ፲፱፻፺ ዓም በውግዘትና በእርማት ከታለፉት ጀምሮ በየጊዜው ሥልጠና እየሰጡ የተራቡት እንዲሁም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚተባበሯቸው ክህነት ያላቸውና የሌላቸው የቤተክርስቲያን ተቀጣሪዎች ሕጋዊና ሕገወጥ ትጥቅ ይዘው የመገኘታቸውን ነገር ትኩረት የሰጠው መኖሩን እጠራጠራለሁ።

በፕሮቴስታንት ጸሐፍቱ «በቤተክርስቲያን የመሸገው ጠላት»፣ በበጋሻው ስብከት «የጠላት ወረዳ»፣ የተባሉትና በግልጥ ማብራሪያ በጋሻው እውነተኛ የተዋሕዶ ማንነቷ ይጠበቅ የሚሉ ካህናትና ምእመናን እነሱ እንደፈለጉ እንዳይሆኑ ስለሚቃወሟቸው «ጠላት» የመባላችን ነገር መጨረሻው ደግሞ በበጋሻው ማብራሪያ «በቤተመቅደሱ የሚፈጠር ጫጫታ፣ ግብግብ» እንደሚኖር ይህንም መግጠምና መዋጋት እንዳለባቸው ገብቷቸውም ሆነ ሳይገባቸው ለሚደግፉት የሰጠው መመሪያ ነበረ። በተግባርም ደግሞ ሐዋሳ ላይ «ወጣቶች በርቱ፣ በርቱ፣ በርቱ፣ የእግዚአብሔር ቃል ውሀ ሲሞላ መንሳፈፍ ጀምሩ እባካችሁ፤በየትኛውም የጠላት ሰልፍ ውስጥ… እግዚአብሔር ጊዜውን ከሰጠን ከረዳን ወደኋላ ማለት የለም ወደፊት ብቻ…» በማለት አስቀድሞ ለዓመጽ መሪዎች የተሰጠውን ሥልጠና እንዲስማሙ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰቡት በሺዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን ማዘዙ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት ያፈራረሱትን ሕጋዊ የሰንበት ትምህርት ቤትና የሰበካ ጉባኤ የአስተዳደር መዋቅር በመተካት ለብዙ ደም መፋሰስና የከተማ ሰላም ማጣት ምክንያት መሆናቸው ለነገውም ዕቅዳቸው በቂ ማስረጃ ነው።

እዚህ ላይ ግን ሐዋሳ ላይ ብቻ የተፈጠረ፣ ድንገት የተከሠተ አድርጎ ማሰብ የዋኅነት ይመስለኛል። በሐዋሳው ብጥብጥ መጀመሪያ ላይ እነ … መቅደስ ገብተው ሽጉጥ መያዛቸውን ካህናቱ እንዲያውቁና በፍርሐት እንዲተባበሯቸው አለያም ዝም ብለው እንዲቀመጡ ለማስፈራሪያነት ቀበቷቸውን እያስተካከሉ ያሳዩን ነበረ። ሌሎች አኅጉረ ስብከትም ላይ ከቤተክህነቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ችግር ያለባቸው በዋናነት ቢያንስ ሽጉጥ ይዘዋል። ጥቂት የኑፋቄ ሙከራ ሲያደርጉ የተቃወሟቸውን ለማስፈራሪያነት ያወጡባቸውም ቦታዎች /መቅደስ ውስጥ ጭምር/ ማውጣቸውን ያያችሁ ሁሉ አስተውሉ። ስለዚህ መጨረሻቸውን አስቀድመው «በግብግብና ጫጫታ» ቤተክርስቲያኗን መረከብ እንደሆነ መዘንጋት ሊቀነስ ለሚችለው ጉዳት አለመጣር ይሆናል። እንደ ገብርኄር ዘገባ ደግሞ የትግራዩ የገዳም «አበምኔት» በማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ላይ ያቀረበው ዛቻ በሌላ ምእመናንና የዚያው ገዳም መነኮሳት ላይ ጭምር ሲፈጸም የነበረና አሁን መጨረሻው የቀረበ መስሎት ፬ ኪሎ ላይ በአደባባይ የሞከረው ትጥቁን ተማምኖ ነው።

በአጭሩ በተሐድሶነት ከደብር እስከ ገዳም፣ ከዲያቆን እስከ ቄስ ከአዲስ አበባ እስከ ገጠሪቱ ክፍል ድረስ የትጥቅ ዝግጅት እንዳላቸውና ለዘመናት የለፉበትን የሠርጎ መረከብ ሤራ እንዳይከሽፍ ቢያንስ በኃይልም ቢሆን ተጠቅመው ደም ካፋሰሱ በኋላ ለግልግል ዳኝነት መንግሥትን እንደሚጠይቁ ዓለም አቀፉ አጀንዳቸው ነው።

መጽሐፉ ግን «ሄዳችሁም። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ።… በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ።… ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥ ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።» ማቴ ፲፥፯-፲ «ዲያቆንም ቢሆን ቄስ ወታደር ወይም ነጋዴ ቢሆን ከክህነቱ ይሻር»ይላል ፍትሐ ነገሥት በእንተ ቀሳውስት ።

ስለዚህ፡-

፩/ ምእመናን በየአጥቢያው ትጥቅ ያላቸውን የቤተክህነት ሰዎችን መረጃ ቢሰበስብ፣

፪/ ተሐድሶ በተወገዘበት ጉባኤ ወዲያው ከቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጥ መመሪያና ለመንግሥት በሚሰጥ ኃላፊነት ትጥቅ መሣሪያ ያላቸው ሁሉ በቤተክርስቲያኒቱ ለማገልገልና ክህነት ያላቸውም በክህነታቸው መቆየት ከፈለጉ ሕጋዊም ቢሆን ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ቢደረግ፤ ይሻላል ብዬ አምናለሁ። የምእመናን ሕይወት እንዳይጠፋ፣ የሀገሪቱ ሰላም እንዳይታወክ፣ ሀገሪቱ የጀመረችው ጥቂቱ ልማትም እንቅፋት እንዳያገኘው። አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልጉም ሌሎች ብዙዎች የከፋ ጉዳት ሊያመጡ ይፈልጋሉና።

1 comment:

  1. ድሮም ቢሆን መሳሪያ ሳይኖራቸው በስጋዊ ነገር ሳይመኩ ይህን ድፍረት ለመፈፀም አይሞክሩትም እግዚአብሔርን እንደሆነ አያውቁትም:: እግዚአብሔር እንዲህ ካለ ፈተና ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን አሜን

    ReplyDelete