መ/ር ዘመድኩን በቀለ 0911-60-80-54
ኢ-ሜይል አድራሻዬ zemedkunbekele@yahoo.com
- ቪሲዲው የበጋሻው ደሳለኝን የዐላዋቂነት እና ድፍረት ንግግሮች በማጋለጥ ከፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ጋራ ባላቸው ቁርኝት ላይ ትኩረት አድርጓል
- በጋሻው ደሳለኝ ስሕተቱን ለማስተባበል ያደረጋቸውን ሙከራዎች “በአሥቂኝ ቀልዶች የታጨቁ ምክንያቶች” በማለት ተሣልቆባቸዋል
- “ይሄ ልጅ ለዚህ ሁሉ ሥራው እና ጥፋቱ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ጠይቆ ይመለሳል ወይ ለምትሉ ሰዎች እኔ በበኩሌ አይመስለኝም፡፡”/መ/ር ዘመድኩን በቀለ/
- ቪሲዲው ዝግጅቱን በመቀጠል በቁ.፫ ዝግጅቱ ከሚዳስሳቸው ጉዳዮች ውስጥ በኬንያ-ካኩማ ካምፕ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በዱባይ አድርጎ እስከ አሜሪካን ስለተዘረጋው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ የጉዞ መሥመር የሚመለከተው እንደሚገኝበት ተገልጧል::
(ደጀ ሰላም፤ መስከረም 24/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 4/2011)፦ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው የመምህር ዘመድኩን በቀለ “አርማጌዶን ቁ.፪” ቪሲዲ በገበያ ላይ ዋለ፡፡ “የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” (የሐዋ. ሥራ 9፣5) የሚለው ኀይለ ቃል በሽፋኑ ላይ የሚነበበው ይኸው ቪሲዲ በዋናነት በጋሻው ደሳለኝ ያሳተማቸው ሲዲዎች፣ ቪሲዲዎች እና ጽሑፎች፣ የሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ከፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አስተሳሰብ ጋራ ባላቸው መስማማት፣ ከኦርቶዶክሳዊ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነት እና ክርስቲያናዊ ትውፊት አኳያ ደግሞ በሚታይባቸው ተቃርኖ ላይ በማተኮር የተዘጋጀ ነው፡፡
ከመስከረም 18 - 21 ቀን 2004 ዓ.ም በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለክብረ በዓል ለመጣው በርካታ ምእመን የሚሰጠውን የትምህርት መርሐ ግብር እንዲያስተባብር የደብሩ አስተዳደር በጻፈለት ደብዳቤ የታዘዘውና በሥፍራው የሚገኘው የቪሲዲው አዘጋጅ መ/ር ዘመድኩን በቀለ፣ የአሳታሚው የጌልጌላ መንፈሳዊ መዝሙር ቤት ባለቤት ነው። የቪሲዲውንም መውጣት ይፋ ያደረገው በግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከአራቱም ማዕዝናት ለክብረ በዓል ለተሰበሰበው ምእመን የሚሰጠው የትምህርት መርሐ ግብር በተጀመረበት መስከረም 18 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፤ የቪሲዲው ሽያጭ ትርፍም ለደብሩ አገልግሎት ገቢ እንደሚሆን አዘጋጁ ተናግሯል፡፡
የስብከተ ወንጌሉ መድረክ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በርካታ የጉዞ ማኅበራት በሚያዘጋጇቸው የተለያዩ ድንኳኖች ውስጥ ሳይሆን በዐውደ ምሕረቱ ብቻ በወጥነት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለአራት ቀናት በዘለቀው የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር መድረኩን እንዲያስተባብር ሓላፊነት የተጣለበትን መ/ር ዘመድኩንን ጨምሮ በደብሩ አስተዳደር ጥሪ የተደረገላቸው ስምንት መምህራን (መ/ር ያረጋል አበጋዝ፣ መ/ር ኅብረት የሺጥላ፣ መ/ር በላይ ወርቁ፣ መ/ር ዳዊት ጥበቡ፣ መ/ር ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ እና ዘማሪ እስጢፋኖስ ሣህሌ/ቄሴ) አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄን ምንነት፣ አደጋ እና ምእመኑ ሊያደርግ ስለሚገባው ጥንቃቄ በመ/ር ያረጋል አበጋዝ ሰፊ ገለጻ እንዳቀረበ ለማወቅ ተችሏል።
“አርማጌዶን ቁ.፪” ቪሲዲ ቀደም ሲል የተሰራጨው ሲዲ ተከታይ ነው፤ ዓላማውም የተሐድሶ እንቅሰቃሴ ዐይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጥጦ መታየቱን ለመግለጥ፤ የአጉራ ዘለል ሰባክያንን ሕጸጾች፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሸረቡ የውስጥ ሤራዎች እንዲሁም በዐውደ ምሕረት ሆነ ተብለው የሚሰጡ የስሕተት ትምህርቶች እና አስተማሪዎቹ ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዱን ማሳየት፣ ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ መኖሩን ባለማወቅ በጭፍን የሚደግፉና የሚከራከሩ ወገኖች ትክክለኛ ማስረጃውን አግኝተው አሰላለፋቸውን እንዲያስተካክሉ ማስተማር መሆኑ ተገልጧል፡፡
“ተቀበላችሁም አልተቀበላችሁም፣ ተዋጠላችሁም አልተዋጠላችሁም፣ ወደዳችሁም ጠላችሁም ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ወደ ውስጣችን ዘልቆ በመግባት አደገኛ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን” መ/ር ዘመድኩን በቪሲዲው መግቢያ ላይ ያረጋግጣል፡፡ “ተሐድሶ የለም ብዬ ከምኖር ተሐድሶ አለ ብዬ ባልኖር እመርጣለሁ” በማለት “ተሐድሶ የለም” የሚሉትን፣ በተለይ “ተሐድሶ እንደ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፤ ካለ ቢሮውን ቢያሳዩን” እያለ የሚሣለቀውን በጋሻው ደሳለኝንና “መናፍቅ እና ተሐድሶ የሚባል ነበር የለም” የሚለውን የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ክፍል ምክትል ሓላፊ ሆኖ ከሚሠራበት ቦታው በቅርቡ የተባረረው ታሪኩ አበራን ምስላቸውን በማሳየት እና ድምፃቸውን በማሰማት ስለ አደጋው እውንነት ይከራከራቸዋል፡፡
መ/ር ዘመድኩን ካዘጋጀው ቪሲዲ ቀደም ብሎ በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም የተሠራጨውና በማኅበረ ቅዱሳን ዶክመንቴሽን ክፍል የተዘጋጀው “የተሐድሶ መናፍቃን ሤራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ - ቁጥር ሁለት ቪሲዲ” በዋናነት ያጋለጣቸውን በባሕር ዳር አካባቢ የሚገኙና ለጊዜው ስማቸው ያልተገለጹ “የተቀሰጡ መሪጌቶች” በፕሮቴስታንቶች አዳራሽ የተናገሩት ቃል በአርማጌዶን ቁጥር ሁለት ቪሲዲም ለፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ነባራዊነት ዐይነተኛ ምስክር ሆኖ ቀርቧል፡፡ በቪሲዲው ላይ ከ”ተቀሰጡት መሪጌቶች” አንዱ እንዲህ ይላል፡- “ናፍቆታችን ሁሉም ሰው ነፍስ ወከፍ ክርስቶስን ሲያከብር ማየት ነው፡፡ ካህን የለ፣ ኤጲስ ቆጶስ የለ ክርስቶስን ብቻ መናገር ካልጀመረ አፌ ዝም አይልም፤ ሰይጣንም ዝም አይልም፤ ወደ ኢየሱስ መምጣታቸው አይቀርም፤ እኛ የገባን ወንጌል ለሁሉም እንዲገባው፤. . .ኢየሱስ ክርስቶስ የግል አዳኝ ነው ብዬ ስናገር አያሳፍረኝም፤. . .ተሐድሶ የሚባሉ አሉ? አዎ! ለክርስቶስ ያልሆነውን ሁሉ ለክርስቶስ እናድሳለን፡፡”
የዚህን “የተቀሰጠ መሪጌታ” መወሻከት ተከትሎ ፕሮቴስታንታዊው ፓስተር ወደ መነጋገሪያው ቀርቦ፣ “ነገ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፤ አሁንም እዚያ ነው ያሉት፤ እዚህም ነው ያሉት፤ እስከ ዛሬ ስትጨፍሩ ስትዘሉ ነበር፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ ታስቀድሳላችሁ” ሲል “የተቀሰጡት መሪጌቶች” በማንኛውም መቅረጸ ምስል ወድምፅ እንዳይቀረጹ ታዳሚውን ያሳሰበው ሌላው ፓስተር ደግሞ፣ “ነገ ደግሞ ታቦቱን እንዳያመጣ” በማለት በፍና ተሣልቆ ይናገራል፤ እነርሱን የመሰሉ ብዙዎች በኅብአት (በስውር) እንዳሉም ይጠቁማል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳኑ ቪሲዲ የጠቀሰው “Evangelical Faith Movement In Ethiopia” በሚል ርእስ ፈቃዱ ጉርሜሳ የተባለ ፕሮቴስታንታዊ ጸሐፊ ያሰፈረው ቃል ይህን የመሪጌቶቹን እና የፓስተሮቹን ድራማ የሚያብራራ ነው፤ “ሚሲዮኑ የተለየ ቤተ ክርስቲያን የማቋቋም ዓላማ የለውም፤ ነገር ግን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ሕይወት ለማደስ ይተጋል፡፡ እጅግ አስተዋይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻችንም እስካሁን ይህ ዓላማ አላቸው፡፡”
በቀለ ወልደ ኪዳን የተባለ ሌላው ፕሮቴስታንታዊም “ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው” በሚል በጻፈው መጽሐፍ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከገጠር እስከ ከተማ በሁሉም አብያተ ክርስቲያን እየተካሄደ ስለመሆኑና “ያልነካካው ደብር እንደሌለ”፣ የተሐድሶ እንቅስቃሴውን ከውስጥ በአጠፌታ የሚካሄድ ፀረ-ተሐድሶ እንቅስቃሴ ቢፈታተነውም የተሐድሶ ወኪሎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከተ መምጣቱን ያትታል፡፡
የመ/ር ዘመድኩን በቀለ አርማጌዶንም በጋሻው የእኒህ አዝማቾቹ ‹አውራ ጎዳና ሠራተኛ› /መንገድ ጠራጊ/ መሆኑን በሚያስረዳ አኳኋን “ሃይማኖትህን አትለውጥ ራስህን ለውጥ፤ ቦታህን አትለውጥ ማንነትህን ለውጥ” በማለት የተናገረውን ቃል በድምፅ ያሰማናል፡፡ እንደ በጋሻው አነጋገር “ማንነትን በመለወጥ” ወይም እንደ እነፈቃዱ ጉርሜሳ ጽሑፍ “መንፈሳዊ ሕይወትን በማደስ”/ክርስትናን ለኢትዮጵያውያን እንደ አዲስ በመስበክ/ የሚጀምረው ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ዋነኛ ግቡ በሆነው “አስተምህሯዊ ለውጥ” እንደሚያሳርጉት የበቀለ ወልደ ኪዳን ጽሑፍ እንደሚያትት ተመልክቷል፡፡
አርማጌዶን ቁጥር ሁለት ቪሲዲ ለምእመኑ ይደርሳል ከተባለበት ጊዜ መዘግየቱን በተመለከተ “አጉራ ዘለል ሰባክያኑ ልብ ገዝተው ከጥፋታቸው ተመልስው ወደ ትክክለኛው መሥመር ይገባሉ በሚል እምነት እና ተስፋ በመጠባበቅ” እንደነበር ያስረዳው መ/ር ዘመድኩን፣ ይሁንና አጉራ ዘለሎቹ፡- “በገንዘብ እና በሌላ መልኩ አቅም ያላቸውን ግለሰቦች በመጠቀም ቅዱስ ፓትርያርካችንን በመጠጋት በእርሳቸውም ስም መንቀሳቀስ በመጀመራቸው፣ ግለሰቦቹ በየትኛውም ዐውደ ምሕረት ላይ መውጣት እንደማይችሉ ሲያውቁት፣ የቪሲዲ ስብከቶቻቸውንና ዝማሬዎቻቸውን የሚገዛቸው ሲያጡ በቤተ ክርስቲያን ስም የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመክፈት የጥፋት ድርጊታቸውን ዓለም አቀፋዊ በማድረጋቸው፣ በአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ በድፍረትና በማንአለብኝነት ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነ ትምህርት በማስተማራቸው፣ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸውን ማኅበራት ቢሮ [በዲላ የማኅበረ ቅዱሳን ወረዳ ማእከል ቢሮ] በማዘጋታቸው” እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ቪሲዲውን ለማዘጋጀት መገደዱን ተናግሯል፡፡
በቪሲዲው በጋሻው ደሳለኝ ከተናገራቸው የድፍረት ንግግሮች መካከል፡- “የእኛ ጌታ ተኝቶ ዓለምን ይገዛል”፤ “እግዚአብሔር እና ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን አትቀላቅሉ፤ ኢየሱስ የሚለውን ስም ሽሽት እግዚአብሔር፣ ሥላሴ ወደዛ ወደዛ አትበሉ…”፤ “ጉደኛው ሕፃን ኢየሱስ”፤ “እኛ ብንወድቅ ይሄ ሁሉ ሕዝብ ይወድቅ ነበር፤…ወደፊት ጳጳስ፣ ካህን የሚሆኑት ዛሬ በመቅደሱ ውስጥ ግብግብ የሚፈጥሩት ናቸው”፤ “ከዝነኛው እግዚአብሔር ጋራ ተጣብቀን ዝነኛ ሆንን፤ እኛ ብንሸነፍ ይሄ ሁሉ ሕዝብ ይሸነፍ ነበር”፤ “የኔ ጌታ ዕንጨት ላይ፣ መስቀል ላይ ተንጠልጥሎም ያሸንፋል”፤ “እግዚአብሔር ቆራሌው ነው፤ አሮጌ ጣሳ ሰብሳቢ…” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በማንአለብኝነት ከተናገራቸው ውስጥም በማኅበረ ቅዱሳን የዲላ ወረዳ ማእከል ጽ/ቤትን፣ “እግዚአብሔር በራችሁን ይዝጋው፤ መጽሔታችሁ ጨው መጠቅለያ ነው የሆነው፤ ሐሜት ነው፤ ወንጌል የለውም፤ ለካ እናንተ ፖሊቲከኞች ናችሁ፤ ነፍሰ ገዳዮች ናችሁ፤ አሳዳጆች ናችሁ፤. . . መንግሥት የፖሊቲካ ማኅበር ነው ሲል አላምን ብዬ ነበር፤ በርግጥ ነው፤ አሁን ትዕግሥቴ አልቋል፤ ከይቅርታ ጋራ ነገ ጠዋት ልቀቁ” ሲል ራሱን በዳኝነት ቦታ አስቀምጦ ትእዛዝ ያስተላለፈበት ቃሉ ይደመጣል፡፡ ፕሮቴስታንቶቹን ፓስተሮች እና ተማሪዎቻቸውን “ወንድሞቼ” የሚለው በጋሻው በደሴ ከተማ ባስተማረው ትምህርት ኦርቶዶክሳውያን አበው ካህናትን በአገልግሎት ፍቅር ማጣት፣ ለምእመኑ ባላቸው ጨካኝነት፣ በዐላዋቂነት እና በገንዘብ ወዳጅነት ሲሸነቁጣቸው ይሰማል፡፡
በየተሐድሶ መናፍቃን የነበሩትና ቅዱስ ሲኖዶስ በ1990 ዓ.ም አውግዞ የለየው ‹አባ› ዮናስ በኤግዚቢሽን ማእከል፣ “አሮጊቷ ሣራ እኔን ወለደች፤ ዘውዱን ወለደች፤ ፍሥሓን ወለደች፤ ገብረ ክርስቶስን ወለደች. . .ሃሌ ሉያ” እያሉ አብረዋቸው የከዱ የስም መነኮሳትን እየጠሩ ሲዘሉ በነበረበት አኳኋን በጋሻው ደሳለኝም፣ “አሮጊቷ ሣራ እምነቴ ናት፤ አሮጊቷ ሣራ እኔን ወልዳለች፤ ትዝታውን ወለደች፤ አሸናፊን ወለደች፤ ተረፈን ወለደች፤ በሪሁንን ወለደች፤ ምርቴን ወለደች፤ ዘርፌን ወለደች” እያለ የአስተሳሰብ እና የተግባር አጋሮቹን የሚጠራበት ተመሳስሎም በቪሲዲው በንጽጽር ቀርቧል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ልዩነት፣ “እነዚያ ተወግዘው መለየታቸው እነዚህ ግን ዕድሜ ለእገሌ እና ለእገሊት እያሉ ስልታቸውን ቀይረው መቀመጣቸው ነው፤” ብሏል፡፡ በጋሻው ደሳለኝ ስሕተቱን ለማስተባበል “ቪሲዲዎቼ ተቆራርጠው የወጡ ናቸው”፤ በአኒሜሽን የተሠሩ ናቸው”፤ “በስሎው ሞሽን የተፈበረኩ ናቸው” በማለት በየመድረኩ ያደረጋቸውን ሙከራዎች “በአሥቂኝ ቀልዶች የታጨቁ ምክንያቶች” በማለት ተሣልቆባቸዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በምእመናን መካከል ጠብ እና ክርክር የሚያሥነሱ፣ በሃይማኖቶች መካከል ደም መፋሰስ የሚያደርሱ ንግግሮችን በማድረግ የሚንቀሳቀሰው በጋሻው ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደማይወክል፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተቀበለው ምንም ዐይነት የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ይሁን ሌላ የአገልግሎት ፈቃድ እንደሌለው የሚያትተው አዘጋጁ ለወደፊቱም ለሥራው እና ለጥፋቱ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ጠይቆ ይመለሳል የሚል ተስፋ እንደሌለው ገልጧል፡፡ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጋሻው እና መሰሎቹ ተከልለው ስላለበት ሁኔታ ያሬድ አደመ “አባ ጳውሎስ ባይኖሩ'ኮ እኛ ጠፍተን ነበር” በማለት የተናገረውን በማስረጃነት ይጠቅሳል፡፡
ፓትርያርኩ በቅርቡ ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶን በማጋለጥ ረገድ ያስተላለፉትን መመሪያ ግለሰቦቹ እየተጠቀሙበት ስላለው ሁኔታና ራሳቸው ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ ላይ ስለተፈጠረው ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ያላቸውን ግዕዘ ኅሊና በሚመለከት ያለው ነገር የለም፡፡
በበጋሻው ደሳለኝ በተመሠረተበት የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ ጥቅምት አራት ቀን 2004 ዓ.ም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት የሚቀርበው መ/ር ዘመድኩን በአርማጌዶን ቁጥር ሁለት ቪሲዲው፡- ስም ባወጡ፣ “ንብረታችንን ሸጠንም ቢሆን የት እንደምናስገባህ ታያለህ” እያሉ በስልክ በሚዝቱበት ሰዎች እና የፕሮቴስንታዊ-ተሐድሶ-ኑፋቄ አራማጆች ፊት ያለውን ጽኑነት እና ቆራጥነት(steadfastness and resoluteness) በገሃድ አስመስክሯል ለማለት ይቻላል፡፡ በቪሲዲው ሽፋን የጀርባ ገጽ ላይ መ/ር ዘመድኩን እንዲህ ብሏል
- “በሚቀጥለው አርማጌዶን የጀመርኩትን እቀጥላለሁ፤. . .ለማንኛውም አስተያየቶቻችሁ በስልክ ቁጥር 0911-60-80-54 ደውሉ፤ አንሥቼ አወራችኋለሁ፡፡
የኢ-ሜይል አድራሻዬን ከፈለጋችሁም zemedkunbekele@yahoo.com ነው፤ ጻፉልኝ፤ በተለይ ተናዳጅ እና ተቆርቋሪዎች”።
ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ
ReplyDeleteዘመድኩን እባክህ የሚረባ ነገር ስራ ምክንያቱም ሃሜት ስራ አይደለም ተሃድሶ የሚያስፈልገው ቢኖር የመጀመሪያው ሰው አንተ ነህ ድንግል ማርያም ጥሩ ነገር ታሳስብህ አንት እኮ ስይጣን የቅናት መንፈስ በውስጥህ ከቶ የሚጫወትብህ ሰው ነህ የምታስበው በምን በልጬ ነው ብለህ ነው እንጂ ለክርስቲያኑ አስበህ አይደለም እግዚሃብሄር ልቦና ይስጥህ ለመሆኑ የአግዚሃብሄር ቃል በዲግሪና በዲፕሎማ ነው ያለህ ማነው መቼም እንደአንተ ዲግሪ ባይኖረንም ትንሽ እናነባለን ይሄንን ሁሉ የህይወት መመሪያ የተውልን አባቶች ከየትኛውም ዩኒቨርስቲ ተመረቁ የሚል አላየንም እግዚሃብሄር ልቦናህን ከፍቶ መንፈስ ቅዱስ ካደልህ የማይሆን የለም ትምህርት ለፍልስፍና ነው እግዚሃብሄር ፍቅር ነው
ReplyDelete