Saturday, October 1, 2011

‹‹መለያየት›› . . የቤተክርስቲያን የወቅቱ አደጋ

  • አንድነትን ውደዱ፤ መለያየትን ግን ፈጽማችሁ ተጸየፉ
  •  ቤተክርስቲያን ተጠግቶ የሚሰርቅ ካህን ከመላእክት ወገንም ቢሆን መታገድ ነው የሚኖርበት፡
  • ዘራችን ክርስትና ሀገራችንም በሰማይ እንደሆነ ስንሰበክ አንዳንዶቻችንም ስንሰብክና ስንዘምር ኖረናል
  • መጽኃፍ እንደሚል ''እርስ በእርሷ የተከፋፈለች መንግሰት ደሞ ትወድቃለች::''

በንስሐ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ለመመለስ የሚፈልጉትን ሁሉ በምህረትና በርህራሄ መቀበል ይገባል፤ ከዲያብሎስ ወጥመድ ያመልጡ ዘንድና በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት በእርሱ መንግስት ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያገኙ ዘንድ፡፡ወንድሞች ሆይ አትታለሉ፡፡ራሱን ከእውነት የሚለየውን ሰው የሚከተለው ቢኖር የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርስም፡፡ ሐሰትን ከሚናገርና ከሚያስተምር ሰው ራሱን የማይለይ ሰውም እርሱ በሲኦል ይፈረድበታል፡፡ መልካም ከሆነው እንዳንለይ ክፉ ከሆነው ደግሞ እንድንሸሽ ግዴታ ነውና፡፡ ነገር ግን ሁላችሁም መከፋፈል በሌለበት በአንድ ልቡና፣ ሙሉ ፈቃድ ባለው ሕሊና አንድ ሁኑ፡፡ በሰላማችሁ ጊዜም ሆነ በችግር ላይ ስትሆኑ፣ በሐዘንም ሆነ በደስታችሁ ጊዜ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖራችሁ ያስፈልጋል፡፡ሰውነታችሁን እንደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ጠብቁ፡፡ አንድነትን ውደዱ፤ መለያየትን ግን ፈጽማችሁ ተጸየፉ፡፡

(by Bekeme Mihiretike from Face Book) መስቀል ለኛ ለምናምንበት ድህነትን ያገኘንበት፤ ተለያይተው የነበሩትን እግዚአብሄርና ሰዎችን እንዲሁም ሰዎችና ሰዎችን አንድ ያደረገና ያስታረቀ ለሰው ልጆች ሰላምን፤ ፍቅርን፤ እርቅን፤ አንድነትን፤ጽድቅን ያደለ ሁሌም ከልባችን የማይጠፋ ውለታ የተዋለበት ነው፡፡ ይሁንና ጌታ በመስቀሉ ያደለንን ነጻ ስጦታ ገፍተን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በተቃራኒው ጠብንና መለያየትን እያስፋፋን ወደ ከፋ ደረጃ እየሄድን ስለመሰለኝ ይህችን መጥጥፍ ጫርኩ፡፡


ቤተክርስቲያን ባለፉት ዘመናት ብዙ ፈተናዎችና አደጋዎችን አልፋለች፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በእግዚአብሄር እርዳታ አባቶቻቸንንና ምእመኖቿ በጋራ ባደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ የተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ የምንታወቅበት ነገር ምንም አይነት ልዩነት ቢኖረን ሀገርንና ሃይማኖትን ሊነካ የውጭ ጠላት ሲመጣ ተባብረን አሳፍረን በመመለሳችን ነው፡፡ ይህ የውስጥ አንድነት ለጥንካሬያችን መሰረቱ ነው፡፡
ቤተክርስቲያን ባሁኑም ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፡፡ ከነዚህም አንዱ ከመናፍቃን በተለያየ ስልት እየተከፈተ ያለው ግልጽም ሆነ ስውር ወረራ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከፖለቲከኞች የሚደርስባት ሌላ ፈተናም አለ፡፡ ኢ-አማንያንና እስማኤላውያንም እንዲሁ የራሳቸውን ፈተና ጋርጠዋል፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት ሌሎች ውጫዊ አደጋዎች የቱንም ያህል የጠነከሩ ቢሆኑ ክርስቲያንና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል እንዲሉ ያጠነከሩን ይሆን እንጂ ሊያጠፉን አይችሉም፡፡


በኔ ግምገማ በአሁን ወቅት ለቤተክርስቲያን ከፍተኛ አደጋ ጋርጠው ያሉት ከላይ የተጠቀሱት ውጫዊ ፈተናዎች ሳይሆኑ ከውስጥ የሚመነጩ ችግሮች ናቸው፡፡ ክፋቱ እነዚህ በውስጣችን ያሉ ፈተናዎች ራሳቸው ከሚጋርጡት አደጋ በመለስ ለውጪያው ፈተናዎች ጥቃት አሳልፈው ይሰጡናል፡፡ እነዚህን ፈተናዎች መቋቋም ከቻልን ከውጭ የሚመጣውንም አደጋ መከላከል ይቻላል፡፡ በመሆኑም የቤተክርስቲያን ቁልፍ አደጋ ከውጪ የሚመጣ ሳይሆን ከውስጣችን የሚመነጭ ይሆናል፡፡
ለመዘርዘር ከሚታክቱት የውስጥ ቸግሮቻችን መሃል ቁልፉና ለቤተክርስቲያን አደጋ የሚሆነው መለያየታችን ነው፡፡ በውስጣችን ከፍተኛ የሆነ ክፉ የመከፋፈል መንፈስ ተዛምቷል፡፡ በዘር፤ በቡድን፤ በማህበር፤ በሰፈር፤ በጓደኝነት…ወዘተ መከፋፈል እጣ ፈንታችን ሆኗል፡፡ ክፍፍል በፓትሪያርኮች፤ ክፍፍል በሲኖዶስ፤ ክፍፍል በጳጳሳት፤ ክፍፍል በካህናት፤ በዲያቆነት፤በሰባኪያን፤ በዘማሪያን፤ በሰንበት ተማሪዎች፤ በሰበካ ጉባኤ…እረ በአሁኑ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ ማን ያልተከፋፈለ አለ፡፡ ሌላው ቀርቶ ባለም ሙት ናቸው በሚባሉት በመነኮሳት ዘንድ ሳይቀር…፡፡ ክፍፍሉ በብሄር ይጀምርና ሰፈርና ጓደኝነት ጋር ይደርሳል፡፡ ከላይ ከሲኖዶስ ተነስቶ እስከ ታች ጽዋ ማህበር ይወርዳል፡፡ በዚህም የተነሳ በሃሳቦች ራሱ መስማማት አልተቻለም፡፡ ቋንቋችን ተደበላልቋል፡፡ መደማመጥም፤ መተማመንም አልቻልንም፡፡ የሆነ ሃሳብ ሲነሳ የሚታየው ስለሃሳቡ ጠቃሚነትና ጎጂነት ሳይሆን ሃሳቡን ያቀረበው ማን ነው …የማን ወገን ሃሳብ ነው የሚል ጥያቄ ነው የሚነሳው፡፡ 

በአጭር ቋንቋ ሃሳቦች ራሳቸው በዘር፤ በቡድን፤ በማህበር፤ በሰፈር በጓደኝነት ተፈርጀዋል፡፡ ከእነንትና ወገን/ቡድን/ማህበር ከቀረበ በፍጹም ለቤተክርስቲያን አይጠቅምም….ከነዚህኞች እንትናዎች ብቻ ነው ጠቃሚ ሃሳብ ሊቀርብ የሚችለው በሚል ከምር እርግጠኛ የሆኑ ሰዎች በዝተዋል፡፡ ጥፋቶችም እንደዛው….እነ እንቶኔ ሁሌም ጥፋት….እነ እገሌ ግን ጥፋት አይሰሩም፡፡ እነ እነቶኔ ደግ ቢሰሩም ማንም አያምናቸውም፡፡ ከጀርባው የሆነ አላማ ቢኖራቸው እንጂ ይባላል፡፡ የራስ ቡድን ካጠፋ ተሳስቶ ነው…የሌላኛው ቡድን ሲያጠፋ አውቆ ነው ስውር አጀንዳ አለው..እርምጃ ይወሰድበት ይባላል፡፡በሚያሳፍር ሁኔታ ዘር ቆጠራ በሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ እርከን ተንሰራፍቷል፡፡ ለሚካሄዱ ክፍ ስራዎች ሁሉ መሸፈኛው ዘር ሆኗል፡፡ ጥናም ሲል በፖለቲካው መስክ የሚሰማው አይነት በፊት ፓትሪያርክ የነበረው የምንትስ ዘር ፕትርክናውን ሊወስድ እንዲህና እንዲያ እያረገ ነው….ያኛው ዘር ደሞ ፕትርክና ስላልደረሰው ይድረሰኝ በሚል መንፈስ ትግል ጀምሯል….ከእነ እነቶኔ ጋር በመሆን እንዲህ ያለ ደባ እየሰራ ነው….እንትን የሚባለው ማህበር እስካሁን አመራር የነበረው ከዚህ ዘር ስለሆነ ያኛውም እንዲደርሰው መንግሰት በመጠየቁ እንትና ከእንትን ዘር ተሾመ የሚሉ ወሬዎችን መስማት እንደ ተራ ነገር እየተቆጠረ ነው፡፡ ካህናቱም እንዲሁ “ ጎጃሜ” “ ጎንደሬ” ወዘተ በሚል ክፍፍል በውስጣዊ ሽኩቻ ላይ ሲሆኑ የራሳቸው ወገን የሆኑ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎችን ለማሾም ጥረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሌላ ዘር ከተሾመባቸውና ካልተስማማቸው ለማስነሳት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ አንድ ከጎጃም የሆነ ካህን በሙስና ተዘፍቆ ከአገልግሎት ቢታገድና የሚያገለግልበት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ጎንደሬ ቢሆኑ እሱ የሚለው በሙስናዬ ታገድኩ ሳይሆን አስተዳደሪው ጎንደሬ ስለሆኑ አገዱኝ ይላል፡፡ በሌላ በኩል አስተዳዳሪው ጎጃሜ ቢሆኑ ወይም እሱ ጎንደሬ ቢሆን ላይታገድ ይችላል፡፡ ሲጀመር ቤተክርስቲያን ተጠግቶ የሚሰርቅ ካህን ከመላእክት ወገንም ቢሆን መታገድ ነው የሚኖርበት፡፡ እንደው ለማሳየት ያህል ዘርን መሰረት አድርጎ ያለውን ክፍፍል ለአብነት ያህል አነሳሁት እንጂ በዚህ አጭር ጽሁፍ ተዘርዝረው የማያልቁ ግን ሁላችን የምናውቃቸው ብዙ መለያያ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሳስበው ሌላውን የማይከፋፍለው ነገር ሁሉ እኛን ይከፋፍለናል…ምናልባትም የሰይጣን ውጊያ ስለሆነ ይሆናል፡፡


ይህን አስቀያሚ መለያየት/መከፋፈል የሚባል ነገር ከየት እንዳመጣነው ከየትስ እንደወረስነው ግራ የሚገባ ነገር ነው፡፡ ሲጀመር ለሁሉ ነገራችን መመሪያችን መጽሃፍ ቅዱስ የሚነግረን ወይም የቀደሙ አባቶቻችን በተግባር ያስተማሩን ይህን አልነበረም፡፡ ይልቁንም መጽሃፍም ሆነ አባቶቻችን ያስተማሩን የአይሁድ ሰው፤የግሪክ ሰው፤ የሮማ ሰው፤ የግብጽ ሰው፤ የኢትዮጵያ ሰው እያልን ዘረኛ እንዳንሆንና እኔ የአፕሎስ እኔ የኬፋ ነኝ እያልን እንዳንከፋፈል ነበር፡፡ ዘራችን ክርስትና ሀገራችንም በሰማይ እንደሆነ ስንሰበክ አንዳንዶቻችንም ስንሰብክና ስንዘምር ኖረናል፡፡ አባቶችም ስለ አንድነትና ህብረት ሲጸልዩ ኖረዋል፡፡ ይሁንና ባሁኑ ወቅት እርስ በእርሳችን ተከፋፍለን በመበላላት ላይ ነን፡፡ መጽኃፍ እንደሚል እርስ በእርሷ የተከፋፈለች መንግሰት ደሞ ትወድቃለች፡፡ ለዚህም ነው ቤተክርስቲያንን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥላት አሁን በስፋት እየታየ ያለው የርስ በርስ መከፋፈል ነው የምለው፡፡


እኛ ኦርቶዶክሳውያን የመለያየትን አደጋ በአይናችን በብሌኑ በራሳችን ተፈጽሞ አይተናል፡፡ ባንድ ወቅት ከወደ ሰሜን አሜሪካ አንድ ድንቅ ዜና ተሰማ፡፡ አቡነ መርቆሪዎስ ያለ አግባብ ከስልጣናቸው መባረራቸውን ገልጸው እውነተኛው ፓትሪያክ እኔ ነኝ አሉ፡፡ አቡነ ጳውሎስም እንዴት ሆኖ አሉ….በአጭር ቋንቋ አቡነ መርቆርዮስና አቡነ ጳውሎስ ተለያዩ፡፡ ሁለቱም ራሳቸውን ትክክለኛ ፓትሪያርክ አድርገው ሌላውን ህገ ወጥ አድርገው አወጁ፡፡ እንዱ የሌላውን ሲኖዶስ ህገወጥ አለ፡፡ እርስ በእርሱ ተወጋገዙ..ተገዛዘቱ፡፡ ውጉዝ ከመ አርዮስ ተባባሉ፡፡ የዚህ የመለያየት አደጋ ከግለሰቦች አልፎ ቤተክርስቲያኗን ሊንጥ የሚችል መሆኑን ማየት የተጀመረው አቡነ መርቆርዮስ የራሳቸውን ጳጳሳት በሰሜን አሜሪካ፤ በአውሮፓ ወዘተ አህጉረ ስብከቶች ሲሾሙና ተቀባይነት ሲያገኙ ነው፡፡ አንድ ሰባኪ ወይም ዘማሪ ወይም ካህን ባሁኑ ወቅት ሰሜን አሜሪካ ሄዶ እንደልቡ የፈለገበት ቤተክርስቲያን ለማገልገል ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አብያተክርስቲያናቱም በሁለቱ ፓትሪያርኮች ጎራ ተከፋፍለዋል፡፡ የማን ደጋፊ ነህ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የታዋቂ ሰባኪዎችና ማህበራት ሳይቀር ራስ ምታት ነው፡፡ ይህ ክፍፍል ሄዶ ሄዶ ቤተክርስቲያኗን ላለመክፈሉ ምን ዋስትና አለ….ይህ የሚያሳየን እንደ ቀላል የተጀመረ መለያየትና ክፍፍል ለቤተክርስቲያን አደጋ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡


ውን በኛ መለያየት በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰው አደጋ የሚያሳስበን ከሆነ ተከፋፍለን በሩቁ ከመተጋተግ ጠጋ ብለን መወያየት የግድ የሚለን ወቅት ላይ ነን፡፡ ያኛው ፓትሪያርክ ናቸው ትክክለኛው…እኚህኛው በጉልበት ነው…ያኛው ቡድን ነው ጥፋተኛው፤ ይህኛው ዘማሪ ያሬዳዊ ዜማን ይከተላል….ያኛው እንደዛ ነው….ይህኛው ሰባኪ ምንትስ ነው….ያኛው ቅብርጥስ ነው…እያሉ ራስን ወይም ቡድንን ትክክለኛ ሌላውን ጥፋተኛ ማድረግ እና ሰውን በመሰለው መፈረጁን አቁሞ….ሁሉም የጥፋቱ….የመለያየቱ… አካል አድርጎ ራሱን ቆጥሮ የመፍትሄውም አካል ማድረግ የግድ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ሁላችንም ጥፋተኞች ነን፡፡ ግማሾቻችን የዚህኛው ወይም የዚያኛው ቡድን/ማሀበር/ ወዘተ ደጋፊ ወይም አባል ሆነን ተለያይተናል፡፡ ሌሎቻችን መለያየቱን እንዲሰፋ አድርገናል ወይም ዝም ብለን አይተናል፡፡ መለያየት ሃጢያት እንደሆነ ሁላችንም የማንስተው ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በድለናል ቤተክርስቲያንን፤እግዚያብሄርንና ምእመናንን አሳዝነናል፡፡

ስለሆነም ያለፈውን በክፋት፤ በበደል፤ በመራርነት፤ በጠብ፤በመለያየት የኖርንበት ዘመንን አቁመን ወደ እርቅ፤ ወደ ሰላም፤ ወደ ይቅርባይነትና ወደ አንድነት መመለስ ወደ ጽድቅ የመመለስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያንንም ከአደጋ የመጠበቅ ጉዳይም ይሆናል፡፡

ግን እኛ ኦርቶዶክሳውያንን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሰላምን፤ ፍቅርንና እንድነትን በመስጠት የዋለልንን ውለታ እንዳናስተውል አዚም ያደረገብን ማን ነው ?

የመስቀሉ ብርሃን ሁላችን ላይ አርፎ ውስጣችን ያለውን የመለያየት፤ የጠብና የመራርነት ክፉ መንፈስ አስወግዶ እንድነትን፤ሰላምንና ፍቅርን ያድለን፡፡


No comments:

Post a Comment