Thursday, October 27, 2011

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ 17 አጀንዳዎችን በማጽደቅ መወያየቱን ቀጥሏል


  • በቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ እምነት ላይ ያለውን ችግር በቀረበው ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ መወያየት፣ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር ፍጻሜ የሚገኝበት ሁኔታ፣ በቃለ ዐዋዲው መሻሻል የሚገባቸውን ክፍሎች መወሰንብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሞተ ሥጋ ሲለዩ [ሀብት፣ ንብረታቸው] ምን መሆን እንዳለበት፣ ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ በአጣሪ ኮሚቴው ተጠንቶ በቀረበው ጽሑፍ ላይ መወያየት የሚሉት ከአጀንዳዎቹ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው
  • የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ማሻሻል የአጀንዳ ሐሳቦች ተቀባይነት አላገኙም
  • ዛሬ ከቀትር በፊት ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ በአጣሪ ኮሚቴው ተጠንቶ በቀረበው ጽሑፍ ላይ ውይይቱንአካሂዷል
በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ጥቅምት 12 ቀን 2004 ዓ.ም የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቋሚ ሲኖዶስ በተቀረጹት እና ብፁዕ አቡነ ማቲያስን ሰብሳቢ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን ጸሐፊ አድርጎ በምልአተ ጉባኤው በተሠየመው አጀንዳ አዘጋጅ ኮሚቴ አማካይነት ዘመኑን የዋጀ እና ወቅቱን የተመለከቱ እንዲሆኑ ተደርገው የቀረቡ 17 አጀንዳዎችን በማጽደቅ በትንትናው ዕለት የጀመረውን ውይይት ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡

ምልአተ ጉባኤው በፓትርያኩ የቀረበውን የተጨማሪ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጥያቄ ከተሚዎች አግባብነት እና በሰሜን አሜሪካ ካሉት አባቶች ጋራ በተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር መሠረትቤተ ክርስቲያን አንድነት ላይ የሚፈጥረውን ዕንቅፋት በመመርመር ሳይቀበለው ቀርቷል፤ በዕርቀ ሰላም ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ መጥተው አሁን አዲስ አበባ የሚገኙትን የዕርቀ ሰላሙ ተነሣሽነት አባላት የሆኑትን ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁንና ቀሲስ ዶ/ር አማረ ካሳዬን ሪፖርትም በትንትናው ዕለት ማዳመጡ ተዘግቧል፡፡ የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ፍጻሜ የሚያገኝበት ሁኔታ በምልአተ ጉባኤው አጀንዳ ተ.ቁ ዘጠኝ ላይ ተመዝግቧል፡፡ ሲኖዶሱ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን ስለ ማሻሻል በተመለከተም “ወቅቱ አይደለም በሚል ውድቅ አድርጎታል ተብሏል፡፡ 

ምልአተ ጉባኤው በዛሬው የቀትር በፊት ውሎው በአጀንዳው ተራ ቁጥር አራት ላይ በተመለከተው ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና ስለ ማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ በአጣሪ ኮሚቴው ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ በንባብ ካዳመጠ በኋላ መወያየት መጀመሩ ተዘግቧል፡፡

በ2003 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሠየመው ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሦስት የሊቃውንት ጉባኤ አባላት እና አንድ የሕግ አገልግሎት ሓላፊ የሚገኙበት አጣሪ ኮሚቴ ሥራውን የጀመረው ከተጠበቀው ጊዜ ዘግይቶ ነበር፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ የተገናኘውም ቢበዛ ለሁለት ጊዜ ብቻ ነበር - አንድም ሰነዶችን ለመለዋወጥ፣ በሁለተኛው ጊዜ ደግሞ በሰነዶቹ ላይ በተለይም አባ ሰረቀ በየጊዜው ለማኅበሩ ስለ ጻፏቸው ደብዳቤዎችና ማኅበሩ ስለሰጣቸው ምላሾች የማኅበሩን ተወካዮች ማብራሪያ በጥያቄና መልስ መልክ ለመስማት፡፡

በፓትርያሪኩ ትእዛዝ የአጣሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ እንዲሆኑ በተመረጡት በብፁዕ አቡነ ገሪማ የተመራውን ይህን መድረክ ብቻ እንደ በቂ በመውሰድ ለሁለቱ አካላት ችግር እንደ መፍትሔ የተወሰደው በ1994 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የጸደቀው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ለማደራጃ መምሪያው ተጨማሪ ሥልጣንን፣ ለማኅበሩ ደግሞ የአንዳንድ ተልእኮዎቹን ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባና የአፈጻጸማቸውን ሂደት በማደራጃ መምሪያው ጥብቅ ክትትል(ቁጥጥር) ሥር በሚያደርግ አኳኋን እንዲሻሻል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም መሠረት ዛሬ በአጀንዳው ላይ የተወያየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ የማኅበሩን ቀጣይ ተልእኮ እና ከማደራጃ መምሪያው ጋራ ያለውን ተዋረዳዊ ግንኙነት በሚወስንበት አግባብ ‹እንዲሻሻል›፣ አልያም 30ው የመንበረ ፓትርያክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በአቋም መግለጫው ላይ እንዳስቀመጠው በቤተ ክርስቲያን የታመነበት የማኅበሩ ‹‹የልማት እና የበጎ አድራጎት አገልግሎት›› ከማ/መምሪያው ጋራ ተግባብቶ በመሥራት ይቀጥል ዘንድ እንደሚወስን፣ ዋና ሓላፊውን አባ ሰረቀንም ከሥልጣናቸው አንሥቶ በሌላ እንደሚተካ ይጠበቃል፡፡

የዛሬው ውይይት እስከ ማምሻው ስለደረሰበት ሁኔታ ደጀ ሰላም ያላት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአጣሪ ኮሚቴው አንዳንድ አባላት ማኅበሩ እስከ አሁን ሲያስፈጸመው የቆየው የአገልግሎት አድማሱ በሚገደብበት እና የቤተ ክህነቱ መዋቅራዊ አሠራር /ቅልጥፍና/ ባልተሻሻለበት ሁኔታ የማደራጃ መምሪያውን ጥብቅ ቁጥጥር በሚያሰፍን አኳኋን የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ እንዲሻሻል አቋም ይዘው ሲከራከሩ ውለዋል፡፡

በአንዳንዶች ግምት የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት የሚኖረው ከሆነ ማኅበሩ በቅዱሳት መካናት እና አብነት ት/ቤቶች እንዲሁም በልዩ ልዩ የልማት ተቋማት አስተዳደር ረገድ የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጽዕኖ ሊያርፍባቸው፣ በኅትመት እና በስብከተ ወንጌል ሥምሪት በኩል የሚፈጽማቸው አገልግሎቶቹ ደግሞ ዘመን በተሻገረው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዘገምተኛ ቢሮክራሲ ሊጓተቱ አልፎ አልፎም ቀና አመለካከት በሚጎድላቸው ሓላፊዎች ጫና ሥር ወድእንደሚችሉ አስግቷል፡፡  

የሆነ ማኅበር መተዳደሪያ ደንብ ከቆመለት ርእይ እና ተልእኮ አንጻር መሻሻሉ የሚገባና የሚቻል ቢሆንም ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የአጣሪ ኮሚቴው አባላት እዚህ መደምደሚያ ላይ ሊያደርሳቸው ያበቃቸውን በጭብጥ የተመዘነ ማሳመኛ ነጥብ እንዲያቀርቡ ሌሎች የጉባኤው አባላት አበክረው በመጠየቃቸው አጀንዳው በውሳኔ ሳይሸኝ ለነገ እንዳደረ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ አጀንዳ ቀደም ሲል ምልአተ ጉባኤው ከተራ ቁጥር 1 - 3 በተጠቀሱት አጀንዳዎች ላይ ማለትም፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩን የመክፈቻ ንግግር፣ የ30ው የመንበረ ፓትርያክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሪፖርት እና የአቋም መግለጫ እና የ2004 ዓ.ም ዓመታዊ በጀት ተወያይቶ መወሰን የሚሉት አጀንዳዎች ተመልክቶ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጧል፡፡ የውሳኔውን ይዘት እንደ ደረሰን እናቀርባለን፡፡

በአጀንዳዎቹ ላይ የተደረሰባቸውን የውሳኔ ይዘት እንደ ደረሰን እናቀርባለን፡፡
(ከደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 15/2004 ዓ.ም)፦

1 comment: