Sunday, October 23, 2011

30ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ 4ኛ ቀን ሪፖርታዥ


30ኛው አጠቃላይ ጉባኤ ባለ33 ነጥብ የውሳኔ ነጥቦች እና የጋራ አቋም የያዘ መግለጫ አውጥቷል፤ ከእኒህም መካከል፡-
 • የአብነት ት/ቤቶች ትምህርት ከዘመናዊው ትምህርት እና ሥርዓት ጋራ ተቀናጅቶ ሊሰጥ በሚችልበት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ሥርዓተ ትምህርት በትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ማዕከልነት እንዲዘጋጅ፤
 • ቃለ ዐዋዲው በአንዳንድ አካባቢ “የመንግሥት ዕውቅና የለውም” የሚል ጥያቄ እያስነሣ መሆኑ ለጉባኤው ስለተገለጸ በሥራ ላይ ያለው ቃለ ዐዋዲ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሻሻልና ለመንግሥት ቀርቦ ዕውቅና እንዲያገኝ እንዲደረግ ጉባኤው በአትኩሮት ያሳስባል፡፡
 • በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተመሳሳይነት እና እኩልነት የሚታይበት አገልግሎትን በትክክል ለመፈጸም፣ የካህናትን ወደ አዲስ አበባ መምጣት ለማስቀረት የበጀት ማዕከላዊነት ቢኖር እንደሚበጅ በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተገለጸውን ጉባኤው በአትኩሮት ተገንዝቦታል፡፡ በመሆኑም በአፈጻጸም ጥልቅ ጥናት ተደርጎ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ተግባራዊ እንዲሆን ጉባኤው አምኖበታል፡፡
 • በማኅበረ ቅዱሳን በኩል የሚደረገው ሐዋርያዊ ጉዞና የበጎ አድራጎት ሥራ መልካም ገጽታ የሚታይበት ስለሆነ ከመምሪያው ጋራ በመግባባት እና መመሪያን በመቀበል አገልግሎቱን እንዲቀጥል ጉባኤው አሳስቧል፡፡
 • በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም እየተጠሩ ያለ ሕግና መመሪያ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ሁሉ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚታቀፉበት፣ ወይም የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅዱስና ክቡር ስም ይዘው ከመንቀሳቀስ የሚገቱበት፣ በሚመለከተው ክፍል በኩል ሕጋዊ የሥራ ርምጃ ይወሰድ ዘንድ ጉባኤው አበክሮ ይጠይቃል፡፡
 • ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስፋፋትና መጠናከር ኅብረተሰቡን በየቋንቋው ማስተማር ወሳኝነት እንዳለው ይታመናል፡፡ ስለዚህ የመናፍቃንንም እንቅስቃሴ ለመግታት ስለሚረዳ በካህናት ማሠልጠኛዎች እና በኮሌጆቻችን በየቋንቋው የሚያስተምሩ ካህናት እንዲሠለጥኑ፣ በአመዳደብ በኩልም ትኩረት ያገኝ ዘንድ የበላይ አስተዳደራዊ መመሪያ እንዲሰጥ እናሳስባለን፡፡
 • በግል ሥጋ ጥቅም ተታለው፣ ሃይማኖታቸውን ክደው፣ ክህነታቸውን ጥለው ወደ መናፍቃን ጎራ የገቡ ካህናት መኖራቸው ስለተገለጸ ካህናት ሳይሆኑ የሆኑ እየመሰሉ ቀድሞ የሚያውቋቸውን ምእመናንን በስውር እንዳያታልሉ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ከተመከሩ በኋላ የማይመለሱ ሆኖ ሲገኝ ተገቢው ቀኖናዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ያስተላልፍ ዘንድ ጉባኤው በአጽንዖት ጠይቋል፡፡
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱን ሕግ አክብራ የእምነቷ ተከታዮች የሆኑትን ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት፣ በሰላማዊ መንገድ እየመራች የራሷን ሥርዓተ አምልኮ በመፈጸምና በማስፈጸም ላይ እንደምትገኝ የታወቀ ነው፡፡ ዳሩ ግን አንዳንድ አክራሪ ፀረ ቤተ ክርስቲያን አቋም ያላቸው ቡድኖች ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌና ከሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር ውጭ ሲፈታተኗት የሚታዩ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ አህጉረ ስብከት እየደረሰ ያለው ችግር ከመባባሱ አስቀድሞ ቅዱስ ሲኖዶስ ዘላቂ መፍትሔን እንዲፈልግ ጉባኤው በአጽንዖት ያሳስባል፡፡ ከዚህም ጋራ መናፍቃንና ተቃራኒዎቻቸው በአብያተ ክርስቲያናት ላይ አደጋን በማድረስ፣ ይዞታዋን በመንጠቅ፣ በምእመናን ላይ ከሕግ ውጭ በተለያየ ስልት የሚያደርጉትን ትንኮሳ ሁሉ ለመግታት በየሀገረ ስብከቱ የተደረገው ትግል የሚደነቅ ነው፤ ነገር ግን ከበላይ የመንግሥት አካላት ጋራ ምክክር ቢደረግ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሚሆን ጉባኤው ያመነበት ስለሆነ ይኸው በሥራ እንዲገለጽ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የጠበቀ አደራውን ሰጥቷል፡፡
 • ከሦስቱም ኮሌጆቻችን የሚመረቁ ደቀ መዛሙርት የመማራቸውን ዋና ዓላማ በውል ተገንዝበው በየተመደቡበት አህጉረ ስብከት በመሄድ ያለምንም ምክንያት አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ከማሳመን ሥራ ጋራ አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ጉባኤው አጥብቆ ያሳስባል፡፡
 • በተለያየ ምክንያት ከውድ እናት አገራቸው ኢትዮጵያ እየወጡ በሁሉም ክፍላተ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛ ከመምጣቱ የተነሣ አምልኮተ እግዚአብሔር የመፈጽሙበት፣ ሀብተ ዉልድና ስመ ክርስትና የሚያገኙበት አብያተ ክርስቲያናት እንዲቋቋሙላቸው ኤጲስ ቆጶሳት እንዲመደቡላቸው የሚጠይቁ ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡
 • በተጓዳኝ መልኩ በውጭ ሀገር ላለችው ቤተ ክርቲያናችን አገልግሎት ከተመደቡት መካከል የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ሌሎቹም ተወካዮች በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ማእከላዊ አስተዳደር ጥሪ አክብረውና ተቀብለው፣ አስፈላጊውን ፍሬ በረከት ይዘው፣ ሪፖርታቸውን አዘጋጅተው የጉባኤው ተሳታፊዎች ሆነው ለተገኙት የቤተ ክርስቲያኒቱ አለኝታዎች ጉባኤው ከፍተኛ ክብርና ሞገስ ሰጥቷቸዋል፡፡
 • በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላስተላለፈችው መንፈሳዊ ጥሪ ትኩረት ባለመስጠት ይሁን በሌላ ምክንያት አብዛኞቹ በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በጉባኤው ላይ አልተገኙም፡፡ በአርኣያነቱም ሆነ በምሳሌነቱ ልዩ በሆነው በዚህ ዓለም አቀፍ ሠላሳኛው ጉባኤ ላይ በመገኘት አንድነትን አለመግለጽ ቅሬታን ከማሳደሩም በላይ ጥያቄን ሊያስከትል ስለሚችል ቅዱስ ሲኖዶስ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን የማስተካከያ መመሪያና ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጉባኤው በአጽንዖት መጠየቁ፤ የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
 • በጉባኤው መጨረሻ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር “ሃይማኖትን እናሻሽላለን” የሚሉ አካላትን በተመለከተ “ሃይማኖት አይደለም የሚሻሻለው፤ የሚሻሻል ሃይማኖት የለም፤ እኛ ነን መሻሻል ያለብን” ያሉት የጉባኤተኛውን አትኩሮት ስቧል፡፡ “በግልጽ መመካከር ወደ መከባበርና ወደ ድኅነት ይመራል” ያሉት ቅዱስነታቸው የማይሆን ነገር የሚናገሩትን ‹ልጆች› በአባትነት መንፈስ መምከር እንጂ የምንጠላው ሰው መኖር እንደሌለበት መክረዋል፡፡
 • አቡነ ጳውሎስ “ከሕገ ቤተ ክርስቲያንና ከቀኖናችን ውጭ የሆነውን ሥራ በመሥራት መስለው ለመገኘት የሚፈልጉትን ሁሉ አንቀበልም” በማለት የተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞችን እንደሚቃወሙ የገለጹ ሲሆን ችግሩን ለመከላከል መወሰድ ስለሚገባው ርምጃ የሚከተለውን ብለዋል፡- “አባቶቻችን የተዉልን የቀኖና አካሄድ አለ፤ መጀመሪያ መምከር ያስፈልጋል፤ ከዚህ ጥሶ የሚሄድ ሰው ካለ ያደረገውን፣ የፈጸመውን ነግረን እያዘንን የበለጠ ምክር እንዲሰጠው በማለት ማስረጃ ይዘን የሚሆነውን እናደርጋለን፡፡”
 • የፓትርያርኩ ንግግር የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ጉዳይ በጥቅምቱ ሲኖዶስ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ስለመሆኑ በጉባኤው ተሳታፊዎች ዘንድ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ይህንኑ በሚያጠናክር አኳኋን ትናንት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ መክፈቻ ጸሎት ሥርዓት በተከናወነበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተካሄደው የፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ እንቅስቃሴን የሚያወግዝ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ደማቅ ትዕይንት ጉልሕ ሆኗል፡፡
 • እነ በጋሻው ደሳለኝ በፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ ላይ የሚካሄደውን የመከላከል እንቅስቃሴ ለመቃወም ትናንት በጸሎቱ መክፈቻ ሥርዓት ወቅት ጠርተውት የነበረውን ትዕይንት በፀረ-ተቃውሞ ትዕይንት ለመመከት በአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተጠሩና ቁጥራቸው ከ500 በላይ የሚሆኑ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተካፋይ ሆነዋል፡፡
 • የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ የሆኑት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም እና የገዳሙ አስተዳደር ወጣቶቹ በጽሑፍ ያዘጋጁት ጥያቄ ካለ እርሱን አስረክበው እንዲወጡ፣ የሰንበት ት/ቤት አባላት በመሆናቸው ጉዳያቸውን ማቅረብ የሚገባቸው በሰበካ ጉባኤ ወይም በማደራጃ መምሪያው በኩል እንጂ በዚህ መልኩ ለማስተናገድ እንደሚከብድ በተደጋማሚ ቢናገሩም ወጣቶቹ ከቀትር 6፡00 ጀምሮ ጸሎቱ እስከሚጀመርበት ሰዓት ድረስ “ቤተ ክርስቲያን አትታደስም” የሚል ኀይለ ቃል የሚነበብበት መፈክር በመያዝ የተለያዩ ያሬዳዊ ዜማዎችን በማሰማት ቆይተው ከጸሎቱ ፍጻሜ በኋላ በሁለት ገጽ ያዘጋጁትን ጥዩቄያቸውንና አቋማቸውን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በንባብ አሰምተዋል፡፡
 • አቋማቸው ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን መቃወም እንደሆነና በሕገ ወጦቹ እንደሚባለው በማኅበረ ቅዱሳን የሚገፋ የተለየ አቋም እንደሌላቸው፤ ጥያቄያቸውም በዚሁ እንቅስቃሴ ውስጥ እጃቸው ያለበት የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረቡትን ማስረጃ ተመልክቶ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ውሳኔ እንዲወስን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ፓትርያሪኩ ወጣቶቹ “እንዲህ ያሉ ቆራጥ ልጆች አሉኝ ለካ” በማለት አመስግነዋቸዋል ተብሏል፡፡
 • በጥብቅ የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኀይል ዙሪያ ክትትል ሥር በተካሄደው የትናንቱ ትዕይንት ከ8:00 በኋላ የሚመጡ የትዕይንቱ ተሳታፊዎች ይሁኑ ሌሎች ተሳላሚዎች ወደ ቅጽሩ እንዳይገቡ ተከልክለው በሩ የተዘጋበት ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ከውጭ ወደ ውስጥ የሚመለከቱ በርካታ ወጣቶችና ምእመናን በዙሪያው ተሰልፈው ታይተዋል፡፡ በሩ የተዘጋበት ምክንያት ቀድመው ወደ ውስጥ በገቡት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ‹በግል ጠባቂዎች› ታጅበው ዘግይተው በደረሱት ጥቂት ሕገ ወጦች (ትዝታው ሳሙኤል፣ አሰግድ፣ ምርትነሽ፣ የትምወርቅ፣ ሀብታሙ ሽብሩ…) ጠብ በመጀመሩ ነው ተብሏል፡፡ በጠቡ ትዝታው ሳሙኤልና ሌሎች ጥቂቶች በተወሰነ መልኩ መጎሸማቸው ተዘግቧል፡፡
 • ሕገ ወጦቹ “በተሐድሶ ሽፋን ማኅበረ ቅዱሳንን ማስቀጠል አይቻልም”፤ “ማኅበረ ቅዱሳን ከኮሌጆቻችን እጁን ያንሣ”፤ የሚሉ መፈክሮችን ይዘው እንደነበር ተመልክቷል፡፡
 • ከትዕይንቱ ፍጻሜ በኋላ ከደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አጥቢያ የመጡ የተወሰኑ ወጣቶች ወደ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተይዘው እንደተወሰዱ ተገልጧል፡፡ ምክንያቱም የሕገ ወጡ ቡድን አባል በሆነው ትዝታው ሳሙኤል ላይ ድብደባ ተፈጽሟል በሚል መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በዕለቱ ሕገ ወጦቹ ከሐዋሳ፣ ከአዲስ አበባ እና ሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በተለያየ መንገድ ያሰባሰቧቸው ከ100 የማይበልጡ ወጣቶች በአብዛኛው ከቤተ ክርስቲያኑ ውጭ ተኮልኩለው ታይተዋል፡፡
ከደጀሰላም ላይ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment