Tuesday, October 25, 2011

እንኳን አደረሳችሁ



(by Wubishet Tekle )ጥቅምት 14 ቤተክርስቲያን የ 3 ታላላቅ አባቶችን መታሰቢያ ታከብራለች፤አንዱ አቡነ አረጋዊ ናቸው ደብረ ዳሞ ላይ በፍጹም ተጋድሎ ኖረው ለኢትዮጵያ ብርሃን ሆነው በ 99 ዓመት ከ 3 ቀናቸው ተሰወሩ፤የአቡነ አረጋዊ እናት ንግስት እድና ንግስናዋን ትታ ልጇን ተከትላ መጥታ ደብረ ዳሞ ተራራው ስር በ89 ዓመቷ አርፋለች፤ 



ሁለተኛው ጻድቅ መናኙ ሙሽራው ገብረ ክርስቶስ ነው እርሱም የንጉስ ልጅ ነው፤ከጫጉላ ቤት ጠፍቶ መነነ፤ አባቱ ወታደሮችን ላከበት፤ ገብረ ክርስቶስ ሌት ተቀን ተጉዞ የእመቤታችንን ደብር አገኘ ተንበርክኮም እመቤቴ ወታደሮች እንዳይዙኝ መልኬን ቀይሪሊኝ አላት የውስጥ ሰውነቱ ተገለበጠ በቁስልም የተመታ ሆነ ደጀ ሰላሙ ላይ ምጽዋት ከሚለምኑ ድሆች ጋር ተቀመጠ ወታደሮቹ ደረሱበት አላወቁትም ምጽዋት ሰጥተውት ያልፋሉ፤ በዚያች በቤተክርስቲያን 15 ዓመት በተጋድሎ ኖረ ከዚያም ወደ አገሩ ተመልሶ በአባቱ ደጅ 15 ዓመት ወድቆ ለመነ፤ አባቱ ለአሸከሮቹ እንዲህ አለ ይህንን ደሃ ምጽዋት ስጡት ልጄ ምናልባት ልክ እንደዚህ ደሃ በሰው አገር እየተንከራተተ ይሆናልና አላቸው፤ የአባቱ አሸከሮች ግን የእጅ እጣቢ፤ሽንት ይደፉበት ነበር በላዩ ላይ አጥንት እየወረወሩ ውሾች እንዲጣሉበት ያደርጉ ነበር፤ በእንዲህ ያለ ተጋድሎ 15 ዓመት ኖረ፤የእረፍቱ ቀን ሲደርስ የንጉሱ የቴዎድዮስ ልጅ መሆኑን የደረሰበትን ሁሉ መከራ ጽፎ ይሞታል፤ሊቀብሩት ሲሰበሰቡ ይህችን ጽሁፍ ያገኛሉ፤ አባትና እናቱ መሪር ለቀሶ አለቀሱ አገሩ በሙሉ አለቀሰለት ከበድኑ ገራሚ ገራሚ ተአምራት ተገለጹ ድውያን ሁሉ ተፈወሱ፤በታላቅ ክብርም ቀበሩት፤ ለእግዚያብሔር ምስጋና ይሁን፤ 



ዳግመኛ በዛሬዋ ቀን የኢትዮጰያዊቷ ንግስት ህንደኬ በጀሮንዷ የሆነውን ጀንደረባውን ያጠመቀው ታሪኩ በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 8፤27 ላይ ተገልጾ የሚገኘው ሐዋርያው ፊሊጰስ ያረፈበት ቀን ነው፤ይህ ሐዋርያ ከ 72ቱ አርድእት አንዱ ነው። የአባቶቻችን በረከታቸው ይደርብን። 



ስለ ደብረ ዳሞ ገዳም ታሪክ ከአኮቴት ቴሌቪዥን መርሀ ግብር ላይ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment