Saturday, October 29, 2011

ቅዱስ ሲኖዶስ ለ4ኛ ተከታታይ ቀን በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ እና ማ/ቅዱሳን መካከል ባሉት ችግሮች ዙሪያ እየተወያየ ነው


(ደጀ ሰላም፤ ጥቅምት 18/2004 ዓ.ም፤ ኦክቶበር 29/2011/ PDF)፦

 • ምልአተ ጉባኤው የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት በተሰጠው መመሪያ መሠረት ባለመቅረቡ አልተቀበለውም፤ ኮሚቴው የአባ ሰረቀን በማስረጃ ያልተደገፉ 20 ክሶች በማጉላት የማኅበሩን 10 ተጨባጭ አቤቱታዎች በማኮሰስ አቅርቧል
 • የአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት ማ/መምሪያው ቋሚ ሊቀ ጳጳስ እንዲመደብለት፣ አባ ሰረቀ ከዋና ሓላፊነታቸው እንዲነሡ፣ የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ አባ ሰረቀ ካቀረቧቸው ክሶች አንጻር የማ/መምሪያውን ሥልጣን በሚያጠናክር አኳኋን እንዲሻሻል በመፍትሔ ሐሳብ አቅርቧል
 • ምልአተ ጉባኤው “አጣሪ ኮሚቴው በሁለቱም በኩል የቀረቡ ማስረጃዎችን ይዞ የማጣራቱን ውጤት እንዲያቀርብልን እንጂ‹እገሌ እንዲህ አለ፤ እገሌ ደግሞ እንዲህ አለ› የሚል ሪፖርት እንዲያቀርብ አልጠበቅንም” በማለት ሪፖርቱን ተችቷል፤ የሪፖርቱን ተቀባይነት ማጣት በመመልከት ጉዳዩ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጠው ፓትርያርኩ ያቀረቡትን ሐሳብ በመቃወምም የማ/መምሪያውን ሦስት ተወካዮች እና የማኅበረ ቅዱሳንን ሁለት ተወካዮች በመጥራት ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ አድርጓል
 • የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮች፣ አባ ሰረቀ ከአስተዳደራዊ /ሥራ አመራር/ አቅም ማነስ እስከ ሃይማኖታዊ ሕጸጽ ድረስ ያለባቸውን ድክመት በጎላ በተረዳ መልኩ በማብራራት ችግሩ ከግለሰቡ ጋራ እንጂ ከማ/መምሪያው ጋራ እንዳልሆነ ምልአተ ጉባኤውን ያረካ መግለጫ ሰጥተዋል፤ አባ ሰረቀ በበኩላቸው ጠቅላይ ቤተ ክህነቱንም በሕይወተ ሥጋ የሌሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትንም ማኅበሩንም በማደበላለቅ የከሰሱባቸውን የበርካታ ደብዳቤዎችን ቁጥር እና ቀን በመጥቀስ አሰልቺና ተጨባጭነት የሌለው ገለጻ ሰጥተዋል፤
 • ሁለቱም አካላት ለየጉዳያቸው አሉን የሚሏቸውን ማስረጃዎች ለአንድ ሙሉ ቀን ያዳመጠው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚከተሉትን የውሳኔ ሐሳቦች አቅርቧል፡-
 1. የማ/መምሪያው ዋና ሓላፊ አባ ሰረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤልከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፤ ከሓላፊነታቸው መነሣት ብቻ ሳይሆንየሃይማኖት ሕጸጽ እንዳለባቸው የተጠቀሰ በመሆኑ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ማስረጃውን መርምሮ፣ ሪፖርት እንዲያቀርብ
 2. ማደራጃ መምሪያው ራሱን የቻለ ሊቀ ጳጳስ (ሀገረ ስብከት የሌለው)እንዲመደብለት፤
 3.  የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ከቃለ ዐዋዲው መሻሻል ጋራተያይዞ እና በሚሻሻለው ቃለ ዐዋዲ ውስጥ ተካትቶ ማኅበሩን ሊያሠራው በሚችል መንገድ እንዲሻሻል፤
 • እንደተጠበቀው የአባ ሰረቀን ከዋና ሓላፊነት መነሣት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ተቃውመዋል፤ ከሓላፊነት እንዳይነሡ መቃወም ብቻ ሳይሆን የአባ ሰረቀን የሃይማኖት ሕጸጽ የሚመረምር በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ መርማሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ምልአተ ጉባኤው ያቀረበውንም የውሳኔ ሐሳብ አልተስማሙበትም፤ በምትኩ ማስረጃው ለሊቃውንት ጉባኤው ቀርቦ እንዲመረመር ነው የአቡነ ጳውሎስ ፍላጎት፡፡
 • ከሊቃውንት ጉባኤው አባላት መካከል የሚጠራጠራቸው እንዳሉ ያመለከቱት የምልአተ ጉባኤ አባላት በበኩላቸው የፓትርያርኩን ሐሳብ ባለመቀበል ውይይቱ ለአራተኛ ተከታታይ ቀን ቀጥሎ ይገኛል፤ ፓትርያርኩም አንገታቸውን ዘልሰው (አጽንነው)“አልስማማም” በማለት ብቻ በተለመደው የማዘግየት ታክቲካቸው የምልአተ ጉባኤው አባላት እንዲሰላቹና አቋማቸውም በቆይታ የሚከፋፈልበትን ሰዓት እየተጠባበቁ ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዋና ሓላፊውን ማንሣት ይችላሉ፡፡
 • አንዳንድ የጉባኤው ታዛቢዎች እንደሚገልጹት አባ ሰረቀ ከዋና ሓላፊነታቸው ተነሥተው ሃይማኖታቸው እንዲመረምር የውሳኔ ሐሳብ መቅረቡ በተሐድሶ ኑፋቄው ፕሮጀክት ላይ ጠንካራ ምት በማሳረፍ ለከፍተኛ ኪሳራ የሚዳርገው በመሆኑ አቡነ ጳውሎስ የሞት ሽረት አቋም ይዘዋል፡፡ በሌላም በኩል ምልአተ ጉባኤውን በዚህ አጀንዳ ላይ ቸክሎ በመያዝና አባላቱን በማሰላቸት በቀጣይ በተያዙት “የሥርዐተ እምነት ችግር” /ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን/ እና አስተዳደርን የተመለከቱ አጀንዳዎች እንዳይታዩ/በቅጡ እንዳይታዩ/ የማድረግ ስልት ነውም ብለዋል፡፡
 • በመሆኑም የምልአተ ጉባኤው አባላት በዛሬውና በቀጣዩ ቀናት ውሏቸው በፓትርያርኩ በማዘግየት የመከፋፈልና እና የማዳከም ስልት ላይ ነቅተው ሳይሰላቹ በመወያየት ቤተ ክርስቲያን ከተጋረጠባት ወቅታዊ አደጋ እንዲታደጓት ተማፅነዋል፡፡ በየአህጉረ ስብከቱ የሚገኙ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና ሌሎችም የፀረ ፕሮቴስታንታዊ-ተሐድሶ አደረጃጀቶች የጀመሩትን ሰላማዊ እንቅሰቃሴ በመቀጠል ከዚህ ጥረት ጎን እንዲሰለፉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዜናውን ዝርዝር ሪፓርታዥ እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡

1 comment: